ለዋሊያዎቹ የኮቪድ 19 ምርመራ ዛሬ በጁፒተር ሆቴል ይደረጋል

 

“ማንም ይመረጥ ማንም ሀገሩን ለሚያስቅድምና ለወዳጆቼ ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅቻለሁ”
ዳዊት እስጢፋኖስ

በአዲሱ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ የተደረገላቸው ተጨዋቾች ዛሬ በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ይሰባሰባሉ፡፡ ከሽመልስ በቀለና ከመስፍን ታፈሰ ውጪ 39 ተጨዋቾች ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 23/2013 ጠዋት ጽ/ቤት በመገኘት ሪፖርት ካደረጉበ በኋላ ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀው ስፍራ የፊዚካል ፊትነስ ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ በወጣው ፕሮግራም መሠረት ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በጁፒተር ሆቴል የኮቪድ 19 ምርመራ እንደሚደረግላቸውና ውጤቱ እስኪታወቅ ከክፍላቸው እንደማይወጡ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ሙሉ አባላቱ በካፍ አካዳሚ ዝግጅታቸው የሚያደርጉ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ታውቋል አሰልጣኝ ውበቱ ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 10/2013 ከኒጀር ጋር ላለባቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ያላቸው የዝግጅት ጊዜ አጭር ቢሆንም የሚችሉትን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ከበርካታ ጊዜያት ተሞክሮ ተጨዋቾች እየተንጠባጠቡ የመምጣት ባህል መስተካከል እንዳለበት ይጠበቃል፡፡ አሳማኝ ከሆነ ችግር ውጪ ቸልተኝነት በታየበት ሁኔታ ተጨዋቾቹ የሚዘገዩ እንዳይሆን አሰልጣኞቹ ጠንካራ የማስገንዘብ ስራ ይሰራሉም ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ጉዳት ላይ የሚገኙ ወይም በኮቪድ 19 ምርመራን ማለፍ ባልቻሉ ተጨዋቾች ምትክ የሚሆኑ ተጨዋቾችን በፕላን ቢ ይያዛሉ ተብሎ እየተነገረ ነው፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ የፊታችን ሰኞ በካፍ አካዳሚ በመቀመጥ ሙሉ ዝግጅቱን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ለምን አልተመረጡም መመረጥ ይገባቸዋል ያሏቸው ተጨዋቾችን መጠቆማቸው መብት ቢሆንም አሰልጣኙ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ትችቶችና የኔ ክለብ ተጨዋች ለምን አልተመረጡም የሚለው ቅሬታን ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ስኬታማ እንዲሆን ሙሉ ድጋፍ ለአሰልጣኞቹ መደረግ እንደሚጠበቅ ተሰናባቹ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ተናግሯል፡፡ አሠልጣኝ ውበቱ አባተም በዚህ ጉዳይ ላይ ሁሉም በጋራ ድጋፍ እንዲያደርግና ከቡድኑ ጎን እንዲቆም መጠየቃቸው ይታወቃል፤ አሰልጣኝ አስራት አባተና አሰልጣኝ አንዋር ያሲን በምክትል አሰልጣኝነት ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት የዋሊያዎቹን ስብስብ በመቀላቀላቸው ጠንካራ የአሰልጣኝ ቡድን ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ2005 የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከመረጧቸው ተጨዋቾች መሀል አንዱ የመሀል ሜዳው ኮከብ ዳዊት እስጢፋኖስ ሆኗል፡፡ በ2003 የኢትዮጵያ ቡና የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ታሪክ ውስጥ አሰልጣኙና ዳዊት አብረው የሰሩ ሲሆን በ2012 የሰበታ ከተማ አባል እንደነበሩና ተጨዋቹ አሰልጣኙ ውበቱ አባተ ካልሆነ ለዋሊያዎቹ አልመረጥም የሚለውን አስተያየቱን ያጠናከረ ሆኗል፡፡ ዳዊት እስጢፋኖስ በመመረጡ ዙሪያ ለሀትሪክ እንደገለፀው “እስከዛሬ በነበረው አለመመረጥ ቅር ሲለኝ ኖሯል፡፡ ተስፋም ቆርጬ ነበር፤ ስሜቴ እንዲህ ቢሆንም አሁን ጊዜው ደርሶ በመመረጤ ተደስቻለሁ፡፡ ከስሜቴ በላይ ሀገሬን አስቀድማለሁ፤ ስትፈልገኝ ዝግጁ ሆኜ ሀገሬን ለማስደሰት እጥራለሁ” ብሏል፡፡ ዳዊት ለሀትሪክ እንደተናገረው “እስካሁን ባለመመረጤ ሲከፉ ለነበሩ አሁን በመመረጤ ለተደሰቱ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ የመመረጥና ያለመመረጥ የእግር ኳሱ አንድ አካል መሆኑን አምናለው፡፡ ዳዊት ባመመረጡ እንደሚቆጨው በችሎታዬ ያመኑትም ሲያስቆጭ ኖሯል፡፡ አሁን ግን ለካሳ ጊዜው ደርሷል፡፡ ባለመመረጤ ሲከፉ ለነበሩ አሁን የደስታቸው ጊዜ በመሆኑ ደስ ብሎኛል፡፡ ለሀገሬና ለወዳጆቼ ሀገሩን ለሚወድና ለሚያከብር ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ሆኛለው፤ ማንም ይመረጥ ማንም ሀገሩን ለሚያስቅድምና ለወዳጆቼ ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅቻለሁ” በማለት ተናግሯል፡፡ “ከዳዊት ጋር የዛሬ አስር አመት ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን ዋንጫ ሲወስድ አብሮት በመሰለፍ ሁነኛ ሚና የተወጣው መስዑድ መሐመድ በመመረጡ አስረኛ አመታቸውን የሚያከብሩበት አስመስሎታል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport