“በዝርክርክነትና በማን አለብኝነት በሚሰሩ ስራዎች የመጫወት እድሌን ተነፍጌያለሁ” መሳይ አያኖ/ሲዳማ ቡና/

“ለሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ጉብዝናዬን በመሠከረ አሰልጣኝ ለዋሊያዎቹ አለመመረጤ ያማል”

“በዝርክርክነትና በማን አለብኝነት በሚሰሩ ስራዎች የመጫወት እድሌን ተነፍጌያለሁ”
መሳይ አያኖ/ሲዳማ ቡና/


ለተደጋጋሚ ጊዜያት ሀገሩን የማገልገል ረሃብ ቢኖረውም በተወሰነ መልኩ ረሃቡን ያጠገበው ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ነው፡፡ ነገር ግን በሚገባውና በፈለገው መጠን ዋሊያዎቹን አልጠቀመም፡፡ በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ፣ በአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ፣ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለና አሁን በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ መዘለሉ ያንገበግበዋል፡፡ በአሁኑ ብሔራዊ ቡድን ውስጥማ መመረጥ ነበረብኝ ሲል ቅሬታውን ይገልፃል፡፡ የግብ ጠባቂው እድል ደግሞ የሚያበሳጨው አልተመረጠኩም ብሎ ሲበሳጭ ተመርጦም የሚፈልገውን ያህል አለመጫወቱ ነው፡፡ በአስተዳደራዊና በቢሮ ሰዎች ስህተት ግጥሚያ ላይ የመሳተፍ እድሉ በተደጋጋሚ መክኗል፡፡ ከዚህ በኋላ በቃኝ ብሔራዊ ቡድናችንን የማገልገል ፍላጎቴ ሞቷል ብጠራም አልሄድም ለምወደው ክለቤ ሲዳማ ቡና ሙሉ ጊዜዬን ባውል ይሻላል ያለው የዛሬ እንግዳችን ተወልዶ ያደረገው ሀላባ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ለአላባ ከተማ፣ ለሀገረ ማርያም፣ ለደቡብ ፖሊስ፣ ለአርባ ምንጭ ከተማና አሁን ደግሞ ለቀጣዮቹ 2 አመታት ለሲዳማ ቡና ለመጫወት ፊርማውን ያኖረው ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ይባላል፡፡ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ለብሔራዊ ቡድን አለመመረጡ የፈጠረበትን ስሜት፣ ለሲዳማ ቡናና አሰልጣኙ ዘርአይ ሙሉ ያለው ፍቅር፣ ክለቡ ስላለው ዋንጫ የማንሣት እድል፣ ከኳስ ስለተለየበት 7 ወራት፣ ከውጪና ከሀገር ውስጥ ምርጥ በረኛ ስለሚላቸው፣ በሲዳማ ቡና የውጪ በረኛ ቦታ እንደሌለው፣ ስለ ፈቱዲን ጀማል መመለስና የአዲስ ግደይ ስንብት፣ ስለ ዲ ኤስ ቲቪና ሌሎች ጉዳዮች ግልፅ የሆነ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ከኮቪድ 19 ነፃ መሆናችሁ በምርመራ ታውቋል… ምን ተሰማህ?

መሳይ፡-አዎ ሲዳማ ቡና ልምምድ ከመጀመሩ በፊት በተደረገልን ምርመራ ነፃ መሆናችን ታውቋል፡፡ ነገ ወደ ልምምድ የምንሄደው በመተማመን መንፈስ ውስጥ ሆነን ነው፡፡ በውጤቱ ደስ ብሎኛል/ቃለ ምልልሱ የተሰራው ባለፈው ረቡዕ ምሽት ነው/

ሀትሪክ፡- ባለፉት 7 ወራት ከኳስ ውጪ መሆናችሁ የፈጠረው ስሜት ምን ይመስላል… 7 ወሩን እንዴት አለፍከው?

መሳይ፡- 7 ወሩ ከባድ ነበር፡፡ በግል አልፎ አልፎ ስሰራ ቆይቻለሁ ቤት ውስጥ ስሰራ ነበር ከክለቡም ደግሞ በአሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ በቴሌግራም በሚሰጠን ስልጠና ቆይተናል፡፡ ከተቋረጠ በኋላ የምችለውን ሰርቻለሁ፡፡ ሰባት ወሩ ግን የቫይረሱ ስርጭት ጣራ የነካበትና በርካታ ሰዎች የሞቱበት በመሆኑ ስሜቱ ጥሩ አልነበረም፡፡

ሀትሪክ፡- አገባህ.. ወይስ?

መሳይ፡- አላገባሁም ነገር ግን የምወዳት ፍቅረኛ አለችኝ…

ሀትሪክ፡- 7 ወር ላይ በደንብ ተገናኛችሁ?

መሳይ፡-/ሳቅ/ በአጋጣሚው ሆኖ ቤቷ ብዙም ባይርቅም የቤተሰብ ጫና ስለነበረ ብዙም አልተገናኘንም ማለት ይቻላል፡፡

ሀትሪክ፡- ረዘም ላለ ጊዜ ሣትጫወት ቆይተህ ታውቃለህ?

መሳይ፡- አዎ አርባ ምንጭ ስጫወት እግሬ ላይ በደረሰ ጉዳት ወደ ስምንት ወር ያልተጫወትኩበት ጊዜ አለ፡፡

ሀትሪክ፡- አሃ የዕረፍት ልምድ አለሃ?

መሳይ፡-/ሳቅ በሳቅ/አዎ እንደዛ በለው

ሀትሪክ፡ ከአላባ የወጡና ታዋቂ የሆኑ ተጨዋቾች አሉ?

መሳይ፡-አሉ.. ሰብስቤ ደፋር፣ ፈቱዲን አወል አሁን ደግሞ እነ ዮናስ ገረመው /ሃላባ/ ይጠቀሳሉ፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ግብ ጠባቂነት እንደት አመዘንክ?

መሳይ፡-ልጅ ሆነን ሳለ ወደዚህ ቦታ የገፋፋኝ ሰፈር ውስጥ ያለ አንድ አሰልጣኝ ነበር፤ ለይቶ ግብ ጠባቂነት ያሰራኝ ነበር፡፡ የአሰልጣኙ ስም አንዋር ሲርጋታ ይባላል፡፡ ከዚያ ውጪ ይበልጥ ወደ ግብ ጠባቂነት ያቀረበኝና እዚህ ቦታ እንድደርስ ያደረገኝ አምዳላ ይባላል ሁለቱንም አመሰግናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከተጫወትክባቸው 5 ክለቦች ስኬታማው የትኛው ክለብህ ነው?

መሳይ፡- ያለ ጥርጠር 4 አመት የቆየሁበት ሲዳማ ቡና ስኬታማው ክለቤ ነው… ዘንድሮ ለተጨማሪ ሁለት አመታት ውሌን አድሻለው እስካሁን ጥሩ ቆይታ ነበረኝ ደስተኛ የነበርኩበት ዘመን ነው፡፡ 2011 2ኛ ወጥተን ያጠናቀቅንበት ዘመን የኔ ምርጡ ጊዜ ነው፤ ያም ቢሆን በጥቃቅን ስህተቶች ዋንጫ ያጣንበት በመሆኑ አሁን ድረስ እቆጫለሁ ሻምፒዮን መሆን እንችል ነበር፡፡

ሀትሪክ፡-ከሀገር ውስጥ ምርጡ በረኛህ ማነው? ከውጪስ?

መሳይ፡- ከሀገር ውስጥ በጣም የምወደውና የማከብረው ቢኒያም ኦሼ ነው ከውጪ ደግሞ የማን ዩናይትዱ ዴቪድ ደሂያ ነው ከሁለቱም በጣም ተምሬያለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ግብ ጠባቂ ባትሆን ምን የምትሆን ይመስልሃል?
መሳይ፡- ሰፈሬ የሚዘወተረው የተለያዩ ቢዝነሶች ስለሆነ ነጋዴ እሆን ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- እስቲ ስለሲዳማ ቡና አስተዋውቀኝ?

መሳይ፡-በክለባችን በ4 አመት ቆይታዬ ብዙ ነገሮች አልፈዋል፤ ስለክለቡ ለመናገር ቃላት ያጥረኛል፡፡ ፍቅሩ አንድነቱ ቤተሰባዊ ግንኙነቱ ይማርካል በመነጋገር የሚያምን ቤተሰብ ማለት ነው፡፡ እግር ኳሱ በኮቪድ 19 ምክንያት ተቋርጦ በነበረበት ሰዓት ያለማቁረጥ ደመወዝ ሲከፈለን ታዝቤያለሁ፡፡ ምናልባት አንዴ ለተጎዱ ሰዎች ለመስጠት 10 በመቶ የተቀነሰው ካልሆነ በስተቀር በጊዜ ነው ደመወዝ ሲከፈለን የነበረው…ክለቦቻችን ከዚህ ክለብ ሊማሩና ሊተገበሩት ይገባል በዚህ አጋጣሚ ኃላፊዎቹን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የአዲስ ግደይ መሄድ ጉዳት አላመጣም?

መሳይ፡-በርግጥ አሪፍና ጠቃሚ ተጨዋች ነው ያም ቢሆን ክፍተት ይፈጥራል ብዬ አላስብም በርግጠኝነት የእርሱን ቦታ በሚገባ ተክተናል ያስፈረምነው አጥቂ ጫላ ተሺታ ይባላል፤ ጥሩ ጊዜ ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- አሠልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ለእኔ ጨመረ የምትለው ምንድነው?

መሳይ፡- በሚገባ ጨምሮልኛል እንደ በረኛ ኳስ ይዤ መጫወት እፈልጋለው ይህን ፈቃድ ሰጥቶ በከፍተኛ ራስ መተማመን እንድጫወት ያደረገኝ አሰልጣኝ በመሆኑ ተደስቻለሁ፡፡ እነ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በረኛ ተጨዋች ነው ብለው ያምናሉ የእኛ አሰልጣኝ እኔ ላይ እምነት መጣሉና ያለኝን እንዳወጣ አድርጎኛል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የኛ ሀገር አሰልጣኞች ዜጋን እንጂ ኢትዮጵያዊያን በረኞችን አይወዱም እምነት አይጥሉባቸው የሚሉ ወገኖች አሉ አንተስ?

መሳይ፡- እድለኛ ሆኜ ያለሁበት ክለባችን ዜጋ በረኛ አይፈልግምና የደረሰብኝ ጫና የለም፡፡ አሰልጣኙ የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂ አይፈልግም፡፡ እስካሁን ድረስ በሀገሪቱ በረኛ ነው ሲጫወት የነበረው.. ይህም ጠቅሞኛል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የዋሊያዎቹ 41 ተጨዋቾች ሲመረጡ የአንተ ስም የለም… ለምን ይመስልሃል?

መሳይ፡- እሱን አላውቅም፤ በእርግጠኝነት ግን መመረጥ ነበረብኝ አሁን ከተመረጡት ግብ ጠባቂዎች መስፈርቱን የማሟላ እኔ ነኝ፤ ያለኝ አቅምም ምርጥ ነበር… በ2011 እና 2012 አመቱን ሙሉ ተሰላፊ ነበርኩ፡፡ በጉዳት የወጣሁበት ጨዋታ ካልሆነ በስተቀር፡፡ የተሰለፍኩባቸው ጨዋታዎች ላይ በስኬት ፈፅሜያለሁ በኮቪድ ሲቋረጥ ክለባችን 4ኛ ነበር፤ በ2011 ደግሞ 2ኛ ሆነን ፈፅመናል፡፡ የክለቤ ደረጃ ጥሩ ነበር፡፡ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የተጠሩት በረኞች ብዙ ጨዋታ ያላደረጉ በረኞች ናቸው ተክለማርያም ሻንቆ ብቻ ነበር ጨዋታዎችን ያደረገው… አብዛኛዎቹ ግን ብዙ ጨዋታ አላደረጉም ለዚህ ነው መመረጥ ነበረብኝ የምለው፡፡

ሀትሪክ፡-ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ ነበረብኝ የምትለው ከመቼ ጀምሮ ነው?

መሳይ፡- መመረጥ የነበረብኝ ከአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ጊዜ ጀምሮ ነው በተለይ ግን በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን ውስጥ የግድ መመረጥ ነበረብኝ፡፡ ያ አልሆነም አሁንም አለመመረጤ ያሳዝናል፡፡ ከዚህ በፊት እድሉን ያገኘሁት በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጊዜ ነው አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም ከአሰልጣኞቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረኝ በቢሮ የፅሁፍ ስህተት ግን ከቡድኑ ውጪ መሆኔ አሳዝኖኛል…

ሀትሪክ፡-የምን ስህተት… እስቲ በይበልጥ አብራራው?

መሳይ፡-በወቅቱ ጥሩ ስለነበርኩ በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ተመርጬ ቡድኑ ውስጥ ተካትቼ ነበር ነገር ግን አልቀጠለም፡፡ ለካፍ በሚላክ የስም ዝርዝር ውስጥ ተካተትኩ ብዬ ሳስብ በተላከው ስም ላይ የስም ስህተት ተገኝቶበት ከጨዋታ ውጪ ሆኛለሁ፤ እኔ የዋናው ቡድን ግብ ጠባቂ ነበርኩ፡፡ እኛ ካፒታል ሆቴል ስናርፍ ከ23 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ዋቢ ሸበሌ አርፈዋል…. ለካፍ በተላከው ደብዳቤ በኔ ስም ቦታ ላይ ዮሴፍ ዮሀንስ የተባለ ከ23 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ስሙ ተላከበት ይሄ ተጨዋች የሲዳማ ቡና 6 ቁጥር ነው ከየት እንደተገናኘ ሳይታሰብ በኔ ቦታ የርሱ ስም ተገኘና አለመሄዴ ሲታወቅ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጠርቶ አበረታታኝ አይዞህ እንዲህ አይነት ነገር ተፈጥሮ ነው ብሎ በሚችለው መንገድ አፅናናኝ አይ ችግር የለም ሌላ ጊዜም አለኝ ዋናው መጣራቴ ነው አልኩና አለፍኩት፤ እንደዛም ሆኖ ከፍቶኛል ግን አሰልጣኙን ላለማስጨነቅ ምክንያቱን ተቀብዬ ዝም አልኩ…

ሀትሪክ፡-2ኛውስ ገጠመኝ…?

መሳይ፡- በቅርቡ ከጅቡቲ ጋር ለነበረ ጨዋታ የተዘጋጀነው አዳማ ላይ ነበር ለጋናው ጨዋታ ሲባል ፓስፖርታችንን ሳንመልስ እዚያው ፌዴሬሽን ይገኝ ነበር፤ በድጋሚ ጠንክሬ ሰርቼ ነው የተዘጋጀሁት… ገና ዋቢ ሸበሌ ላይ እንደገባን ፓስፖርታችሁን አምጡ ሲባል የኔና የተወሰኑ ልጆች ፓስፖርት ፌዴሬሽን ነው ያለው አልናቸው፤ ጉዳዩ ሳይጨረስ ግን ለዝግጅት አዳማ ሄደን ልምምዳችንን ወደ 20 ቀን ሰራን እንደ ነገ ቪዛ ሊመታ በዋዜማው አለ ሲባል የነበረው ፓስፖርቴ ጠፍቷል የለም ተባልኩ.. ተነጥሎ የኔ ብቻ ጠፍቷል፡፡ ደነገጥኩ.. አሰልጣኝ አብርሃም ግን በመደበኛ መኪና ላይደርስ ይችላል በሚል በራሱ መኪና ወደ አዲስ አበባ በለሊት ይዞኝ ሄደ፡፡ የተጨዋቹን ፓስፖርት በአስቸኳይ ጨርሱልኝ ምክንያቱም ለግጥሚያው የምጠቀመው ይሄን በረኛ ነው ብሎ አደራ ሰጥቶ ወደ አዳማ ተመለሰ፡፡ ፌዴሬሽን ሆኜ እንድከታተል ነግሮኝ ነው የሄደው… እርሱ ከሄደ በኋላ ግን ዞር ብሎ ያየኝ ሰው የለም ለጨዋታው አይደርስም ተባለ…ተበሳጨሁ.. ባላወራው ይሻላል ያሳምማል አላወራሁትም እስካሁን አሁን ነው የምናገረው… 8 ቀን ጠበኩ ማንም አልመለስልኝም አላስተናገደኝም ዝምታ መምረጤ ይሻል ነበር መሰለኝ… ብዙም ማውራት ደስ አይለኝም እነዚህ ሁሉ ጎድተውኝ አለፉ፤

ሀትሪክ፡-በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እመርጣለሁ ብለህ ጠብቀሃል?

መሳይ፡- ጠብቂያለሁ መጠራት ነበረብኝ፤ ወጥሬ ሰርቻለሁ አሰልጣኙ በደንብ ያውቀኛል እኔን የማይመርጥበት ምክንያት አለ ብዬ አላምንም… አሰልጣኝ ውበቱ ጨዋታ ካለ ቁጭ ብሎ ያያል፡፡ የሀዋሳ ከነማ ይሁን የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ሆኖ በደንብ ያውቀኛል፡፡ በቅርቡ ፋሲል ከነማ ላይ በኃላፊነት እያለ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲረታ ስታዲየም ተገኝቶ ቁጭ ብሎ ተከታትሏል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ጉብዝናዬን በመሠከረ አሰልጣኝ ለዋሊያዎቹ አለመመረጤ ያማል፡፡ በጣም የተበሳጨሁትም ለዚህ ነው፡፡ በደንብ ስለሚያውቀኝ ይጠራኛል ብዬ ነበር አለመጠራቴ ደግሞ ቅር አሰኝቶኛል አለመመረጤ ያናድዳል ተመርጬም የገጠመኝ ነገር አለ ጎበዝ ሆኜም አልመረጥም ይሄ ሁሉ ቅር አሰኝቶኛል በዚህ ምክንያት ሁሌ ከምናደድ ብዬ ራሴን ማግለል መርጫለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- አሁን ተረጋጋህ…

መሳይ፡-አዎ አሁን እየረጋጋሁ ነው የሁሉም ተጨዋች ትልቁ ግብ አገሩን ማገልገል ነው ይሄ ሲከለከል ቅር ያሰኛል በተለያዩ ምክንያቶች የመጫወት እድሌን ተነፍጌያለሁ፡፡ ይሄ ደግሞ ያበሳጫል በአሰልጣኞች አለመመረጤ እንዲሁም በቢሮ ስራ ከጀርባቸው በሚፈጠር ስህተት አለመመረጤ አናዶኛል፡፡ በዝርክርክነትና በማን አለብኝነት በሚሰሩ ስራዎች የመጫወት እድሌን ተነፍጌያለሁ…. ከላይ የጠቀስኩልህ ሁኔታ ለውሣኔ አብቅቶኛል አሁን ግን ተረጋግቼ ከሲዳማ ቡና ጋር ለሚኖረኝ የዝግጅት ጊዜ ራሴን እያዘጋጀሁ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- እስኪ ወደ ሲዳማ ቡና እንመለስና በ2013 የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ታልማለህ?

መሳይ፡- አዎ ጥሩ ቡደን ነው ያለንኮ… ጠንካራ ጎን አለው የነበሩና የተዋሃዱ ተጨዋቾች ስብስብ ነው ያለን… ከነበረን ስብስብ የተለየን አዲስ ግደይ ብቻ ነው… የርሱን ክፍተት ለመዘጋት ተሞክሯል፡፡ ከጨዋታው መቋረጥ በፊት የነበረብን የተከላካይ መስመር ክፍተት የቀድሞ ተጨዋቻችን ፈቱዲን ጀማልን በመመለስ ቀርፈናል፡፡ ይሄ ጠንካራ አቅማችን ነው.. ከፈቱዲን በኋላ የነበረው አለመግባባቶች ተከላካይ መስመሩን አሳስቶት ነበር አሁን ግን ተጠናክረናል፡፡

ሀትሪክ፡-በፈቱዲን መመለስ ተከለካይ ክፍሉ ሲጠናከር በአዲስ መውጣት ደግሞ ፊቱን አላሳሳውም?

መሳይ፡- አጥቂው ሳስቷል ብዬ አላምንም ከተስፋ ቡድኑ ያደገው ይገዙ ቦጋለ አለ፡፡ ጥሩ ልጅ ነው ግን አንዳንዴ አጋዥ ያስፈልገዋል፡፡ ያንን መስመር ሙሉ የሚያደርግ የአጥቂ መስመር ተጨዋችን አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ አስፈርሟል፡፡ ጥሩ ቡድን ገንብተናል ተፎካካሪ የዋንጫ ቡድን ይኖረናል ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡-ፕሮፌሽናል እድሎችን ከማመቻቸት አንፃር አልሞከርክም…? ወይስ…?

መሳይ፡- እድሎች ነበሩ በተለይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመላው አለም መከሰቱ ሁኔታውን ወደ ኋላ መለሰው እንጂ እድል አግኝቼ ነበር… ከቱርክ ክለቦች ጋር የተደረገው ሙከራ ቢከሽፍም ወደ ፊት እድሉ ይኖረኛል ብዬ አስባለው ከእግዚአብሔር ጋር ይሳካል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዲ.ኤስ.ቲቪ ሊተላለፍ መሆኑን ስትሰማ ምን አልክ?

መሳይ፡- በጣም ደስ ነው ያለኝ… ትልቅ አቅም አለን ብዬ ነው አምናለው ትንሽ ገድቦን የነበረው እድላችንን ያሳጠረው የመታየታችን ችግር ነበር አሁን ግን በዲ.ኤስ.ቲቪ ሊጀመር መሆኑ በተለያዩ ክለቦች የመታየት እድል ስለሚፈጥር ተደስቻለሁ በርትቶ መዘጋጀት ከኛ ይጠበቃል፡፡

ሀትሪክ፡-ክርስቲያኖ ሮናልዶ በኮሮና ቫይረስ ተያዘ የሚለው ዜና ምን ፈጠረብህ…?

መሳይ፡- /ሳቅ በሳቅ/ በጣም ነው የገረመኝ.. ጥንቃቄው መከላከል ላይ ያለው አቋም ስታይ በኮሮና ቫይረስ መያዙ ያስደግጣል ስፖርተኛና የጠንካራ ስራ ባለቤት በመሆኑም ድኖ ይመለሳል ብዬ አስባለው፡፡ ቫይረሱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነና ማንንም ማጥቃት እንደሚችል የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-የውጪ ኳስ ታያለህ.. ካየህስ የማን ደጋፊ ነህ?
መሳይ፡- ለይቼ የምደግፈው… ቡድኔ ነው ብዬ የማውራለት ክለብ የለኝም ግን ጥሩ ለተጫወተ እደግፋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ልቤን የገዛና የምደግፈው ክለብ የለም ማለት አይከብድም?

መሳይ፡- /ሳቅ በሳቅ/ አዎ ድጋፍ ይዤ የምጮህለት ባይሆንም ለሊቨርፑል ትንሽ አደላለው… ልቤን ሰረቅ አድርገውታል… ዋናው ግን ጥሩ ለተጫወተ የምደግፍ እግር ኳስ ወዳጅ ነኝ /ሳቅ/
ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ቃል..?
መሳይ፡- ዋናውን ምስጋና ለአምላኬ ለልዑል እግዚአብሔር ይሁንልኝ፤ ከርሱ በመቀጠል ለኔ እዚህ መድረስ ትልቅ ድጋፍ ያደርጉልኝን ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ከጎኔ ሳይለይ ሁሌ የሚያበረታታኝንን አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉን ማመስገን እፈለጋለው፡፡ ጓደኞቼ፣ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎችና የክለቡ ሰዎች በአጠቃላይ ትልቅ እገዛ ላደረጉልኝ በሙሉ ምስጋናዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

 

የመሳይ አያና ኮሮና

ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ ገባ በተባለበት መጋቢት ወር መጀመሪያ አካባቢ የነበረው መከላከልና ጥንቃቄ ደስ ይል ነበር በሀገር ደረጃ ሳይንሰራፋ ያለው ጥንቃቄ ተረስቶ አሁን በርካቶች እየተያዙና እየሞቱም ሁሉን ነገር ረስተነዋል ይሄ አስፈሪ ነው ሰው ሁሉ ባይዘናጋ ራሱን ቢጠብቅ ደስ ይለኛል አሁንኮ ሁሉን ትተነዋል መስተካከል አለበት.. የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡት ምክርን ተግባራዊ ማድረግ ቢቻል ጥሩ ነው ሁሉም ከፈጣሪ ርዳታና ከፀሎት ጋር በመከላከልና በመጠንቀቅ ቫይረሱን ማጥፋት ይቻላል ሁሉም ኢትዮጵያዊያንን አደራ ማለት የምፈልገውም ይሄንን ነው፤ መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ጥንቃቄ በደንብ ቢቀጥል ደስ ይለኛል፡፡

አባይ ግድብ
ዋው በጣም ነው የተደሰትኩት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ደስታዬ ወሰን አልነበረውም የህብረተሰቡ ድጋፍም መቀጠል አለበት የኛን የቀጣይ ትውልድን ታሪክ የሚቀይር ፕሮጀክት በመሆኑ መደገፍ አለበት ሁላችንም ልንከታተለው ይገባል፤ በግሌ ከተለያዩ ክለቦች ጋር የቦንድ ግዢ ፈፅሜያለው 8100A ላይም አለሁበት ለመላው ህብረተሰቡም አደራ የምለው በኛ ትውልድና ዘመን ይሄ ማየት ክብር ነው እድለኛም ነን ሁሉም ያለምንም ልዩነት ከጎኑ ሊቆሙ ይገባል ባይ ነኝ በመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ግን በጣም ደስ ብሎኛል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport