የጨዋታ ዘገባ | ሀዋሳ ከተማ የመክፈቻውን ጨዋታ በድል ጀምሯል

የ2014 ዓመተ ምህረት የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ 8 ሰዓት ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታድየም በተካሄደ ጨዋታ በይፋ ተጀምሯል ።

በጨዋታው የተገናኙት የሊጉ የመጀመሪያ 9 ሳምንታት ጨዋታዎችን አስተናጋጅ የሆነው ከተማ ክለብ የሆነውን እና የሁለት ጊዜ የሊጉ ሻምፕዮን መሆን የቻለው ሀዋሳ ከተማ እና በ2010 የሊጉ ሻምፕዮን የነበረውን ጅማ አባጅፋር ነበሩ ።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በማርሽ ባንድ የታጀበ የመክፈቻ ፕሮግራም የነበረ ሲሆን የሁለቱ ተጋጣሚ ክለብ ተጨዋቾች እና ዳኞች ወደ ሜዳ ከገቡ በኋላ በስፍራው ከተገኙት የክብር እንግዶች ጋር ሰላምታ ተለዋውጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ብሄራዊ መዝሙር ከተዘመረ በኋላ ጨዋታው ሊጀመር ችሏል ።

በጨዋታው ደጋፊዎች በተወሰነ መልኩ እንዲገቡ መፈቀዱን ተከትሎ የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች እና ጥቂት የጅማ አባጅፋር ደጋፊዎች በስታዲየሙ በመገኘት ክለቦቻቸውን አበረታተዋል።

ጨዋታው በመጀመሪያ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት ሀዋሳ ከተማዎች የተሻለ በመንቀሳቀስ ወደ ጎል ለመድረስ ሞክረዋል ። በተደጋጋሚም በሁለቱ ክንፎች በኩል የጅማ አባጅፋርን የተከላካይ መስመር ሲፈትኑ ተስተውሏል ።

ጨዋታው በተጀመረ 15ኛ ደቂቃ ላይም የሀዋሳ ከተማው 10 ቁጥር መስፍን ታፈሰ ከወንድማገኝ ሀይሉ በግሩም ሁኔታ የደረሰውን ኳስ በማስቆጠር ክለቡን መሪ ማድረግ ቻለ ፤ ይህም የ2014 ዓመተ ምህረት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጎልም መሆን ችሏል ።

በጅማ አባጅፋር በኩል የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች አለመረጋጋት ይታይባቸው የነበረ ሲሆን ኳሶች ወደ ፊት ሲሄዱም በቀላሉ በሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ይነጠቁ ነበር ። ለአጥቂ መስመር ተጫዋቾች የሚላኩት ረጃጅም ኳሶችም በብዛት ከጨዋታ ውጪ በመሆን ይበላሹ ነበር ።

የውሀ እረፍት ወስደው ከተመለሱ በኋላ ጅማ አባጅፋሮች በተደጋጋሚ ሲበላሹ የነበሩትን ረጃጅም ኳሶች በመቀነስ እና አጫጭር ኳሶችን በመጠቀም ጎል ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ሲሆን 39ኛ ደቂቃ ላይ መሀመድኑር ናስር ከሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ዳግማዊ ተፈራ ጋር ፊትለፊት ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ ተጠቃሽ ነበር ።

በመሀል ሜዳው ላይ ብልጫ በመውሰድ ተቃራኒ ተጋጣሚ የበላይነት ለመውሰድ በማሰብ በሚመስል መልኩ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በብሄራዊ ቡድን የነበረውን መሱድ መሀመድን በተስፋዬ መላኩ 41ኛ ደቂቃ ላይ ቀይረው ወደ ሜዳ አስገበተዋል ።የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽም በሀዋሳ ከተማ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።

የሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ እጅግ የተቀዛቀዘ እና ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል ያላስመለከተን ነበር ። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ውጤት ለማስመዝገብ የተለያዩ ቅያሪዎችን ቢያደርጉም ሌላ ግብ መመልከት አልቻልንም ።

በጨዋታው 81ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወጥቶ በተጠባባቂዎች መቀመጫ ላይ የነበረው ዳዊት እስጢፋኖስ ኳስ አቀባይ ላይ የውሀ መጠጫ ፕላስቲክ ጠርሙስ ወርውረሀል በሚል ከአራተኛው ዳኛ ለመሀል ዳኛው ደርሶ ጨዋታውን ሲመሩ የነበሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው በቀጥታ ቀይ ካርድ ሊያሳዩት ችለዋል ። በሁለቱ ክለቦች መካከል የተደረገው ጨዋታም በመስፍን ታደሰ ብቸኛ ግብ ሀዋሳ ከተማዎች 1 ለ 0 አሸንፈው ወተዋል ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport