የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የመከላከያው ተጨዋች ነጂብ ሳኒ ከ4 ወራት ጉዳት በኃላ ወደ ሜዳ ተመለሰ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን መከላከያ ውስጥ ያሳይ በነበረው ጥሩና አበረታች የሆነ የጨዋታ
ብቃት በመቀላቀል ለመጫወት የቻለው ነጂብ ሳኒ ባለፈው ዓመት ከደረሰበት የእግር ጉዳት በመዳን በአሁን ሰዓት ወደ መልካም ጤንነቱ ተመልሷል፡፡
የመከላከያው የመስመር ስፍራ ተከላካይ ነጂብ ሳኒ  ቀደም ሲል ተጫውቶ ካሳለፈበት የሙገር ሲሚንቶ እግር ኳስ ቡድን አንስቶ በሜዳ ላይ ብቃቱ ከፍተኛ መሻሻልን ያሳየ ተጨዋች ሲሆን ሀገራችን አስተናግዳው በነበረው የሴካፋ ውድድር ላይም ለዋልያዎቹ ተመርጦ  ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን አሳይቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ሁለተኛው ዙር ላይ ግን ክለቡ መከላከያ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወት የደረሰበት ጉዳት ከሜዳ አርቆት ባደረገው ሕክምና አሁን ወደ መልካም ጤንነቱ ተመልሶ ዘንድሮ ለሚጀመረው ውድድር ከክለቡ ጋር እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ ይህን ተጨዋች ዓምና ስለደረሰበት ጉዳትና በአሁን ሰዓት ስላለበት ሁኔታ እንደዚሁም ደግሞ በእዚህ ዓመት በምን መልኩ ለመቅረብ እንደተዘጋጀ የሀትሪክ ጋዜጣ ድህረ ገፅ ጠይቆት ምላሹን ሰጥቷል፡፡
የደረሰበትን ጉዳት አስመልክቶ ሲናገር “ጉዳቱ የደረሰብኝ የሁለተኛው ዙር ላይ ከቡና ጋር ስንጫወት ነው፡፡ ጅማቴም ነበር የተቆረጠው፡፡  ይህ ጉዳትም ለአራት ወራት ያህል ከሜዳም እንድርቅ አድርጎኛል፡፡ በኃላ ላይ ግን በዮርዳኖስ ከፍተኛ ክሊኒክ የቀዶ ጥገና ህክምናዬን ሰርጀሪ ሳላደረግኩ በአሁን ሰዓት በመልካም ጤንነት ላይ ሆኜ ልምምዴን ወደመስራትም ላይ ደርሻለሁ” ብሏል፡፡
ነጂብ ሳኒ  ከእግር ኳስ ለአራት ወራት ርቆ በነበረት ጊዜ ስለተፈጠረበት ስሜትና ዘንድሮስ በምን መልኩ ለውድድር ለመቅረብ እንደተዘጋጀም ጥያቄ ቀርቦለት ሲመልስ “ባለፉት አራት ወራቶች በጉዳት ከሜዳ ስርቅ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ሊከፋኝም ችሏል ያም ሆኖ ግን  ጉዳት በእግር ኳሱ የሚያጋጥም ስለሆነ በአሁን ሰዓት በፈጣሪ እርዳታና ዶክተሮችም ባደረጉልኝ እክምና ወደ ጥሩ ጤንነቴ መመለሴ አስደስቶኛል፡፡
በዘንድሮ የውድድር ዘመንም አሁን ካለኝ ጤናማነት አንፃር ክለቤን መከላከያ ለመጥቀምና ውጤታማ ለማድረግ እንደዚሁም ደግሞ ወደ ነበርኩበት ብሔራዊ ቡድንም ለመመለስ እየተዘጋጀውም” ነው ብሏል፡፡
የመከላከያውን ነጂብ ከመሰናበታችን በፊት ሊያስተላልፈው መልዕክትም ጠይቀነው “መከላከያ ባደረገው የሊጉ ጨዋታ ላይ ጉዳቱ ከደረሰብኝ ጊዜ አንስቶ እኔን በተሳካ ህክምና ወደ
ጥሩ ጤንነቴ እንድመለስ ላደረጉኝ የዮርዳኖስ
ከፍተኛ ክሊኒክ ሆስፒታል ዶክተሮች  ለክለባችን ሐኪም ዶክተር ብሩክ  የሆስፒታሉ ሰራተኞች
ላደረጉልኝ እንክብካቤ እንደዚሁም ከጎኔ ሳይጠፉ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሲያደርጉልኝ ለነበሩት
የመከላከያ ክለብና አመራሮቹ እንደዚሁም ደግሞ ለቤተሰቦቼና ለጓደኞቼ ምስጋናዬን በፈጣሪ ስም እያቀረብኩ አዲሱ ዓመትም ለኢትዮጵያ ህዝብ
የሰላም የጤና እና የብልጽግና እንዲሆን እመኛለሁ” በማለት አስተያየቱን አጠቃሏል፡፡

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook