በዮሴፍ ከፈለኝ
“የፕሪሚየር ሊጉ ፎርማት እግር ኳሱን ገድሏል የሚሉ ራሣቸው ተሳስተው ሰውን የሚያሳስቱ ሰዎች አባባል ነው”
በጣም አስገራሚ አቅም እንዳላቸው ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡ አነጋጋሪና አወዛጋቢ ነገሮችን በመናገር ይታወቃሉ… እርሣቸው ግን በእውነትና በሎጂክ የማምን እንጂ አወዛጋቢ ለመሆን ብዬ አይደለም ይላሉ… አስገራሚ ሲቪ አላቸው ያልነኩት ስፖርት የለም፡፡ 4 ኪሎ ያውም ወወክማ ውስጥ አድገው ለምን ከስፖርቱ ጋር አይቆራኙ ሲሉ ይናገሩላቸዋል፡፡ ፊት ለፊት በመናገር ይታወቃሉ… ወደ ኋላ አይሉም ይሏቸው፡፡ ፋርማሲስቱና የእግር ኳሱን ኤክስፐርት አቶ ጌታሁን ገ/ጊዮርጊስ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ሊጉ ፎርማት ጥቅም፣ ሊጉ የዘረኝነት ምክንያት አይደለም፤ ስለ ላይሰንስ አሰጣጥ፣ ስላሰለጠኗቸው ክለቦችና ውጤቶቻቸው፣ ሃሳብ እንጂ ውጤት የላቸውም ስለመባሉ፣ ከጋርዚያቶ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት፣ ስለ ተጨዋቾች ደመወዝ፣ ኮሚቴዎች ተደጋፊ እንጂ ደጋፊ ስላለመሆናቸው፣ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፍነው በሰውነት ቢሻው ሳይሆን በአሰልጣኝ የጋራ ስራ ውጤት ነው፣ ተጫውቶ ለማሰልጠን ተምሮ ማሰልጠን ይሻላል… በማለት አነጋጋሪ ቃለ ምልልስ ሰጥተዋል፡፡
ሀትሪክ፡- አቶ ጌታሁን አመሰግናለሁ… እስቲ ሲቪዎን ይግለፁልኝ?
ጌታሁን፡- ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ 4 ኪሎ ገብርኤል ሰፈር አካባቢ አድጌ ወወክማ ውስጥ የኖርኩ ሰው ነኝ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋካልቲ በስታስቲክስ 3ኛ አመት ስደርስ ስኮላርሺፕ አግኝቼ ወደ ቡልጋሪያ ሄደኩ፡፡ 6 አመት ቆይቼ በእግር ኳስ የMSC ዲግሪ ይዤ ተመልሻለሁ… ሜጀሬ እግር ኳስ ማይነሬ የሰውነት ማጎልመሻ ነበር፡፡ እንደመጣሁ ከፍተኛ የእግር ኳስ ኤክስፐርት ተብዬ ወለጋ ከፋ ኢሊባቡር ማለት ነው እዚያ 1 አመት ከሰራሁ በኋላ ድሬደዋ ሄድኩ የድሬደዋ፣ ሐረር፣ ጅጅጋና አሰበተፈሪ የቀጠና ኃላፊ ሆኜ ተመድቤ ከሰራሁ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡ አዲስ አበባ ስመጣ በእግር ኳስ ኤክስፐርትነት የኢትዮጲያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆኜ ተመድቤ የህፃናት ፕሮጀክትና ፕሪሚየር ሊጉን ሰራሁ…. ከነካሳሁን ከነመንግሥቱ ጋር ሰርቻለሁ ከዚያ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኜ ተሾምኩ እኔ በዋና አሰልጣኝነት ምክትሌ ንጉሴ ገብሬ ሆነን ይዘን ወደ ሞሮኮ ስንጓዝ 16 ተጨዋቾች ጣሊያን ላይ ጠፉ ያኔ ታዲያ ጨዋታውን ሳናካሄድ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስን ስመለስ ግን በኃላፊነቱ አልቀጠልኩም እንዴት ጠፉ በማለት አሰናበቱኝ፡፡ ከዚያ ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተመለስኩ…. ሲያዩኝ ያው እንዳልኩህ እኔ ልዩ ሰው ነኝ የመምሪያ ሃላፊ ተብዬ ተሾምኩ….. በማታው ክፍለ ጊዜ የመማር ዕድል አገኘሁና የፋርማሲ ትምህርቴን ለ5 አመታት ተምሬ በፋርማሲ ዲግሪዬን አገኘሁ፡፡ ስራዬን በመምሪያ ኃላፊነት እየሰራሁ ሳለ የክብርት ሚኒስትር አስቴር ማሞ ዘመን ልዩ አማካሪ ተብዬ ተሾምኩ፡፡ ይህን እየሰራሁ ሳለ መሃል ላይ በቃኝ ብዬ ደብዳቤ አስገብቼ ስራዬን ለቀቅኩ… ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል፡፡
ሀትሪክ፡- አቶ ጌታሁን አሁን ምን እየሰሩ ነው?
ጌታሁን፡- ፋርማሲውን በስሜ ከፍቼ የኢትዮጵያ ህዝብ እያከምኩ እገኛለሁ (ሳቅ)
ሀትሪክ፡- እርስዎ የሊጉን ፎርማት በተመለከተ የሚናገሩት በኩራት ነው፡፡ ሌሎች ወገኖች ደግሞ የፕሪሚየር ሊጉ መጀመር ኳሱን ገድሏል ይላሉ… የሚሉት አለ?
ጌታሁን፡- ከታምሩ ሙሉጌታ ጋር ነው ፎርማቱን የሰራነው….አሁንም የምኮራበት ስራ ነው፡፡ በመሰረቱ የሊጉ መጀመር እድገት አምጥቷል ባይ ነኝ፡፡ ሊጉ ሲጀመር ውድድር ይኖራል፣ ብዙ ክለቦችና ተጨዋቾች ይኖራሉ፣ ብዙ ስታዲየሞች ይሰራሉ፣ ህብረተሰቡ ስፖርት ቤተሰቡና ወጣቱ በሚኖርበት ሠራተኛው በሚሰራበት ቦታ ኳሱን የማየትና የመሳተፍ እድል ያገኛል፤ ብዙ ገንዘብ ኢንቨስት ይደረጋል፣ አካዳሚዎችን በማስፋፋት የህፃናት እግር ኳስን ይደግፋል ይላል፡፡ እነኚህን ውጤቶች ያመጣል ተብሎ ነው ሊጉ የተጀመረው፡፡ ከዚህ አንፃር አብዛኛው ተፈፅሟል ባይ ነኝ፡፡ በየክልሉ የሚገኙ ክለቦች እኩል ተፎካካሪ ይሆናሉ የሚለውም ተሳክቷል፡፡ ከዚህ አንፃር የሊጉ መጀመር እግር ኳስን አሳደገ እንጂ አልገደለም፡፡
ሀትሪክ፡-የፕሪሚየር ሊጉ ፎርማት ባይኖር ኳሱ ግን ይጎዳል?
ጌታሁን፡- ይሄ ፕሪሚየር ሊግ ባይኖር በአዲስ አባል 10 ክለቦች ብቻ ቢወዳደሩ እንዴት ሊኮን ነው? አሰባችሁት… ወይም በድሮው በየ15 ቀኑ ክልሎች መጥተው የሚወዳደሩ ቢሆን ምን ይፈጠር ነበር? በጣም አስቸጋሪ ነው.. ይሄ ሁሉ ወጣትስ የት ይገባ ነበር… ሊጉ መኖሩ መአት ምርጫ ፈጥሯል፡፡
ሀትሪክ፡- ሊጉ የዘረኝነቱን ችግር እንዳይስፋፋ እድል አልሰጠም ይላሉ?
ጌታሁን፡- ፎርማቱ ሲጀመር በኛ ሀገር አዲስ አይደለም…. ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ቀደም ሲል በኤርትራ በድሬዳዋ፣ በሀረርና አዲስ አበባ ያሉ ጥቂት ክለቦች በመዟዟር እንዲጫወቱ አድርገው ነበር በደርግ እስኪፈርስ ድረስ ውድድሩ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ከቦታ ቦታ ተዛዙሮ መጫወት የኛ የመጀመሪያ አይደለም ኬንያ፣ ሱዳን፣ ኡጋንዳ… ፎርማቱ ተመሳሳይ ነው ችግርም የለበትም፡፡ የኛም ከተነሳንበት አንፃር ተሳክቷል ማለት ይቻላል፡፡ ፎርማቱ ችግር የለበትም ነገር ግን ውስጡ የአሰራር ችግሮች ካሉ እነርሱን ማየት እንጂ በደፈናው አይሰራም ማለት ልክ አይደለም፡ አሁን ብዙ ስፖርተኞች ራሣቸውን ለውጠውበታል… ህብረተሰቡንም ያለጡሩምባ ማግኘት ተችሏል ክለቡን ደግፎ ውስጣዊ በሆነ ፍቅርና ስሜት የሚመጣው ሊጉ በመጀመሩ ነው ይሄ ነው የሚበልጠው? ወይስ አዲስ አበባ ውስጥ እንደ ድሮው 8 እና 10 ክለቦች ብቻ በየጊዜው እየተጫወቱ መቆየታቸው ነው የሚመረጠው? ሌሎች ክልሎች ከአዲስ አበባ እኩል ተፎካካሪ መሆናቸው ያኮራኛል፡፡ የዘር ችግሩ በአውሮፓም በብዙ ሜዳዎች ላይ ነበር፡፡ በሊቨርፑል፣ በጁቬንቱስኮ ያሉ ደጋፊዎች ተመሳሳይ ስሜት ነበራቸው…. እነዚህ የእድገት ምልክቶች ናቸው፡፡ የአንድ ክለብ ደጋፊዎች የስፖርቱ ጌጥ ናቸው፡፡ ያለደጋፊ ኳሱ አያምርም….እነርሱ ናቸው 12ኛ ተጨዋቾች፡፡ ይሄም ስፖርቱ ኃያል መሆኑን ያሳያል ጥልቅ ስሜትና ፍላጎትን የሚቆጣጠር መሆኑን ያስመሰከረ ነው፡፡ ይሄንን ወደ ንግድ መለወጥ ነው ያቃተን እንጂ የምናያቸው ችግሮች የእድገቱ እንጂ የጥፋት ምክንያቶች አይደለም… ዘረኝነትን የሚያጠፋ ስፖርት ነው እግር ኳስ….አንፈላለግም አንስማማም ያሉት ተናበው ወንድማማች የሆኑት በኳሱ ነው፡፡ ኳሱ በስርዓት ሲቀጥል ችግሩ ይወገዳል፡፡ ፕሮግራም ቀርጾ ዳኛ መድቦ ማጫወት እንጂ ህብረተሰቡን አላስተማርንም ማስተማርኮ አለብን ህብረተሰቡን አሳታፊ አድርጎ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ከራሣቸው ውስጥ እየወጡ እንዲያስተምሩ ማድረግ አለብን ያ ከሆነ ሰውን መለወጥ ዘረኝነቱን ማጥፋት ይቻላል…. ያኔ እግር ኳስን የሠላም የፍቅር የአንድነት ትልቅ መሳሪያ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይሄን የሚሰሩ ሰዎች አሉ ወይ ነው ጥያቄው? ይሄን ለመለወጥ የተሞከሩ ትንንሽ ነገሮች አሉ የጊዮርጊስ፣ የፋሲል የደደቢት ደጋፊዎች ሙከራ ማድረጋቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡በጥናቱ ላይ የተቀመጡትን ስንሰራ ስናጤን ስፖርቱ የሞተው በሊጉ ፎርማት ነው ማለት ስህተት ነው፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ፎርማቱ እግር ኳሱን ገድሏል የሚሉ ራሣቸው ተሳስተው ሰውን የሚያሳስቱ ሰዎች አባባል ነው፡፡
ሀትሪክ፡-የሁሉም ክልል ክለቦች በየክልላቸው ቢጫወቱ ምንም አይነት የዘረኝነት ችግር አይፈጠርም… የሚሉ አሉ?
ጌታሁን፡-ይሄን ዘረኝነት ፎርማቱ አልፈጠረውም፡፡ በፎርማቱ ውስጥ ያለው የአሰራር ሂደትና የስፖርት ቤተሰቡ ግንዛቤ ካልሆነ በስተቀር ስራ ሊሰሩ የሚገባቸው ባለመስራታቸው የመጣ ችግርን በፎርማቱ ማሳሰብ አይገባም፡፡ ይሄ የዘረኝነት ችግር እንደ ሀገር የመጣ እንጂ ኳሱ ላይ ብቻ አይደለም በርግጥ እግር ኳስ ድርሻ አለው ለማስተካከል መስራት ይጠበቃል በሌሎች ቦታዎች እየተሰራ ነው፡፡ መንግሥት የሠላም ሚኒስትር አቁቁሟል እግር ኳስ ፌዴሬሽንስ ለዚህ ችግር ምን መፍትሔ እያዘጋጀ ነው…? ምንም ሳይሰራ መለወጥና ማደግ ይችላል እንዴ? መጀመሪያ ራሣቸውን ማየት ምን ሰራን ብለው መጠየቅ አለባቸው፡፡ መነጋጋር ያለባቸው ወደ ራሣቸው ዞረው ነው…ውቅያኖስ ውስጥ የነበረ ሰው በአንዴ ነፃ መውጣት ይፈልጋል እንዴ? መምከር ማስተማር ማስተባበር መደገፍ…. ይሄን የሚሰራ አካል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አለ በኛ ሀገር እግር ኳስ? የለም…… መንግሥት ግን ይሄን ለማጥፋት የሚችል መዋቅር በሚኒስቴር ደረጃ አቋቁሟል፡፡ እኛ ግን በኮሚቴ ደረጃ የለንም፡፡ እነዚህ ላይ ነው መሰራት ያለበት፡፡ ለውጡ ከተፈለገ ዘረኝነቱ እንዲጠፋ አመራሮቹ በዚህ ላይ መረባረብ አለባቸው፡፡ ስትራቴጂካዊ አሰራር መከተል ለዚህ የሚሆን ኃይል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ነው እውነቱ፡፡
ሀትሪክ፡- የአሰልጣኞች ላይሰንስ እንደ ሰርግ ካርድ ይበተናል ሲሉ ተችተዋል…. ኃላፊነቱ ታዲያ የማን ነው?
ጌታሁን፡- ይሄንንማ ዋና መከታተል ያለበት ቴክኒክ ኮሚቴ ነው… የተሰጠው ላይሰንስ በሙሉ መሰብሰቡ የግድ ነው… የኢትዮጵያ ቴክኒክ ኮሚቴ ነኝ የሚለው ሰውዬና ሰዎቹ ይሄን መስራት አለባቸው፡፡ መንግሥት አላግባብ ወረቀት የያዙትንኮ ተከታትሎ ርምጃ ወሰደ… ኳሱ ላይ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላቱስ ምን እየሰሩ ነው? ይህን ስራ ኮሚቴው ቁጭ ብሎ እቅድ አቅዶ ስራውን መስራት አለባቸው፡፡ ይሄንን የደረጃ ልዩነት መስመር ማስያዝ የሚቻለው እንዴት ነው ብለው መነጋገር አለባቸው፡፡ የዕለት ተዕለት ውድድር ኢንተርናሽናል ውድድር ሲኖር አሰልጣኝ የመምረጥ ስራ ብቻ የሚሰሩ ከሆነ ልክ አይደለም ይሄ ዋነኛ ስራቸው መሆኑን ማወቅ አለባቸው፡፡ ኮሚኒዝምኮ ሆነ ኮሚኒዝም በአለም ላይ ጠፍቷል፡፡ ኮሚኒዝም በኛ ሀገር ኳስ እንደገና ሊመጣ ነው እንዴ? ሁሉም እኩል እንዴት ይሆናል? የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊቱን ወስዶ ሰዎችን መድቦ ለችግሩ መፍትሔና ለቀጣዩ ጉዞ ስርዓት ማውጣት አለበት፡፡
ሀትሪክ፡- ለእግር ኳስ ትንሳኤ ነው የሚሉት ምንድነው?
ጌታሁን፡- የኳሱ ለውጥ ካስፈለገ ታዳጊ ላይ ማተኮር አለብን፡፡ ታዳጊና ወጣት ላይ ጥናት አድርጌ ምን አይነት ውጤት እንደሚገኝ አስቀምጫለው የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ አዘጋጅቼ ለመላ አገሪቱ በመፅሀፍ ደረጃ ሰጥቻለው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን ተረክቦ መስራት አልቻለም፡፡ በጥናቱ ላይ ምን መሆን እንዳለበት ተቀምጧል የኢትዮጵያና የየክልሎቹ ፌዴሬሽኖች ጥናቱን ቢወስዱም አልተጠቀሙበትም፡፡ 40 ቡድኖች እያንዳንዱ 25 ተጨዋቾችን ይዞ (ከ13፣ 15ና 17 አመት በታች) ከፋፎሏቸው መፅሀፎቶቹን አዘጋጅቼ ፕሮጀክቱን ከነበሩት ባለሙያዎች ጋር ሰርቼ በመላው አገሪቱ እንዲጀመር ቢደረግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ አሁን ያሉት አሰልጣኞች በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ፕሮጀክቱ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ መጨረሻ ላይ ግን የሚከታተለውና የሚሰራው ሰው ባለመኖሩ ተበተነ…. ይሄ ወረቀት አሁንም አለ፡፡ የተከፈቱት አካዳሚዎች አሉ ትልቁ ስራቸው ይሄን መስራት ነው ስራውን ሰርተው ኳሳችን የሚለውጥበትን መንገድ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሀትሪክ፡- በዚህ ፕሮጀክት ላይ እነማን ነበሩ?
ጌታሁን፡- አስራት ኃይሌና ስዩም አባተ አልነበሩም ነገር ግን ሰውነት ቢሻው፣ አብርሃም መብራቱ፣ ገ/መድህን ኃይሌ፣ ፀጋዬ ኪዳነማርያም፣ ውበቱ አባተ የመሳሰሉ ነበሩበት፡፡ ምን ያደርጋል… የየክልሎቹ ፌዴሬሽኖች መከታተልና መስራት ባለመቻላቸው ውጤት አልተገኘም፡፡
ሀትሪክ፡- በአሰልጣኝነት ሙያዎ እነማንን አሰልጥነዋል?
ጌታሁን፡-ንግድ ባንክ፣ አየር መንገድ፣ መከላከያ፣ መድን፣ ኪራይ ቤት፣ ባህርዳር ከተማ፣ ደሴ ውሃ ስራዎች፣ አግሮ ኢንዱስትሪ (ጊዮርጊስን ያሸነፈ ጠንካራ ቡድን ነበር) የኢሊባቡርና የጅማ ምርጦች፣ ድሬደዋ ጨርቃጨርቅ፣ ጋምቤላ… በሀገር ደረጃ ብሔራዊ ቡድኑን (ዋናውና ወጣቱን) ሁሉ አሰልጥኛለው፡፡
ሀትሪክ፡- ብሔራዊ ቡድን ይዘው የርስዎ ምክትል የነበሩት እነማናቸው?
ጌታሁን፡- በዋናነት ስሰራ አብረውኝ በምክትል አሰልጣኝነት የሰሩት አሰልጣኝ ንጉሴ ገብሬ፣ አሰልጣኝ ተስፋዬ ገብሩ፣ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ፣ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ… ረዳቴ ሆነው ሰርተዋል፡፡
ሀትሪክ፡- ከኛ ሀገር አሰልጣኞች በተለይ ከነ አሰልጣኝ አስራትና አሰልጣኝ ሰውነት ጋር ትገናኛላችሁ.. ሠላም ናችሁ?
ጌታሁን፡- ከማናቸውም ጋር ችግር የለብኝም፡፡ ምክንያቱም ረጅም አመት በተለያየ ዘርፍ በመማሬም ይሁን በመስራቴ ከሰዎች ጋር መግባባት እችላለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-በተለይ ከአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ጋር የነበረውን አለመግባባት ፈታችሁት?
ጌታሁን፡ አዎ ከዚያ በኋላ ችግሩን ፈተነዋል፡፡ ያለ ችግር እነነጋገራለን፡፡ ሁሉ ተረስቷል፡፡
ሀትሪክ፡- ከሰሩባቸው ክለቦች ትልቁ ስኬትዎ ምንድነው?
ጌታሁን፡- በተለያየ ጊዜ የተለያየ ውጤት አስመዝግቤያለው… እነ አየር መንገድ ወደላይ ማምጣትና ጥሩ ተፎካካሪ ማድረግ ችያለው… ያኔ ፕሪሚየር ሊግ የለም መጠሪያው ሱፐር ሊግ ነበር ወደ ሱፐር ሊግ አሳድጌያለው ያ ጥሩ ስኬቴ ነበር፡፡ ጨዋታው እዚው አዲስ አበባ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-የርስዎን ሲቪ የስራ ዘመንዎን የትምህርት ደረጃዎን ስመለከት ውጤትዎ የሚመጥኖት አልሆነብኝም፤…ያልተመቾት ነገር ስለነበር ነው?
ጌታሁን፡- በምሰራባቸው ስራዎች ሁሉ ለራሴ ውጤታማ ነኝ፡፡ በብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚዬን ደጋግሜ ያሸነፍኩበት ጊዜ ነበር ዋንጫ አይኑር እንጂ ከሀገር ውስጥም ከውጪም ያሸነፍኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ከሚጠበቀው በላይ የሆንኩበት ጊዜ እንደነበር አልረሳውም፡፡ ክለቦችን ሳሰለጥን ያለ ችግር ነበር የምሰራው፡፡ ነገር ግን ዝም ብሎ ገብቶ አንበጫርቃለው የሚል ሲኖር አልቀበልም ጣልቃ ሲገቡብኝ አልወድም፡፡ ባህርዳር ከተማ ስይዘው ወራጅ ቦታ ላይ ነበር ይዤው ግን አራተኛ ደረጃ አድርጌያለው… አመቱን ሙሉ ሳልባረር የጨረስኩት እኔ ነኝ በጣም አስቸጋሪ የነበረ ክለብ ነው፡፡ ደጋፊው የፈለገውን ሊል ይችላል ስለደጋፊው ብዙም መጨነቅ የለብንም፡፡ ነገር ግን ደጋፊውን ለመለወጥ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ሆነው በአለቃም ይሁን በደጋፊ ታዝዘው ተጨዋች አስገብተው ወይም አስወጥተው ያውቃሉ?
ጌታሁን፡- በፍፁም በምንም አይነት አይደረግም… ከብዙዎቹ አሰልጣኞ ጋር ያለው ልዩነታችንኮ ይሄ ነው፡፡ ባህርዳር ከተማ ምሳሌ ብናይ ብዙ የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ ግን አልቻሉም በሙያዬ ማንም አይወስንም፡፡
ሀትሪክ፡- ፈረንሣዊው አሰልጣኝ ዲያጎ ጋርዚያቶ ሲባረሩ የአቶ ጌታሁን እጅ አለበት ተባልኩ…. እውነት ነው?
ጌታሁን፡- የጋርዚያቶ የቅርብ ጓደኛና ረዳት መሆኔን ነው የማውቀው፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ ቅሬታ ሲያቀርቡበት የነበሩት ሌሎች ናቸው፡፡ ለኔ ወዳጄ ነው አሁንም እንኳን በፌስቡክ እንገናኛለን፡፡ በስልጠናው ወቅት እኔና እርሱ ከመግባባታችን የተነሣ በጣም የምከራከረው ለርሱ ነው ለርሱ መጥፎ አይደለሁም በቅርብ ጊዜ የሱዳንን ቡድን ይዞ ሲመጣ የፈለገው እኔን ነው… በአጋጣሚ መብራት ኃይል ነበርኩና ዋቢ ሸበሌ አርፈው ሜዳ አግኝቼላቸው ሳግዛቸው ቆይቻለው…. በወዳጅነት እንጂ በፀብ እኔና ጋርዚያቶ አንተዋወቅም ያው ስሜን ለማጥፋት የተወራ ወሬ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ስለ ተጨዋቾች ደመወዝ ስናነሳ ለሁሉም ተጨዋች እኩል መከፈሉ ተገቢ ነው…?
ጌታሁን፡- እርሱን ለማጥራት አሰራሩን መፈተሽ አለብን በየኮሚቴው ያለው ሰው ሌላ ስራ የሚሰራ እንጂ ቡድኑን የሚደግፍ እውቀቱን የሚሰጥ የሚያግዝ አይደለም፡፡ አሁንኮ ኮሚቴው ውስጥ ራሱ የሚበረታታ የሚደገፍ እንጂ የሚያግዝ ጠፍቷል፡፡ ይሄ መፈተሽ አለበት ያን ማፅዳት የግድ ይላል፡፡ ሰጪና ተቀባይ ሆነው እየተከፋፈሉኮ ነው እነርሱ መወገድ አለባቸው፡፡ ይሄንን ማጥራት እንጂ ፎርማቱ ላይ መጮህ አያወጣም ተጨዋቾቹ በሌላ ሀገር ያሉ በጥሩ ሁኔታ ይደገፋሉ ይከፈላቸዋል… እዚህ ግን የለም… ይሄንን ለማስተካከልና ለተጨዋቹ የተሻለ ለመክፈል ህጋዊ ያልሆኑ ሰዎችን ማሰናበት የግድ ይላል፡፡ የአሰልጣኞች ደረጃ ከፍ ማለት ይጠበቅበታል፡፡ ስልጠና መስጠት የግድ ይላል ያለበለዚያ ዋጋ የለውም ሳናውቅ እንዴት ተወዳዳሪ እንሆናለን?
ሀትሪክ፡-የኛ ሀገር አሰልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ኮርስ ብዙ ጊዜ ሲወስዱ አይታዩምና ለውጡ የጠፋው ተደጋጋሚ ነገር የምናየው ለዚህ ይሆን?
ጌታሁን፡-አዎ አሰልጣኞቻችን በየአመቱ አቋም ማጠናከሪያ ስልጠና ሲወስዱ ይገባል፡፡ ይሄ መደረጉ አቅማቸውን አይተው እንዲያሳድጉ አዳዲስ የስልጠና መንገዶችን እንዲረዱ ያደርጋል በኛ ሀገር ግን የለም ታዲያ አሰልጣኞቹ እንዴት ይለወጡ…? እንዴት ከሌሎች ሀገር ቡድኖች ይወዳደሩ…?
ሀትሪክ፡- በየክለቡ ያሉ አብዛኞቹ ኮሚቴዎች ኳሱን የሚያግዙ አይደሉም ?
ጌታሁን፡-እነርሱ ላይም ሊሰራ ይገባል… የሰው ኃይልና የፋይናንሱ አደረጃጀት መስተካከል አለበት… ይሄን የሚሰራው አካል ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቀዋል ሁሉም ባይሆን ብዙዎቹ ኮሚቴዎች ሊመረመሩ ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- አቶ ጌታሁን በንድፈ ሃሳብ ልዩ ናቸው የተግባር ምዘናው ላይ ግን አነስ ይላሉ የሚሉ ወገኖች አሉ… ምላሽዎ ምንድነው?
ጌታሁን፡- እግር ኳስ ላይ የመስራት ፍላጎት ነበረኝ በተከታታይ የመስራት እድል ግን አላገኘሁም፡፡ የተማርኩ ሰው ስለሆንኩ በከፍተኛ ኃላፊነት ተመድብኩ ከአሰልጣኝነት የወጣሁት በ1992 ዓ.ም ነው በኃላፊነት ደረጃ የሚያበቃኝ አቅም ስለነበረኝ ከዚህ የተሻለ ስራ ይሰራል ተብዬ ተመደብኩ በዚህ ምክንያት ስልጠናው ውስጥ ብዙም ባለመስራቴ ነው ውጤት የሌለው፡፡ እንደ አሰልጣኞቹ ቁጭ ብዬ እየደጋገምኩ ያቺኑ የምሰራ ብሆን አሳይ ነበር፡፡ ፕሪሚየር ሊግ በ1990 ተጀምሮ ከ2 አመት በኋላ ከአሰልጣኝነቱ ወጥቼ የመምሪያ ኃላፊ ሆኜ ተሾምኩ፡፡ የትምህርትና የስልጠና የመምሪያ ኃላፊ ነበርኩ፡፡ ስለዚህ በስልጠና ልገመገም አልቻልኩም፡፡ በሰራሁባቸውም ቦታ ላይ ጥሩ ነበርኩ ይናገራሉ ነገር ግን መሬት አይወርድም መባሉን አልቀበልም፡፡ በነገራችን ላይ ምንም ነገር ለመናገርኮ እውቀት ይጠይቃል ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ ማስተማርም ሆነ ማሠልጠን አይችልም፡፡ በዚያ ላይ በንግግርም ሆነ በተግባር አልታማምኮ፡፡ የተናገርነውን የህፃናት ፕሮጀክት በተግባር መክፈቱ ፕሪሚየር ሊግ በመጀመሩ የዘረዘርኳቸው ስኬቶች አሉ…በማሰልጠን ደግሞ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከሀገር ውጪ በማሸነፍ አሳይቻለው፡፡ ታዲያ ምኑጋ ይሆን መሬት አልወረደም የሚባለው? በነበረኝ ደረጃኮ ሚኒስቴር ደረጃ መስራት የሚያስችል አቅም ነበረኝ፡፡ ብዙ መናገር የምችለው ለጊዜው የማያስፈልግ ስለሆነ ብዙ ነገር ዝም ብያለው….. በዚያ ላይ ናይጄሪያ ላይ በተካሄደው የመላው አፍሪካ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በ13 የስፖርት አይነት ስትወዳደር የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን መሪ ነበርኩ፤ በተጨማሪም በአልጄሪያ በተካሄደ ተመሳሳይ ውድድር ላይም ቡድን መሪ ሆኜ ሄጃለው፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢሮቢክስ ስፖርት በየቀኑ ለ30 ደቂቃ እንዲካሄድና ለህዝቡ እንዲላለፍ አድርጌያለው፤ ዛሬ ስንት ሰው እንጀራ ይበላበታል፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮም እንዲተላለፍ ማድረጌ ይታወቃል፡፡ ስፖርት ኮሚሽን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲሽ እንዲተከል አድርጌያለው… ይሄኮ ከባድ ታሪክ ነው፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ የሀገሪቱን እግር ኳስ አፍቃሪ ያነቃነቀ ስፖርቱ ሀገር አቀፍ እንዲሆን ያደረኩ ሰው ነኝ ይሄ መዘንጋት የለበትም፡፡…. መድንን ስረከብ 2ኛ ዙር ላይ ደረጃው 13ኛ ነበር አመቱን ስጨርስ ግን 3ኛ ሆኖ ነበር… ይሄ ውጤት አይባልም? ባህርዳር ወደ ታች ለመውረድ ጣር ላይ የነበረ ቡድን ነው… ከተረከብኩ በኋላ በአመት ውስጥ 4ኛ ወይም 5ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው… ይሄ ውጤት አይደለም?
ሀትሪክ፡- በውጤት ደረጃ የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ወይም እንደ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ከ31 አመት በኋላ ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳተፍ…..አይነቱ ትልቅ ስኬት የሎትም ቢባልስ ምላሽዎ ምን ይሆን?
ጌታሁን፡- ውጤት ዝም ብሎ አይመጣም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ሰውነት ያመጣው ውጤት ነው? የራሱ ስራ ብቻ ነው? እያንዳንዱ አሰልጣኝ ባደረገው አስተዋፅኦና ባሰለጠናቸው ተጨዋቾች ነው…ውጤቱ የመጣው… ማነው የርሱ ብቻ ያደረገው?….
ሀትሪክ፡-ክሬዲቱ ግን የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውኮ ነው?
ጌታሁን፡-ግዴለም ይሁን…. ምንም ችግር የለም በሰዓቱ የተገኘው እርሱ ነዋ… የተሰራውን የጋራ ስራ ድምር ውጤት አገኘው እድለኛ ነው… ጥሩ ነው ይሞገስ ደስ ይላል… በአንድ ወር ግን ውጤት አይመጣም….በአሰልጣኝ ሰውነት ስራ ብቻ ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፍን ለምን ደጋግሞ አላሳለፈንም? ይሄ ትክክለኛ ግምት አይደለም… ግን እድለኛ ነው ዝና አግኝቷል… ይሄ ያለ ነው፡፡ በተከታታይ ሲሰራና ውጤት ሲመጣ ነው መሞገስ ያለበት፡፡ አንድ አመት ወይም 6 ወር ስለ ሰራ ውጤት አይመጣም ይሄ ነው እውነቱ፡፡
ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ጥያቄ… አሁንም የመጀመሪያው ኤክስፐርት እርስዎ ኖት?
ጌታሁን፡- በእግር ኳስ በሲቪል ሰርቪስ ደረጃ የምታውቀው የመጀመሪያው
ኤክስፐርት እኔ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-እነ መንግሥቱ ወርቁስ?
ጌታሁን፡- ይሆኑ ይሆናል… ነገር ግን የከፍተኛ ኤክስፐርትነት ማዕረጉን ያገኘሁት የመጀመሪያ ሰው እኔ ነኝ፡፡ ወረቀት ትምህርት ይፈልጋላ… (ሳቅ) ከነሙሉ ክብሩና ዲግሪው ከነ ሙሉ ኃላፊነቱ ነው የወሰድኩት፡፡
ሀትሪክ፡- በከፍተኛ ደረጃ ተምሮ ማሰልጠን ወይም ተጫውቶ ከማሰልጠን የቱ ይበልጣል?
ጌታሁን፡-ተናግሬያለሁ.. እግር ኳስ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ስፖርት መጫወት፣ ማጫወት፣ ማሰልጠንና መዳኘት የምችል ሰው ነኝ የተለያዩ ስፖርቶች እጅ ኳስ ቅርጫት ኳስና መረብ ኳስ የፍፃሜ ጨዋታ መርቻለሁኮ….. እግር ኳስንምኮ ተጫውቻለሁ የሚያውቅ ያውቀኛል… (ሳቅ) በተጫወትኩት ሳይሆን ከዚህ የደረስኩት በተማርኩት ነው፡፡ ያም ስለሆነ ነው መፅሀፍ የጻፍኩት….ሰው የሚጨቃጨቅበትን ፕሪሚየር ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ 11 ክልል አሣምኜ የሰራሁት….. በኳስ ተጫዋችነትኮ ይሄ አይሰራም፡፡ ይሰራል እንዴ? ፈፅሞ ….. በኳስ ውስጥ አለፍኩ ማለት ብቻ አይበቃም፡፡ ያስፈልጋል ግን ብቻውን አይሆንም… ያግዛል ጥሩ ነው ግን አይበቃም.. የምናወራውኮ ሎጂክ ነው መተማመን አለብን፡፡ በአለም ውስጥ ስንት የጥናትና የምርምር ማዕከል ተከፍቶለት የሚከናወንን ስራ በኳሱ ውጥ አልፌያለው ብለህ ልታወራ ትፈልጋለህ… ይሄማ አይሆንም…. ከባድ ነው አይቻልም…. ድርሻ አላቸው ድርሻቸውን ይሞክራሉ… በቃ፡፡
ሀትሪክ፡-እኔም አበቃው
ጌታሁን፡-አመሰግናለሁ…..
አስተያየት ይስጡ