“ቅ/ጊዮርጊስን የሚመጥን ውጤት እያስመዘገብን አይደለንም፤ ይሄን ደጋፊ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለን ልንክሰው ይገባል” ባህሩ ነጋሽ /ቅ/ጊዮርጊስ/

ለቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ በግብ ጠባቂነት እየተጫወተ የሚገኘው ባህሩ ነጋሽ ቡድኑ ዘንድሮ እያስመዘገበ የሚገኘው ውጤት ድል የለመደውን ደጋፊ የማይመጥነውና ይህንን ደጋፊና ክለቡንሞ በቀጣዩ ጊዜ የውድድር ተሳትፎም በፍጥነት በውጤት ሊክሱት እንደሚገባም አስተያየቱን ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታው የመሰለፍ ዕድልን እያገኘባቸው ባሉት ጨዋታዎች ጥሩ ብቃቱን እያሳየ ያለው ባህሩ ከሀትሪክ ጋር ያደረገው አጠቃላይ ቆይታም የሚከተለውን ይመስላል።

የቅ/ጊዮርጊስ ቆይታውን አስመልክቶ

“ከታዳጊው /u-17/ አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በክለቡ ውስጥ ስቆይ አሁን ላይ ስምንተኛ ዓመቴን ይዣለሁ። በዚህ ጊዜ ውስጥም ለታዳጊው ቡድን ለሶስት ዓመት፣ ለወጣት ቡድኑ /u-20/ ለሁለት ዓመት እንደዚሁም ደግሞ ለዋናው ቡድን የዘንድሮውን ጨምሮ ተቀይሬ በመግባትና አንድአንዴም በቋሚ ተሰላፊነት በመጫወትም ሶስተኛ ዓመቴንም እያስቆጠርኩ ነውና የዚህ ቡድን ቆይታዬን የምመለከተው ጣፋጭ በሆነ መልኩ ልክ እንደ ትምህርት ቤት ነው። ቅ/ጊዮርጊስ ውስጥ በመቆየቴ ብዙ የተማርኳቸው ነገሮች አሉ፤ እነዛም እኔን በጣም ጠቅመውኛል። በተለይ ደግሞ በዚህ ቡድን ባለኝ ቆይታ ትላልቅ የሆኑ የውጪ ሀገርና የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ነበሩና ከእነሱ ያገኘሁት የጨዋታ ልምድ ቀላል የሚባል አይደለም። ገና ከስር አድጌ በመጣሁበት ወቅት ኡጋንዳዊው የቡድናችን ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ይገኝም ነበርና ከእስ ስር ሆኜ መስራቴ ለችሎታዬ መሻሻል በጣም ሊጠቅመኝ ችሏል። ይሄኔ በዚህ ቡድን ቆይታዬ ለምን አልሰለፍም በሚልና ትዕግስትም በማጣት ክለቡን በመልቀቅ ወደ ሌላ ቡድን አምርቼ ቢሆን ኖሮም በዚህ ብቃት ደረጃ እገኛለሁ ብዬም አላስብምና አሁን የመጫወት እድሉን ከማግኘቴ ጋር ራሴን ስመለከተው የቅ/ጊዮርጊስ ቆይታዬን በጣም ነው የወደድኩት”።

በቅ/ጊዮርጊስ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው በአብዛኛው ግጥሚያዎቹ ተጠባባቂ እንደነበረና አሁን ላይ በቋሚ ተሰላፊነት መጫወቱ

“እውነት ነው ቀደም ባለው ጊዜ ለእዚህ አሳዳጊዬ ቡድን በቋሚ ተሰላፊነት ልጫወትለት ያልቻልኩት ትላልቅ ስም ያላቸውና ጠንካራ የሚባሉ ግብ ጠባቂዎች ስለነበሩ ነው። ቅ/ጊዮርጊስ ውስጥ ሳለህም ከክለቡ ትልቅነት እና በስኳዱም ከሚይዛቸው ተጨዋቾች አንፃር በረኛም ሆንክ ተጨዋች ዝም ብለህ የመሰለፍ እድልን በቀላሉ አታገኝም። ያን እድል ለማግኘት በጣም መስራትና መልፋትም አለብህና እኔ አሁን ለቡድኑ እየተጫወትኩ ያለሁት በዛ ውስጥ ስላለፍኩና ባገኘዋቸው የመሰለፍ እድሎችም ውስጥ ችሎታዬን በሜዳ ላይ በማሳየት ስለተጠቀምኩበትም ነው”።

እንደ ግብ ጠባቂነትህ ለአንተ አርአያ ተጨዋችህ ማን ነው?

“ሮበርት ኦዶንካራ ነዋ! እሱ እኛ ቡድን ውስጥ በነበረ ጊዜ እኔ የታዳጊ ቡድኑ ውስጥ በረኛ ነበርኩኝ። ሲጫወት ስመለከተው በጣም ወደድኩት። ከዛም በቢጫ ትሴራ ወደ ዋናው ቡድን በመምጣት ልምምድ ስሰራም እሱን አግኝቼው ከልምዱ የቀሰምኳቸው እና የተማርኳቸው ብዙ ነገሮች ስለነበሩም ሮበርት ለእኔ ተምሳሌቴ ነው፤ በጣምም ነው የማደንቀው”።
አሁን ላይ ራሱን ምርጥ ግብ ጠባቂ አድርጎ ያስብ እንደሆነ
“እኔ ራሴን በዛ ደረጃ የምገልፅ ተጨዋች አይደለሁም፤ በቅ/ጊዮርጊስ ቆይታዬ አሁን ላይ የመሰለፍ እድሉን እያገኘሁኝ ነው። ይህን እድል ስታገኝ ደግሞ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። ተሰልፎ መጫወቱም ያለብህን እና የሚቀርህን ክፍተት ጎኖችም እንድትሞላበትም ያደርግሃል እና ምርጥ ግብ ጠባቂ ለመባል ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብኝም ነው ለመረዳት የቻልኩት”።

ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር እልሙ

“ከእዚህ አሳዳጊ ቡድኔ ጋር ብዙ መጓዝ እፈልጋለሁ፤ በአፍሪካ ክለቦች የኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ ጨዋታ ላይም በመሳተፍና ጥሩ ውጤት በማምጣት የክለቤንና የራሴን ስም በወርቅ ቀለም በማስፃፍም ማስጠራት እፈልጋለሁ። ከዛ ውጪም የዚህ ቡድን ተጨዋች ሆኜም ችሎታዬን ከፍ በማድረግም ለሀገሬ ብሄራዊ ቡድን በመመረጥ ስኬታማ ውጤትን ማስመዝገብም ዋንኛ ዓላማዬ ነውና በዛ ደረጃ ላይ ነው እየሰራው ያለሁት”።

ቅ/ጊዮርጊስና ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው

“ቡድኑ ካለው ስምና ዝና አንፃር እንደዚሁም የበርካታ ዋንጫዎች ባለቤት ከመሆኑና ከትልቅ ቡድንነቱ አኳያ አሁን እያስመዘገበው ያለው ውጤት የሚመጥነው አይደለም፤ ያ ስለሆነም ዘንድሮ ቢያንስ 2ኛ ሆኖ መፈፀም ወደ አፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ካፕ ያሳልፋልና ለደጋፊው ስንል መስዋዕትነትን ልንከፍል ይገባል”።

የቅ/ጊዮርጊስ የውጤት ማጣት ችግር

“በእግር ኳስ እንዲህ ያሉ ነገሮች የሚያጋጥሙ ቢሆንም ምክንያቶቹን ግን ማወቅ አልቻልንም፤ ቅ/ጊዮርጊስ ውጤት እያጣ ያለው ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብን ይዞ ነው ይሄን ችግር አውቀን የክለቡን የቀድሞ ስምና ዝናውን ልንመልስለት ይገባል”።

በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፈው ከቀናቶች በኋላ በወራጅ ቀጠና ላይ ከሚገኘው ጅማ አባጅፋር ጋር አቻ ስለመለያየታቸው

“ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፍንበት የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ በቡድናችን ውስጥ ይታይ የነበረው ቁርጠኝነት በጣም ይገርም ስለነበር በጨዋታው ድሉ ቀንቶን ነበር። ቡናን ያን ዕለት ስናሸንፍ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ ጥለን በመምጣት ነበር። ይሄን ጨዋታ ከደርቢ ግጥሚያ አንፃር ማሸነፋችን መልካም ቢሆንም ቡድናችን ሌሎችንም ግጥሚያዎች እያሸነፈ በመጓዝ ነጥቡን ወደላይ ከፍ አድርጎ መጓዝ ይጠበቅበትም ነበርና ከጅማ አባጅፋር ጋር ባደረግነው ጨዋታ ክለባችን እንደ ቡድን ጥሩ ስላልነበር አቻ ተለያይተናል። ይሄን ጨዋታ አለማሸነፍ መቻላችንም በነጥብ ልዩነቱ ከእኛ ክለብ በትንሹ ከፍ ካለው የቡና ቡድን ጋር እንዳንስተካከልና በሰፊ ነጥብ ከሚበልጠን ፋሲል ከነማ ጋር ደግሞ ያለንን ርቀትም ይበልጥ እንዲሰፋም በር እየከፈትን ነውና ያ ደግሞ ዋጋ እንድንከፍልም እያደረገን ይገኛል”።

በሸገር ደርቢው ላይ መጫወትህ መቻልህ

“ያ ግጥሚያ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለእኔ የመጀመሪያዬ ነበር። ከዚህ ቀደም በሲቲ ካፕ ላይ ነበር የተጫወትኩትና የመሰለፍ ዕድሉን በማግኘቴ በጣም ነበር ደስ ያለኝ። ሸገር ደርቢ ላይ መጫወት መቻል መታደል ነው ያለውን ስሜትም በቢ ቡድን ደረጃ ጀምሮ ከእነሱ ጋር ስንጫወት አውቀዋለውና አንዱ በአንዱ መሸነፍን ፈፅሞ ስለማይፈልግም ይህን ጨዋታ በድል ስለተወጣነው ያን ዕለት ልደሰት ችያለሁ”።

ቅ/ጊዮርጊስ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በምን ውጤት ሊያጠናቅቅ ይችላል

“አሁን ከዋንጫው ፉክክር ወጥተናል ማለት ይቻላል። ሁለተኛነት ለአፍሪካ ክለቦች የኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ስለሚያሳልፍ ያን እድል ለማሳካት እስከመጨረሻው ጨዋታ ድረስ እንፋለማለን”።

በመጨረሻ

“በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ዘመን ቆይታዬ ለቡድኔ ተሰልፎ የመጫወት እድልን በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል። ይሄን የመሰለፍ እድልንም አጠናክሬ በማስጓዝ ቡድኔንም ለመጥቀም በሚገባ ተዘጋጅቻለው። ቀጣዮ እልሜም ለብሄራዊ ቡድን ተሰልፌም መጫወት ነው። ይህን ካልኩ በእግር ኳስ ህይወቴ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ የረዱኝን ሙሉ ቤተሰቦቼን በአስኮ ፕሮጀክት ያሰለጠነኝን አብይን የግብ ጠባቂያችን አሰልጣኝ የነበረውን ኤሚ ዳንዳን እንደዚሁም ደግሞ ሁሌም ከእኔ ጎን ባለመጥፋትና በመምከር በአህምሮም ሆነ በሁሉም ነገሮች እንድዘጋጅ የሚያደርገኝን የቡድናችንን ተጨዋቾ ምንተስኖት አዳነን እና የአሁኑን የቅ/ጊዮርጊስ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ውብሸት ደሳለኝን የውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ለክለቡ ተሰልፌ መጫወት በምችልበት ሰዓት በእጄ ላይ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞኝ ከጨዋታ ለጥቂት ጊዜ ከሜዳ ከራቅኩበት ሰዓት ጀምሮ ወደ ሜዳ እስክመለስና ለቡድኑም ጥሩ ግልጋሎትን እንድሰጥ በእኔ ላይ የሰራው ስራ አለና ለእሱና ለቡድኔ ተጨዋቾች እንደዚሁም ለደጋፊዎቻችን ከፍተኛ ምስጋናን ነው የማቀርብላቸው”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website