የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢኮስኮን ተረከበ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን /ኢኮስኮ/ የወንዶች እግርኳስ ቡድን የርክክብ ስነስርዓት ተካሄደ።

ዛሬ ምሽት በረመዳን ሆቴል በተካሄደ የፊርማ ስነስርዓት ላይ እንደተገለጸው በከፍተኛ ሊግ ይወዳደር የነበረውን የኢኮስኮን የወንዶች ቡድንን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረከቡ ታውቋል።

በዚህ ስነስርዓት ላይ የንግድ ባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ እንደተናገሩት “ንግድ ባንክ ከስፖርት ጋር ከፍተኛ ትስስር ያለውና የተሻለ የስፖርት ማዘውተሪያ ካላቸው ክለቦች መሃል አንዱ ነው በተለይ በአትሌቲክስ ዘርፍ ቀዳሚ ታሪክ እንዳለን ይታወቃል ይህ ውጤታማነት ቀጣይነት እንዳለው አይጠራጠርም ” ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ ኤፍሬም ጨምረውም “በ2009 የወንዶች ቡድን በመፍረሱ በርካታ አካላት ተቆርቁረው ለምን ይፈርሳል በሚል ብዙ ጥያቄ ማቅረባቸው ቆም ብሎ ለማሰብ አስገድዶናል በወቅቱ ቡድኑ ሲፈርስ የቻለው አስገዳጅ ሁኔታ በመከሰቱ ነው ነገር ግን ጊዜው ፈቀደና ቡድኑ እንዲመለስ በመደረጉ ደስተኞች ነን ይህም የባንኩ ጠቃሚነትና ድርሻው ቀጣይነቱ አያጠያይቅም በዚህ አጋጣሚ ቡድኑ እንዲመለስ ለጎተጎታችሁን ወገኖች ምስጋና አቀርባለሁ ዳግም እንዲመለስ ወሳኙን ሚና ለተወጡት አመራሮችም ምስጋናዬ ይድረሳቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የዋና ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ሀላፊና የስፖርት ማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አመንቲ ዳዲ በበኩላቸው ” ሶስት ትላልቅ ተቋማትን ይዘንጨከተደራጀን አምስት አመት ሞልቶናል ተቋማችን 50 ቢሊየን ዋጋ ያላቸውን 60 ፕሮጀክቶችን የሚመራ ተቋም እንደመሆኑና ለእግርኳሱ የሚፈለገውን አመራርነት ለመስጠት አለመቻላችን ርግጥ ነው ነገር ግን ቡድኑ እንዳይበተን በማድረጋችንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች ቡድናችንን በመረከቡ ተደስተናል።

ክለባችንን ስናስረክብ አዝነናል ነገር ግን በንግድ ባንክ አመራር ሰጪነት ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንደሚያልፍ ተስፋ አደርጋለሁ ጥሩ እጅ ላይ መወሰደቁም ይሰማናል” በማለት ተናግረዋል። ሁለቱን ወገኖች በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት የአቶ አመንቲ ዳዲና የንግድ ባንክ ስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አሊ አህመድ ናቸው።

የእለቱ የክብር እንግዳ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ “በዚህ ሰአት ንግግር ባላደርግ እመርጣለሁ ሁለቱም ተቋማት ቡድን ቢኖራቸው ደስ ይለኝ ነበር በሁለት ልጆቼ መሃል ሆኜ እንደ መናገር ነው የሚሰማኝ ኢኮስኮን ንግድ ባንክ በመረከቡ ጮቤ አልረግጥም በደንባችን አንቀጽ 18 ላይ ባለው ሂደት ኢኮስኮን ከመበተን ሜዳ ላይ ከመጣል እንዲህ ርከከብ በመካሄዱ ግን ደስተኛ ነኝ ንግድ ባንክም ፈርሰው እንደቀሩት ሌሎች ክለቦች ፈርሶም ባለመቅረቱ ተደስቻለሁ መልካም እጅ ላይ እንደወደቀና እንደሚያድግ ልጅ ርክክቡ ደስ ብሎኛል

በዚህ አጋጣሚ ደመወዝ የመክፈል ችግር ውስጥ ያሉ ክለቦች በበዙበት እግርኳሳችን የዚህ አይነት ችግር የሌለበት ንግድ ባንክ ሲመጣ በማየታችን ተደስተናል እዚህ ላይ በዚህ ርክክብ መረሳት የሌለበት ውል ያላቸው ተጨዋቾች መባረር የሌለባቸውና መብታቸውን የምታከብሩ እንደሚሆን ላሳስባችሁ እወዳለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport