የሁለተኛው ዙር የ5ኪሜ ቨርቹዋል ሩጫ ምዝገባ በዛሬው እለት በሚሊኒየም ፓርክ ችግኝ በመትከል በይፋ ተከፍቷል

 

በዚህ ፈታኝ ወቅት ሰዎች ሁሉ በአካላዊ እንቅስቃሴ ጤንነታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ለማበረታታት ሲባል በሚያዚያ ወር “ደህና ቆዪ ኢትዮጵያ” በሚል ስያሜ የተጀመረው ዘመቻ ስኬታማ መሆኑን ተከትሎ የዚያው እንቅስቃሴ አካል የሆነው “ያ ደስ የሚል ነገ” የሚል መልእክት ያነገበ የ2ኛ ዙር ቨርቹዋል ሩጫ ተዘጋጅቷል፡፡

የውድድሩ መልእክት እንደሚያመላክተው መጪውን አመት በአዲስ ተስፋ ተሞልተን
እንድንቀበለው ለማበረታታት ታስቦ የተደረገ ነው፡፡ በዚህ ውድድር በአጠቃላይ 1000 ከሁሉም የእድሜ ክልል እና ከመላው የአለም ክፍሎች የተውጣጡ ተወዳዳሪዎችን ያሳትፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የህጻናትና ሴቶችን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ ያበረታታል፡፡

የቨርቹዋል ሩጫው የሚካሄደው ከጳጉሜ 1 እስከ ጳጉሜ 5 ባሉት ቀናት መሆኑ ደግሞ ሁላችንም ስለ መጪው ዘመን ከፍ ያለ ተስፋ ሰንቀን አዲሱን ዓመት ለመቀበል መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ
ያምናል፡፡ የተስፋ መገለጫ በሆነው ቢጫ ቀለም አሸብርቆ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ሁሉም ተሳታፊዎች ተመሳሳይ (ቢጫ ቀለም) ያላቸውን አልባሳት አድርገው ሩጫቸውን እንዲያከናውኑ ይበረታታሉ፡፡

በተጨማሪም በውድድሩ ለመሳተፍ ለሚመዘገቡ ተሳታፊዎች የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች በቤታቸው ወይም በአከባቢያቸው
እንዲተክሉ ይበረከትላቸዋል፡፡ ውድድራቸውን ላጠናቀቁ ተሳታፊዎች ደግሞ በአትሌት ሀይሌ ገብረ ስላሴ
የተፈረመ ኢ-ሰርተፍኬት የሚሰጥ ይሆናል፡፡
በዚህ አጓጊ እና አስደሳች ውድድሩ ለመሳተፍ የሚፈልጉ የግል ተወዳዳሪዎች ለክፍያ 150 ብር ብቻ ሲጠየቁ
በቤተሰብ ከ 3 እና ከዚያ በላይ በመሆን የሚመዘገቡ ደግሞ 120 ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡

የምዝገባውን ክፍያ በአሞሌ እና በሌሎች የባንክ አማራጮች መፈጸም የቻላል፡፡ በዚህ ውድድር ለሚሳተፉ የሀገር ውስጥ እና የሀገር ውጪ ተወዳዳሪዎች ድርጅታችን ሁለት በማንኛውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚደርስባቸው መዳረሻዎች መሄጃ ወይም መመለሻ የአየር ቲኬቶች እና የተለያዩ ልዩ ማበረታቻ ሽልማቶችን አዘጋጅቷል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዙር የቨርቹዋል ሩጫውን ባሳለፍነው ግንቦት መጨረሻ ላይ ያካሄደ ሲሆን ከሩጫው ምዝገባ የተገኘው ገቢም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለተጠቁ ወገኖቻችን ተበርክቷል፡፡ ድርጅታችን ለብሔራዊ ድጋፍ አሰባሰብ ኮሚቴ ካበረከተው የ500,000 ብር ድጋፍ ተጨማሪ ከመጀመሪያው ቨርቹዋል ሩጫ
ምዝገባ በአጠቃላይ 79,067 ብር ተሰብስቧል፡፡

ከዚህም ውስጥ በኢትዮቴሌኮም ገቢ ማሰባሰቢያ (444) በኩል 21,700 ብር ገቢ ተደርጓል፡፡ ቀሪው 57,367 ብር ለአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን እንዲሰጥ በተወሰነው መሰረት በቨርቹዋል ሩጫ ምዝገባ መክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ለተገኙት የፌደሬሽኑ ተወካይ ተበርክቷል፡፡

ስለ ውድድሩ የበለጠ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት በድህረ ገጻችን www.ethiopianrun.org ወይም በስልክ
0936-011084 ማግኘት ይችላሉ፡፡

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor