ቀን 10:00 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ መሪነት በጀመረዉ የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ወላይታ ዲቻን ማሸነፍ ችሏል።
ገና በመባቻዉ በፊት መስመር አጥቂዉ ማይክል ኪፖሩቪ አንድ ሁለት ሙከራዎች በጀመረዉ መርሐግብር ሲዳማ ቡናዎች በ12ተኛዉ ደቂቃ ላይ ጥሩ ዕድል አጊኝተዉ ነበር ፤ በዚህም ይስሀቅ ካኑ ከበረኛ የተመለሰዉን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ግን ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ስትወጣ ፤ በድጋሚ ይሄዉ ተጫዋች በዚሁ መስመር ላይ ከሳጥን ዉጭ አስገራሚ ሙከራ ማድረግ ቢችልም ነገር ግን ኳሷን የግቡ አግዳሚ መልሷታል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ ላይ በ22ተኛዉ ደቂቃ ግብ ተቆጥሯል ፤ በዚህም ይስሀቅ ካኑ ከበዛብህ መለዮ ጋር በአንድ ሁለት ጥሩ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ከደረሱ በኋላ ይስሀቅ ካኑ ወደ ቀኝ ካመዘነዉ የሜዳዉ ክፍል በግሩም ሁኔታ ግብ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል መድረስ የጀመሩት ወላይታ ዲቻዎች ምንም እንኳን አደገኛ የሚባሉ ሙከራዎችን ማድረግ ላይ እምብዛም የነበሩ ባይሆኑም ፤ ነገር ግን በ24ተኛዉ ደቂቃ በአበባየሁ ሀጪሶ እና በ26ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ በብስራት አማካኝነት ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል ።
በ41ኛዉ ደቂቃ ላይም ዲቻዎች አስቆጭ ሙከራ አድርገዉ ነበር ፤ በዚህም ከግራ መስመር በኩል ባየ ገዛኸኝ ያቀበለዉን ኳስ ተጫዋቾች በተዘናጉበት ወቅት አጥቂዉ ቢኒያም ፍቅሬ ከሳጥን ዉጭ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሷን የግቡ አግዳሚ መልሷታል። ከዕረፍት መልስ በ55ተኛዉ ደቂቃ ላይ ማይክል ኪፖሩቪ ከግራ መስመር በኩል ኳሷን እየገፋ በነፃነት ሳጥን ዉስጥ ገብቶ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሷ ለጥቂት ወደ ዉጭ የወጣችበት አጋጣሚ በሲዳማዎች በኩል የተደረገች አስቆጭ ሙከራ ነበረች ።
በድጋሚ በ60ኛዉ ደቂቃ ላይ ማይክል ኪፖሩቪ ከቀኝ መስመር በኩል ወደ ሳጥን ያሻማዉን ኳስ በዛብህ መለዮ በጭንቅላቱ በመግጨት ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ግብ ጠባቂዉ ኳሷን እንደምንም ተቆጣጥሯል። ከዚች ሙከራ ከአንድ ደቂቃ በኋላም በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ ይስሀቅ ከሳጥን ዉጭ ድንቅ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ግን ለጥቂት ወጥታለች። የአቻነት ግብ ለማግኘት መታተር የቀጠሉት ዲቻዎች በ72ተኛዉ ደቂቃ ላይ በቢኒያም ፍቅሬ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ነገር ግን የግቡ ቋሚ ሲከለክላቸዉ ፤ በ74ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን ሲዳማዎች በማይክል ኪፖሩቪ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዉ ጨዋታዉን ሁለት ለዜሮ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችለዋል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ሀድያ ሆሳዕናን ማሸነፍ ችሏል።
አመሻሽ 12:00 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ ፊሽካ በጀመረዉ ጨዋታ ገና በጊዜ ብልጫ በነበራቸዉ አፄዎቹ በኩል ፍቃዱ አለሙ ድንቅ ሙከራ ማድረግ ቢችም ግብ ጠባቂዉ ፔፔ አልዛየር ኳሷን በቀላሉ ተቆጣጥሯል። በአብዝሀኛዉ የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመጫወት ላይ የነበሩት ሀድያዎች በዳዋ ሆቴሳ እና ብሩክ ማርቆስ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ከቻሉ በኋላ በ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም እዮብ ማትያስ ለቡድን አጋሩ ለማቀበል የሞከረዉን ኳስ በስህተት ለዳዋ ሆቴሳ አቀብሎት ተጫዋቹ ዳዋ ደግሞ በግሩም ሁኔታ ኳሷን ከሳጥን ዉጭ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸዉን ግብ ለማግኘት ጥረት ማድረግ የጀመሩት አፄዎቹ ከብዙ ጥረቶች በኋላ በ65ተኛዉ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ከግራ መስመር በኩል ሽመክት ያሻገረዉን ኳስ ጃቢየር ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን ወደ ጨዋታዉ መመለስ ችሏል ። አቻ ከሆነ በኋላ በይበልጥ ተጭነዉ መጫወት የቀጠሉት አፄዎቹ በ80ኛዉ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተገኘዉን ኳስ ሽመክት ጉግሴ አሻምቶ ጋቶች ፓኖም ከጨረፈዉ በኋላ ያገኘዉ ምኞት ደበበ ወደ ግብነት በመቀየር በመርሐግብሩ አፄዎቹ ወሳኝ ሶስት ነጥብ እንዲይዙ አስችሏል።