“ስሜን በሀሰት አጉድፈው የቤተሰቤንና የወዳጆቼን አንገት ያስደፉትን በፍትህ አደባባይ ለመፋረድ ዝግጅቴን ጨርሻለሁ”ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው

“ስሜን በሀሰት አጉድፈው የቤተሰቤንና የወዳጆቼን አንገት
ያስደፉትን በፍትህ አደባባይ ለመፋረድ ዝግጅቴን ጨርሻለሁ”

“ውጪ ተምረናል፣ ፕሮፌሽናልም ሆነ የሀገር ውስጥ ላይሰንስ
አለን የሚለው ጉዳይ በላይሰንስ ምዝገባ ጊዜ ምላሽ ያገኛል”

ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው


በይስሀቅ በላይ

ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ማንም ማውረድ ያልቻለው ርቆ የተሰቀለ ውጤትና ታሪክ ባለቤት ናቸው፤ ከ31
አመት በኋላ
የአፍሪካ ዋንጫ መስራች አገርን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመለሱበት ስኬታቸው ስድስት አመታትን ቢያስቆጥርም ይሄንን
ውጤት
የተጋራም ይሁን ሪከርዱን ያሻሻለ አንድም አሰልጣኝ ባለመገኘቱ ውጤቱ ዛሬም ድረስ ስሜቱ ትኩስ ነው፤ የኢትዮጵያ ብ/
ቡድንም ከረጅም ጊዜ ትዕግስትና ቆይታ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በመመለስ በሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ልብ ውስጥ
የማይነቃነቅ ሀውልት
ለመትከል የበቁት የዛሬው እንግዳችን ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በዚሁ ስኬታቸውም ብዙዎች ዛሬም ድረስ ጀግናችን
ይሏቸዋል፤
ባርኔጣቸውንም ከፍ አድርገው ያነሱላቸዋል፡፡ “ከዚህ በፊት በደረሰብኝ የሀሰት ስም ማጥፋት ቤተሰቦቼ፣ ወዳጆቼ፣
ያሰለጠንኳቸውና
የሚያከብሩኝ ሁሉ አንገታቸውን ደፍተዋል፤ ስጠብቅ የነበረው የፍ/ቤቱን መከፈት ነበር፤ ያለ ስሜ ስም የሰጡኝን
በፍትህ አደባባይ
ለመፋረድ ተዘጋጅቻለሁ” የሚሉት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው “ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ኢንስትራክተር የላትም
የሚለው ሙሾ
አብቅቶለታል፤ ካፍ ሙሾውን ሲያወርዱ ለነበሩ የማያዳግም ምላሽ ሰጥቶበት ስርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል” ብለዋል፡፡
የሀትሪክ
ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ደረጃውን በጠበቀው በኢንስትራክተር ሰውነት
ቢሻው መኖሪያ ቤት በክብር ተጋብዞ ባለቤቱ እየሩሳሌም ያዘጋጀችውን እጅ የሚያስቆረጥም ቁርስ በሻይ እያወራረደ
ከአንድ
ሰዓት በላይ የፈጀውን ቃለ ምልልስ ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቅርቦታል፡፡ ኢንስትራክተር ሰውነት
ቢሻውና ባለቤታቸው ወ/ሮ እየሩሳሌም ለጋዜጠኛና ለሀትሪክ ክብር ሰጥተው ላደረጉለት መስተንግዶ
ክብረት ይስጥልኝ ማለትን እናስቀድማለን፤ መልካም ቆይታ፡፡


ሀትሪክ፡- …አዲስ አመት አደል…?…እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሰህ ብልህ…የመልካም ምኞቴ…የዘገየ ይሆን…?

ኢንስ.ሰውነት፡- …ኧረ በፍፁም…አይዘገይም…2013ት ገና ሣምንት እንኳን ስላላለፈው ትችላለህ…እኔም በዚህ
አጋጣሚ አንተንም…የጋዜጣችሁ አንባቢዎችንም…መላው የኢትዮጵያ ህዝብን…እንኳን አደረሳችሁ…፤…መልካም አዲስ
አመት…ማለት እፈልጋለሁ…፡፡

ሀትሪክ፡-…ሰውነት…ፖለቲከኛ ሆንክ እንዴ…?
ኢንስ.ሰውነት፡- …/ደንገጥ ኮስተር ብሎ/…ከመልካም ምኞት…በአንዴ ፖለቲካ ውስጥ ገባህ…?…(እንደ መሳቅ
እያለ)…የምን ፖለቲካ አመጣህ ደግሞ…?

ሀትሪክ፡- …ኢንስትራክተር እንደውም ይሄን ጥያቄ ላቆየው…አዲሱን አመት እንዴት ተቀበልከው…?…እንዴትስ
አሳለፍክ…?…የሚለውን ጥያቄ ባስቀድም ይሻላል…?

ኢንስ.ሰውነት፡- …(እንደ መሳቅ እያለ)…ይሻልሃል…!…አዲሱን አመት በተለመደው መልኩ በኢትዮጵያዊ የባህል
አከባበር ስሜት ነው የተቀበልኩት…፤…ቤተሰብ ተሰባስበን…ለዚህ ያደረሰንን አምላካችንን እያመሰገንን…ደስ በሚል
ስሜት ነው ተቀብለን ያሳለፍነው…፤… የዘንድሮውን የሚለየው ይህቺ ኮረና የሚሏት ነገር ስላለች…ተራራቅን
በጥንቃቄ…እንደ ከዚህ በፊቱ…በርከት ብለን ሳንሰባሰብ ማሳለፋችን ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …“አሮጌው” ብለን መጥራት የጀመርነው 2012 ዓ.ም…መጥፎ የሚባል አመት ነበር…?
ኢንስ.ሰውነት፡- …ዘመናት የየራሳቸው ባህሪ አላቸው…አንደኛው አመት መጥፎ መዓት ይዞ ይመጣል፤ ሌላኛው ደግሞ
የራሱን በረከት ይዞ ይመጣል፤ያንን ደግሞ የሰው ልጅ አምላኩ በሰጠው ጥበብና በእሱ እርዳታ ያልፈዋል፡፡ዘመኖች
የመቀያየር ባህሪ አላቸው፤ለምሣሌ ከ100 አመት በፊት አለም ለወረርሽኝ ተጋልጣ ነበር…ያ ታሪክ ሆኖ አልፏል፤አሁን
ደግሞ በእኛ ዘመን ክፉ ወረርሽኝ መጥቷል…ሀገራችንን ጨምሮ በመላው አለም ብዙ የሰው ዘርን
ጨርሶብናል፤ኢኮኖሚውንም ክፉኛ አናግቶታል፤ሀብታም…ደሃ…ያደገ…ያላደገ…ሳይል ሁሉም ላይ ጉልበቱን አሳይቷል፤ይሄን
ሁሉ መዓትና ፈተናን አውርዶ…ይሄም ያልፋል…፤…ከእኛ የሚጠበቀው…መጠንቀቅና እንደየ ዕምነታችን…ለፈጣሪያችን
መፀለይና መለመን ብቻ ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …የተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በእንግድነት…በአምባሳደርነት እየታጨህ ስትቀርብ ትታያለህ…ሰውነትቴሌቪዥን
ስክሪን ላይ በዛ የሚሉ ሰዎች አጋጥመውኛል…ምን ልበላቸው?

ኢንስ.ሰውነት፡- …እንግዲህ ምን ላድርጋቸው…?…ምንም ልረዳቸውአልችልም… (እየሳቀ)… “ታስፈልጋለህ…
አምባሳደራችን ነህ…ተፅዕኖ ፈጣሪነትህን፣ ተወዳጅነትህን…ተጠቅመህ ህዝብህን…ሀገርህን አገልግል” ብላ…ሀገሬ…ህዝቤ
ወገኔ ሲጠራኝ እምቢ ልበል…?…በፍፁም አልልም…!…ምክንያቱም እኔን ያከበረኝን…እውቅና የሰጠኝን…ለዚህ
ክብር ያበቃኝን ህዝብ ለማገልገል…የምሰስተው…የምቆጥበው ጉልበት የለም…፤…አቅሜ እስከፈቀደ…በበጎ ነገሮች ላይ
መሳተፌን… ወገኔን ማገዝ… ማበረታታት… ማንቃት… ልምዴን… ህይወቴንና ስኬቴን ማጋራቴን…አጨብጭቦ…አበረታቶ
የእውቅና ካባ ሳይሰስት የደረበልኝን ወገጌን…ማገልገሌን እቀጥላለሁ፤ምክንያቱም ከሰው የተፈጠርኩ ሰው ነኝ…ብቻዬን
ተደስቼ አልኖርም…ከወገኔ ጋር ደስታውንና ችግሩን መጋራቴን እቀጥላለሁ…በዚህ የሚከፋ ካለ…ምንም ልረዳው
አልችልም…፡፡

ሀትሪክ፡- …በቅርቡ ከሰላም ሚኒስትሯ…ክብርት ሙፈርያት ካሚል ጋር…ፊርማ የማሰባሰብ ሥራ ውስጥ ገብተሃል…ይሄስ
የዚያ አካል ነው…?

ኢንስ.ሰውነት፡- …በትክክል…!…ሀገሬን ወገኔን መልሶ የማገልገል አንደኛው ኃላፊነቴ ነው…የሠላም ሚኒስትሯ
ክብርት ሙፊሪያት በበላይነት የሚመሩት ይሄ ስብስብ…ሠላምን ለማምጣት የሚተጋ…“ሠላም ለትውልድ”…የሚል
መርህን አንግቦ…ለሠላም ፊርማን የሚያሰባስብ…የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣የፖለቲካ ሰዎችና ታዋቂ ግለሰቦችን
ያሰባሰበ ከ1 ሚሊዮን በላይ ፊርማን የማሰባሰቡን ሥራን የሠላም ሚኒስትሯ ክብርት ሙፊርያት ካሚል፣የተፎካካሪ
ፓርቲዎችን በመወከል አቶ ሙሣ፣ከታዋቂ ሰዎች ደግሞ እኔና አርቲስት መቅደስ እንደ ቅደም ተከተላችን በመፈራረም
የፊርማ ማሰባሰቡን ስራ በይፋ አስጀምረናል፤ሠላም የሁሉም ነገር መሰረትና በጣም አስፈላጊው ነገራችን በመሆኑ
የዚህ አካል በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- …አንተ የስፖርት ሰው ነህ…ይሄንና ከዚህ በፊት በተለያዩ የመንግስት ፕሮግራሞች ላይ መገናኘትህን
የታዘቡ…ይሄ ሰውዬ…ስፖርቱን ትቶ…ፖለቲከኛ ሆነ እንዴ…?…ብለው ሲያሙህ ሰምቻለሁ…እውነት ሰውነት
ፖለቲከኛ ሆነ…?

