“ሳላሀዲን ብቻ ሣይሆን እኛም እንደተመታን ነው የቆጠርነው…”ምንተስኖት አዳነ/የቅዱስ ጊየርጊስ አምበል/ ክፍል 1

 

“ሳላሀዲን ብቻ ሣይሆን እኛም እንደተመታን ነው የቆጠርነው…”

“የኮሮና ቫይረስን መመለስ የሚቻለው በፀሎት ብቻ ይመስለኛል”

“በገዛ ሜዳህ በደጋፊህ… ክልል ስትሄድ ደግሞ በተጋጣሚ ደጋፊ ጫና ውስጥ ሆነህ ውጤት መጠበቅ ይቻላል?”

ምንተስኖት አዳነ/የቅዱስ ጊየርጊስ አምበል/


ዱስ ጊዮርጊስ በሰበታ ከተማ 1ለ0 መረታቱን ተከትሎ ወደ 3ኛ ደረጃ ወርዷል፡፡ ይህም በርካታ ደጋፊዎችን አበሳጭቷል ያንን ተከትሎ በጨዋታ እንቅስቃሴ ኢንተርናሽናል አርቢትር ሃ/የሱስ ባዘዘውን በመናገሩ በቀይ ካርድ የተባረረው ሳላህዲን ሰይድ በ2 ደጋፊዎች በቦክስ መመታቱ አነጋጋሪ ሆኗል ሁለቱ ደጋፊዎቹ ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም ድርጊቱ ብዙኃኑን አነጋግሯል፡፡ ይህን ተከትሎ ባልደረባችን ዮሴፍ ከፈለኝ ከክለቡ አምበል ምንተስኖት አዳነ ጋር በነበረው ቆይታ ድርጊቱና ተጨዋቾቹ ጋር ስላለው ስሜት፣ ስለ አሰልጣኞቹ ስንብትና ስለ አምበልነቱ፣ ስለ ኮሮና ቫይረስና ስለ አባይ ግድብ፣ ስለደካማው ውጤት፣ ስለደጋፊው ስሜት፣ ስለ ዋንጫ ተፎካካሪነት፣ ተገቢ አምበል ነኝ ስለ ማለቱ፣ በጊዮርጊስ ማሊያ የእግር ኳስ ዘመኑ ለመጨረስ ስላለው ፍላጎት፣ ስለ ፍቅር ህይወቱና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- የአሁኑ የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጉዳይ ኮሮና ቫይረስ ሆኗል… አገራችን ገባ ሲባል ምን ተሰማህ?

ምንተስኖት፡- አለም አቀፍ በሽታ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ይገመታል… በየቀኑ የሚገባባቸው ሀገራት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ኢትዮጵያ ውስጥም ሊገባ እንደሚችል መገመት አያቅትም፡፡ ገባ ሲባል ብዙም አልደነገጥኩም ከገባ በኋላም ምንም ማድረግ አይቻልም…ያለው አማራጭ ከእግዚአብሔር ጥበቃ በታች ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-አሜሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አውጃለች… ለኛስ መፍትሔው ምንድነው ትላለህ…?

ምንተስኖት፡- ፀሎት………ከዚህ ውጪ ምንም መፍትሔ ያለው አይመስለኝም፤ ሊኖርም አይችልም መፍትሔ ቢኖር መድሃኒት ይኖረው ነበር መድሃኒት ካለ ደግሞ መላው አለምን ባላስደነገጠ ነበር ከፀሎት ውጪ ምንም አይነት መፍትሔ የለውም፡፡ ከፈጣሪ ጋር የተያያዘ በኛው ሀጢያት በኛ ስህተት ከፈጣሪ የመጣ ቁጣ ነው ብዬ አስባለው፡፡ ወደ ፀሎቱ ፊትን ማዞር ብቻ ነው የሚያዋጣው… የኮሮና ቫይረስን መመለስ የሚቻለው በፀሎት ብቻ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡-የሀገራችን አኗኗር በቡድንና በጋራ መሆኑ ቫይረሱ እንዲዛመት ያደርገዋል ተብሎ ይሰጋል…አንተስ ምን ትላለህ?
ምንተስኖት፡- ትልቁ ስጋት ሆኖ በሽታው እንዳይገባ የተፈራውም በአኗኗራችን ነው፡፡ በሰለጠኑ አለማት በጣም ከተቸገሩ እነ አሜሪካ፣ ቻይናና ጣሊያንን የመሰሉ የበለፀጉ አገራት ከተጠቁና ከተፈተኑ እኛ ሀገር ደግሞ የህክምናው ደረጃ ብዙ የሚያስተማምን ባለመሆኑ ስጋት መፍጠሩ አይቀርም አኗኗራችን በራሱ ለበሽታው ተጋላጭ ያደርጋልና በጣም ከባድ ይሆናል ብዬ አስባለው እግዚአብሔር ይርዳን ማለት ብቻ ነው የምችለው፡፡
ሀትሪክ፡- እስቲ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጤት እንመለስና ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ማግኘት ከነበረባችሁ 6 ነጥብ 1 ብቻ ማሳካት አያበሳጭም?

ምንተስኖት፡- በጣም ተበሳጭተናል፡፡ ከሽንፈት የራቅነው ወልዋሎን 4ለ1 ያሸነፍን እለት ነው… ከዚያ ከፋሲል ጋር ከሜዳ ውጪ አቻ ወጣን፡፡ የመሪነቱን ስፍራ ስንይዝ ቦታውን አንለቅም ብለን ርግጠኛ ሆንን… አዳማን በሜዳችን ስለምንገጥም እናሸንፋለን ብለን አሰብን በተቃራኒው ፋሲል ከነማና መቐለ 70 እንደርታ ከሜዳ ውጪ ከሀዋሳና ከድሬደዋ ጋር ተጫውተው ነጥብ ሲጥሉ ልዩነቱ ይሰፋል ብለን ሂሣብ ሰራን… በርግጥም ሁለቱም ክለቦች ነጥብ ጣሉ ነገር ግን እኛ ደግሞ የራሣችንን የቤት ስራ መስራት አልቻልንም ቡድናችን የሚጫወተው በጫና ውስጥ ነው አንድ ወይም ሁለት ጨዋታ ነጥብ ከጣልን የቡድናችን መተማመን ሲሸረሸር አይተናል፡፡ በተለይ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ስለምንገባ ተደጋጋሚ ጊዜ ነጥብ ጥለናል ያ ነው አሁንም የገጠመን… አቅም አንሶን ወይም ከሌላዉ ክለብ ይልቅ አቋማችን ወርዶ አይደለም የጭንቀት ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡-የማጥቃት ኃይላችሁ መዳከምንስ አያሳይም?

ምንተስኖት፡- አዎ ማሸነፍ ስንጀምር ትልቁ ኃይላችን የነበረው የአጥቂው መስመራችን ነው… በሁለት ጨዋታ 10 ግብ ያገባ ቡድን አሁን ደግሞ በ4 ጨዋታ 1 ግብ ማግባት ከብዶታል፡፡ በርግጥ ይሄ ያጋጥማል…… በስነ-ስርዓት ድል አድራጊ ለመሆን የግብ እድል መፍጠር የተፈጠረውን መጠቀም የግድ ነው አለበለዚያ አቻ ነው አሊያም ይገባብህና ትሸንፋለህ በርግጥ የማጥቃት ኃይላችን የደከመው ልጆቹ ወርደው ሳይሆን ችግሩ እንደ ቡድን ነው የገጠመን … የአዕምሮ ዝግጅት ችግር ይመስለኛል፡፡ ለምሣሌ ከሰበታ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ብዙ የግብ እድል የፈጠርነው እኛ ነበርን፤ ከዚህ በፊት አጥቂዎቻችን ከዚህ የባሱ የማይታመኑ ኳሶችን ጨርሰው አግብተዋል፡፡ በዚህ ጨዋታ ግን አልተሳካም በጫና ውስጥ ሆኖ መጫወትና በራስ መተማመን ተሞልቶ መጫወት ይለያያል፡፡ ለማሸነፍ ካለን ጉጉት ቡድናችን ከፍ እንዲል ከነበረ ምኞት እንጂ የአቅም ማነስ አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡-አሰልጣኞቻችሁ ታግደው አንተ አምበል ሆነህ ቡድንህን መርተሃል… ኃላፊ ነቱን አልከበደህም?

ምንተስኖት፡- አይከብድም… ኃላፊነቱ የኔ ብቻ አልነበረም… 7 ሲኒየር ተጨዋቾች ተጠርተን በቦርዱ አማካይነት ኃላፊነት ተሰጥቶናል የአምበልነት አርማውን ላርግ እንጂ ከኔ በበለጠ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሳላህዲን ሰይድና ጌታነህ ከበደ ላይ ነበር ኃላፊነቱ የወደቀባቸው… ሰባታችንም የምንችለውን አድርገናል ከእንቅስቃሴ አንፃር ጥሩ ብንሆንም ውጤት አልመጣም.. በዚህም ቅር ብሎናል፡፡

ሀትሪክ፡-የሳላሀዲን በቀይ ካርድ መው ጣት እንደ አምበል ምክንያቱን አውቀሃል?

ምንተስኖት፡- በርግጥ ራቅ በማለቴ ቦታው ላይ ተገኝቼ የተባባሉትን አልሰማሁም፡፡ እግር ኳስ በመሆኑ ስሜታዊ ያደርግሃል… በርግጥ አጠቃላይ ሂደቱን አላወኩም ከጨዋታ በኋላም አልሰማሁም ከዳኛው እንዳተረዳሁት ግን ወደ ረዳት ዳኛው አትሂድ ስለው የመለሰልኝ ምላሽ ተገቢ ያልሆነና በጥሩ መንገድ ስላላናገረኝ በቀይ ካርድ አባርሬዋለው ብሎኛል… ከዚያ ውጪ የማውቀው ነገር የለም፡፡

ሀትሪክ፡-ሁለት የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሳላሀዲንን በቦክስ መትተውታል.. እናንተ ላይ ምን ፈጠረ?

ምንተስኖት፡- በጣም ተከፍተናል.. ተገቢ ድርጊት አልነበረም ድርጊቱ ሳላሀዲንን ብቻ የሚወክል አይደለም ሁላችንም የሚወክል ነው… ሁላችንንም የሚወክል ነው ሳላሀዲን ብቻ ሣይሆን እኛም እንደተመታን ነው የቆጠርነው… ስሜቱ ክፉኛ ተጎድቷል በድርጊቱ እኛም አዝነኛል… ሳላ ለጊዮርጊስ ብቻ ሰይሆን ለሀገር ክብር የሆነ ብዙ ዋጋ የከፈለ ተጨዋች ነው ባለውለታ መሆኑ መታሰብ አለበት፡፡ በዚህ ደረጃ ይከሰታል ብዬ ፈፅሜ አልጠበኩም መሰደብና መተቸትኮ የተለመደ ነው ከዚህ በፊትም አይተናል በዚህ ደረጃ ተጨዋች መመታት አለበት ብዬ ግን አላሰብም እንደ አምበልም አዝኛለው በርግጥም ድርጊቱ ምርጡንና ብዙኃኑን ደጋፊያችንን አይወክልም፡፡ በርግጥ ደጋፊዎች ሲያበረታቱን አይዟችሁ በርቱ እያሉ ሲያረጋጉን የነበሩ ብዙ ደጋፊዎችን አይቻለው በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ፡፡ በርግጥም ሳለ ስሜቱ ተጎድቷል፡፡ የአብዛኛው ተጨዋች ስሜትም ተመሳሳይ ነበር፡፡ በውጤቱ ተበሳጭተን ወጥተን ድጋሚ ይሄ ሲፈፀም ሀዘን ተሰምቶናል፡፡ ይሄ ወደፊት በፍፁም መደገም የለበትም፡፡

ሀትሪክ፡-ታክሞ ወጥቷል….? ተረጋጋ ል…?

ምንተስኖት፡- አዎ ማታውኑ ሆስፒታል ነበር በጥሩ ሁኔታ ታክሞ ወጥቷል፡፡ አሁን መረጋጋት ይታይበታል በዚህም ደስ ብሎኛል፡፡

ሀትሪክ፡-በደረጃ ሰንጠረዥ 3ኛ ናችሁ.. .ቀጣዮቹ ጨዋታዎች አያሰጉም?

ምንተስኖት፡- አሁንምኮ በሜዳችን ከወላይታ ድቻ ጋር ነው የምንጫወተው፡፡ በራስ መተማመኑን መመለስ ከቻልን የአሰልጣኝነት ክፍተቱ ስለሚተካከል ጥሩ ውጤት እናመጣለን የተሻለ ደረጃ ላይ የመገኘት ስጋት የለብኝም የሚያስፈራ ነገር የለም፡፡ ከመሪው በ3 ነጥብ ርቀት ዝቅ ብለን ነው ያለው… የማይቻል አይደለም ገና 13 ጨዋታ ከፊታችን አለ ተስፋ አልቆርጥም ደጋፊው እስከመጨረሻው ቢደግፈን ለመቃወም አመቱ ሲያልቅ ይደርሳል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡-ስለደጋፊው አንስተሃል.. በርግጠ ኝነት ከደጋፊው የምትፈልጉት ምንድነው?

ምንተስኖት፡- ለመቃወሙ አመቱ ሲያልቅ ይደርሳል ባይ ነኝ… አሁን የሚያስፈልገው የነርሱ ሙሉ ድጋፍ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ቡድኑ በራስ መተማመኑን እያጣ ጨዋታ ማሸነፍ እያከበደው እንዳይሄድ ያሰጋል፡፡ በዚያ ላይ በሜዳችን እንኳ ነጥብ መያዝ አልቻልንም ክልል ወጥተን ታዲያ እንዴት ነጥብ ይጠበቃል? እስቲ የክልል ቡድኖችን ተመልከት ደጋፊው የሜዳ ላይ አድቫንቴጃቸውን እንዲጠቀሙ ያደርጋቸዋል ደጋፊው 90 ደቂቃ ከነርሱ ጋር ይቆማል… በተቃራኒ የተጋጣሚ ቡድን ላይ ነው መጥፎ ጫና አድርገውና ተቃውመው ቡድናቸው ውጤት እንዲያመጣ የሚያደርጉት… ይሄ የሚገርመኝ ልዩነት ነው… የክልል ክለቦች ደጋፊዎቻቸው የሜዳ ላይ አድቫንቴጁን እንዲጠቀሙ ያደርጓቸዋል ይሄ ደግሞ በአዲስ አበባ ክለቦች ላይ አይታይም፡፡ በራስህ ደጋፊ ጫና ውስጥ ገብተህ የምትጫወት ከሆነ ይከብዳል ባይ ነኝ፡፡ በገዛ ሜዳህ በደጋፊህ… ክልል ስትሄድ ደግሞ በተጋጣሚ ደጋፊ ጫና ውስጥ ሆነህ ውጤት መጠበቅ ይቻላል? አይመስለኝም….በደጋፊዎቻችን ይሄ ጉዳይ ቢታረም ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡-አሁንስ የዋንጫ ተፎካካሪ የሚባሉት የተለመዱት ክለቦች ናቸው?

ምንተስኖት፡- በተለየ መንገድ የወጣ የለም… ፋሲል ከነማ መቐለ 70 እንደርታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ ደረጃ ላይ ቢገኙም የዋንጫ ፉክክሩ ለሌሎች ክለቦችም ክፍት ነው፡፡ ገና 13 ጨዋታ ይቀራል የ39 ነጥብ ጨዋታ እያለ በ1 እና በ2 ነጥቦች ልዩነት ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ይሄ ደግሞ የዋንጫውን ፉክክር እንደሚያደምቅ ከመናገር ውጪ ሌላ የምለው የለም፡፡ ፉክክሩ የሊጉ ፍፃሜን ያሳምረዋል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- እስቲ ስለአምበልነትህ እና ውራ… ተገቢ አምበል ነኝ ትላለህ? ደጋፊው ዝምተኛ አምበል መሆንህ አልተዋጣለትም?

ምንተስኖት፡- ይሄም ለኔ ምንም አይገርመኝም፡፡ አለማችን በታላቅ ሞራል ቡድኑን የሚያነሳሳውን ስቴቨን ጄራርድ የማየቷን ያህል ዝምተኛውን አምበል አድሪያን ፒርሎንም አሳይታናለች አምበልነት ለእኔ ጯሂነት ነው ብዬ አላምንም… እንደ ደጉ ወይም አዳነ አይነት አምበል መሆን አልችልም ባህሪዬ አይደለማ ያ ደግሞ መስፈርት መሆን አይገባውም፡፡ ተጨዋቾች ሁሉ የሚጮህ አምበልን የሚቀበሉ ይመስልሃል? አይደለም የሚከፉ ይህን ተጨዋች አሳርፈው የሚሉ የቡድናችን አባላት አሉ… የጊዮርጊስ አሰልጣኞች ሲሰናበቱ አመሰግነውን ነው የሄዱት… የእኔ አምበልነትና ባህሪ ተመችቷቸዋል ማለት ነው…አንዳንዱ ተጨዋች በዳኛ ውሳኔ ተማርሮ ዳኛ ሲናገር ካርድ ሊያይ ይችላል…ይሄ የሆነው ምንተስኖት ስለማይናገር ነው ይላሉ ይሄም ልክ አይደለም… ደጋፊ የሚያነሳሱት ይሄን አይነት ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች ናቸው እየተባለ መጮህ ዘራፍ ማለት እንዴት ይበረታታል? ዳኛው እኔ ስናገር ካልሆነ በስተቀር ተጨዋቹን ካርድ ሊሰጥ ይችላልና መታቀብ አለባቸው…ሌላው ደግሞ ምናልባት እድለኛ አይደለሁም የምለው አምበል በሆንኩበት 2 አመታት ቡድኑ ዋንጫ አለማግኘቱ ነው ይሄ ደግሞ የአምበልነት ባህሪዬ ምክንያት ተደርጎ እተችበታለሁ …ሻምፒዮን ብንሆን ኖሮ የኔ ባህሪይ እንደምክንያት አይነሳም ነበር፡፡ ትክክልኛ አምበል ነው ይባል ሁሉ ነበር.. ግን አልሆነም… በዚህ ባህሪዬ አምበል ሆኜ መቀጠሌ አይቀርም በነገራችን ላይ ደጉም ቢሆን ከኔ ጋር ተመሳሳይ አይነት ባህሪይ ነው ያለውና በዚህ ደረጃ ሰበብ ማድረግ ይከብዳል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የለበሱትን ማሊያ የሚስሙ ተጨዋቾች ለክለባቸው ፍቅር አላቸው ይባላል….ይህን ታምናለህ?

ክፍል ሁለትን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ 👇

https://www.hatricksport.net/ሳላሀዲን-ብቻ-ሣይሆን-እኛም-እንደተመታ-2/

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport