ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአራቱም ኮከቦቻቸው ላይ የጨከኑ ይመስላል…

በዮሴፍ ከፈለኝ

ርግጠኛ የሆነ መረጃ እንደያዙ በድፍረት ይናገራሉ…. በተለይ አስቻለሁ ታመነ፣ ሙሉዓለም መስፍን /ዴኮ/እና ጋዲሳ መብራቴ ላይ ቅሬታቸው ጨምሯል…”ከምንችለው በላይ መክረናል ታግሰናል በውሳኔያችን ፈጽሞ አንጸጸትም የሚሉት ለዚህ ነው…ሶስቱም ላይ በጅማ፣ በባህር ዳርና በድሬዳዋ የማያወላዳ ማስረጃ የቪዲዮ ሳይቀር ይዘናል ከዚህ በኋላ ከክለቡ በላይ ማንም ሊሆን አይችልም”ሲሉም እንደውም ውሳኔያቸው መዘግየቱን ይናገራሉ።

“ክለቡ የሚገባቸውን ሳይሆን ከሚገባው በላይ የሆነ ድጋፍ አድርጓል አንገታቸውን ቀና አድርገው የቅዱስ ጊዮርጊስ መሆን ምን አይነት ክብር እንዳለው አሳይተናቸዋል እነሱ ግን ይህን ታሪካዊ እድል መጠቀም አልቻሉም” የሚሉት አመራሮቹ “ጌታነህም ቢሆን እንደ አምበል መሪነቱን አልተጠቀመበትም ተጨዋቾቹን ተቆጣጥሮ በየክፍላቸው መሆናቸውን አረጋግጦ መተኛት ሲኖርበት እሱም እንደነሱ ከተፈቀደለት ሰአት በላይ አምሽቶ መግባቱ አስቆጥቶናል እንደ አምበል ቡድኑን አልመራም ቁጭ ብለን የግድ እንነጋገራለን” በማለትም አምበሉ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

“ቡድናችንን ሀትሪክ ሰርቶ ውጤታማ የሚያደርግ ተጨዋች እንጂ በዲሲፕሊን ግድፈት ሀትሪክ ለሚሰሩ ተጨዋቾች ቦታ የለውም” የሚሉት አመራሮቹ ጥሩ ክፍያ እየከፈልን በስራቸው ታማኝ ሆነው ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው መኖር ሲገባቸው ለቡድናቸውና ለሚንከባከባቸው ክለብና ደጋፊ ውጤት መታገል ሲኖርባቸው በዚህ መሰል ተግባር መገኘታቸው የማያዳግም ርምጃ እንዲወስዱ እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል።

ተጨዋቾቹ ከጅማ አባጅፋር ጋር ከተደረገው ጨዋታ በኋላ ባመጡት ውጤትና በተጫወቱት ከአቅም በታች በሆነ ጨዋታ መጸጸትና ማዘን ሲገባቸው ሁሉንም ርግፍ አድርገው ትተው ወደ መዝናናቱ መሄዳቸው ታውቋል። አራቱም ተጨዋቾች ጠዋት ለቁርስ ሲሄዱ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መወሰኑን ተነግሯቸው በአውሮፕላን ከቡድኑ ተለይተው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጉ ታውቋል።

ክለቡም ከጨዋታውና ከተመዘገበው ውጤት ባለፈ በአሁኑ ሰአት ያለው የኮቪድ 19 ስርጭት ከፍተኛ መሆኑ እየታወቀ ምሽት ላይ ወጥተው እንደፈለጉ መሆንና መመለስ ከሞራልና ከቫይረሱ ስጋት አንጻር ለሌሎች የቡድኑ ተጨዋቾች ትልቅ አደጋ መሆኑን ቦርዱ በማመኑ አራቱም ተጨዋቾች ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጉ ታውቋል።
የክለቡ ቦርድ ከክለቡ ቡድን መሪ የሚቀርብለትን ሪፖርት በመገምገም አጠቃላይ ውሳኔውን ያሳውቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃም በድሬዳዋ ከሚካሄደው ቀሪ አንድ ጨዋታ ጀምሮ በተጨዋቾቹ ላለመጠቀም መወሰናቸው ታውቋል።

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *