“የአውሮፓ ኮሚኒቲ ውድድር ላይ በክብር እንግድነት ተጋብዤ መምጣቴ አስደስቶኛል”

“የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ዕድልን ለማግኘት ጥረትን እያደረግኩ ነው”
ውብዓለም ፀጋዬ

የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን እና የደደቢት የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተደናቂ ተከላካይ የሆነችው ውብዓለም ፀጋዬ በቅርቡ በሆላንድ አምስተርዳም ከተማ ላይ ተካሂዶ በነበረው የኢትዮጵያኖች ኮሚኒቲ የአውሮፓ እግር ኳስ ውድድር ላይ በክብር እንግድነት ተጋብዛ ከሄደች በኋላ በድጋሚ ወደ ሀገሯ የተመለሰች ሲሆን ተጨዋቿ እዚያ ስለነበራት ቆይታ ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ድህረ ገፅ አስተያየቷን ሰጥታለች፤ ከእዚያ ውጪም ስለእግር ኳስ ሕይወቷም ላቀረብንላት ጥያቄ ምላሽንም ለመስጠት በቅታለች፡፡
የደደቢት እግር ኳስ ክለብ የተከላካይ ስፍራ ጠንካራ ተጨዋች የሆነቸው ውብዓለም ፀጋዬ በተጨዋችነት ዘመኗ እልኸኛና አልሸነፍ ባይ ተጨዋች ስትሆን ተጨዋቿ ባለፈው ዓመት ላይ በደረሰባት የእግር ጉዳት ከሜዳ እርቃ እንደነበር ይታወሳል፤ በአሁን ሰዓት ደግሞ ባደረገችው ጥሩ ህክምናና በውጪ ሀገርም ጭምር በሰራችው ልምምድ በጤንነቷ ላይ መሻሻልን በማሳየቷና ዶክተሮችም መጫወት እንደምትችል ስለነገሯት የአዲሱን የውድድር ዘመን በመጠባበቅ ላይ መሆኗን እየተናገረችም ነው፤ የደደቢት ተከላካይ የሆነቸው ውብዓለም በዘንድሮ የውድድር ዘመን ደደቢትን በጥሩ ብቃት ለማገልገል እና ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ዳግም ለመመለስ ፍላጎቷ ከፍ ያለ እንደሆነ ሀሳቧን እየሰጠች ሲሆን የፈጣሪ እርዳታ ይታከልበትና ወደፊት በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃም በውጪ ሀገር ሄዶ ለመጫወት ግንኙነት መጀመሯና ለእዚያም እየተነጋገረች መሆኗን ለድህረ ገፁ አስተያየቷን ጨምራ ሰጥታለች፡፡ ከተጨዋቿ ጋር በውጪ ስለነበራት ቆይታ እና በኳስ ሕይወቷ ዙሪያ ያደረግነው ቃለ-ምልልስ ይህንን ይመስላል፡፡
ሀትሪክ፡- የአውሮፓ ኮሚኒቲ የኢትዮጵያኖች እግር ኳስ ውድድር ላይ በክብር እንግድነት ዘንድሮ መጋበዝሽን ሰምተን ነበር፤ በቅድሚያ እንኳን ደህና መጣሽ?
ውብዓለም፡- አመሰግናለው፤ እናንተም እንኳን ደህና ቆያችሁኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በቅድሚያ የግብዣው ጥሪውን እንዴት አገኘሽው?
ውብዓለም፡- የግብዣ ጥሪውን ለማግኘት ያስቻለኝ ዋንኛው ምክንያት እኔ ከበፊት ጀምሮ በየትኛውም አጋጣሚ በውጪ ሀገር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር በድህረ ገፅ ላይ ባለኝ አጋጣሚ በራሴ ዌብሳይት ላይ እፃፃፋለው፤ ከብዙ ሀገራት ነዋሪዎች ጋርም ግንኙነትም አለኝ፤ ይህኔ ታዲያ እኔ ስላለሁበት አጠቃላይ ሁኔታ ስነግራቸውና የፍቶግራፍ መረጃዎችንም ስልክላቸው ወደ ሆላንድ ሀገር ተጉዤ ውድድሩን በክብር እንግድነት ተገኝቼ እንድከታተል ወረቀት ፅፈውልኝና የግብዣውን ወረቀትም ስለላኩልኝ እዚያ ተገኝቼ በጣም ምርጥ የሚባል እና የወደድኩትንም ጊዜ አሳለፌ መጥቻለው፡፡
ሀትሪክ፡- በሆላንድ ቆይታሽ የክብር እንግዳ ሆነሽ ሽልማት ከማበርከትሽ ባሻገር ታላላቅ ሰዎችንም ማግኘትሽም ታውቋል.. በእዚህ ምንድነው የተፈጠረብሽ?
ውብዓለም፡- በመጀመሪያ ደረጃ በእንደዚህ አይነት ታላቅ ውድድር ላይ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵዊ የሴቶች እግር ኳስ ተጨዋች ሆኜ በመክፈቻውም በመዝግያውም ጨዋታ ላይ በጣም ከማከብራቸውና ከምወዳቸው እንደዚሁም ደግሞ የእሳቸውን ታሪክ ካነበብኩላቸውና ከሰማውላቸው ታላቁ ኢትዮጵያዊ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ጋር በመሆን ከእሳቸው ቀጥዬ በክብር እንግድነት እንድገኝና ብሎም ደግሞ ለአሸናፊዎቹ የታዳጊና የዋናው ቡድኖች ዋንጫ እንድሰጥ በመደረጌ በውስጤ የማላውቀው አይነት የደስታ ስሜት ነው የተሰማኝ፤ የውድድሩ አዘጋጆች ከእዚያ ውጪ እኔን ገና ከአምስተርዳም አየር መንገድ ጀምሮም ነው ደማቅ አቀባበል አድርገውልኝ የተቀበሉኝ በአጠቃላይ ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፤ በውድድሩ ላይ ከእኛ ሀገር ተጨዋቾች ሳላዲን ሰይድን እና ሻምፒዮና ከሆኑት ቡድን ተጨዋቾች መካከል ሳሙኤል አለባቸው ግቻን አግኝቻቸዋለው፤ ጥሩ ሲጫወትም ነበር፤ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ኢትዮጵያን ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችንም ተመልክቻለውም፡፡

image

አጠቃላይ ሴሪሞኒው በጣም ደስ የሚልም ነበርና ይህንን የግብዣ እድል ላሳገኙልኝ የውድድሩ አዘጋጆች እንደዚሁም ደግሞ ለለንደን ከተማ ለሚጫወተውና በጀርመን ሀገር ነዋሪ ለሆነው ታላቅ ወንድሜ ጌቱ ፀጋዬ እንደዚሁም እዚያ በነበርኩበት ቆይታ እኔን በመምከር ጥሩ ነገር እንድሰራ ብዙ ነገር ላስተማሩኝ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔና ለሁሉም አካላቶች ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- በሆላንድ ቆይታሽ ጋዜጠኞች ቃለ-ምልልስ እንዳደረጉልሽ ሰምተን ነበር…? ምን ነበር ያሉሽ?
ውብዓለም፡- ውድድሩን በተመለከተ እና ስለእኔም ነበር የጠየኩኝ፤ በውድድሩ እና እኔ የክብር እንግዳ በመሆኔ በጣም ደስተኛ መሆኔን እና እድለኛ እንደሆንኩም ነው የነገርኳቸው፤ ከእዚያ ውጪ የሀገራችን የሴት እግር ኳስ ተጨዋቾች ጥሩ ብቃት እንዳላቸውና እኔም ፈጣሪ ፈቅዶ ተሳካልኝ እንጂ ሌሎች ከእኔ የተሻለ ችሎታ ያላቸው እና የማከብራቸው በርካታ ተጨዋቾች እንደሞዴል ሊሆኑም የሚችሉ እንደእነ ወይንሸት ፀጋዬ፣ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ሄደን ሽፈራው የመሳሰሉትን ተጨዋቾች ጨምሮ ስለቡዙዎቹ በእንደዚህ አይነት ውድድር ላይ ቢጋበዙ ጥሩ ነው የሚል ሀሳብን ስላቀረብኩ ያን ማለቴ አስደሳች ነው የሆነልኝ፤ አዘጋጆቹም ከእዚህ ቀደም በእንዲህ ያለ ውድድር የወንዶች ኳስ ተጨዋቾችን እንጂ ሴቶችን ጋብዘው ስለማያውቁና እኔም ፈር ቀዳጅ ለመሆን በመቻሌ ተደስተው ወደፊት ሌሎች ተጨዋቾችንም ለመጋበዝ እንደሚችሉ ቃል ነው የገቡልኝና በእዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ልጅ ሆነሽ መጫወት የጀመርሽው የት ነው… ከደደቢት በፊትስ በየት ክለብ ነው ተጫውተሽ ያሳለፍሽው?
ውብዓለም፡- የልጅነት ዕድሜዬ ላይ ኳስን መጫወት የጀመርኩት ተወልጄ ባደግኩበት አብነት አካባ ነው፤ ዓለሙ ሜዳ ላይም እጫወትም ነበር፤ የመጀመሪያ ክለቤም እናንተም እንደምታውቁት ተክለኃይማኖት ፔፕሲ ነበር፤ ያኔ ቡድኑ በአሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ ተቋቁሞም ነበር እንሰለጥን የነበረው፤ በቡድኑም ጥሩና ጣፋጭ የሆነ ወቅትን አሳልፈናል፤ የመጀመሪያ ክለቤ ተክለኃይማኖት ፔፕሲም በወቅቱ ቡድን ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ የፋሚሊም ያህል ጭምር ነበር እንተሳሰብና እንዋደድም የነበረው፤ በእዚያን ጊዜ ቡድናችን ከሚሰጠን ጠቃሚ ትምህርት አንፃር በሳይኮሎጂ ደረጃም ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የሚገኝበት ወቅትም ላይ ነበር በትምህርት ደረጃም ጥሩ ነበርንና ያን ጊዜ መቼም ቢሆን አልረሳውም፡፡
ሀትሪክ፡- የደደቢት ክለብን ቀጥለሽ ተቀላቀልሽ፤ ቡድኑ ውስጥ ስትገቢ ምን ተሰማሽ? ቆይታሽስ ምን መልክ ነበረው?
ውብዓለም፡- የደደቢት ክለብን በተቀላቀልኩበት ያን ጊዜ የተሰማኝ ስሜት ከፍ ያለ ነበር ለእዚህ ደግሞ እንደምክንያት የሆነኝ በሀገሪቱ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በችሎታቸው አከብራቸውና አደንቃቸው የነበሩት ተጨዋቾች በቡድኑ ውስጥ ይገኙና እኔም ከእነሱ ጋር የምጫወትበት እድሉ ስለተፈጠረልኝ ያኔ በጣም ነው የተደሰትኩት፤ ከእዚያ ባሻገር ቡድኑም ጠንካራ ስለነበርም ከእነሱ ጋር ልጫወት በመቻሌ የተለየ ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡
የደደቢት ክለብ ቆይታዬን በሚመለከት ጥሩ ጊዜን ከቡድኑ ጋር እንዳሳለፍኩ ሁሉ የተበሳጨሁበት አጋጣሚም አለ፤ ከጥሩነቱ ስነሳ ክለቡ ለእኛ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ በሕይወታችን ጥሩ ለውጥ እንድናመጣ አስችሎናል፤ ከእዚያ ውጪ ደግሞ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከአንድም ሁለት ጊዜ ከማንሳታችን ባሻገር የዞናችንም የጥሎማለፍም ዋንጫ ልንወሰድ መቻላችን በመልካምነቱና በአስደሳችነቱ የሚጠቀስ ነው፤ ሌላው የክለቡ ቆይታዬ ላይ የቁጭት ስሜት የሚፈጥርብኝ ደግሞ ሌሎች የሊጉን ዋንጫ ማንሳት እየቻልን ያጣንበትን ወቅት ነው፤ በተለይ ከሁሉም አዳማ ከተማ ላይ ተዘጋጅቶ የነበረውን ዋንጫ እስከመጨረሻ ሰዓት ድረስ 1-0 መርተን በመጨረሻው 30 ሰከንድ ላይ ጎል ገብቶብን አቻ ከተለያየን በኋላ በፍፁም ቅጣት ምት በባንኮች በመሸነፍ ዋንጫውን ማጣታችን ሁሌም ነው የሚቆጨኝ፤ ያም ሆኖ ግን ዘንድሮ የዞኑንም የሊጉንም ዋንጫ በማግኘት የድርብ ድል ባለቤት ስለሆንን ልፋታችን የተካካሰልን ነው የሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ባጣችሁበት እና በማንኛውም ጨዋታ ላይ አንቺ የምትጫወቺበት ቡድን ሲሸነፍ ሁሌም አልቅሰሽ ወደ መልበሻ ቤት ስታመሪ ነው የምናይሽ… ያ የሆነው ከምን አንፃር ነው….?
ውብዓለም፡- ከባንክ ጋር ለፍፃሜ እየቀረብን የምናጣው ዋንጫ ሁሌም ያስቆጫል መርተንና የመጨረሻውን ደቂቃ እየጠበቅን ባለንበት ሰዓት ነው በትኩረት ማነስ ግብ እየተቆጠረብን ነው ተሸናፊ የሆነው በጥቃቅን ስሕተትና ባለቀ ደቂቃ በሚቆጠርብን ግብ ስለምንሸነፍም ነው ከጨዋታው በኋላ ሁሌ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ሲያለቅሱ የሚጣዩት ዘንድሮ ግን ተክሰናል፤ በአጠቃላይ ግን እኔ በየትም ጨዋታ ላይ ላለቅስ የምችለው ሽንፈትን አጥብቄ ስለምጠላ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ተጫዋችነትን ስትጀምሪ የአንቺ ተምሳሌት እና ሞዴል የሆነችሽ ተጨዋች ማን ነች? የቅርብ ጓደኞችሽስ እነማን ናቸው?
ውብዓለም፡- ብዙ ተጨዋቾች ያሉ ቢሆንም የመጀመሪያዋ ግን የቀድሞ የብሔራዊ ቡድናችን ተከላካይ የነበረችው ዘይቱና ያሲን ናት፤ እሷን በጣም አደንቃትም ነበር፤ በተለይ የፊዚካል አፒራንሷንና እግር ኳስንም በእውቀት ትጫወት ስለነበር እወዳት ነበር፤ በመቀጠል ደግሞ የብዙሃን አድናቂም ነበርኩና ሁለቱ ለእኔ ሮል ሞዴሌ ናቸው፡፡ የእኔ የቅርብ ጓደኞቼ ኳስን አብረን የተጫወትነውና አሁንም ድረስ በጣም የምንዋደደው ሰሚራ ዲኖ እና የባንኳ ዳግማዊት መኮንን እንደዚሁም ደግሞ ዮዲት ተስፋዬ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- ለብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ መች ተመረጥሽ፤ ያኔ ምንስ ተሰማሽ? ምንስ ትዝታው አለሽ…
ውብዓለም፡- በጊዜው በጣም በማደንቀው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ አማካኝነት ሀገሬን ወክዬ ለምጫወትበት የብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጥኩት ከናምቢያ ጋር በተደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ነው፤ ከክለቤ ተመርጬም ስሄድ በቋሚ ተሰላፊነት ለመጫወት እንጂ ለመቀነስ ፈፅሞም አስቤም አልነበረም የሄድኩት፤ ከሀገር ወጥተንም ነበር ግጥሚያውን ያደረግነው፤ ያኔ ለብሔራዊ ቡድን መመረጤ ሲነገረኝ የመመረጥ እድሉን በጣም እፈልገው ነበርና በጣምም ነበር የተደሰትኩት፤ በጊዜው የነበረው ጨዋታ ላይም እኔ የማስታውሰው በቋሚ ተሰላፊነት እንድምገባ ነበር ግን ተጠባባቂ ሆንኩኝ ያኔ ምንም አይነት የተሰማኝ ስሜትም አልነበረም፤ በጨዋታው በናምቢያም 1-0 እየተመራን ነበር ለእረፍት የወጣነው፤ ከእረፍት በኋላ ግን እኔ ተቀይሬ ገብቼ ውጤቱ ባይቀየርም ጥሩ መንቀሳቀሴን አስታውሰዋለው፤ አሰልጣኝ ስዩምም በወቅቱ አሁን ገና አሳመንሽኝ በሚልም ከጋና ጋር የነበረን ጨዋታ ላይ በቋሚ ተሰላፊነት ያጫወተኝን አጋጣሚ የማልረሳው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የሴቶች እግር ኳስን በፊትና አሁን ወደ ኋላ መለስ ብለሽ ስታስታውስው㕲
ውብዓለም፡- የሴቶች እግር ኳስ ላይ በፊት ሁላችንም በአብዛኛው ተጠቃሚ አልነበርንም፤ ተክለኃይማኖት ፔፕሲ እያለንም ደሞዛችን 150 ብርም ነበር፤ ክፍያው ለምንም ነገርም አይሆንምም ነበር ግን ስንቀበለው ለሁላችንም ብሩ ብርቃችን ነበር፤ ኳሱን በጣም ስለምንወደውም ነው እንጫወት የነበረው፤ ቤተሰቦቻችን ያኔ በፋይናንስ ተጠቃሚ እንድንሆን ሌላ ስራ እንድንሰራም ያስገድዱን ነበር ዛሬ ላይ ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል፤ ፈጣሪ ይመስገንና በሺዎች የሚቆጠር ክፍያ እያገኘን ቤተሰቦቻችንን ከማስተዳደር አልፎ ራሳችንንም እየጠቀምን ነው ያለነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የመመረጥ ዕድል በጉዳት ሳቢያ አጥተሸዋል…. ምን ተሰማሽ?
ውብዓለም፡- አዎን፤ ዘንድሮ እንኳን ባለፈው ዓመት የብሔራዊ ቡድን ልምምድ ላይ በደረሰብኝ ጉዳት ህክምናና እረፍት ላይ ስለነበርኩ እንደዚሁም ከጌምም ርቄ ስለነበር ነው ያልተመረጥኩት፤ ለቡድኔ ደደቢትም ጭምር ያልተጫወትኩበት አጋጣሚ አለ፤ ያምናውን ስናነሳ ግን ከብሔራዊ ቡድኑ ጉዞ ያገደኝና አሁንም ላለው ቡድን እንዳልመረጥ ያስቻለኝ ልምምድ ላይ የደረሰብኝ ጉዳት ነው፤ ለአልጄሪያው ጨዋታ ለመጓዝ እየተዘጋጀን እያለም ነበር በልምምድ ጨዋታ ላይ እግሬ ላይ ተጎድቼ ለእኔ በጣም አናዳጅ በሚባል ሁኔታ ከጉዞው የቀረሁት፤ ስፖርተኛ ላይ ደግሞ ጉዳት ያጋጥማል፤ ፈጣሪ ሁሉንም ነገር ሲያደርግ ዓላማ አለው በአንዱ ብጎዳ በሌላ ማለትም በደደቢት ቡድን አሸናፊነት እና ወደ ውጪ ሀገርም ማለትም ወደ አውሮፓ ሀገራትም ራሴ ግንኙነት በመፍጠር እና በኢሜይልም ከሰዎች ጋር በመገናኘት እና በመፃፃፍ የሴቶችም የወንዶችም እግር ኳስ ተጨዋቾች በውጪ ሀገር ምን እንደሚመስሉም ያየሁበትና ብዙ ጠቃሚ ትምህርትም ስላገኘሁበት የተካስኩበት ሁኔታ አለ፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…..?
ውብዓለም፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ላይ ሆኜ ጉዳትን ባስተናገድኩበት ወቅት ወደመልካም ጤንነት እንድመለስ ከእኔ ጎን ባለመጥፋት ለጠየቁኝ እና ለቤተሰቦቼ እንደዚሁም ደግሞ ለክለቤ ደደቢት እና ለጓደኞቼ ምስጋናዬን እያቀርብኩ ሉሲዎቹ በኡጋንዳ እያደረጉት ባለው የውድድር ተሳትፎ ደግሞ መልካም የስኬት ድል እንዲገጥማቸው ምኞቴን አስተላልፋለው፤ ሌላው ለሀገራችን የሴት እግር ኳስ ተጨዋቾች ማስተላለፍ የምፈልገው የተለያዩ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነትም ሆነ ሌሎች በውጪ ሀገር የሚደረጉ አንድአንድ ውድድሮች ላይ በመገኘት እድሉን ለማግኘት እግር ኳስን ከመጫወት ባሻገር በኢሜል ግንኙነትን እየፈጠሩ የግብዣ እድልን እንዲያገኙ ሊጥሩ ይገባል ነው የምለው፤ በተረፈ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም አዲሱ ዓመት የፍቅር የሰላምና የመተሳሰብ ጊዜ እንዲሆንም እመኛለው፡፡
በፎቶው ውብዓለም ፀጋዬ ከአቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ጋር ትታያለች

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook