“ተቀይሬ በገባሁባቸው ሁለት ጨዋታዎች ፋሲልን ጠቅሜያለሁ፤ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ደግሞ እስከ ኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክሩ ውስጥ የመግባት ራዕዩ አለኝ” ፍቃዱ ዓለሙ /ፋሲል ከነማ/

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ለሚመራው ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በአጥቂ ስፍራው ላይ የተጠባባቂ ስፍራ ተጨዋች ሆኖ ወደ ሜዳ ተቀይሮ በገባባቸው አንድአንድ ጨዋታዎች ላይ ክለቡን የውጤት ተጠቃሚ አድርጎታል። ይሄ ተጨዋች በተለይ ደግሞ ክለቡ ከቅ/ጊዮርጊስ አድርጎት በነበረው ጨዋታ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት በማስገኘትና ወላይታ ድቻን ባሸነፉበት ጨዋታ ደግሞ የድል ጎልን በማስቆጠር ጠቃሚ ተጨዋች መሆኑን እያስመሰከረም ይገኛል።

በመከላከያ እና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ክለብ ውስጥ ብዙዎች ሲጫወት የሚያውቁትን ፍቃዱ ዓለሙን ሀትሪክ ስፖርት በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ በጋዜጠኛዋ መሸሻ ወልዴ አማካኝነት አናግራው ምላሽን ሰጥቷታል፤ ቃለ-ምልልሱንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል

ሀትሪክ፦ የመጀመሪያ ጥያቄ ላድርግልህና ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ ዓለም በምን መልኩ በ መጣህ? የእናንተ ትውልድ አካባቢስ እነማንን ተጨዋቾች አፈራ?

ፍቃዱ፦ የእግር ኳስን ተጫውቼ የመጣሁበት መንገድ በተወለድኩበት የሞጆ አካባቢ ከህፃንነት እድሜዬ አንስቶ ለኳሱ ጥልቅ ፍቅር አድሮብኝ ነው። በኳስ እኔን እንድታወቅ ያደረገኝም የትምህርት ቤት ጨዋታም ነው። እዛ ጥሩ ስለተጫወትኩም ወደ ክለቦች ደረጃ ተሸጋግሬ ለአሁኑ እውቅናዬ በመብቃትም ላይ ነው የምገኘው። የእኛን የትውልድ አካባቢ አስመልክቶ በኳስ ሊፈሩ ከቻሉ ታዋቂ ተጨዋቾች መካከል እኔ የማውቀው ያሬድ ዝናቡንና ሀይሌን ነው። ሁለቱ የሚታወቁም ተጨዋቾች ናቸው።

ሀትሪክ፦ በቤተሰብህ ውስጥ ስንት ወንድምና እህት አለህ? ስፖርተኛስ አንተ ብቻ ነህ? አስተዳደግህስ በምን ደረጃ ላይ የሚገለፅ ነው አስቸጋሪ ነበርክ? ወይንስ በተቃራኒው….?
ፍቃዱ፦ እኛ ቤት ውስጥ ሁለት ወንድምና ሁለት እህቶች ናቸው ያሉኝ። ከእኔ ውጪ አንዱ ወንድሜም አባይ ዓለሙም ኳስን ይጫወት የነበረ ነው። በአስተዳደግ ደረጃም እኔ የመጣሁበት መንገድ በጣም ደስ የሚል ነው። የምወደው ኳስን እየተጫወትኩ በመምጣት ነው እዚህ ደረጃ ላይም የደረስኩት አስቸጋሪ ባህሪም አልነበረብኝም።

ሀትሪክ፦ የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር አርአያ ያደረግከው ተጨዋች ማንን ነበር?

ፍቃዱ፦ መጀመሪያ ወንድሜን ነበር፤ እሱ በክለብ ደረጃ ለሞጆ ከተማ ይጫወት ስለነበርም ነው በችሎታው ያደነቅኩት። ከዛ በኋላ ደግሞ ያሬድ ዝናቡ በእግር ኳሱ ትልቅ ስምና ዝና ስለነበረውና በልጅነቴ ሲጫወትም ስለተመለከትኩት እሱንም ነው አርአያዬ ላደርገው የቻልኩት።

ሀትሪክ፦ የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር የዛሬው ደረጃ ላይ እገኛለሁ ብለህ ጠብቀህ ነበር?
ፍቃዱ፦ እነ ያሬድ ዝናቡን ሲጫወቱ እንመለከት ስለነበር አዎን ጥሩ ደረጃ ላይ ስለመድረስ በጭላንጭል ደረጃ አስብ ነበር። በርትቼም እግር ኳሱ ላይ ሰራውኝም የምፈልገውን ምኞቴንም በማሳካት ላይ እገኛለሁ።

ሀትሪክ፦ በቤተሰብ ዘንድ ኳስ ከመጫወትህ ጋር በተያያዘ ጫና ነበረብህ?

ፍቃዱ፦ በፍፁም፤ እነሱ እንደውም ያበረታቱኝ ነበር።

ሀትሪክ፦ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ የመጀመሪያ ክለብህ ማን ነው? ከዛስ ለማን ለማን ቡድኖች ተጫወትክ ?

ፍቃዱ፦ የመጀመሪያ ክለቤ በተወለድኩበትና ባደግኩበት አካባቢ የሚገኘው የሞጆ ከተማ ክለብ ሲሆን እዛም ለአንድ ዓመት ያህል ነበር በአጥቂ ስፍራ ላይ ልጫወት የቻልኩት። በመቀጠል የተጫወትኩባቸው ሌሎች ቡድኖቾ ደግሞ በአሰልጣኝ አረጋዊ ይመራ ለነበረው ደብረማርቆስ ዩንቨርስቲ፣ ከዛም ለስድስት ወራት ለቆየሁበት ድሬዳዋ ከተማ፣ በመቀጠል ደግሞ ለአዲስ አበባ ከተማ እና ለመከላከያ ቡድኖች ነው ልጫወት የቻልኩት።

ሀትሪክ፦ በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ቆይታህ ምርጡን የጨዋታ ጊዜ የት አሳለፍክ?

ፍቃዱ፦ በመከላከያ እና በአዲስ አበባ ከተማ ክለቦች ውስጥ ነው ጥሩ የሚባል ጊዜን ያሳለፍኩት። የመከላከያ ቆይታዬ ላይ በተለይ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ እያለም ሆነ እሱ ከሀላፊነቱ ከተነሳ በኋላ ለቡድኑ 9 የሚደርሱ ጎሎችን ከማስቆጠር ጀምሮ የተሻለ የሚባል ግልጋሎትንም ስለሰጠሁትና በአዲስ አበባ ከተማ ክለብ ቆይታዬም አሁንም ስዩም እያለ ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲሸጋገር ካደረጉት ተጨዋቾች መካከል አንዱም ነበርኩኝና ይሄም ጭምር ፈፅሞ አይረሳኝም።

ሀትሪክ፦ በመከላከያ ቆይታህ ቡድናችሁ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ወርዶ ነበር፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ዳግም የፕሪምየር ሊጉን ተቀላቀለ፤ አሁን የእዚሁ ቡድን አባል ባትሆንም ስለ ቡድኑ ያለህን ስሜት ግለፀው?

ፍቃዱ፦ መከላከያ የምወደው ክለቤ ነበር። ከሊጉ ሲወርድም በጣም ነበር ያዘንኩት። እንደዛም ሆኖ ግን ይህን ቡድን እታችኛው ሊግ የማይመጥነው ስለነበር ሊጉን ተመልሶ እንደሚቀላቀል እናውቅ ነበርና ያን ተግባራዊ ለማድረግ ዓምና ቡድኑን ወደ ነበረበት ሊግ ለመመለስም ቃል ገብተንም ነበርና ኮቪድ ሊጉን አቋረጠው እንጂ ያን እልማችንን ለማሳካት እየጣርን ነበር። ዘንድሮ ደግሞ እኔ በቡድኑ ውስጥ ባልኖርም ክለቡ ጠንካራ ቡድንን በመፍጠር የነበረበትን ሊጉን ዳግም ሊቀላቀል ችሏልና በዚህ አጋጣሚ ለመላው የክለቡ አመራሮች እና አባላቶች እንደዚሁም ደግሞ አብሬያቸው ለተጫወትኳቸው ጓደኞቼ እንኳን ደስ አላችሁ ልላቸው እወዳለሁ።

ሀትሪክ፦ በመከላከያ ቆይታህ ለብሄራዊ ቡድንም ለተተኪ ቡድኑም የመመረጥ እድሉን አግኝተህ ነበር፤ ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ አልናፈቀህም?

ፍቃዱ፦ ይናፍቃል እንጂ! ምክንያቱም ሀገርን ወክሎ መጫወት የማይፈልግ ተጨዋች ማንም የለምና። እንዳልከው በመከላከያ ቡድን ቆይታዬ ከዚህ ቀደም ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆነው ብሄራዊ ቡድን መመረጤ ይታወሳል። በእዛው ዓመት ውስጥ ለዋናው ቡድንም ተመርጨ ነበርና በፋሲል ከነማ ክለብ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬም በቀጣይነት በማገኛቸው የመሰለፍ ዕድሎቾ ከእኔ የሚጠበቀውን ብቃት በማሳየት ዳግም ለመመረጥ እና ለሀገሬም ከተመረጥኩ በኋላም በርካታ ጎሎችን ለማስቆጠርም ጥረትን አደርጋለሁ።

ሀትሪክ፦ በፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ ያለህ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ቆይታህ በበርካታ ግጥሚያዎች ላይ በቋሚነት በመሰለፍ የታጀበ አይደለም? በተወሰኑ ግጥሚያዎች ላይ ግን ተቀይረህ በመግባት ነው የምትጫወተው፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ?

ፍቃዱ፦ ፋሲል ከነማን በተቀላቀልኩበት የዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ ለቡድኑ በቋሚ ተሰላፊነት ወደ ሜዳ በመግባት አለመጫወቴ በቡድኑ ውስጥ ካለው ሲኒየር እና በችሎታውም ከማደንቀው እና ጎል በማስቆጠሩም ላይ ክብር ለምሰጠው እንደዚሁም ደግሞ በአጥቂው ስፍራም ላይ እያስገረመኝ ካለው ሙጂብ ቃሲም ብቃት አኳያ ከፍተኛ ልምድን እንድቀምስ የሚያደርገኝ በመሆኑም በመቀመጤ ፈፅሞ አይከፋኝም። በዚህ ቡድን ቆይታዬ ሌላው በቋሚ ተሰላፊነት የማልጫወተውም ብቃቱ ሳይኖረኝ ቀርቶ ሳይሆን ቡድኑ ከያዘው የአጨዋወት ታክቲክ አኳያም በአንድ አጥቂ የሚጫወትበትን እንቅስቃሴን በመከተሉም ነው። ያም ሆኖ ግን ለክለቡ ገብቼ በተጫወትኩበት ጨዋታ ላይ ለውጤት የበቃንበትን ጎል ከማስቆጠር ባሻገር በ3 ደቂቃ ውስጥም ተቀይሬ ገብቼ የፍፁም ቅጣት ምትን በቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታችን ላይ ምክንያትም የሆንኩባቸው አጋጣሚዎችም ስላሉ ነገም ለእዚህ ቡድን በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፌ ክለቤን የምጠቅምባቸውም አጋጣሚዎች ስለሚኖሩም በእስካሁኑ የቡድኑ ቆይታዬ ደስተኛ ነኝ።

ሀትሪክ፦ ሲዳማ ቡናን ባሸነፋችሁበት ጨዋታ በመጨረሻው ደቂቃ የድል ጎልን አስቆጥረሃል፤ ስሜቱን እንዴት አገኘኸው?

ፍቃዱ፦ ይሄ ጎል ለቡድናችን ወሳኝ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሆነ ነበርና ልክ ጎሉን እንዳስቆጠርኩ በጣም ነበር የተደሰትኩት። ጎሏ ከእኔ ውጪም መላው ፋሲላዊያንንም በደስታ እንዲቦርቁም ያደረግኩበት አጋጣሚና ወደ ሻምፒዮናነቱም ለመቃረብ እድላችንን ይበልጥ ያሰፋንበት ስለሆነም ቀኑ የሚገርምና አስደሳችም ነው የሆነልኝ።

ሀትሪክ፦ ከባህርማዶ ክለቦች የማን ደጋፊ ነህ የምታደንቀውስ ተጨዋች?

ፍቃዱ፦ የማደንቀው ተጨዋች ዋይኒ ሩኒን ነው። የምደግፈው ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድን።

ሀትሪክ፦ በመጨረሻ….?

ፍቃዱ፦ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ወደፊት በርካታ ግቦችን አስቆጥሬ የምጫወትለትን ቡድን ለውጤት እንደማበቃው አምናለሁ፤ በኮከብ ግብ አግቢዎች ፉክክሩ ውስጥ መግባትንም አልማለውና ለዛ ያድርሰንም እላለሁ። በተረፈ በኳሱ ዛሬ ላይ ለመጣሁበት መንገድ ቤተሰቦቼን ማመስገን እፈልጋለው። ከእነሱ ውጪም አሰልጣኝ አረጋዊ ደብረብርሃን ዩንቨርስቲ ቡድን ውስጥ በምጫወትበት ሰዓት እኔ ላይ እንደ ቡድንና ልምምድን ከጨረስን በኋላም በግል ያሰራኝ ስለነበር እሱ ለፕሪምየር ሊግ ተጨዋችነት ቀርፆኝ ለዚህ ስላበቃኝና ሌላው ደግሞ የቀድሞ አሰልጣኜም እሸቱ ከስር አውጥቶኝ ለዚህ ስላበቃኝ ላመሰግናቸው እወዳለሁኝ።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website