ሶዶ ላይ በ12ኛው ሳምንት መርሀ ግብር ወላይታ ድቻ ድሬዳዋን ካሸነፈ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
ከመጀመሪያው ሰከንድ ጀምረን ለማጥቃት ተጫውተን አሸንፈን ወጥተናል (ደለለኝ ደቻሳ የወላይታ ድቻ ጊዚያዊ አሰልጣኝ)
ስለጨዋታው
- ማሰታውቂያ -
ጨዋታው እንዳያችሁት ነው። በታሪክ ደግሞ ድሬዳዋን ስናሸንፍ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው። ባለፈው ሳምንት እራሳችን በሰራነው ስህተት ነው ነጥብ አጥተን የተመለስነው። ቢሆንም ስህተቶቹን ለቅመን በመስራት በደጋፊያችን ፊት ጥሩ ውጤት ይዘን ለመውጣት ነው የገባነው። እንዳያቹህ ከመጀመሪያው ሰከንድ ጀምረን ለማጥቃት ተጫውተን አሸንፈን ወጥተናል።
በሁለተኛው አጋማሽ መቀዛቀዛቹ ውጤት አስጠብቆ ከመውጣት ጋር ሊያያዝ ይችላል ?
አዎ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደተመለከታችሁት ሶስት ግቦችን አግብተናል። ሁለተኛው አጋማሽ ግን ጥንቃቄ መሰረት አድርገን ነው የገባነው። ግባችንን ዘግተን ማጥቃት ባለብን ስአት እያጠቃን ነበር። ይህም ደግሞ ተሳክቶልናል።
በ45 ደቂቃ ነው ተሸንፌ የወጣሁት ስምዖን አባይ (ድሬዳዋ ከተማ)
ስለጨዋታው
እንግዲህ እግር ኳስ ይህ ነው። በ45 ደቂቃ ነው ተሸንፌ የወጣሁት። ያማለት ደግሞ በመጀመሪያው ግማሽ የኛ ቡድን ፈፅሞ ዝግጁ አልነበረም። ከወገብ በታች እና መከላከሉ የተበታተነ ብሎም ያልተቀናጀ ነበር። እነሱም ይህን ተጠቅመው ሶስት ግቦችን በተከታታይ ሊያስቆጥሩብን ችለዋል። በመጀመሪያው ግማሽ ከነበራቸው እንቅስቃሴ ሶስት ግቦች ማስቆጠራቸው ሚያንስ ነው። በመጀመሪው ግማሽ ብልጫ ተወስዶብኝ መሸነፍ ችያለው። ተጫዋቾቼም ላይ ድካም ይታያል እንደምክንያት ባይቆጠርም።