“የሜድሮክ ግሩፕ ተቋማት ያልከፈሉን ወደ 67 ሚሊዮን ብር አለን አሁንም ታግሰን ክፍያውን እንዲሰጡን እየጣርን ነው “
” 8 አመት ሙሉ ተካሰናል ከአስራ አምስት ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት ቀርበናል ሁሉንም ግን ረተናቸዋል”
አቶ ዳዊት ውብሸት
/ የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ አባል/
ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ሁለት አመታት የገጠመውን ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ለማስወገድ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
- ማሰታውቂያ -
“የድርሻዬን ለታላቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ” በሚል የፊታችን ቅድሜ በሚጀመረው የስጦታና የድጋፍ የኦንላይን ዘመቻ ዙሪያ በክለቡ ጽ/ቤት በተሰጠው መግለጫ ላይ የክለቡ የቦርድ አባልና የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዳዊት ውብሸት እንደተናገሩት ” እውነት ነው ከፍተኛ የበጀት ችግር ተከስቶብናል አሉ የተባሉ ክለባችንን ያግዛሉ ብለን ያሰብነውን ስፖንሰሮች ጠይቀን በተወሰነ ፐርሰንት አልተሳካልንም። ስፖንሰሮቹ ኳሳችንን ወደው እስኪመጡ ድረስ ደጋፊዎቻችንን እናምናለን ጠንክረን እንደምንቀጥል ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሚቴው ከነሀሴ 20 እስከ ጳጉሜ 4/2015 ድረስ ቅዳሜ በሚገለጹ የክለቡ የባንክ አካውንቶች፣ በአለም አቀፍ የገቢ መለኪያ ስልቶችና በቴሌ ብር የገቢ ማሰባሰቢያ ስልት ከ5-10 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማድረግ እንደታቀደ ተገልጿል። ከ100 ብር ጀምሮ በተቀመጡት የአካውንት ቁጥሮች ሁሉም ድጋፉን እንዲያደርግ ተጠይቋል። በቅዳሜ መክፈቻ ከቀኑ 6 ሰአት ተጀምሮ ከለሊቱ 6 ሰአት ድረስ በክለቡ ሁሉም ማህበራዊ ፔጆችና 1ሚሊዮን ተከታዮች ባሉት በአባይ ቲቪ የፌስቡክ ገጽ ላይ ይተላለፋል ተብሏል። ክለቡንም ለማጠናከር አመታዊ 150 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋልም ተብሏል። ቡድኑ በቀጣዩ አመት ሻምፒዮናነቱን እንዲያስጠብቅ ለማድረግ የተጨዋቾች ዝውውር ላይ ጠንካራ ስራ ለመስራት እንደተዘጋጁም ገልጸዋል።
ታሪካዊ የክለቡ ተወዳጅ ተጨዋቾች ማሊየዎች ለሽያጭ የሚቀርብ ሲሆን የስመጥር የቀድሞ ተጨዋቾች ማሊያዎች ለጨረታ ይቀርባሉ ተብሏል። አንድ ግለሰብ የክቡር ይድነቃቸው ማሊያና የጌታቸው ዱላ ቤተሰብ ደግሞ ማሊያውን ሰጥተውናል ደጋፊዎቹም ክለቡን የሚጠቅምና ታሪካዊ ነው ያላችሁት ማሊያ ሜዳሊያና ቁሳቁስ ለክለባችን እንድትሰጡን እንጠይቃለን ብሏል ኮሚቴው።
በክለቡ ጽ/ቤት በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው ” በ87 አመት የክለባችን በድል የታጀበ ጉዞ ለሀገራችን ትልቅ ስራ ሰርተናል። ደጋፊዎቻችን፣ ለሀገራችን እግር ኳስ
ጥቅም እንደነበረን ለሚያምኑ የስፖርት ቤተሰቦች ጥሪ እናደርጋለን የመፍረስ ችግር ለገጠማቸው ክለቦች ደርሰናል አሁን ደግሞ እኛ ድጋፍ እንጠይቃለን እንደ ሀገራችን እግርኳስ ራሳችንን መሸጥ አልቻለም አለም ላይ እንዳለው ኢንዱስትሪ አይደለም ለዚህ ነው ስፖንሰር ያጣነው። እስካሁን ሲደግፉን እንጂ በኛ ተጠቅመው ነው ብለን አናስብም ራሳችንን ሸጠን ውጤታማ እስክንሆን ድረስ ድጋፍ እንጠይቃለን” ብለዋል አስተባባሪው።
በተፈጠረው የፋይናንስ ችግር ዙሪያ አቶ ዳዊት ሲናገሩ “ከዚህ በፊት በነበረው የረጅም አመት የቅ/ጊዮርጊስ ታሪክ ውስጥ በተለይ ከ1982 ጀምሮ የሜድሮክ ግሩፖች ፔፕሲ፣ ደርባንና ዳሽን ባንክን ጨምሮ ወደ 13 የሚጠጉ ተቋማት ሲያግዙን ኖረዋል። ባለፉት ሁለት አመታት ግን አትክፈሉ የሚል ትዕዛዝ ደርሶናል በሚል ክፍያውን በማቆማቸው ችግር ውስጥ ገብተናል። ከ7-10 አመት የሚጠጋ ውል አለን የተፈጠረው ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ታግሰናል።ተቋማቱ ያልከፈሉን ወደ 67 ሚሊዮን ብር አለን አሁንም ታግሰን ክፍያው እንዱሰጠን እየጣርን ነው ለሚድሮክ ግሩፕ ተቋማት
ከ8 ጊዜ በላይ በደብዳቤ ጠይቀን ምላሽ የለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ከሜዳ ችግር ዙሪያ እንደተገለፀው ” እውነት ነው ሜዳ ቸግሮናል ያንን ሜዳ ለማሰራት ሜድሮክ ወደ 400 ሚሊዮን ብር በጅቶ ቢንቀሳቀስም አልተሳካም በአሁኑ ወቅት 1.2 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ይህንን ማድረግ ግን አልቻልንም ከዚህም በላይ የሊጉ ውድድር ተዟዙሪ ቢሆን ኖሮ ከ30 ጨዋታ በ 15ቱ የሜዳ ገቢ ይኖረን ነበር በአሁኑ ፎርማት የሆቴልና ሌሎች ወጪዎች ከፍተኛ ሆኖብናል ተጨዋቾቻችንን በዲሲፕሊን ደረጃ መቆጣጠር አልቻልንም” ያሉት አቶ ዳዊት በተለይ ክለቡን ለቅቀው ስለወጡ ተጨዋቾች እንደገለጹት ” ተጨዋቾቹ ክለባችንን ለቅቀው የወጡት በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በእኛም በኩል ውል ማደስ ስለማንፈልግ ነው አጎሮ ለተሻለ ለውጥ ተጓዘ ቻርለስን ስላልፈለግነው ውል አላደሰም በዝውውር ላይም መጣን ብለንው የቀሩ ተጨዋቾች አሉ ከውጪ ሞክረን እንመጣለን ብለው ሳይመጡ የቀሩ አሉ እውነቱ ይህ ነው
ከውጪ ተጨዋች አመጣችሁ ለተባለው ኮታ ስላለ ከ3ቱ ውጪ አላመጣንም ምክንያቱ ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ ያለው ውድድራችንን ከፍ ለማድረግ ነው በሀገር ውስጥ ለሚካሄደው ውድድር የኛ ሀገር ተጨዋቾች በቂ ናቸው ከክፍያ ጋር ተያይዞ የተጋነነ ክፍያ አለ ብለን አናምንም
በኛ በኩል ሶስት አይነት የደመወዝ ክፍያ መንገድ አለን 1ኛ ደረጃ ሲኒየር ለሆኑና ኮከብ ለሆኑ 2ኛ ደረጃ ሲኒየር ተጨዋች ሆነው ከክለቡ ጋር የቆዩ የመጨረሻው 3ኛ ደረጃ ከቢ ቡድን ያደጉ ብለን እንደየደረጃቸው እንከፍላለን” ሲሉ አስረድተዋል።
ከፋይናንሺያል ፌርፕሌይ ህግ ጋር ተያይዞ የተጠየቁት አቶ ዳዊት ” እውነት ነው ህጉ ይኑር ብለን ለአመታት ጨቅጭቀን መልስ አጥተን ኖረናል ዘንድሮ በሊጉ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ባሉት ክለቦች መሃል ያለው ልዩነት 300ሺህ ብር አይሞላም በ1ኛና በ16 ኛ ደረጃ ባሉ ክለቦች መሃል ያለው የገቢ ልዩነት 3 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው ልዩነቱ ማነሱ ልክ አለመሆኑን ነግረናል ጥሩው ነገር ከፋይናንሺያል ፌርፕሌይ ህግ አንጻር ምላሽ አግኝተን ህጉ እየተጠና ስለሆነ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ያሳውቃሉ ብዬ አምናለሁ” ሲሉ አብራርተዋል። አቶ ዳዊት ያለፉት አመታትን የማርኬቲንግ ጥረታቸውና ውጤቱን ሲያብራሩ ” ከኮቪድ በፊትኮ በአመት ሶስቴ ለገና፣ ለፋሲካና ለእንቁጣጣሽ ባዛር እናዘጋጅና በየአመቱ 17 ሚሊዮን ገቢ እናገኝ ነበር በጊዜውም ጥሩ ስራ ሰርተናል አርፈንም አልተቀመጥንም ነበር 1000 ማሊያ በሶስት ሰዓት የሸጥንበት ጊዜም ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።
ከክለቡ ጋር የነበሩ በተፈጠረ ልዩነት ክለቡን የለቀቁ ፍርድ ቤት ድረስ ድረስ የተካሰሱት ደጋፊዎች ዙሪያ በሰጡት ቁጣ የተሞላበት ምላሽ ” 8 አመት ሙሉ ተካሰናል ከአስራ አምስት ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት ቀርበናል ሁሉንም ግን ረተናቸዋል። ክሳቸው ጠቅላላ ጉባኤ አልተጠራም ነው በጎን ጉባኤው እንዳይጠራ የሚያደርጉት እነሱ ናቸው የግል ጥላቻ ክለባችን ላይ አይሰራም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከማንም በላይ ነው ጉዳዩን ከስሩ ገብታችሁ ብታዩት የግለሰብ ጸብ ነው አንድም ቦታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የለበትም ባለብኝ ሃላፊነት የክለቡን መብት ለማስከበር የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” ሲሉ አቶ ዳዊት ውብሸት ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ዳዊት በሰጡት ማጠቃለያ “ለ15 ቀናት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ የሚዲያ አጋር ለመሆን የተስማማው ዓባይ ቲቪን እናመሰግናለን 1 ሚሊዮን ተከታይ ባለው የፌስቡክ ፔጁና ሌሎች መንገዶች ከኛ ጋር ሊሰራ በመዘጋጀቱ ተደስተናል በክለባችን ማህበረሰብ ስምም እናመሰግናለን” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።