አዲሱ አሰልጣኝ ዋልያዎቹን ለአፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ለማድረስ ይሰራሉ አሰልጣኙ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ አሸናፊ በ100 ሺህ ብር ወርኃዊ ደመወዝ ዋልያዎቹን ለማሰልጠን የሁለት ዓመት ኮንትራት ተሰጥቷቸዋል።
ኮንትራቱ ከመጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ የካቲት 30 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይ ነው።
በሁለት ዓመት ቆይታቸው ዋልያዎቹን ካሜሮን ለምታስተናግደው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
አሰልጣኙ ብሄራዊ ቡድኑን ለማሰልጠን የተወዳደርኩት የተሻለ ነገር ለመስራት ስለሆነ ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን ለሩብ ፍጻሜ ለማድረስ እሰራለሁ ብለዋል።
የገቡት ውል ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫና ለቻን ውድድር ማሳለፍን እንደሚያካትትም ገልጸዋል።
“ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ብቻ አይደለም ለቻን ውድድር ማሳለፍ ካልቻልኩ ሁለት ዓመት አልጠብቅም፤ በራሴ ፍቃድ እለቃለሁ” ብለዋል።
“በአፍሪካ ዋንጫ ለሩብ ፍጻሜ ማድረስ ትግል እንደሆነ አውቃለሁ፤ ነገር ግን በኅብረት ከሰራን የፈለግንበት መድረስ እንችላለን” ሲሉም አክለዋል።
ዋልያዎቹን ለማሰልጠን የተወዳደሩት ገንዘብ ፈልገው ሳይሆን በእግር ኳሱ አሻራቸውን ለማስቀመጥ መሆኑን ተናግረዋል አሰልጣኙ።
ከቀድሞ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ የስፖርት ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ጋር እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።
“ተባብረን ከሰራን ብዙ እርምጃ እንጓዛለን፤ ስለሆነም ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን፤ እኔም ከሁሉም አካላት ጋር ተባብሬ ለመስራት ፍቃደኛ ነኝ” ብለዋል።
የተሻለ ልምድና ወቅታዊ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች በቡድኑ እንደሚያካትቱ የገለጹት አሰልጣኝ አሸናፊ በመጪው ግንቦት ሶስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የወዳጅነት ጨዋታዎቹን ከምስራቅ፣ ከደቡብና ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ጋር እንደሚያካሂዱም ይፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዘርይሁን ቀቀቦ አሰልጣኝ አሸናፊ በላይሰንስ፣ በልምድና በወቅታዊ አቋም መመረጣቸውን ተናግረዋል።
“የአገር ውስጥ አሰልጣኝ ለመቅጠር የተገደድነው ባለፉት ዓመታት ከውጭ አሰልጣኞች የተሻለ ውጤት በማስመዝገባቸው ነው” ብለዋል።
ከውጤት ማጣት እንዲሁም ከገንዘብ ወጪ አንጻር ሲታይ የውጭ አገር አሰልጣኝ ከጥቅሙ ጉዳቱ ማመዘኑን ነው አቶ ዘርይሁን የተናገሩት።
አሰልጣኙ የመኪና፣ የህክምና፣ የሞባይል ካርድና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ጨምሮ በወር 100 ሺህ ብር እየተከፈላቸው ለሁለት ዓመት ብሄራዊ ቡድኑን ይመራሉ።
ቡድኑን ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው የገለጹት አቶ ዘርይሁን የሚፈለገውን ውጤት ካላመጡና የቀጣሪውን አካል መልካም ስም የሚያጎድፍ መግለጫ ከሰጡ ውላቸው እንደሚቋረጥ አስታውቀዋል።
አስተያየት ይስጡ