ኢንስ.ሰውነት፡- …የማይባል ነገር የለም…እኔ ሰውነት ግን ፖለቲከኛ አልሆንኩም፤ ብሆንም ግን ፖለቲከኛ መሆን ማለት
እኮ ነፍሰ ገዳይ መሆን ማለት አይደለም…አልሆንኩም እንጂ ብሆንስ…?…ለምን ሰው በዚህ ደረጃ
ይገረማል…?…ፖለቲከኛ መሆን የሚያስጠላው እኮ ሰው ገዳይ…ጥቅምን አሳዳጅ…ህዝብን የምትበድል ስትሆን
እንጂ…ፖለቲከኛ ሆነው እኮ ለህዝባቸው የሚኖሩ…የሚያገለግሉ…ለሀገራቸው እድገት እንቅልፍ የሚያጡ ፖለቲከኞች አሉ
እኮ…የህብረተሰቡን ችግር የሚቀርፉ…የሚቆረቆሩ…የሀገሪቱን ገፅታ የሚቀይሩ…የምታኮራ ሀገር እንድትሆን
የሚሠሩ…የሚተጉ ፖለቲከኞች አሉ፤በዚህ ደረጃ ያሉትን ፖለቲከኛ ስለሆኑ ብቻ ነፍሰ ገዳይ አድርጎ ማሰብ ስህተት
ነው፤ሌላው ደግሞ ፖለቲከኛ ሣትሆን ለሀገሩ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ አለ፤ግለሰቦች ፖለቲከኛ ሳይሆኑ ለበጎ
ሥራ…ለህዝባቸው ሲሉ ራሣቸውን አሳልፈው የሚሰጡ አሉ…ምክንያቱም ሀገራቸው ናታ፤እኔም ከእንደዚህ አይነቶቹ
ወገኖች ውስጥ የምደመር ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡
ታዳጊ፣ወጣት፣ትንሽ፣ትልቁ በሙያዬ ስለሚያውቀኝ…ስለሚወደኝና ስለሚያከብረኝ ይሄንን እውቅናና ፍቅር ተጠቅሜ
ህዝቤን ለለውጥ፣ለሠላምና ለስኬት እንዳነሳሳ ሀገሬ ጥሪ ስታደርግልኝ ሁሌም ከፊት ቀድሜ መገኘትን ነው
የማስቀደመው…ህዝቤን ማገልገል ካለብኝ የትም ቦታ ገብቼ ማገልገል ስላለብኝ ነው እንጂ …ፖለቲከኛ ሆኜ አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- …በዚህ አጋጣሚ ልጠይቅህ…ፖለቲካስ ትወዳለህ…?

ኢንስ.ሰውነት፡- …ፖለቲካ አልወድም አይመቸኝምም…በህይወት ዘመኔ ብዙ መንግስታትን
አሳልፌያለሁ…በኃይለስላሴ፣በደርግ፣በኢ.ህ.አ.ዴግም ነበርኩ…አሁንም በለውጡ አለሁ…በእነዚህ ጊዜያቶች ውሰጥ
አንዴም ፖለቲካ ውስጥ አልገባሁም…ፖለቲከኛ ሆኜም አላውቅም…፤ …ለምሣሌ በደርግ ዘመን…ሁሉም ኢ.ሠ.ፓ
ሲሆን ሰውነት ቢሻው ግን የለሁበትም፤የኢ.ሠ.ፓ ካኪውንም አለበስኩ…በወቅቱ እኔ አስተማሪ ነበርኩ…የውይይት
ክበብ የሚባል ነበር…ሁሌ አርብ አርብ…ስብሰባ በለው…ውይይት ነበር…ግን አንድም ቀን…ተሰብስቤ አላውቅም…እኔ
የምገኘው የስብሰባ ቦታው ሣይሆን ስፖርት ሜዳ ላይ ነበር፤በአንተ የፖለቲካ እውቀት ወይም ፖለቲከኛነት…የህብረሰቡ
አኗኗር…ህይወት…አገርም እንደ አገር ለመቀየር ከሆነ ፖለቲከኛ መሆን ክፋት የለውም…ፖለቲከኛ መሆን አውሬነት
ወይም ነፍሰ ገዳይነት አይደለም…፡፡

ሀትሪክ፡- …አሁን ኮስተር ወደሚለው ጉዳያችን እንግባ…ኢትዮጵያ ኢንስትራክተሮች አሏት የላትም…የሚለው ጉንጭ
አልፋ ክርክር ከዚህ በኃላ ይሰማል??

ኢንስ.ሰውነት፡- …ይሄንን አይነቱ ጥያቄ ከባለፈው የቪደዮ ኮንፈረንስ በኋላ አፈር የበላ ያረጀ ጥያቄ
ይመስለኛል…፤…ምክንያቱም ጉዳዩ በዋናነት የሚመለከተው ካፍ ከፍተኛ ኃላፊዎች ኢትዮጵያ ኢንስትራክተር የላትም
ብለው ሲያላዝኑ ለነበሩ ሰዎች ኢስትራክተሮች እንዳሏት አረጋግጠው አጀንዳው ዳግም አንዳይነሳ ተቀብሯል፡፡

ሀትሪክ፡- የፖሊስ ምርመራ የሚመስል ጥያቄም ቢሆን ከመጠየቅ ወደ ኃላ አልልም፤አንተ የኢንስትራክተርቱን ማዕረግ ከየት
አመጣኸው?

ኢንስ.ሰውነት፡- …(በጣም ሳቅ) ከየት አመጣዋለሁ?…ኢንስትራክተር ብሎ ከሚሰጠው ተቋም ነዋ…!በነገራችን
ላይ እኔ ኢንስትራክተር እንድሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አላከኝም …እድሉንም አልሰጠኝም…

ሀትሪክ፡- …ታዲያ ማነው የሰጠህ…?

ኢንስ.ሰውነት፡- …የአህጉሪቱ እግር ኳስ የበላይ የሆነው ካፍ ነው እድሉን የሰጠኝ… በወቅቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ፌዴሬሽን የኢንስትራክተርነት አንድ እድልን ለዶ/ር ጌታቸው ሲሰጥ ለእኔ ደግሞ ካፍ “ለሰውነት ቢሻው” ብሎ በቀጥታ
በስሜ ነው እድሉን የሰጠኝ፤ እንግዲህ አንተም ሆንክ ይሄንን ሲትጠራጠሩ የነበራችሁ…ምን ትሆኑ…?…ካፍ ነው
በቀጥታ በስሜ ልኮ እድሉን የሰጠኝ…፡፡

ሀትሪክ፡- …የአንተ በተለይ ለምን እንዲህ ሆነ…?…የሚል ጥያቄ ቢነሳብህስ…?

ኢንስ.ሰውነት፡- …ካፍን መጠየቅ ነዋ…!…እኔ እስከማውቀውና እስከተነገረኝ ድረስ ግን…በሴካፋ ዋንጫ
በማግኘቴ፣ከ31 አመት በኋላ ሀገሬን ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለቻን ውድድር በማሳለፌ…ለእግር ኳሱ ያበረከትኩትን ሁሉ
መዝኖ ለኢንስትራክተርነት ራሱ በቀጥታ “ለሰውነት ቢሻው” ብሎ ልኮ ጋቦን ለአፍሪካ ዋንጫ በሄድኩበት ጊዜ ነው
እድሉ የተሰጠኝ፤ ይሄ እውነት ስለሆነ ልንጋፋው አንችልም፡፡

ሀትሪክ፡- …ከዚህ በፊትም ሌላ ባለሙያ ጠይቄያለሁ…አሁን ደግሞ የአንተን መስማት እፈልጋለሁ…፤…እግር ኳሱ
የለም…ኢንስትራክተሮች ግን አልበዛችሁም…?

ኢንስ.ሰውነት፡- …የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፤ የማይገናኝ ነገርንም ነው ያገናኘኸው… ብዙ ጊዜ…ኢንስትራክተሮች በዙ
ሲባል እሰማለሁ…ኢንስትራክተር በዛ ሲባል ምን ማለት ነው…?…ለ110 ሚሊዮን ህዝብ 8 ኢንስትራክተር ስላለ
ነው በዛ የሚባለው…?…ለምን 80 ሺህ ኢንስትራክተር አይኖርም…!…ያንስ እንደሆነ እንጂ አይበዛም…፤…ከዚህ
በፊትም ኢትዮጵያ ኢንስትራክተሮች ነበሯት…(ነፍሱን ይማረውና)…ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ፣ ኢንስትራክተር
ካሳሁን ተካን የመሳሰሉ ኢንስትራክተሮች ነበራት…አሁን ደግሞ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣አንተነህ
እሸቴ፣አብርሃም ተ/ኃይማኖት፣ዶ/ር ሲራክ፣እኔ፣ኢንስትራክተር ዳንኤል በሴቶች ደግሞ ሠላም ኢንስትራክተር
ሆናለች፡፡ከዚህ ውጪ ኢንስትራክተር እንደሌለን ሲጠራጠሩ የነበሩትን ካፍ አረጋግጦላቸዋል፤እነዚህ ሰዎች በካፍ
የታወቁ ሰርቲፋይድ የሆኑ ኢንስትራከሮች ናቸው…ፌዴሬሽኑም ካፍን በደብዳቤ ጠይቆ ተረጋግጧል፤እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ
ሰዎች ለምን በዚህ በኢንስትራክተርነት ጉዳይ እንደሚጨቃጨቁ አይገባኝም፡፡
ኢንስትራክተር ማለት ገንዘብ የሚታፈስበት መሰላቸው ከሆነ ተሳስተዋል፤ኢንስትራክተርነት ማለት ማስተማሪያ ማለት
ነው…የካፍ ኢንስትራክተር ስለሆንን ፌዴሬሽኑ የሚሰጠን ሰባራ ሳንቲም የሚከፍለንም ደሞዝም የለም…የሀገራችንን
እግር ኳስ በማገዛችን…በማስተማራችን እንደ ክፍያ ካልተፅናናን በስተቀር የምናገኘው ነገር የለም፤እንደውም ልፋትና
ድካሙ ነው ትርፉ፤ልክ ጥቅም እንዳለው ነገር ሰዎች እንቅልፍ ሲያጡ ሳይ በጣም ይገርመኛል፡፡

ሀትሪክ፡-“የእኔ ኢንስትራክተርነት የህይወት ዘመን ነው” ብለሀል ምን ማለት ነው?

ኢንስ.ሰውነት፡- …አዎን ብያለሁ የእኔ ኢስትራክተርነት ኤክስፓየር አያደረግም… /የማብቂያ ዘመን የለውም/…ይሄንን
ስልህ ግን በዘመናዊ እግር ኳስ አዳዲስ ነገሮች ሲመጡ ሪፍሬሽ አታደርግም ማለት አይደለም…የሪፍሬሽመንት ኮርስ
መጥቶ ብገባ ግን እወድቃለሁ ማለት አይደለም፤እንደውም ላስተምረው ሁሉ እችላለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …ከዚህ ከኢንስትራክተርነት ጉዳይ ጋር በተያያዘ…በሀገር ውስጥ…እኔ ነኝ…እከሌ አይደለም…በሚል
በየሚዲያው ከመነታረክ ባለፈ…ካፍ ድረስ ጉዳዩ ተወስዶ…የካፍ ሰዎች ሣይቀር እንደታዘቡን ተሰምቷል…መከባበር
ሲገባን እርስ በርስ ተናንቀን ጉዳዩ አደባባይ መውጣቱ እንደ ሀገር አያስፈራም… ?

ኢንስ.ሰውነት፡- …በጣም ያሳፍራል…!…ሀፍረቱ ግንይሄን ወደዚያ ለወሰድት ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም ነው፤ እኔን
በግሌ ብትጠይቀኝ በጣም አፍሬያለሁ…በዚህ ዙሪያ ማለት የምፈልገው…ይሄን የሚያደርጉ ሰዎች ልቦና
ቢሰጣቸው…ራሣቸውን ከማምለክ ወጥተው ለሀገራቸው ቢያስቡ ባያዋርዱን ብዬ ነው የምመክረው፤ኢንስትራክተር
መሆን ማለት እኮ አለምን መግዛት እኮ አይደለም…ኢንስትራክተር መሆን ማለት እኮ የራስን ትልቅነት ማንፀባረቂያም
አይደለም…ኢንስትራክተርነት ማለት ሌላውን ባለሙያ እግር ኳሱን ለመርዳት የምትደክምበት የሙያ ማዕረግ
ነው፤ስለዚህ መጨነቅ ያለብን ኢንስትራክተር ስለሆንን ስላልሆንን ሣይሆን…እንዴት እግር ኳሱን
አግዛለሁ…?…እንዴትስ በወጣቶች ላይ እሠራለሁ…?…እንዴትስ ለውጥ ይመጣል…?…በሚለው ነው፤አሁን
እየታየ ያለው ግን ሌሎች ኢንስትራክተሮችን ለማንቋሸሽ መሞከርና እኔ ኢንስትራክተር ስላልሆንኩ ሀገር ትገለበጣለች…
እዚህች ሀገር ምንም አይነት ኮርስ አይሰጥም…እግር ኳስ ብሎ ነገር የለም አይነት ነገር ነው… ይሄ ደግሞ ጤነኝነት
አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- የካፍ ከ ፍተኛ ኃላፊዎች ይሄንን አለመከባበራችንን ታዝበው እርስ በርስ መከባበር እንዳለብን ኢንስትራክተር
አብርሃም መብራቱ ከካፍ አልፎ በፊፋ ውስጥም አህጉሪቱን ወክሎ የሚሠራ በመሆኑ ተገቢውን ክብር ልትሰጡ እርስ በርስ
ልትከባበሩ ይገባል ማለታቸውስ ምን ፈጠረብህ?

ኢንስ.ሰውነት፡- … በጣም ትክክል ነው፤ እርስ በርስ ልንከባበር ሲገባ ሰው እስኪታዘበን መሆን አልነበረብንም፡፡
ኢንስትራክተር አብርሃም በካፍ ትልቅ ቦታና ክብር ያለው ኢትዮጵያዊ ነው፤ እሱን ልናከብረው ይገባል የካፍ ሰዎችም
አስረግጠው የተናገሩት ይሄንን ነው፡፡ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሀገራችን ብቸኛው ኤሊት ኢስትራክተር መሆኑን
መካድ አይቻልም ከካፍ 21ዱ ኤሊት ኢንስትራክተሮች አንዱም ነው፤ ይሄ ብቻ አይደለም በፋፊ ውስጥም ሀገራችንን
ወክሎ እየሠራ ያለ ባለሙያ ነው፤ ለምሣሌ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ስልጠናዎች የፕሮላይሰንስ ስልጠና ቢመጣ እነዚህን
ስልጣናዎች አብርሃም ሊሰጥ ይችላል፤ ምክንያቱም ኤሊት ኢንስትራክተር ስለሆነ፤ አብርሃም ኮርሶችን በሀገር ውስጥ
ብቻ ሳይሆን በውጪም መስጠት ይችላል፡፡ ስለዚህ ይሄን በአህጉሪቱና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅን ሙያተኛ
አለማክበር እንዴት ይቻላል? እርስ በእርስ መከባበር አለብን፡፡ ሰውን የሚንቅ የተናቀ ብቻ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ከዚህ በፊት በሀገራችን ያላችሁት ኢንስትራክተሮች ላይ የአቅም ጥያቄ ሲነሳባችሁ ይደመጣል? በእርግጥም ይሄ
ችግር ነበረባችሁ?

ኢንስ.ሰውነት፡- ብቃት የላቸውም እያልን ስናብጠለጥላቸው የነበሩ ኢንስትራክተሮችን ካፍ ብቃታቸውን አረጋግጦ
ሠርቴፋይድ አድርጓቸዋል፤ማንም ስለ ተመቀኘ፣ ብዙ ስላወራ ሊነጥቃቸው አይችልም፤ ከካፍ ሰዎች አንዱ የሆነው
አንቶኒ እኮ እንደዚህ አይነት ደካማ አስተሳሰብን ሲያራምዱ የሰውን ክብር ሲነኩ ለነበሩ ሰዎች ነግረዋቸዋል፤ እንደሙ
ምን እንዳለ ታውቃለህ?

ሀትሪክ፡- ምን… አለ?

ኢንስ.ሰውነት፡-… “እስቲ ኢንተርኔት ግቡና ሰውነት ቢሻው ብላችሁ ጎግል አድርጉ እሱ ትልቅ ፐርሰናሊቲ ያለው አሰልጣኝ
እንደሆነ ትረዳላችሁ፤ ሰውነት ቢሻውን ሁሉም ካፍም ያውቀዋል፤ ይሄንን ክብር ማንም ሊነጥቀው አይችልም”
ብሏቸዋል፡፡ ኢንስትራክተር አብርሃምን ውሰድ፤ እሱ ኤሊት ኢንስትራከተር ነው፤ እንዳልኩህ ነው ስልጠና ቢመጣ
በዋናነት የሚሰጠው እሱ ነው፤ እኛ ልንንቀው የምንሞክረው ሰው በአህጉሪቱም በአለምም ትልቅ ቦታ አለው፤ ስለዚህ
እንደዚህ አይነት ያረጀ ወሬ ሊቀር ይገባል፤ ከዚህ በኋላ ኢስትራክተር የለም አቅም የላቸውም እያሉ የሚያላዝኑ ሰዎች
ካሉ እነዚህ ሰዎች በሽተኞች መሆን አለባቸው፡፡

ሀትሪክ፡- የፌዴሬሽኑ የቴክኒክና ልማት ሰብሳቢ ስለሆንክ ይሄ ጉዳይ ይመለከተሀል ብዬ አስባለሁ፤ ሀገራችን ውስጥ ፕሮ
ላይሰንስ ያለው ወይም ከውጪ ይዞ የመጣ ባለሙያ አለ?

ኢንስ.ሰውነት፡- እኔ ወደ ፌዴሬሽኑ ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ነው የማወራው፤ አንድም የፕሮ ላይሰንስ አለኝ የሚል
ባለሙያም ማስረጃም አላየሁም፤ አለኝ ብሎ ትክክለኛውን ማስረጃ ያሳየኝ ሰውም አላጋጠመኝም፡፡

ሀትሪክ፡-ኢንስትራክተር ሰውነት አንተና ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለሀገራችን የመጣውን የፕሮ ላይሰንስ ስልጠና
እድል አፍናችሁ አስቀርታችሁ የሙያተኞችን እድል አቃጥላችኋል በሚል ትወቀሳላችሁ እስቢ በዚህ ዙሪያ የእምነት ክህትደ
ቃልህን ስጠኝ….?

ኢንስ.ሰውነት፡-ይሄ በጣም ውሸት ነው፤ ይሄንን በማሰወራት በሚያተኞች መካከል ልዩነት ሲፈጥሩ የነበሩት ግለሰቦትን
ካፍ ራሱ አጋልጧቸዋል፡፡ ከምቀኝነት፣ ከክፋት የመነጨ ተራ ወሬ ነው፤ የፐሮ ላይሰንስ ኮርስ ቢኖርም እኮ በቀጥታ
የሚመጣው ለሰውነት ወይም ለአብርሃም ሣይሆን ለፌዴሬሽኑ ነው፤ ለፌዴሬሽኑ የመጣ እድልን እንዴት እኛ ልናፍነው
እንችላለን? ተራና ርካሽ ወሬ ነው፤ ፕሮ ላይሰንስ ዝም ብለህ ዘለህ የምትገባበት አይደለም፤ ፕሮ ላይሰንስ ይዘህ እቤትህ
የምትቀመጥበት ሣይሆን የምትሰራበት ነው፡፡ ፐሮ ላይሰንስ የሚባል ነገር ላለፉት አመታት በካፍ ደረጃ አልተሰጠም
ሞሮኮ ላይ ለሙከራ ያህል እንጂ የተሰጠ ነገር የለም፤ እኛ የማንንም የማስቀረት መብቱም፣ ኃላፊነቱም፣ ፍላጎቱም
አልነበረንም ለወደፊትም አይኖረንም፡፡ ሙያተኞችን ከሙያተኛ ለማጋጨት ተፈብርካ የተወራች ወሬ ናት፡፡

ሀትሪክ፡-ባለፈው በኢንስትራክተሮች ጉዳይ በሰጣችሁት መግለጫ ላይ “ስማችንን እያጠፉ ያሉ ከአንድ እጅ መዳፍ
የማይበልጡ ግለሰቦችን በህግ እንጠይቃለን” ብለህ ነበር ስላልገባኝ እስቲ አብራራው?

ኢንስ.ሰውነት፡- .. አሁን ጉዳዩን በሕግ በባለሙያ የያዝነው ጉዳይ በመሆኑ እንዲህ ነው አልልህም፤ ግን አንድ
እንድታውቀው የምፈልገው ነገር ማንኛውም ሰው የራሱ የሆነ ክብር አለው፡፡ ዝም ብለህ ከመሬት ተነስተህ የሰውን
የተከበረ ስም አታጠፋም፡፡ በጣም ጥቂት ከሁለትና ከሶስት ጣት የማይበልጡ ግለሰቦት በሀሰት ስማችንን በአደባበይ
አጉድፈዋል፡፡ በቅርቡ የጎደፈውን ስማችንን፣ የጠፋውን ክብራችንን በፍትህ አደባባይ ለማስጠበቅ መረጃዎችን
አሰባስበን ዝግጅታችንኝ አጠናቀናል፡፡
በአደባባይ ያለ ስሜ ስም ተሰጥቶኝ ቤተሰቦቼ፣ ወዳጆቼ፣ አድናቂዎችና ነገ እንደ እኔ መሆን የሚፈልጉ፣
ያስተማርኳቸው፣ ያሰለጠንኳቸው ሰዎች አንገታቸውን እንዲደፉ እምነታቸው እንዲሸረሸር አድርገዋል፡፡ አንገታቸውን የደፉ
ሰዎች ቀና ብለው እንዲሄዱ በፍትህ አደባባይ ክብሬን ለማስመለስ እታገላለሁ፡፡
እኔ ደደብ አመሆኔን፣ ያለኝ ሰርተፌኬት እኔነቴን የሚገልፅ ማስረጃ ይዤ ቀርቤ እታገላለሁ ያኔ እኔ ልክ አለመሆኔን
ማስረጃ ይዘው ሲቀርቡ እኔ እታሰራለሁ ወሬውን ያወሩት ነፃ ሆነው ይወጣሉ፡፡ ከዚህ በተረፈ የደረሰብኝን የስም ማጥፋት
እስከመጨረሻው በህግ ለመፋረድ የፍ/ቤቱን መከፈት እየጠበኩ ነበር፤ አሁን ጉዳዩን ወደ ሕግ አደባባይ ለመውሰድ
ዝግጅቴን ጨርሻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ይሄ ጥያቄ የማነሣው የሰይጣን መልዕክተኛ ሆኜ ሣይሆን ከዚህ በፊትም እንደዚህ ብለህ ነበር የአሁኑ ከእዚህ
በፊት የተለየ ለመሆኑ ማረጋገጫህ ምንድነው ብሎ የሚፈታተንህ ጥያቄ ድንገት የሚያነሳ ቢኖር መልስህ ምንድነው?

ኢንስ.ሰውነት፡- እንኳን የግለሰቦች የፖለቲካ ችግርም (ግጭትም) አንዳንዴ በሽምግልና (በእርቅ) ይፈታል፤ ደግሞም
ይቅር ማለት ትልቅነት እንጂ ለወቀሳ የሚደረግ አይመስለኝም፡፡ እንዳልከው ከዚህ በፊት መረጃዎችን አሰባስቤ
ከጨረስኩ በኋላ በምወዳቸው፣ በማልጨክንባቸው ቤተሰቦቼና ወዳጆቼ መጡብኝ፤ በሽማግሌዎች ተሸንፌ ይቅር አልኩ
አሁን ግን በሀሰት በተነዛው ወሬ የተጎዳሁት እኔ ብቻ አይደለሁም ብዙዎች ተጎድተዋል፤ 10 ሽማግሌ ይምጣ በቀላሉ
የምተወው አይደለም፡፡ በሀሰት በተነዛው ወሬ የተጎዳው ስሜታችን የሚጠገነው በፍትህ በሚሰጠው ፍርድ ብቻ በመሆኑ
መተው አለመቻሌ የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያዊ ብ/ቡድን አሰልጣኝ የለውም፤ ብ/ቡድኑ ከፊት ጨዋታዎች አሉት ያለ አሰልጣኝ ብ/ቡድን ያለን
እና ብቻ አንመስልህም?

ኢንስ.ሰውነት፡-ይሄንን ጥያቄ እኛም አንስተናል፤ ከፌዴሬሽኑም አቅም በላይ በመሆኑ ለስፖርት ኮሚሽን ደብዳቤ
ተፅፏል፤ በዚያ የሚፈታ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-… ኢንስትራክተር አብርሃም ኮንትራቱ ሊቋረጥ ሲል ተቃውመህ ነበር፤… ዛሬ ላይ መቃወምህ ልክ እንደነበር
የመሰከሩ ብዙዎች ናቸው ምን ተማህ?

ኢንስ.ሰውነት፡-.. እንደ እግር ኳስ ሰው እንደ ባለሙያ ይሄ ከእኔ የሚጠበቅ ነው፤ ብ/ቡድን ካለ፣ ውድድሮች ካሉ
የብ/ቡድን አሰልጣኝ መኖር ግድ ነው፤ ልክ በተጠንቀቅ እንዳለ ወታደር (Stand By Army) ማለት ነው፡፡ ብ/ቡድን
ሀገሪቷን በተለያዩ መድረኮች የሚወክል በመሆኑ ስትፈለግ የምትበትነው ስትፈልግ የምታቋቁመው ሲመችህ አሰልጣኝ
የምታባርርና የምትሾም መሆን አለበት ብዬ አላምንም፡፡ በየትኛውም ዓለም ብ/ቡድን አሰልጣኝ ሳይኖረው ቀርቶ
አያውቅም፤ እንግዲህ እኛ ጋ የተለያዩ ምክንያቶች ነው የሚሰጡት ገንዘብና የተለያዩ ችግሮች፡፡ እስከዛሬ በነበረው ሂደት
ብ/ቡድኑም አሰልጠኝ ትጠራለህ ትበትናለህ ቋሚ የሚባል ነገር የለም ለወደፊት ግን ይሄ በጣም መታረም አለበት
አሰልጣኝ ለ15 ቀንና ወር የምንቀጥርበትን ጨዋታ መቀየር ይኖርብናል፡፡ ለምሣሌ የጀርመኑን አሰልጣኝ ዮሀኪም
ሎውን ተመልከተው ብ/ቡድን ከያዘ ስንት አመቱ ነው? ካልተሳሳትኩ ከ2006 ጀምሮ እያሰለጠነ ነው ስኬታማ
መሆን፣ ጥሩ ነገር መስራት የምትችለው ገብተው ስለወጣህ ሣይሆን ስትቆይ ነው፤ ስለዚህ ጊዜ የግድ ያስፈልጋል የእኛ
ግን ጊዜው የፈጠረው ችግር ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ራሱ ውሣኔ ይሰጥበታል መንግሥት (ስፖርት ኮሚሽን) የያዘው
ጉዳይ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- .. አንተ ሙያተኛ ነህ የብ/ቡድኑን አሰልጣኝ ቀጣይ ህልውናን በተመለተ በተደረገ የስራ አስፈፃሚው ስብሰባ ላይ
ሃሳብህ ሙያተኛ ባልሆነ ሰዎች በድምፅ ብልጫ ውድቅ ተደርጎብሃል… ይሄስ አላሣፈረህም..?

ኢንስ.ሰውነት፡-ይሄ ለእግር ኳስ በጣም ከባድ ነገር ነው፤ የሙያተኛ ሃሣብ ጆሮ ሊያገኝ ስለሚገባ ወደፊት በጣም
ትኩረት ሰጥተን ልናስተካክለው ይገባል፤ ሙያን ወይም የሙያተኛ ሃሣብ ሙያተኛ ባልሆኑ ሰዎች መሻሩ አያሳምንም፡፡
ለምሣሌ ይሄንን ነገር በህክምና ቋንቋ ብናወራው አንድ ዶክተር በህክምና ቋንቋ የሚሰነዝረውን ሃሣብ የህክምና ሙያ
ውስጥ የሌለ ሰው ሲቃወመው ወይም በድምፅ ብልጫ ሲጥለው ምን አይነት ስህተት ሊፈፀም እንደሚችል አስበው፤
አሁን በፌዴሬሽኑ ብዙ ነገሮች እየተቀያየሩ ነው ለወደፊቱ ይስተካከላል ብዬ አስባለሁ፤ መንግሥትም እግር ኳሱን
የሚፈልገው ከሆነ ይሄንን ነገር ማስተካከል አለበት ከአወካከል ጀምሮ ያለው ጨዋታ መቀየርና ሙያተኛውን ማዕከል
ያደረገ መሆን አለበት፤ ስፖርት የአንድ ሀገር ህዝብን የማስተሳሰር፣ ሠላምን የሚያመጣ፣ ገንዘብ የሚያስገኝ እስከሆነ
ድረስ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ ስፖርቱ በሙያተኞች መመራት አለበት፡፡

ሀትሪክ፡- የፌዴሬሽኑ የቴክኒክና ልማት ሰብሳቢ ስለሆንክ ከውጪ ተምረው እውቀትም ላይስንስም ይዘው ለሚመጡ እነሱን
ለመቀበል ልብህም አዕምሮህም ክፍት ነው?

ኢንስ.ሰውነት፡- እኔም እኮ ራሴ ውጪ ተምሬ ነው የመጣሁት ውጪ ተምሬ ስለመጣሁ ብቻ ግን ፌዴሬሽኑ ላይ
ካልተንጠለጠልኩ አላልኩም፤ ክለብ ነው የገባሁት ፕሮፌሽናል ላይሰንስም ይሁን በታወቁ ዩኒቨርሲቲ ተማር ከፌዴሬሽኑ
ጋር ምን አለህ? ከክለብ ጋር እንጂ፤ እኔ አንድ የማምነው ውጪ ተምረናል አዋቂ የሆነ የተሻለ እውቀት ካላቸው
ወርደው ሠርተው ማሳየት እንጂ በውዝግብና የሰውን ስም በማጥፋት ጊዜያቸውን መጨረስ የለባቸውም ደግሞም እኮ
ሁላችንም አንድ ልብ ማለት ያለብን ውጪ ተምሬያለሁ እንደዚህ አይነት ላይሰንስ አለኝ ስለተባልን ብቻ እውነት አድርገን
መቀበል ሣይሆን ማጣራት ያስፈልጋል እኔ ሰውነት ቢሻው የነገርኩህን ብቻ ሣይሆን ያሳየሁንም ነው ማመን ያለብህ፡፡
በነገራችን ላይ ከዚህ በኃላ ይሄ ላይሰንስ አለኝ ከውጪ የመጣ የሚለውን ነገር አይሰራም፤ አለኝ የተባለው ላይሰንስ
በራሱ ይጣራል (Approved) ይደረጋል እንጂ እንደ ድሮ በወሬ ብቻ ወይም ሳይጠራ የሚሰራ ነገር የለም ከእንግዲህ
በኮንቬንሽኑ መሠረት ማርስ ላይ ተምሬያለሁ ብትልም ፎቶ ኮፒውን ሣይሆን ኦርጅናሉን ማስረጃ የሚያቀርቡም አለብህ፡፡
ከዚህ ከላይሰንስ ጋር በተያያዘ አንድ ትልቅ ነገር ልንገርህ?

ሀትሪክ፡-… ምን.. ?

ኢንስ.ሰውነት፡- ውጪ ተምሬያለሁ…ፕሮፌሽናል ላይሰንስ አለኝ ስላልክ ብቻ የሚሆን ነገር የለም…ላይሰንስህ
(Approve) ይደረጋል…ይጣራል፤ተማርኩበት፣ሰለጠንኩበት የምትለውን ት/ቤት በኢ-ሜይልም፣በስልክም፣በአካልም
የመጠየቅ የማጣራት ስራ ይሠራል እንጂ እንደ ድሮ በፎቶ ኮፒ ወይም ማስረጃ ሣይኖርህ የሚሰራ ሥራ የለም፤እንደውም
ከዚህ ከላይሰንስ ጋር ያለው ችግር በቀጣይ ይጣራል፤ውጪ ተምሬያለሁ…ፕሮፌሽናልም ሆነ የሀገር ውስጥ ላይሰንስ አለኝ
የሚለው የሚጠራው የዳግም የላይሰንስ ምዝገባ ጊዜ ነው፤ፌዴሬሽኑ የማንንም ሙያተኛ ክብር አይነካም…ግን እኔ
ውጪ ተምሬያለሁ…ፕሮፌሽናል ላይሰንስ አለኝ የሚሉ ትክክለኛውን ኦሪጅናል ማስረጃ ማቅረብ አለባቸው…ከዚህ በኋላ
ነው እውነት የተማረ ከሆነ ሊያግዘን ሊያስተምርልህ ሁሉ ይችላል…በዚህ ዙሪያ ያለው ብዥታ በዳግም የላይሰንስ ምዝገባ
ጊዜ ይጣራል፤ከዚህ ውጪ በየሚዲያው እኔ እንዲህ ነኝ ብሎ መፎከር ያበቃል…በወሬ የሚሆን ነገር የለም፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.