የጨዋታ ዘገባ | ድሬዳዋ ከተማ በሄኖክ አየለ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ወላይታ ድቻን አሸንፏል

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ድሬደዋ ከተማ ወላይታ ዲቻን በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ በተቆጠረ ብቸኛ ጎል 1 ለ 0 አሸንፈዋል ።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ የተጀመረው ጨዋታ ፈጣን እንቅስቃሴን እና በቶሎ ወደ ጎል የመድረስ ፍላጎት በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያሳየ ነበር ። ነገር ግን ግብ ጠባቂዎችን የፈተነ የጎል ሙከራ አልነበረም ።

በመጀመሪያው አጋማሽ በወላይታ ዲቻ በኩል ምንይሉ ወንድሙ ከርቀት የመታው ቅጣት ምት እና በተደጋጋሚ የቆሙ ኳሶችን ወደ ድሬዳዋ ከተማ የጎል ክልል ሲያደርስ የነበረው እድሪስ ሰይድ መቶት በእንየው ካሳሁን ተጨርፎ የድሬደዋው ግብ ጠባቃ ፍሬው ጌታሁን ያወጣው ኳስ ተጠቃሽ ነበሩ ።

በድሬደዋ ከተማ በኩል ግን ይህ ነው የማይባል የጎል ሙከራ ሳይደረግ ነበር የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀቀው ። በሁለተኛው አጋማሽም ከመጀመሪያው አጋማሽ እምብዛም የተለየ ነገር አልተመለከትንም ።

የጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች በተቃረቡ ጊዜ በአንፃራዊነት በሁለቱም በኩል በተለይም በድሬዳዋ ከተማ በኩል ጎል ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል ።በወላይታ ዲቻ በኩል 86ኛ ደቂቃ ላይ ስንታየሁ መንግስቱ ከአዲስ ህንፃ የደረሰውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።

ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የወላይታ ዲቻው ግብ ጠባቂ ፅዮን መርዕድ የሰራውን ስህተት ተከትሎ ተቀይሮ የገባው ሄኖክ አየለ ጎል አስቆጠረ ። ድሬዳዋ ከተማም በዚህች ብቸኛ ጎል ወላይታ ዲቻን 1 ለ ዐ ማሸነፈሰ ችሏል ።

 

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport