” ለደጋፊያችን የምለው በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያ ቡናን ጠብቁ ነው” ተክለማርያም ሻንቆ/ ጎሜዝ/

“ለዋሊያዎቹ ቋሚ ሆኜ ለኢትዮዽያ ቡና ተጠባባቂ መሆኔ በራስ መተማመኔን አያወርደውም”
” ለደጋፊያችን የምለው በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያ ቡናን ጠብቁ ነው”
ተክለማርያም ሻንቆ/ ጎሜዝ/

ተወልዶ ያደገው ከአዲስ አበባ 163 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዝዋይ ባቱ ከተማ ማንም ሰው አሁን የደረሰበት ደረጃ ይደርሳል ከተማዋ በሀገር ደረጃ የምትጠራበት ታሪክ ይሰራል ብሎ የገመተ የለም…. ለአጥቂነት ሄዶ ያለው ቦታ የግብ ጠባቂነት ቦታ ብቻ ነው ሲባል ከጓደኞቹ ላለመለየት ሲል እሺ ግብ ጠባቂ ልሁን ብሎ ተመዘገበ እግዚአብሔር ያየለት መኖርያው መጠሪያው ነበርና በዚህ የግብ ጠባቂነት ቦታ እየተሳበ ሄዶ አሁን ያለበት የከፍታ ቦታ ደርሷል፤ ለተወለደበት ከተማ ክለብ ባቱ ከነማ፣ ሼር ኢትዮጵያ፣ አላባ ከተማ አዲስ አበባ ከተማና ሀዋሳ ከተማን የበረኛውን ግልጋሎት ለሁለት ለሁለት አመት ብቻ አግኝተዋል፤ ይሄ ሰው ማነው ትላላችሁ ብዬ አልጠብቅም…..ዋሊያዎቹ ከ8 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፉ ቋሚ ብረቶቹን የመጠበቅ ኃላፊነት የወደቀበት የዋሊያዎቹና የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ ተ/ማርያም ሻንቆ /ጎሜዝ/ መሆኑ ይጠፋችኋል ብዬ አላምንምና… የቶተንሀሙ ግብ ጠባቂ ሂላሪዮ ጎሜዝን ትመስላለህ በሚል በቀድሞ የዝዋይ ከነማ ተጨዋች ደነቦ ቦኩ የወጣለት “ጎሜዝ” የተሰኘው ቅፅል ስሙ ደግሞ ተክለ ማርያም የሚሰኘውን ዋነኛ ስሙን እያስረሣ ይገኛል…. ዮሴፍ ከፈለኝ በኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ አመቱ ላይ ከሚገኘው ተክለማርያም ሻንቆ /ጎሜዝ/ ጋር በነበረው ቆይታ ሰፋ ያሉ ጥያቄዎችን አንስቶለት የሚከተለውን ምላሽ አግኝቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ተክለማርያም ግብ ጠባቂነትን እንዴት መረጠ?

ተ/ማርያም፡- አስቤበት ሣይሆነ ገጠመኝ ነው፤ አጥቂ ቦታ መጫወት ነበር ምርጫዬ…ነገር ግን በተወለድኩበት ከተማ ፕሮጀክት ተቋቁሞ ስለነበር የሠፈር ልጆች ሊሞክሩ ሲሄዱ እኔ አልቻልኩም ቤተሰብ በተለይ አባቴ ትምህርት እንድማር እንጂ ኳስ እንድጫወት አልፈቀደልኝም፡፡ የሰፈር ልጆች ግን በሳምንት ሶስቴ መስራት ሲጀምሩ እኔስ ለምን አልሰራም ብዬ ሄድኩ ነገር ግን ሁሉም ቦታ በመያዙ የግብ ጠባቂነት ቦታ ብቻ ነው ያለው ተባልኩና ፕሮጀክቱን ለመቀላቀል ስለጓጓሁ ግብ ጠባቂ ሆኜ ጀመርኩ ነገር ግን አሁን ድረስ የህይወቴ መኖሪያየዬ ሆኖ ሀገሬን ለማገልገል ሁሉ በቃሁ፡፡ በወቅቱ የህይወቴ መገለጫ ይሆናልም ብዬ አላሰብኩም ነገር ግን እግዚብሔር በራሱ ጊዜ የከፈተልኝ እንጀራዬ ሆኖ ቀርቷል፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያና ከሀገር ውጪ ልብህን የሰረቁ በረኞች አሉ…?

ተ/ማርያም፡- አዎ አሉ የተወለድኩበት ከተማ የነበረ ለዝዋይና ለድሬዳዋ ከነማ ሲጫወት የነበረ በለጠ ተስፋዬ ይባላል እያየሁት ያደኩና ድጋፍ ያደረግልኝ የነበረ ሰው ነው…. በሊግ ደረጃ ካየኋቸው ተምሣሌት የነበረኝ ለአለም ብርሃኑ ነው ከውጪ የባየር ሙኒክና የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የሆነው የማኑኤል ኑየር አድናቂ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፉክክርን እንዴት አገኘኸው…?

ተ/ማርያም፡- እጅግ ጠንካራ ፉክክር እየተደረገበት ነው ሁሉም ክለቦች ጠንክረው የመጡበት አመት ነው የዲ.ኤስ.ቲቪ መምጣትም ሊጉን አጠንክሮታል ተጨዋቾቹም ራሣቸውን ለማሳየት ስለሚጥሩ ጥሩ ፉክክር ነው ሊጉ በብዙ ቦታ ላይ የነበረው ግምት አሁን የለም… መላው አለም ላይ መታየቱ ክለቦቹም ሆነ ተጨዋቾቹ በርትተው እንዲመጡ አድርጓል፡፡

ሀትሪክ፡- ከፋሲል ከነማ ጋር ያላችሁ የነጥብ ልዩነት 12 ሆኗል… ዋነኛ ምክንያቱ ምን ይሆን…?

ተ/ማርያም፡- አንደኛው የፋሲል ከነማ ጥንካሬ ነው ጥሩ ነጥብ ሰብስቧል ነጥቦችን እየጣለም አይደለም በተቃራኒው እኛም አንዳንድ የማይጠበቁ ነጥቦችን እየጣልን መሆኑ የነጥብ ልዩነቱን አስፍቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ዋንጫውን ለፋሲል ከነማ ሰጣችሁት ማለት ይቻላል…?

ተ/ማርያም፡- /ሳቅ/ በፍፁም አላለቀም /ሳቅ/ ….ፋሲል ዋንጫ ቢወስድ እንኳን ለሁለተኛ የምናደርገው ትግል ይቀጥላል እስከመጨረሻ በእግር ኳስ ላይ የሚፈጠረውን ነገር አናውቅም የሚጠበቀው የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ብቻ ነው ሁለተኛ ሆነን በኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ ለመሳተፍ ብናቅድም ለዋንጫው የምናደርገው ትግል እስከመጨረሻ ይቀጥላል፡፡

ሀትሪክ፡- ተጠባባቂ ተጨዋችም ሆነ በረኛ ቋሚ የሆነው ተጨዋች እንዲጎዳላቸው ይፈልጋሉ የሚሉ አሉ ጎሜዝስ እንዴት ነው…?

ተ/ማርያም፡- /ሳቅ በሳቅ/ እንደዚህ አይነት እምነት የለኝም ማንኛውም ተጨዋች ገብቶ ሊጫወት 30 ሰከንድ ይጫወት 40 ሰከንድ ወይም 90 ደቂቃ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጎ መውጣት እንጂ የሌላውን ጉዳት መጠበቅ የለበትም፡፡ ነገም ተጠባባቂ የነበረው ቋሚ ሆኖኮ ይገባል ምን እንደሚያጋጥም ስለማይታወቅ ሌላው ላይ ጉዳት አልመኝም በይበልጥ የሚገኘው እድልን መጠቀም ላይ ነው ትኩረት የማደረግው፡፡

ሀትሪክ፡- አንተ ላይ የተሻለ ተፅዕኖ የፈጠረ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ማነው…?

ተ/ማርያም፡- እስካሁን ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞች የየራሳቸውን ነገር ሰጥተውኛል፤ ውብሸትን በብሔራዊ ቡድን፣ ፀጋዘአብን ከ20 አመት ብሔራዊ ቡድን ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡና ላይ እያሰለጠነኝ ይገኛል በዋሊያዎቹ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ እያሰለጠኑኝ ነው እነዚህ ባለሙያዎች የየራሣቸውን የተሻለ ነገር ሰጥተውኛል የየራሣቸውን ጥሩ ነገር አካፍለውኛልና ሁሉንም ነው የማመሰግነው፡፡

ሀትሪክ፡- የሸገር ደርቢ ሽንፈት ስሜት ይጎዳልና አሁን ላይ ስሜቱ ምን ይመስላል…?

ተ/ማርያም፡- /ሳቅ/ በጣም ቅር የሚያሰኝ የሚያናድድ ውጤት ነው የገጠመን.. ሽንፈቱም ሆነ ድሉ ምን አይነት ስሜት እንዳለው የሚገባው የሁለቱ ክለብ ተጨዋች ስትሆንና ሜዳ ውስጥ ስትገባ ነው.. በእውነት ያማል.. የበላይ ለመሆንና የነጥብ ተፎካካሪነታችንን የሚያስቀጥል ስለነበር ሽንፈቱ አበሳጭቶኛል የዋንጫ ጉዟችን በተወሰነ መንገድ ቀንሶብናል፡፡

ሀትሪክ፡- በሸገር ደርቢ የታየው ዳኝነት እንዴት አየኸው…?
ተ/ማርያም፡- ዳኝነቱን በተመለከተ ብዙም ተቃውሞ ማሰማት አልወድም ዳኞች እንደኛ ሰው ናቸው በቴክኖሎጂ የታገዙ ዳኞች አለም ላይ ሲሳሳቱ እያየን ነውና በኛ ሀገር ዳኞች ላይ መናገር አልፈልግም ሙያውን ለነርሱ ብተው ደስ ይለኛል ምንም ቴክኖሎጂ በሌለበት ትልቅ ደረጃ የደረሱ ዳኞችን በተለይ በአምላክ ተሰማን ስታይ ደስ ይላል.. ለርሱ ትልቅ ክብር አለኝ በትልልቅ መድረኮች የዳኘ ትልቅ ዳኛ ነው እርሱን የምተችበት ምክንያት የለኝም የዳኞች ኮሚቴ ግምገማ ነው ውጤቱን መግለጽ ያለበት… የኔ ስራ መጫወት የርሱ ስራ ዳኝነት በመሆኑ ብዙም ባላወራ እመርጣለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ሁለተኛ ደረጃን ለማግኘት የሚደረገው ፉክክር አያሰጋም…?

ተ/ማርያም፡- በርግጥ ፉክክሩ ጠንከር ማለቱ አይቀርም ቦታውን ለማግኘት አጠቃላይ አራት ክለቦች ተፋጠዋል ይህም ቢሆን ጠንክረን ሰርተን ዋንጫው ባይቻል ሁለተኛ ሆነን በኮንፌዴሬሽን ካፕ የመሳተፍ እድላችንን ለማሳካት እንጥራለን፡፡

ሀትሪክ፡- ግብ ጠባቂ ሆነህ በክለብ ደረጃ ተጠባባቂ መሆንህ አቋሜን ያወርዳል ብለህ አትሰጋም…?

ተ/ማርያም፡- በችሎታዬ ላይ ሙሉ እምነት አለኝ ጥርጣሬ ገብቶኝም አያውቅም ተደጋጋሚ ጊዜ መሰለፍ ልምድና በራስ መተማመንን ይፈጥራል ያ ርግጥ ነው …ነገር ግን በየትኛውም ጨዋታ ላይ ቋሚ ሆኖ መግባት የአሰልጣኙ ውሣኔ ይመስለኛል ያንን መቀበል የግድ ነው በኔ በኩል አንድ ደቂ ቃም ይሰጠኝ 90 ደቂቃ ብቃቴን ስለማውቅ በራስ መተማመን ነው ወደ ሜዳ የምገባው እንጂ ተጠባባቂ በመሆኔ የሚፈጠር ችግር የለም፡፡

ሀትሪክ፡- በክለብ ተጠባባቂ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ቋሚ ተሰላፊ መሆንስ ሌላ ስሜት አይፈጥርም?

ተ/ማርያም፡- /ሳቅ/ ክለብ ላይ ተጠባባቂ ሆኜ በብሔራዊ ቡድን ቋሚ መሆኔ በራስ መተማመኔን አያወርደውም ያለኝን አቅም አውቀዋለው ብቃቴን አምነው ቋሚ ተሰላፊ ያደረገኙን አሰልጣኝ ውበቱ አባተና የአሰልጣኞች ቡድንን አመሰግናለሁ እነሱ ቋሚ ያደረጉኝ እኔ ላይ ያዩት ብቃት ስላለ ነው ብዬ አምናለሁና ምንም ማድረግ አይችልም አሁንም በተሰጠኝ እድል ላይ ብቻ ማተኮር እፈልጋለሁ ያ ነው የሚጠቅመኝ…. ተቀመጠኩ ብዬ አቋሜ ከወረደማ ልክ አይሆንም በነገራችን ላይ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሰርጂዮ ሮሜሮ በማን.ዩናይትድ ረዘም ላለ ጊዜ ተጠባባቂ ነበር፡፡ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ግን አቅሙን ስለሚያውቁ አሰልፈውታል፡፡ እኛ ሀገር አቅም ሳይሆን የማቻቻል ስራ የሚሰራ መሆኑ ነው መጥፎው ነገር… እገሌ ይህን ያህል ተጫውቷል አልተጫወተም ከሚለው አሰራር በቦታው ብቃቱን ያሳየ መግባት እንዳለበት በአርጀንቲናው በረኛ ሰርጂዮ ሮሜሮ የታየ እውነታ ነው በአጠቃላይ በየትኛውም መድረክ ላይ አቋሜን አሳያለሁ ብዬ አምናለሁ የኮንፊደንስ ችግር የለብኝም፡፡

ሀትሪክ፡- ከሜዳ ውጪ ያለው ተቀባይነት የጨመረው በክለብህ ወይስ በብሔራዊ ቡድኑ ቆይታህ ነው..?

ተ/ማርያም፡- ለኔ ሁለቱም ትልቅ ድርሻ አላቸው በክለብም ቋሚ ያለመሆኔ የችሎታ ማነስ አይደለም በብሔራዊ ቡድንም ደግሞ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ጠቅሞኛል በዋሊያዎቹ ተሰላፊነቴ ያለኝ ሪከርድ ጥሩ የሚባልለት ነው ሁለቱም የየራሳቸው በጎ ጎን አላቸውና ተቀባይነቱ በሁለቱም ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በራስ መተማመኑ ከልክ ያለፈ ነው ለክለብም ሆነ ለሀገር ዋጋ ያስከፍላል የሚሉ አሉ… ትስማማለህ…?

ተ/ማርያም፡- በራስ መተማመን ለበረኛ ወሳኝ ነው ያን ባህሪዬን ደግሞ እወደዋለሁ በኛ ሀገር በረኞች ሜዳቸው ላይ ብቻ ቆመው እንዲመልሱ ብቻ ነው የሚጠብቅባቸው.. ነገር ግን ከተከላካይ ጀርባ የሚመጡ ኳሳችን ወጥቼ መመለሴ ቡድኖቹን ጠቅሟል፡፡ የኔ ቡድን ሲያጠቃና ተከለካይ ክፍሉ ወደ ተጋጣሚ ክልል ሲጠጋ ከተጋጣሚ የሚጣሉ አደገኛ ኳሶች በተከላካይና በበረኛ መሀል ባሉ ክፍተቶች ላይ እንዳይጠቀሙ ወጥቼ መጫወቴ ብዙ ነገሮችን አቅሏል ብዬ አስባለው፤ በራስ መተማመኔ ደግሞ እንድጠቅም አድርጎኛል ስህተቶችን አልፈራም ከስህተቶቼ ጥሩ ነገሮቼ ይበዛሉና ስህተቴ ላይ እየሰራሁ ጥሩ ነገሮቼን እጨምራለሁ ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- በሀገር ደረጃ ትልቁ ፈተና ኮቪድ 19 ነው ድሬደዋ ላይ ኢትዮጵያ ቡና እያደረገ ያለው መከላከል ምን ይመስላል?

ተ/ማርያም፡- ኮቪድ 19 በድሬዳዋ ትልቅ ፈተና ሆኗል በድሬደዋ አስቸጋሪ የሆነው ደግሞ ኮቪዱ ብቻ አይደለም ከሜዳ አንፃር የልምምድ ሜዳ የለም ማለት ይቀላል ያለው አፈር ሜዳ ነው አርቴፊሻል ሜዳ ቡና ላይ የሚለጠፈውን ነገር ነው በስርዓት ደረጃውን ያሟላ አርቴፊሻል የለም፡፡ በዚያ ላይ አፈር ሜዳ ላይ ከሊጉ ውጪ የሰፈር ቡድኖችም ሳይቀሩ ይጫወቱበታል ሜዳ ስንገባ ተከትሎን የሚገቡ አሉ…. አቧራው ላይ ያለው ምራቅ ሲተፋ ላቡ ሲጨመርበት ብዙ ችግር ይፈጥራል የኮቪድ 19 መስፋፋት አንዱ ምክንያት ይሄ ይመስለኛል… እንደ ክለብ ብዙም አልተጠቃንም ምክንያቱም መከላከሉ ላይ በደንብ እየሰራን ነው ከሆቴል አይወጣም ግዴታ ከወጣን ግን ማክስ ማድረግ የግድ ነው በአጠቃላይ ኮቪድን በመከላከል ደረጃ ጥሩ ስራ ሰርተናል ብዬ አስባለው….. እንደ ግልም እንደ ቡድንም ጥንቃቄያችን ጥሩ ነው እግዚብሔር ይመስገን፡፡

ሀትሪክ፡- በብሔራዊ ቡድን የሽልማቱ ነገር ቀዝቀዝ አለሳ…?

ተ/ማርያም፡- /ሳቅ በሳቅ/ ቀዝቅዟል ምን እንደታሰበ አላውቅም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሰጡን ሽልማት ብቻ ነው.. እርሱም ቢሆን እጃችን ገና አልገባም /ሳቅ/ ያው ፕሮሰስ ላይ ይመስለኛል የሀገራችን ሁኔታ ይመስለኛል ያቀዘቀዘው…..ፖለቲከኞቹ አመራሮች ቢዚ ሆነዋል ምርጫው ቀርቧል በስራ ላይ ተወጥረው ይሆናል እንጂ በርግጠኝነት ይሸልሙናል እኛ የሚጠበቅብንን ጨርሰናል የሚጠበቅባቸውን ይፈፅማሉ ብዬ አምናለሁ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ትዳር አባትነት እንዴት ይዞሃል…?

ተ/ማርያም፡- እግዚብሔር ይመስገን ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ፤ ባለቤቴ ኤደን አድማሱ ትባላለች. የመጀመሪያው ልጄ ናታኒየም ሁለተኛው አምነን ይባላሉ ብዙ ጊዜ አብሬያቸው አይደለሁም ዘንድሮ ሁለት ሶስቴ የተገናኘን ሁሉ አይመስለኝም የኳሱ ሁኔታ አራርቆናል ከቤተሰቦቼ ጋር ረጅሙን ጊዜ ያሳለፍኩበት በኮቪድ እገዳ ጊዜ ነው ስራ በመሆኑ አቻችዬው እየኖርኩ ነው ወደፊት ግን አዲስ አበባ የምቆይ ከሆነ ቤተሰቦቼን ለማምጣት አስባለሁ በዚሁ አጋጣሚ ውጤታማ ለመሆን የባለቤቴ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው እኔ በሌለሁበት ክፍተቴን ደፍና ቤቱን ያስተዳደረችው ባለቤቴ ኤደንን ማመስገን እፈልጋለሁ….በጣም እንደምወዳትና እንደማፈቅራት ልገልፅላት እፈልጋለሁ /ሳቅ/
ሀትሪክ፡- ከኳሱ ውጪ ዘና የምትለው በምንድነው…?
ተ/ማርያም፡- ከጓደኞቼ ጋር ሻይ ቡና ማለት ያዝናናኛል የማዘወትረውም ይህን ነው ከዚያ ውጪ መንፈሳዊ ቦታዎች መሄድ ያስደስተኛል ፊልምና ቲያትር ላይ ግን የለሁበትም፡፡

ሀትሪክ፡- ከውጪ ኳስ የማን አድናቂ ነህ…?

ተ/ማርያም፡- አርሰናልና ባርሴሎናንን በጣም እወዳለሁ የምደግፈውም እነርሱን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የአርሰናል በረኛ በርናንድ ሌኖን አቅም ገመገምክ… ?

ተ/ማርያም፡- /ሳቅ/ በርናንድ ሌኖማ ጥሩ በረኛ ነው… እያደነኩ ያደኩት ማኑኤል ኑኤርን ቢሆንም በኑኤር ውስጥ ሌኖን ታየዋለህ፡፡ አንዳንዴ ስታይ አርሰናሎች ሙሉ በሙሉ ባይተገብሩትም ሌኖ በአስቸጋሪ ሁኔታ ኳስ እየተቀበለ በእግሩ ፓስ ሲያደርግ ታየዋለህ ኳሱ በእግሩ ስር ስትገባ ያለውን መረጋጋት አደንቃለሁ ከኑኤር ቀጥሎ ያን አካሄድ ሌኖ እያመጣው ይመስላል፡፡

ሀትሪክ:- ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ያለህን ኮንትራት ዘንድሮ ትጨርሳለህና ቀጣዩ እቅድህ ምንድነው?

ተ/ማርያም:- እውነት ነው ኮንትራቴ ዘንድሮ ይጠናቀቃል….ኮንትራቴን ለማደስ በሁለታችንም በኩል ፍላጎቱ ስላለ ንግግር ተጀምሯል እኔም ኮንትራቴን ለማደስ ዝግጁ ነኝ እንደምንስማማም ተስፋ አደርጋለሁ

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ.. የመጨረሻ ቃል…?

ተ/ማርያም፡- ለኢትዮጵያ ቡና ያለኝን ክብር መግለፅ እፈልጋለሁ… ዘንድሮ እየተሻሻለ የመጣ ቡድን ይዘናል እስከመጨረሻው ድረስ ታግለን ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ጋር በዋንጫ ድል መጨፈር እንፈልጋለን ይሄ ህልማችን ነው ይሄ ባይሳካ ግን በቀጣዩ አመት በኮንፌዴሬሽን ካፕ የመሳተፍ እድል እናገኛለን ብዬ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ ለኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች የምለው ኢትዮዽያ ቡናን በአፍሪካ መድረክ ጠብቁ ነው….. እንደ ሀገር ያው ያለንበት ሁኔታ ቅር የሚያሰኝ ነው በዘር በጎጥ የተከፋፈልንበት መልሶ በሠላም መኖር የምንችልበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ እግዚአብሔር ለዚህም አምነዋለው ህዝቡ በብሔራዊ ቡድን ተቃቅፎ የሚጨፍርበት ስለ ኢትዮጵያ ብቻ የሚያወራበት ጊዜ እንዲመጣ እመኛለሁ፡፡ የሚሰማው ነገር ይዘገንናል እግዚአብሔር እንዲያፋቅረን እለምነዋለው ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፋችን አንድ ቀን በጋራ ጨፍረን ነው በነጋታው ወደ ሀዘን የገባነውና እግዚብሔር ይህን ችግር ከኢትዮጵያ እንደሚያርቅ ተስፋ አደርጋለሁ… በጎጥና በዘር የተከፋፈልነው ህዝብ ወደ ሠላምና አንደነት የሚመለስበት ዘመንን እናፈቃለሁ።

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport