የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ግንቦት 12 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሳምንቱ መርሃ ግብር በተደረጉ ጨዋታዎች ሰባት በመሸናነፍ ቀሪ አንዱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ 26 ጎሎች በ21 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። 35 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ ሁለት ቀይ ካርድ ተመዝግቧል።
በሳምንቱ በአምስት ተጫዋቾች እና አንድ ክለብ ላይ የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ተላልፈዋል። ሽመክት ጉግሳ(ፋሲል ከነማ)፣ እንየው ካሳሁን(ሃዋሳ ከተማ) እና ግሩም ሃጎስ(መቻል) በሳምንቱ ጨዋታ አምስተኛ የጨዋታ ቢጫ ካርድ በመመልከታቸው ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ እንዲሁም መስፍን ታፈሰ(ኢትዮጵያ ቡና) እና ሰይድ ሃብታሙ(አዳማ ከተማ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀማቸው በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱ ተወስኗል።
በሳምንቱ የአዳማ ከተማ ክለብ ተጫዋቾች የሆኑት አቡበከር ሻሚል፣ ሰይድ ሃብታሙ ፣ ታዬ ጋሻው እና ቦና አሊ በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