“የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ዘንድሮ ማንሳት የግድ ይለናል”ሳምሶን ጥላሁን /ደደቢት/


የደደቢቱ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሳምሶን ጥላሁን ወይም ደግሞ እንደ ብዙዎቹ አሰያየምም ሳሚ ባሪያው ተብሎ የሚጠራው ይኸው ተጨዋች የእግር ኳስን በክለብ ደረጃ መጫወት የጀመረው በቅድሚያ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ካለፉት ሁለት ዓመታቶች አንስቶ የደደቢት ቡድን ውስጥ በመግባት ለክለቡ ስኬታማ ግልጋሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በልዩ ስሙም የአዲስ ከተማ አካባቢ በመወለድ የእግር ኳስን አሀዱ ብሎ መጫወት የጀመረው ይህ ወጣት ተጨዋች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደረጃ ብዙዎቹ ተመልካቾች አጨዋወቱን የሚያደንቁለት ሲሆን በተለይ ደግሞ ከቀድሞ ጊዜ ተጨዋቾች ውስጥ ብዙዎቹ ተጫወተው ያሳለፉ ተጨዋቾች የችሎታው አድናቂ እንደሆኑ ሲናገሩ እና እንቅስቃሴውንም ሲያበረታቱለት እንደነበር ለመመልከት ችለናል፡፡ የደደቢት የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ወደ ቡድኑ ከገባ ጀምሮ የእግር ኳስ ብቃቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ በመጓዝ ላይ ሲሆን ተጨዋቹ ይህንን ብቃቱን አሳድጎ በመጓዝም ክለቡን ለድል ለማብቃት እና የዘንድሮውም የሊጉ ሻምፒዮና ቡድናቸው እንደሚሆንም ይናገራል፤ የደደቢቱ  ሳምሶን ጥላሁን በአሁን ሰአት  63 ኪ.ግራም የሚመዝን ሲሆን 1.73 ሜትርም ይረዝማል፡፡ ከእዚህ ተጨዋች ጋር የቤስት ስፖርት መፅሔት የስራ ባልደረባ እና አዘጋጅ የሆነው መሸሻ ወልዴ /ጂ ቦይስ/  በኳስ ሕይወቱና በሌሎች ተዛማች ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን ያደረገ ሲሆን አጠቃላይ ምልልሱም የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ለቤስት ስፖርት መፅሔት ቃለ-ምልልስን ለመስጠት ፍቃደኛ ስለሆንክ ከልብ እናመሰግናለን

እኔም በተወዳጇ መፅሔታችሁ ላይ እንግዳ አድርጋችሁ ስላቀረባችሁኝ ከልብ አመሰግናችኋለው፡፡

ስለ ስሙ የመጠሪያ ስያሜ እና ማንስ ስሙን እንዳወጣለት

ሳምሶን የሚለውን ስም ያወጣልኝ የአባቴ አባት የሆነው አያቴ ነው፤ ስያሜውን ለምን  እንዳወጣልኝ ግን አሁንም ድረስ ለማወቅ አልቻልኩም፤ ከእዚያ ውጪ ሌላ የምጠራበትም የቅፅል ስም አለኝ ‘ሳሚ ባሪያው‘ የሚል እንደውም ብዙዎች በእዚሁ ነው ከስሜ በላይም የሚጠሩኝ፡፡

ስለቤተሰቦቹ ብዛትና አኗኗር

በእኛ ቤተሰብ ውስጥ እናትና አባቴን ጨምሮ አምስት ሰዎች ነው የምንኖረው፤ ሁለት እህቶች አሉኝ፤ እኔም የመጀመሪያው ልጅ ነኝ የአኗኗራችንን ሁኔታ በተመለከተ ሁለቱ እህቶቼ ተማሪዎች ሲሆኑ እናቴ የቤት እመቤት ናት፤ አባቴ ደግሞ የግል ስራ በመስራት ላይ ነው የሚገኘው፤ እኔም የእግር ኳሱ ላይ የተሰማራሁ ነኝና የአኗኗር ሁኔታችንን በተመለከተ ፈጣሪ ይመስገነውና ደህና ነን፡፡

የእግር ኳስ ጨዋታ አጀማመሩ ላይ ተምሳሌት ስላደረገው ተጨዋች

የልጅነት ዕድሜዬ ላይ ኳስን በሰፈር ደረጃ መጫወት ስጀምር ለእኔ ሮል ሞዴል ወይም ደግሞ ተምሳሌቴ የሆነኝ ተጨዋች ከቤተሰባችን አባላት ውስጥ አንዱ የሆነው ሙሉቀን ወ/ዮሃንስ ነው፤ እሱ የእናቴ ወንድም እና አጎቴም ነው፤ እንደወንድሜም ነው የምመለከተው፤ ልጅ ሆኜም የእሱን ጨዋታ በማየትም ነው ላደንቀው እና ተምሳሌትም ላደርገውም የቻልኩትና ያንን ወቅት መቼም ቢሆን አልረሳውም፡፡

ሙሉቀን ወ/ዮሃንስ /ዣንቫልዣ/ በጊዜው ተደናቂ ችሎታ የነበረው ተጨዋች ነበር፤ የእሱን ብቃት የቱን ያህል ነበር ልትመለከተው የቻልከው?

የእኔ አጎት እና ወንድሜ የሆነውን ሙሉቀን ወ/ዮሃንስን ያኔ ልጅ ሆኜ ትንሽ ትንሽ  የተመለከትኩትና ያስታወስኩት  ለብርሃንና ሰላምና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድኖች ሲጫወት ነው፤ ከብርሃንና ሰላም በተሻለ ግን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ውስጥ እያለ የነበረውን ችሎታ ነው ትንሽ አድጌም ስለነበር ይበልጥ የእሱን ችሎታ ለማስታወስ የቻልኩትና ጥሩ ችሎታ እንደነበረው አውቃለው፤ ያኔ ከእሱ ችሎታ ውስጥ በተለይ ከርቀት ይመታቸው የነበሩትና ያስቆጥራቸው የነበሩትም ግቦች ማራኪ ነበሩ፤ የወቅቱ ሹቶቹም እጅግ አስገራሚ ከባድ እና የመደፍም ያህል ድምፅ የነበራቸውም ነበሩ፤ ከእዚያ ውጪ ፈጣን እና ጥሩ ጉልበትም ያለው ተጨዋች ነበርና በልጅነት አህምሮዬ ያንን ያህል ልመለከተው በቅቻለው፡፡

የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ ስትጫወት ዛሬ ለደረስክበት ደረጃ የተደረገልህ ድጋፍና አስተዋፅኦ ነበር?

የታዳጊነት ዕድሜዬ ላይ ኳስን ስጫወት ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ለእኔ ትልቁን አስተዋፅኦን ካበረከቱልኝ አባላቶች መካከል በዋናነት የምጠቅሰው አጎቴን ሙሉቀን ወ/ዮሃንስን ነው፤ የመጀመሪያው የእሱ የእግር ኳስ ተጨዋች መሆን እኔን ወደዚሁ ስፖርትና ሙያው እንድሰማራ እና እንድሳብ አርአያ ሊሆነኝ ችሏል፤ ከእዚያ ውጪ እሱ በሚጫወትበት ሰዓትም ለእኔ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማለትም እንደትጥቅ እና ሌሎች መሰል ነገሮችንም በመስጠት ጥሩ የሚባል ድጋፍ እና እገዛ ያደርግልኝ ስለነበር በእዚሁ አጋጣሚ አጎቴን ሙሉቀንን በጣም ነው ለማመስገን የምፈልገው፤ በጥሩነታቸው ሌሎቹ የምጠቅሳቸው ደግሞ ቤተሰቦቼንም ጭምር ነው፡፡

በእግር ኳስ ተጨዋችነትህ ላይ ቤተሰቦችህ አካባቢ ስላለው ፍላጎት

በጣም የሚገርምህ ነገር የእግር ኳሱን ያኔ በመጫወቴ የእኔ ቤተሰቦችን ከሌሎች አንፃር ስመለከታቸው በጣም የሚለዩ ሆነው ነው ያገኘዋቸው፤ ምንአልባት ሙሉቀን ወ/ዮሃንስን እግር ኳሱ ጥሩ ደረጃ ላይ ስላደረሰው  አስበው ሊሆን ይችላል እኔን በኳሱ ላይ ከልጅነቴ አንስቶ ሳይጫኑኝ እንድጫወት ይፈቅዱልኝ የነበሩት፤ ያኔ እነሱ ትምህርቴንም እንድማርም ይፈልጉ ነበርና አንዳችም ተፅዕኖ ሳይፈጥሩብኝ ነው የእግር ኳስን በመጫወት ያደግኩት እና የእነሱም አስተዋፅኦ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ አባቴ ወጣትም ስለነበር ትምህርቴን እየተማርኩ በነበርኩበት ሰአት እኔን የቱን እነደምመርጥ ካናገረኝ በኋላ ኳስን ብዬ ስለነገርኩት ያንን ምርጫዬንም ፈቅዶ ነው ኳሱንም እንድቀጥልበት ያደረገኝና የእሱም  ድጋፍ  የማይረሳ ነው፡፡

የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ ስትጫወት ስላጋጠመህ የተለየ ሁኔታ

የእግር ኳስን አፍቅሬ እና ወድጄው ከመጫወት ውጪ ብዙም አስገራሚ ሁኔታ አላጋጠመኝም፡፡

በእግር ኳሱ ስለወጣበት የአዲስ ከተማ አካባቢየትውልድ ስፍራዬን አዲስ ከተማን በጣም የምወደው እና ዛሬ ለደረስኩበትም ደረጃ ያበቃኝ ቦታ ነው፤ ይህ አካባቢም እስከ አብነት በሚወስደው መንገድም ከእዚህ ቀደም አጎቴን ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን ለሀገራችን እግር ኳስም ያፈራም ሰፈር ነውና  ከእዚህ አካባቢም በቅርብ ጊዜ ውስጥ  በመውጣቴ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ ሰፈሩን በተመለከተ ዓለሙን ሜዳ ጨምሮ ጥሩ ጥሩ የመጫወቻ ሜዳዎች ነበሩት፤ ከአካባቢውም የአሁን ሰአት ላይም በተወሰነ መልኩም ጥሩ ጥሩ ልጆችም እየወጡ ነውና ይሄ መሆኑ በቀጣይ ለሚመጡ ወጣቶች ጥሩ መነሳሻ ነው የሚሆንላቸው፡፡

የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮስ ትምህርቴን ከመማር ውጪ ሌላ ሙያ ላይ አልገባም ነበር፤ ጊዜዬንም ከአባቴ ጋር ምን አልባት ስለነበር ምንአልባት ውጪ አገር ልሄድ እችል ይሆናል፡፡ የእናንተ አካባቢ አብዛኛው ወጣቶች በንግድ ሙያ ላይ የተሰማሩ ናቸው፤ አንተስ ንግድን አልሞከርክም?

የእግር ኳስን ከመጫወት ውጪ የንግድ ሙያ ላይ አንድም ቀን ተሰማርቼ አላውቅም፤ በእርግጥ የእውነት ነው የእኛ አካባቢ ላይ ብዙዎቹ ወጣቶች የንግድ ሙያው ላይ የተሰማሩ ናቸው፤ እኔ ግን ከኳሱ ውጪ ጊዜዬን ከአባቴ ጋር አልያም ደግሞ እቤቴ ነው የማሳልፈው፡፡

የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ ስትጫወት ለዛሬ እውቅና እበቃለው ብለህ አስበህ ነበር?

እንደራሴ እምነት እና እንደነበረኝ ጥሩ የኳስ ችሎታ አዎ! ጥሩ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ሰዎች ደግሞ ስለ ጥሩ ችሎታዬ ተጨማሪ ነገሮችን ሲነግሩኝ እና ሲመክሩኝም እንደዚሁም ደግሞ ጥሩ ደረጃ ላይም ትደርሳለህ ሲሉኝም አሁን ላይ እንዳሰብኩት ስፍራም ላይ ነው የደረስኩት፡፡

የእግር ኳስን ስትጫወት ስላለ ጠንካራ እና ደካማ ጎን

የእግር ኳሱን እየተጫወትኩ ያለሁበት የአሁን ሰአት ላይ የእኔን ጠንካራ ጎን ብዬ የማስበው ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ለጓደኞቼ በተስተካከለ መልኩ ፓስ አድርጌ ከማቀበል አንስቶ ኳስን የምቆጣጠርበትና ከባላጋራ ተጨዋቾች ላይም የምነጥቅበት የቴክኒክ ብቃቴን የምጠቅሰው ነው፤ የእኔን ደካማ ወይም ደግሞ ክፍተት አለብኝ በማለት የማስበው ደግሞ እንደማንኛውም የእግር ኳስ ተጨዋች ፍፁም ስላልሆንኩ ከአነስተኛ ሰውነቴ አኳያ በአካል ጥንካሬዬ ላይ ሙሉዕ ያልሆንኩ መሆኑ ነው፤ እዚህ ላይ ግን ምን አልባት ከዕድሜዬ ወጣትነት አኳያም ሊሆን ይችላል ክፍተቱ ሊፈጠር የቻለው እና እድሜዬ እየጨመረ ሲሄድ ይህንን ክፍተት ልደፍነው እችላለሁና የአካል ብቃቱ ላይ አነስ ማለቴ ብቻ ክፍተቴ ስለሆነ ይህን አሁን እየሰራሁት ባለው ልምምዴ በሚገባ ችግሬን አስተካክዬ እቀርባለሁ ብዬ አስባለው፡፡

የእግር ኳስን ካለህ አነስተኛ ሰውነት አንፃር ከባላጋራ ተጨዋቾች ላይ ነጥቀህ የምትጫወትበት መንገድ ብዙዎችን ያስገርማል፤ ድፍረትህ እና አይበገሬነትህም በጥሩ መልኩም ይጠቀስልሃልና በእዚህ ዙሪያ ምን ማለት ትችላለህ?

የእግር ኳስ ሜዳው ላይ እኔ ሁሌም ከአካል ብቃቴ ትንሽነት በመነሳት ኳስን በድፍረት የምነጥቅበት መንገድ እና ተሯሩጬም የምጫወትበትን ሁኔታ ብዙዎች ያወሩኛል፤ እንዴት ነው በእዚህ ሰውነትህ ኳስን የምትነጥቀው፤ እንዴት ነውስ ከአቅም በላይም ሆነህ በመልፋት የምትጫወተውም ይሉኛል፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታን ግን የምትጫወተው ሰውነትህ ስለገዘፈህ ብቻ አይደለም፡፡ ጥንካሬም ያስፈልግሃል፡፡ እኔ ለምሳሌ ሰውነቴ አነስተኛ ቢሆንም ጥንካሬው አለኝ ያም ነው የሚያጫውተኝ፤ ጥንካሬውንም ከተፈጥሮ ይሁን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተጨዋች በነበርኩበት ጊዜ ያገኘሁት ያ እየጠቀመኝ ነው እየተጫወትኩ ያለሁት እና ይበልጥ ጠንካራ ለመሆን ደግሞ ወደፊትም  የማስብ ስለሆንኩ ሌሎች ልምምዶችን እሰራለሁኝ፡፡


የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ለመጀመሪያ ጊዜ ስለተቀላቀለበት ሂደት

ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትኩበት ቡድኔ ነው፤ ወደዚሁ ቡድንም ልመጣ የቻልኩት በሰፈር ፕሮጀክት ደረጃ ለመርካቶ ዩኒየን ፕሮጀክት ከተጫወትኩ በኋላ የቡድኑ አሰልጣኝ የነበረው ተሻለ ምንዳዬ ጠርቶኝም ነው፤ እሱ ያኔ የመርካቶ ዩኒየን ፕሮጀክት አሰልጣኝ ስለነበር እኔን ከሰፈር ላይ ጠርቶና በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ውድድርም ላይ እንድጫወት አድርጎኝም ነው  ካሳየሁት እንቅስቃሴ በመነሳት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዋናው ቡድን እንድጠራ ያደረገኝ፤ ቅዱስ ጊርጊስ ስገባ በወቅቱ በጣም ልጅም ነበርኩና ሄጄ ልምምድ ሁሉ ሰራሁኝ የዋናው ቡድን መሆኑን ግን በፍፁም አላመንኩም ነበርና በድጋሚ ሲጠሩኝ አልሄድኩም በኋላ ላይ ልጅ ስለነበርኩና ምንም ነገርንም ማመን ስላልቻልኩ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ እና ወጣት ቡድን ትፈለጋለህ ተብዬ ስጠራ ወደዚያው ሄድኩና የክለቡ ተተኪ ቡድን ውስጥ ገብቼ መጫወት ቻልኩኝ በፍጥነትም  ወደ ዋናው ቡድንም አስገቡኝ፡፡

ለቅዱስ ጊዮርጊስ የዋናው ቡድን ሲያድግ ስለተፈጠረበት ስሜትና በክለቡ ስለነበረው አጠቃላይ ቆይታ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በሀገሪቱ ውስጥ ትልቅ የሆነ ቡድን ነው፤ የእዚህ ክለብ ውስጥ ታዲያ ወደ ዋናው ቡድን ከማደግ ባሻገር ከነበሩት ሲኒየር ተጨዋቾችም ጋር በፍጥነት በመግባባት የቡድኑን ማሊያ አድርጌ ልጫወት በመቻሌ በወቅቱ የተሰማኝ ስሜት የላቀ እና ከፍተኛ ነበር፤ በቡድኑ በነበረኝ አጠቃላይ ቆይታዬም በጣም ደስተኛም ነበርኩ፤ በቡድኑ ውስጥ ከተደሰትኩባቸው ምክንያቶች ውስጥም ለቡድን ተሰልፌ ስጫወት በሜዳ ላይ ያለኝ አቅም የቱን ያህል እንደሆነም  በሚገባም ራሴን የተመለከትኩበት ወቅት ስለነበር ጥሩ ቆይታው ነበረኝ፤ ክለቡ ዛሬ ላይ ጥሩ ደረጃ ላይም እንድደርስ  መነሻዬም የሆነኝና ያሳደገኝም ቡድን ነው በተለይ ደግም ለእኔ ወደ ዋናው ቡድን ማደግም ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ዶሴና የፈጠረልኝ ነገርም በጣም ጥሩ ስለነበር የክለቡን ቆይታዬ በአጠቃላይ  ለሁለት ጊዜያት ያህልም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አንስቼም የለቀቅኩት ቡድን ስለሆነ ያንን ወቅት ፈፅሞ አልረሳውም፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ጋር ስለመለያየቱ ሚስጥር

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ጋር ስለተለያየሁበት ምክንያት ስዎች ብዙ ነገርን ሊሉ ይችላሉ የእኔ ግን ከቡድኑ መለየት እውን የሆነው በጊዜው ቡድኑ ጣሊያናዊውን አሰልጣኝ አሰናብቶ እና አዲሱን ጀርመናዊም አሰልጣኝ ማርቲን ክሩገርን አሰምጥቶ ስለነበር ከእሱ ጋር በጨዋታ ዘይቤ ላይ ልንስማማ ባለመቻላችን ነው፤ ያኔ እኔ የልጅነቱ ባህሪ ስለነበረብኝና ተሰልፎ መጫወትንም ስለፈለግኩትም ነው ከእሱ ጋር ሳንስማማ በመቅረቴ ከቡድኑ ጋር የተለያየሁት፤ ክለቡ ግን እኔን በወቅቱ እንደአሁኑ ሁሉ በጣም ይፈልገኝ እንደነበር ነው የማውቀውና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያኔ የተለያየሁት በሌሎች ምክንያቶች ሳይሆን ከአሰልጣኙ ጋር ብቻ ባለመስማማቴ ነበር፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ አድገህ ስትጫወት የሀገሪቱ ትላልቅ ተጨዋቾችን አግኝተህ ነበርና ከእነሱ ጋር ያለህስ ግንኙነት የቱን ያህል ነበር?

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ውስጥ በፕሪምየር ሊጉ ደረጃ ላይ አድጌ ስጫወት በወቅቱ 18 አመቴ ላይ ነበርኩ፡፡ ያኔ ክለቡን ተቀላቅዬ ስጫወትም የቡድኑ ልምድ ያላቸው እና ሲኒየር የሆኑትም ተጨዋቾች እኔ ላይ በችሎታዬ ጥሩ ነገርን ስላዬ ለቡድኑ ተሰልፌ እንድጫወት ፍላጎትን ሲያሳድሩ ነበር የተመለከትኩት፤ በወቅቱ የቡድኑ ተጨዋቾች ማለትም እነ ደጉ ደበበ፣ ሳምሶን ሙሉጌታ ፍሌክስ፣ ሚካኤል ደስታ /ጣሊያን/ እና የመሳሰሉት ተጨዋቾች ኳስ የሚችል እና ታለንት ያለው ሰው ይጫወት የሚልም አመለካከት ስለነበራቸው ያ ፍላጎታቸው ደስም ይል ነበርና እኔም ያኔ ለብዙ ጊዜያቶች ባልቆይም በጥሩ መልኩ ነው ቡድኑ ውስጥ ለመጫወት የቻልኩት፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስን በሚመለከት ልጅ ሆነህ የቱን ያህል ግንዛቤው ነበረህ?

የታዳጊነት ዕድሜዬ ላይ እያለሁ በሰፈር ውስጥ ኳስን ከመጫወት ውጪ ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙም ግንዛቤው አልነበረኝምና በእዚሁ ዙሪያ ምንም የምለው ነገር የለኝም፡፡

ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ያደረግከው የመጀመሪያ ጨዋታህ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስን መለያ በማጥለቅ የመጀመሪያዬን ጨዋታ ያደረግኩት ከደደቢት ጋር  በነበረው የ2003ቱ የፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ነው፤ ያኔም ቡድናችን ግጥሚያውን ምንም እንኳን 3-1 ሲሸነፍና ብበሳጭም የታላቁን ቡድን መለያ በትልቅ ጨዋታ ላይ አድርጌ መጫወቴ ግን እንድደሰት አድርጎኝ ነበር፡፡

የደደቢት ቡድን ውስጥ ዝውውር ካደረግክ በኋላ እስከአሁን ስለነበረህ አጠቃላይ ቆይታህስ ምን የምትለው ነገር አለ?

የደደቢት ክለብ ውስጥ ከገባሁ ጀምሮ ያለኝ ቆይታ ጥሩ የሚባል ነው፤ በቡድኑ ውስጥ ተደጋጋሚ የመሰለፍ እድልንም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በተሻለ ማግኘትም ችያለውና ያ  ችሎታዬን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዳሻሽል እና እንዳሳድግ በጣሙን ረድቶኛል፤ደስተኛም አድርጎኛል፤ የክለቡ ውስጥ ባለኝ የእስካሁን ቆይታም እኔ ከተጨዋቾች አንስቶ እስከ አመራሮች ጋርም ጥሩ ግንኙነት ነው ያለኝ እና ይህንንም ብቃት  አጠናክሬ በመጓዝ ቡድኑን ለተሻለ ደረጃ ማብቃት ከፍተኛ ፍላጎቴ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንጂ ከደደቢት ጋር አላነሳህምና፤ በእዚህ ዙሪያስ ምን የምትለው ነገር አለ?

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ውስጥ በነበረኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ የሊጉን ዋንጫ ከአንዴም ሁለቴ ነው ለማንሳት የቻልኩት፤ ይሄን ማሳካት መቻልም መታደል ነው፤ የደደቢት ክለብ ውስጥ ደግሞ ከጥሎ ማለፍ ዋንጫ በስተቀር ይህንን የሊጉን ዋንጫ ማግኘት አልቻልኩም፤ ይህም ስለሆነ ከአሁን በኋላ በሚኖሩት የሊጉ ተሳትፎአችን ዋንጫውን የማግኘት ፍላጎቴ ከፍተኛ ነውና ይህንን ዘንድሮ የምናሳካው ይመስለኛል፡፡

ስለደደቢት ክለብ እና ስለዘንድሮው የፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ

የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ከአጭር ጊዜ ምስረታው እና ውስን ከሆነውም የፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎው አንፃር በአሁኑ ወቅት ያለበት ደረጃ ጥሩ የሚባል ነው፤ ይህ ቡድን የረጅም አመታት ምስረታ አድርገው አንድም ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ካላገኙት ቡድኖች በተሻለ እሱ የሊጉን ዋንጫ ማግኘት መቻሉ ሊያስደንቀው ነው የሚገባው፤ የጥሎ ማለፍ ዋንጫውንም ያነሳ ጠንካራ ቡድን ነው፤ የሊጉን ውድድርም ባለፉት ተከታታይ ዓመታቶች ከታች ከመምጣቱ አንፃር ሞቅ ደመቅ እንዲልም ያደረገም ቡድን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የእዚህ ዓመት የሊጉን ጅማሬ በተመለከተ ቡድናችን ከሞላ ጎደል ጥሩ ጅማሬ ነው ያደረገው ብዬ ነው የማስበው፤ ቡድናችን በእዚህ ዓመት እንደ አዲስ የተዋቀረም ከመሆኑ አኳያም በአራት ግጥሚያዎች 7 ነጥብ መያዙም ጥሩ ነው በሂደት ደግሞ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ስንጓዝ ክለባችን ብዙ ነገሮችን በመቅረፍ ይበልጥ ጠንካራውን ቡድን ይፈጥራልና ለእዚያ ነው ልንዘጋጅ የሚገባን፡፡

ብዙዎች ከሜዳ ተቀይረህ ስትወጣ አኩራፊህ ነህ ይሉሃል፤ የእውነት አኩራፊ ነህ?

የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች እያለሁም ሆነ አሁን የደደቢት ክለብ ውስጥ ብዙ ጊዜ እኔ ተቀይሬ የወጣሁበትን ወቅት አላስታውስም ብዙም የማልቀየርም ተጨዋችም ነበርኩ ከተፈጥሮዬ ግን አንዳንዴ የመቀየር ፈንታው ሲደርሰኝ ለእኔ ሁሉም ነገር አዲስ ነው እየሆነብኝ ያለውና ተቀይሬ ስወጣ የሚነበብብኝ ነገር ለእኔ የተለየ አይነት ባህሪ ነው የሆነብኝ እንጂ ሌላ የተለየ ነገር ኖሮብኝ አይደለም፤ ብዙ ጊዜ ተቀይሮ የማይወጣ ተጨዋች ሲቀየር ብዙ ነገሮች አዲስ ነገር ይሆንበታልና እኔንም ያጋጠመኝ ይሄ ነው፤ ያም ሆኖ እኔ አኩራፊ ተጨዋችም አይደለሁም፡፡

የደደቢት ክለብ ውስጥ ስትገባ የተመለከትከውን ነገር ከቀድሞ ቡድንህ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንዴት ታነፃፅረዋለህ?

የደደቢትም የቅዱስ ጊዮርጊስም ቡድኖች ውስጥ በተጫወትኩባቸው ጊዜያቶች የሁለቱ ክለቦች ላይ በተመለከትካቸው ነገሮች ተመሳሳይ የሆኑ ነገሮችን እንጂ ብዙም ልዩነት አላቸው ብዬ የምጠቅሳቸው ነገሮች የሉም፤ ምንአልባት ልዩነት አለ ብዬ ልጠቅስ የምችለው ደደቢት ውስጥ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በተሻለ በነፃነት የእግር ኳስን የምትጫወትበት ሂደት መኖሩ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ግን ቡድኑ ካለው ስምና ዝና አንፃር እንደዚሁም ደጋፊው እና አመራሮቹ ሁሌም ውጤትን ከመፈለጋቸው አንፃር በነፃነት መጫወቱ ላይ የሚቀል ስለሆነ ያንን ልገነዘብ ችያለው፤ የሁለቱ ክለቦች ላይ ያለውን አንድነት በተመለከተ ደግሞ ልናገር የምፈልገው ሁለቱም ቡድኖች ጋር ተጨዋቾችን በጥሩ መልኩ የሚይዙና ጥሩም እንክብካቤን የሚያደርጉ መሆናቸውም ነው፡፡ በሊጉ ተሳትፎአቸውም ሁለቱም ቡድኖች ሩቅና ረጅም ጉዞን መጓዝም ስለሚፈልጉና ሌት ተቀንም ያን ለማሳካት የሚጥሩም ስለሆነ ይህን መልካም ነገርን ነው ልመለከትላቸው የቻልኩት፡፡

የእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ላይ ሆነህ ደስተኛ የሆንክበት እና የተከፋህበት ጊዜ የቱ ነው?

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ስጫወት ያገኘሁት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ በህይወቴ እጅጉን ከተደሰትኩባቸው ጊዜያቶች መካከል የምጠቅሰው ነው፤ ሌላው ደግሞ የምወደውን እግር ኳስ አሁንም እየተጫወትኩ መሆኑ ያስደስተኛል፤ የተጨዋችነቴ ላይ ብዙ ጊዜ የምከፋው ደግሞ የምጫወትበት ቡድን ሽንፈትን ሲያጋጥመው እና ሜዳ ውስጥ ገብቼም ጥሩ ሳልጫወት ስቀር ነው፡፡ ከእዚያ ውጪ ከቤተሰብ ጋር ወይም ደግሞ ከአንድአንድ ሰዎች ጋር ሳልሰማማ የቀረሁበት ቀን ላይ ያኔ ይከፋኛል፡፡

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ ዕድሉን ከእዚህ በፊት ስለማግኘቱ እና አሁን አሁን ላይ ደግሞ የመመረጥ ዕድሉን ስላለማሳካቱ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የመመረጥ እድሉን ያገኘሁት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና  ቡድን አድጌ ገና አራት ጨዋታዎችን እንዳደረግኩኝ ነበር ያኔም በትውልድ ናይጄሪያዊው በዜግነት ደግሞ እንግሊዛዊው ኤፌ ኦኔራ ነበር የ2003 ዓ.ም ላይ የመረጠኝና በወቅቱ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ከእዚያ በኋላም ብዙ ጊዜ እመረጣለሁ፡፡ ያም ሆኖ ግን ጠጋ ብለው ሲያዩኝ ከሌሎች ተጨዋቾች አንፃር በእድሜ ያነስኩ ስለሚሆንባቸው ወደፊት የመጫወት ተስፋ አለው በሚል ወደነበርኩበት ስፍራ ይመልሱኛል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስን  ብዙ ጊዜ እንደተመለከትኩት ለብሄራዊ ቡድን ትመረጥና በዕድሜ ከሌሎች ተጨዋቾች አኳያ አነስተኛ ከሆንክ የመመለስ እድልህ ፈጣን እና ሰፊ ነው፡፡ ወጣት ሆነህ እንድትጫወት በድፍረት እድሉን ሰጥተው አይሞክሩህም፡፡ የውጪም አለም ላይ ስትሄድ ግን ለመጫወት የተጨዋቾች እድሜ ሳይሆን የሚታየው በሜዳ ላይ ልጁ የሚያሳየው ብቃቱ ነውና በእዚህ መልኩ ነው እኔ በተደጋጋሚ ስመለስ እና ያለመጫወት እድሉንም ሳላገኝ የነበረው፤ የወደፊቱ የእግር ኳስ ህይወቴ ላይ ግን የእኔም እድሜ አሁን እየጨመረ ስለሚሄድ ያንን የመመረጥ እና ለብሄራዊ ቡድንም ተሰልፎ የመጫወትም እድልን ላገኝ እችላለሁና ብዙም ተስፋ የምቆርጥ ተጨዋች ስላይደለሁ ጠንክሬ በመስራት እድሉን ለማግኘት ጠንክሬ እሰራለው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የአንተን ጨዋታ ሌት ተቀን በመመልከት ስለጥንካሬህ እና ክፍተቶችህ የሚነግርህ የተለየ ሰው አለ

አዎን፤ የአክስቴ ባለቤት ታደሰ ሽታዬ የሚባል ሰው አለ፡፡ እሱ ነው የእኔን አብዛኛው ግጥሚያዎች በመመልከት ጠንካራና ደካማ ጎኖቼን የሚነግረኝ ከእሱ ባሻገርም አባቴም ብዙ ነገሮችን በመምከር እንድበረታ ያደርገኛል፤ ሌሎችም ሁሌ ባይሆንም አልፎ አልፎ በስልክ  እንዲህ ብታደርግ ብለው የሚያበረታቱኝም ሰዎች አሉና ሁሉንም ማመስገን እፈልጋለውኝ፡፡

የወደፊት የእግር ኳስ ህልሙን በተመለከተ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጫወት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ እኔም የትኛውም ተጨዋች እንደሚመኘው ሁሉ በእግር ኳሱ ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ፍላጎት ስላለኝ ያንን በተደጋጋሚ አስበዋለው፤ የአንድ እግር ኳስ ተጨዋች ዋናው ግቡም ሊሆን የሚገባው ደግሞ የፕሮፌሽናል ተጨዋች መሆንን ነው፤ እኔም ከአንድም ሁለት የውጪ እድሎችን በመሞከር ሳይሳካልኝ የቀረበት ወቅት አለ፤ የመጀመሪያውን እድል ያገኘሁትም ከቱኒዚያው ሴፋክሲያን ቡድን ነበር ሌላው ደግሞ የአረብ አገር ከሆነችው  ኳታር የደደቢት ቡድን ውስጥ እያለሁ ያገኘሁትና በአንዳንድ ሁኔታዎችም ሳይሳካልኝ የቀረውም ነውና የቀጣይ ጊዜ ላይ ግን ይህንን እድል ማግኘቱን በጣሙን እፈልገዋለው፡፡

የደደቢት እግር ኳስ ክለብ የፕሮፌሽናል ተጨዋቹን ጌታነህ ከበደ ስለማግኘቱ እና ከእሱም ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ክለብ ውስጥ ስለመጫወቱ፤ የጌታነህ ከበደን ብቃት ከሌሎች አጥቂዎች ጋር ስታነፃፅረውስ በምን ይለያል…..

የደደቢት እግር ኳስ ቡድን የፕሮፌሽናል ተጨዋች የነበረውን ጌታነህ ከበደን ሊያገኝ መቻሉ ቡድኑን በሁሉም መልኩ ይጠቅመዋል፤ ተጨዋቹ ከወዲሁም ለክለቡ በአራት ጨዋታዎች አምስት ጎሎችንም ሊያስቆጥርለት መቻሉ የልጁን ምርጥ ብቃት ያሳየም ሆኗል፤ ከእዚህ ተጨዋች ጋርም የአሁን ሰአት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የአንድ ቡድን ላይ ሆኜ መጫወት መቻሌን ጥሩ ብቃት ያለው ከመሆኑ አኳያ ወድጄዋለሁ፡፡ የጌታነህ የአጥቂነትን ብቃት በተመለከተ ከሌሎች ተጨዋቾች አንፃር ስመለከተው የራሱ የሆነ ተሰጥኦ አለው፤ የእኛ ቡድን ውስጥ አሁን ለምሳሌ ዳዊት ፍቃዱን ብትመለከት ከፍተኛ ፍጥነት እና ተከላካዮችን አምልጦ የመግባት ብቃቱ አለው፤ ጌታነህ ደግሞ የአጥቂ ስፍራው ኤሪያ ላይ የሚያገኛቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብነት በመቀየር እና አንድ አጥቂ ሊኖረው የሚችለውንም ብቃት በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ በጥሩነት አጥብቄ የተመለከትኩለት ስለሆነ ከሀገሪቱ አጥቂዎች የተለየ ብቃቱን የአሁን ሰዓት ላይ ለመያዝ ችሏል ብዬ ነው የማስበው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከብዙ የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾች ጋር አብረህ የመጫወት እድሉን አግኝተሃል፤ የአማካይነት ሚናው ላይ በጣም የተመቹኝ የምትላቸው ተጨዋቾች የትኞቹ ናቸው….

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ የአማካይ ስፍሪው ላይ ስጫወት ለእኔ የጨዋታ ሚና የተጨዋችነት ብቃቴን ከጎናቸው ሆኜ ስጫወት በጣም እንዳሻሽል የረዱኝ የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾች ሚካኤል ደስታ ጣሊያኑ፣ ታደለ መንገሻ፣ ጋናዊው ሻይቡ ጅብሪል እና  ያሬድ ዝናቡ ናቸው፤ ከእነሱ ጋር በቆየሁባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ደስ የሚል ጊዜንም በተጨዋችነቴ ወቅት አሳልፌበታለውም እላለው፡፡

ከእዚህ ቀደም ወደ ግብ ጠንካራ ምቶችን የመምታት ብቃቱ ነበረህ… እነዚያ ምቶች ከእዚያች ትንሽ እግር ነበር የሚወጡት…

የእግር ኳስ ተሳትፎዬ ላይ ከእዚህ ቀደም ወደ ግብ ጠንካራ ምቶችን ወደግብነት የምመታው የፕሪምየር ሊጉ ውስጥ ሳልገባ በፊት ጀምሮ ነበር፤ ወደ ግብ የምመታቸው ጠንካራ ኳሶችም ከእኔ እግርም የሚወጡም አይመስለኝም ነበር፡፡ ነገር ግን በተፈጥሮዬ ካለኝ ጥንካሬዬ ነው እነዚያን ኳሶች እመታቸው የነበሩት አሁን እንደውም መምታቱ ላይ እንደበፊቱ አይደለውም እና ያን ብቃቴን ተመልሼም ለማምጣት ጥረትን እያደረግኩኝ ነው ያለሁት፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የእዚህ ዓመት አጀማመር እና የቡድኖች ተሳትፎን በሚመለከት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ አመት አጀማመር ጥሩ ነው፤ በየስቴድየሞቹ በርካታ የስፖርት ተመልካቾች በመገኘትም ሜዳውን አጥለቅልቀውት ግጥሚያዎችን እየተከታተሉም ነው፤ ከእዚያ ውጪ የስፖርታዊ ጨዋነትም ላይ ያለው ጅማሬም መሻሻል እየታየበት ነውና ይህ ይባል የሚያሰኝ ነው፤ ሊጉ ከእዚያ ባሻገር በርካታ የውጪ አገር ተጨዋቾችም በየክለቡ ውስጥ እየታዩበት መሆኑም ይህ ውድድርን ከሌላው ጊዜ ለየት እንዲልም እያደረገው ይገኛል፡፡ የሊጉ ተሳትፎን በተመለከተም አሁን ግጥሚያው የአራተኛ ሳምንት ላይ ቢደርስም ጥሩ ፉክክር እየታየበት ነው፤ በተወዳዳሪ ክለቦች መካከልም የነጥብ ልዩነቱ ብዙም የተራራቀ አይደለምና ከእዚህ በኋላም ጥሩ ነገር ይኖራል ብዬም ነው የማስበው፡፡

በውጪ ሀገር እና በሀገር ውስጥ አሰልጣኞች ስለሰለጠንክ ስላለው ልዩነት ምን ትላለህ…

በውጪና በአገር ውስጥ አሰልጣኞች መግባት ስትስጠኝ ልዩነት ያለ ቢሆንም የውጪወቹ ትንሹ ከቆዩ በኋላ እንደአበሾቹ ነው የሚሆኑት ካሰብነው አንዳንዳች ብቻ በሙሉ ትኩረት ሊጓዙ ቢሞክሩም ከክለቡ ሲሰናበቱ ይታያል፡፡ የአገር ውስጥ ጥሩ ጥሩ አሰልጣኞች አሉ፡፡

የግል ህይወቱን በሚመለከት

የግል ሕይወቴን በተመለከተ ጋብቻዬን ያልፈፀምኩ ቢሆንም ምርጥና በጣም የምወዳት ፍቅረኛ አለችኝ፤ ሊዲያ ሳሙኤል ትባላለች፡፡ እሷን ስገልፃትም በጣም ጥሩና የምወዳትም ልጅ ነች፤ ለእኔ የምትሆንና በጣምም ተስማሚዬም ናትና ከእሷ ጋር ወደፊት ጋብቻችንን የምንፈፅምም ይሆናል፡፡

የደደቢት እግር ኳስ ክለብ የእዚህ አመት ላይ ምን ውጤት ያመጣል ብለህ ትጠብቃለህ…

የደደቢት እግር ኳስ ክለብ የአሁኑ ሰአት ላይ  ያለው የሊጉ አጀማመር በጣም ጥሩ ነው፤  የአሁኑ ሰአት ላይ በእያንዳንዱ ተጨዋቾች ላይ ከሚታየው ከፍተኛ የአሸናፊነት መንፈስ አኳያም ቡድኑን ሳየው ዘንድሮ ቡድናችን የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ነው የሚጫወተው፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች የቴክኒካል ችሎታ አላቸው የላቸውም የሚሉ አካላቶች ተፈጥረዋል አንተ መን ትላለህ

የኢትዮጵያን በአሁን ሰአት እግር ከስ ተጨዋች ያላቸው የቴክኒክ ችሎታ በጣም የተጋነነ ሳይሆን ለእራሳቸው ግን በቂ የሆኑ ቴክኒካል አላቸው በእዚህ በላይ ጠንከሮ ከተሰራ ደግሞ ሙሉውን ቴክኒካል ማምጣት የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለምና እዚያ ላይ ነው መስራት የሚያስፈልገው፡፡የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች የቴክኒካል ችሎታ አላቸው የላቸውም የሚሉ አካላቶች ተፈጥረዋል አንተ መን ትላለህ

የኢትዮጵያን በአሁን ሰአት እግር ከስ ተጨዋች ያላቸው የቴክኒክ ችሎታ በጣም የተጋነነ ሳይሆን ለእራሳቸው ግን በቂ የሆኑ ቴክኒካል አላቸው በእዚህ በላይ ጠንከሮ ከተሰራ ደግሞ ሙሉውን ቴክኒካል ማምጣት የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለምና እዚያ ላይ ነው መስራት የሚያስፈልገው፡፡

የስፖርታዊ ጨዋነትን በሚመለከት ከአንተ አንደበት አንድ ነገርን ብንሰማ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የስፖርታዊ ጨዋነት እንዳብር ሁሉም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ እርብርቮሽ ሊይደርግ ይገባው የሜዳ ላይ ጨዋታ ውበት ደጋፊወች ቡድናቸውን ብቻ ሲያበረታቱና ተጨዋቾቹን ባይሰድቡ ተጨዋቾችም ተመልካቹን ለፀብ የሚያነሳሳ ነገርን ባይጠቀሙ ጥሩ ነው አሁን ለይ ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማስፋት እየታየ ያለው ጅማሬ ጥሩ የሚባል ነውና ይህ የሚቀጥል ከሆነ የአገርንም እግር ኳስ ለማሳደግ ያስቻለልኝ ሁሉም ከዚያ ላይ ትኩረት ባያደርግ ጥሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በአደጋገፍ ድባብ የየቱ ክለብ ደጋፊዎች ቀልብህን ይስቡታል…

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ስጫወት እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎችም ተጨዋቾች ሲናገሩ እንዳዳመጥኩት በድጋፍ ድባብ ደረጃ ሜዳ ውስጥም ሆነን ስንጫወት ከሜዳ ውጪም ሆነን ኳስን ስንመለከት ቀልባችንን በጭፈራ የሚገዙት ደጋፊዎች የኢትዮጵያ ቡና ናቸው፤ ይህንንም በተደጋጋሚም ነው የተመለከትኩት፡፡
የስፖርታዊ ጨዋነትን በሚመለከት ከአንተ አንደበት አንድ ነገርን ብንሰማ….

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የስፖርታዊ ጨዋነት እንዲዳብር ሁሉም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ እርብርቦሽን ሊያደርጉ ይገባል፤ ደጋፊዎች የሜዳ ላይ ውበት ስለሆኑ ሁሌም ቡድኖቻቸውን ብቻ ተመልክተው ሊያበረታቱት ይገባል፤ ደጋፊዎች ተጨዋቾችን ባይሳድቡ ጥሩ ነው፤ ተጨዋቾችም ተመልካችን ለፀብ የሚያነሳሳ ነገርን ባይጠቀሙ ጥሩ ነው፤ አሁን ላይ ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማስፈን እየታየ ያለው ጅማሬ ጥሩ የሚባል ነው፤ ይህ የሚቀጥል ከሆነም የአገርንም እግር ኳስ ለማሳደግ ያስችላልና ሁሉም በዚያ ላይ ትኩረትን ቢያደርግ ጥሩ ይመስለኛል፡፡
የማጠቃለያ ሀሳብ ካለህ…

የእግር ኳስ ላይ በአሁን ሰአት ላይ ለደረስኩበት ደረጃ በቅድሚያ የፈጠረኝን አምላክ በመቀጠል ቤተሰቦቼን፣ ፍቅረኛዬን ጓደኞቼን፣ የቡድኔ ልጆችና አመራሮቻችንን፣ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች እና ሁሌም የሚያበረታቱኝን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የደደቢት ክለብ ደጋፊዎችን በጣሙን ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

የሳምሶን ጥላሁን ድሪም ቲም

ግብ ጠባቂ – ሮቤርቶ አዶንካራ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

ተከላካዮች – ስዩም ተስፋዬ /ደደቢት/

አስቻለው ታመነ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

ደጉ ደበበ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

ብርሃኑ ቦጋለ /ደደቢት/

አማካዮች – ሳምሶን ጥላሁን /ደደቢት/

ኤልያስ ማሞ /ኢት.ቡና/

ታደለ መንገሻ /አርባምንጭ/

ሻይቡ ጀብሪል /ኢት.ንግ.ባንክ/

አጥቂዎች – ዳዊት ፍቃዱ /ደደቢት/

ጌታነህ ከበደ /ደደቢት/

ተጠባባቂዎች

ግብ ጠባቂ

ጀማል ጣሰው /ጅማ አባቡና/

አይዛክ ኢዜንዴ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

አበባው ቡታቆ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

አሉላ ግርማ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

አስራት መገርሳ /ደደቢት/

ሳላህዲን ሰይድ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

አዳነ ግርማ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

የሳምሶን ጥላሁን የመጀመሪያ ምርጫ

ከምግብ – በጥሬ ስጋ ስለማልደራደር እሱን ነው የማስቀድመው፡፡

ከመጠጥ – ፋንታ አናናስ ተቀዳሚ ምርጫዬ ቢሆንም ወይንንም ግን እወዳለሁ፡፡

ከሙዚቃ – የአስቴር አወቀ ዘፈኖች ሁሉም ተደማጭነታቸው የላቀ ስለሆነ እሷን ነው ምርጫዬ ያደረግኳት፡፡

ከውጪ ሀገር ስቴድየሞች – የባርሴሉና ኑ ካምፕ ለእኔ ምርጥ ስለሆነ እሱን ነው የማስቀድመው፡፡

ከውጭ ሀገር ደጋፊዎች – የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎችም ምርጫ ስለሆነ የሊቨርፑል ደጋፊዎችን የአደጋገፍ ድባብ በቀዳሚነት የማስቀምጠው ነው፡፡

በዲኤስ ቲቪ ከሚተላለፉ የውጪ ሀገር ጨዋታዎች – የስፔን ላ ሊጋ ብዙ ጥበብ የምትመለከትበት ግጥሚያ ስለሆነ  ላሊጋው ለእኔ የመጀመሪያ ምርጫዬ ነው፡፡

ከውጪ ሀገር ተጨዋቾች – አንድሬስ ኢንኤስታ

ከውጪ ሀገር ክለብ – ባርሴሎና

ከብሔራዊ ቡድን – ብራዚል

ከመዝናኛ ስፍራዎች – የሲኒማ መታያ ቦታዎች በተለይ ደግሞ ኤድናሞልን እመርጣለሁ፡፡

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook