የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ በሚደረጉ 3 ጨዋታዎች ጅማሬውን ያደርጋል። በአ/አ 2 ጨዋታዎች ሲደረጉ በክልል ጎንደር ላይ 1 ጨዋታ የሚደረግ ይሆናል። አ/አ ላይ 9፡00 ሲል ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልድያ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ 7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጅማሬውን ያደርጋል። በኢትዮጵያ ቡና የደጋፊዎች ተቃውሞ እና በአዲስ አሰልጣኝ ታጅቦ እንደሚጀምር ይጠበቃል። በ6ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ወደ ጅማ ተጉዞ በጅማ አባጅፋር የ2-0 ሽንፈትን ሲያስተናግድ ወልድያ ላይ እሁድ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው እና በፀጥታ ችግር ምክንያት ለሌላ ጊዜ የተዛወረው የወልድያ እና የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ጨዋታ ሳይደረግ በመቅረቱ ወልድያ የ7ኛ ሳምንት መርሃ ግብሩን ማካሄድ አልቻለም። ካደረጋቸው 6 ጨዋታዎች 2ቱን በማሸነፍ 2ቱን አቻ በመውጣት 2ቱን የተሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና በ8 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወልድያ በአንፃሩ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች 1 በማሸነፍ 3ቱን አቻ በመውጣት 1 ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ቡና በ2 ነጥቦች አንሶ ማሳካት ከነበረበት 15 ነጥቦች 6ቱን ብቻ ሰብስቦ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አክሊሉ አየነው፣ ክሪዝቶም ንታንቢ እና ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን ከጅማ አባጅፋር ጋር ሲጫወቱ ተጎድቶ ተቀይሮ የወጣው አጥቂው ሳሙኤል ሳኑሚ የመግባቱ ነገር አልተረጋገጠም። ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ርቆ የነበረው አማካዩ መስዑድ መሀመድ ከጉዳቱ በማገገሙ ነገ ይሰለፋል ተብሎ ይጠበቃል። በወልድያ በኩል ተስፋዬ አለባቸው(ቆቦ) እና አዳሙ መሀመድ በጉዳት ብሩክ ቃልቦሬ በህመም የማይሰለፉ ይሆናል።
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ የማነ ወ/ፃዲቅ
11:30 ሲል በሌላ የአ/አ ስታዲየም ጨዋታ የአቋም መዋዠቅ ውስጥ ያለው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከሊጉ መሪ ደደቢት ጋር የሚገናኙበት ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በ7ኛ ሳምንት ከወልዲያ ጋር ሊጫወት ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ጨዋታው ለሌላ ጊዜ መተላለፉ የሚታወስ ነው። በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተጫወታቸው 5 ጨዋታዎች 1 ጨዋታ ብቻ ድል ማድረግ የቻለው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከወራጅ ቀጠናው በ1 ግብ ክፍያ ብቻ ከፍ ብሎ በ5 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ደደቢት በአንፃሩ በ7ኛ ሳምንት በአቤል ያለው ሀትሪክ ታግዞ ሲዳማ ቡናን በሰፊ ግብ ልዩነት በማሸነፍ 13 ነጥቦችን በመሰብሰብ የሊጉ አናት ላይ መቀመጥ ችሏል። በኢትዮ-ኤሌክትሪክ በኩል አዲስ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን በደደቢት በኩል ብርሀኑ ቦጋለ(ፋዲጋ) በጉዳት በነገው ጨዋታ የማይገባ ይሆናል።
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ ፌ/ዳኛ ሳህሉ ይርጋ
በዚሁ ቀን ክልል ላይ 1ጨዋታ ሲደረግ ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ከተማን የሚያስተናግድ ይሆናል። በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ በሜዳው ሲቸገር የተስተዋለው ፋሲል ከነማ በ7ኛ ሳምንት ጨዋታው ወደ አዳማ ተጉዞ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለምንም ግብ አቻ መለያየት ችሏል። ሀዋሳ ከተማ በሀዋሳ ስታዲየም ድሬዳዋ ከነማን አስተናግዶ በድንቁ አማካይ ሙሉዓለም ረጋሳ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል እንደቻለ ይታወሳል። 1 ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ፋሲል ከነማ በ10 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ሀዋሳ ከተማ በእኩል 10 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበልጦ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በፋሲል ከነማ በኩል ቅጣት ላይ የነበረው አብዱራህማን ሙባረክ(ግሪዳው) ቅጣቱን በማጠናቀቁ በነገው ጨዋታ የሚሳተፍ ይሆናል። ያሬድ ባየህ በረጅም ጊዜ ጉዳት ምክንያት የማይሳተፍ ይሆናል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ እስራዔል እሸቱ፣ ዳንኤል ደርቤ እና ተክለማርያም ሻንቆ በጉዳት የማይገቡ ይሆናል።
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ ፌ/ዳኛ ተፈሪ አለባቸው
[team_standings id=”6559″ title=”የኢትዮጵያ ኘሪሜየር ሊግ ደረጃ ሰንጠረዥ ” number=”16″ columns=”p,gd,pts” show_team_logo=”1″ show_full_table_link=”0″ align=”none”]
አስተያየት ይስጡ