በሀያ አምስተኛዉ ሳምንት የመጨረሻ ዕለት ቀዳሚ ጨዋታ አዳማ ከተማ ሲዳማ ቡናን 2ለ1 ማሸነፍ ችሏል።
በከፍተኛ ዝናብ ታጅቦ ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ ገና በመባቻዉ በ2ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሯል። በዚህም ጀሚል ያዕቆብ ያቀበለዉን ኳስ አማካዩ መስዑድ መሐመድ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ገና በጊዜ ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች አደጋ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረዉ በተቃራኒው በ20ኛዉ ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል።
በዚህም ፍቅሩ አለማየሁ ከግራ መስመር በኩል ወደ ውስጥ ያሻማዉን ኳስ ግብ ጠባቂዉ መክበብ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ ቢኒያም አይተን ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታዉ ለመመለስ ጥረት ማድረግ የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች ምንም እንኳን ጥሩ ቢጫወቱም ነገር ግን በሙከራ ረገድ ተዳክመዉ ታይተዋል።
- ማሰታውቂያ -
አጋማሹ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረዉ ግን ሲዳማ ቡናዎች ጥረታቸዉ ፍሬ አፍርቶ ወደ ጨዋታዉ የመለሳቸዉን ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም በ44ተኛዉ ደቂቃ ላይ በሳጥኑ ጠርዝ አቡበከር ሻሚል ይገዙ ቦጋለ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠዉን የቅጣት ምት ኳስ ደስታ ዮሐንስ ወደ ግብነት ቀይሮ አጋማሹ ሁለት ለአንድ ተገባዷል።
ከዕረፍት መልስ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቀይረዉ ወደ ሜዳ ያስገቡት ሲዳማ ቡናዎች ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸውን ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረት ማድረግ የቀጠሉ ሲሆን ነገር ግን አደጋ ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በጨዋታው መሐልም 73ተኛዉ ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማዉ ግብ ጠባቂ ከሳጥን ውጭ ኳስ በዕጅ መንኳቱን ተከትሎ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
የአዳማ ከተማዉ ግብ ጠባቂዉ ሰይድ ሀብታሙ ከሜዳ ከወጣ በኋላ ከፍ ባለ ጥረት የማጥቃት ሀይላቸዉን የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች ዉጥናቸዉ ሰምሮ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ 2ለ1 በሆነ ዉጤት ተሸንፈዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ሻሸመኔ ከተማን 2ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል !!
ምሽት 12:00 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ፊሽካ በጀመረዉ ጨዋታ አጀማመሩ ላይ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክር እየተደረገበት የጀመረ ሲሆን ገና በ18ተኛዉ ደቂቃ ላይ ቡናማዎቹ ሙከራ ማድረግ ችሏል። በዚህም ብሩክ በየነ ከአብዱልከሪም ወርቁ የተቀበለዉን ኳስ ከሳጥን ውጭ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ግብ ጠባቂዉ ኬን ሰይዲ መልሶበታል።
ከተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በዘለለ ይህ ነዉ የሚባል ተጠቃሽ ሙከራ እምብዛም ባልተመለከትንበት አጋማሹ በ25ተኛዉ ደቂቃ ላይ የሻሸመኔ ከተማዉ የቀኝ መስመር ተመላላሽ ማይክል ኔልሰን ለማሻማት በሚል በቀጥታ ወደ ግብ የላከዉ ኳስን ግብ ጠባቂዉ በረከት አማረ እንደምንም አውጥቶታል።
በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ሙከራ ሳንመለከትበት አጋማሹ የተገባደደ ሲሆን ከዕረፍት መልስ በ52ተኛዉ ደቂቃ ላይ አማካዩ አማኑኤል ዮሐንስ ከሳጥን ዉጭ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሱ በግቡ አናት ላይ ወደ ዉጭ ወጥቷል። በ55ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ኢዮብ ገ/ማርያም ከግራ መሰመር በኩል ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ ሁዛፍ አሊ ከበረኛ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ በ72ተኛዉ ደቂቃ ላይ በፍቃዱ አለማዩ ከመስፍን ታፈሰ ጋር ተቀባብሎ ያገኘዉን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር ከሁለት ደቂቃ በኋላ ግን የሻሸመኔ ከተማዉ ሁዛፍ አሊ ከተከላካዩ ራምኬል ጀምስ ታግሎ ያገኘዉን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አቻ አድርጓል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ መደበኛዉ ዘጠና ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመረ ደቂቃ በ90+1 ቡናማዎቹ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም አብዱልከሪም ያሻገረዉን የቅጣት ምት ኳስ ተከላካዩ ራምኬል ጀምስ በግንባሩ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አሸናፊ ማድረግ ችሏል።