ፕሪሚየር ሊጉና የኮቪድ ምርመራ ውዝግብ “የኮቪድ ምርመራ ውጤቶችን ልክ ነው አይደለም ለማለት ሥልጣኑም፣ ክህሎቱም፣ ዕውቀቱም የለንም” አቶ ክፍሌ ሠይፈ የሊግ ካምፓኒ ሥራ አስኪያጅ

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ጅማ ገብቶ ባህርዳር ሰንብቶ አሁን መዳረሻውን በምስራቃዊቷ የሀገራችን ክፍል ድሬደዋ አድርጓል።
ስሟ በእንግዳ ተቀባይነቷ፣በደግነቷ ከፍ ብሎ የምትነሣው ድሬ የፕሪሚየር ሊጉ ወደ ክልሏ መግባቱን ተከትሎ በአሉታዊ ጎኗ እንድትነሣ እያደረጋት ነው፤የአየር ንብረቷ (ሙቀቱ)፣ በቂ የልምምድ ሜዳ አለመኖር፣የስታዲየም መብራት(ፓውዛ) ችግርና የኮቪድ 19 ስርጭት መብዛት ለውድድሩ የደከመችውን ድሬዳዋን እጀ ሰባራ እያደረጋት ነው፤
በተጨዋቾች፣በአሰልጣኞች በክለብ አመራሮች ገና በጠዋቱ እሮሮ የበዛባት ድሬዳዋ ለወቀሳ የዳረጓትን ችግሮች ለማረም ደፋ ቀና ማለቷን ብትቀጥልም አሁንም የሁሉንም የደስታ ስሜት ለመመለስ እንደተቸገረች ነው…ከዚህ በተቃራኒ የቆመ አመለካከት ያለው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ የሆነው አቶ ክፍሌ ሰይፈ ግን “ችግሮች ቢኖሩም በተለይ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ውድድሩ ያማረ ለተወዳዳሪዎች ምቹ እንዲሆን እየለፉ እየደከሙ በመሆኑ ሊተቹ ሣይሆን ሊመሰገኑ ይገባል” በማለት በሃሣብ መሞገትን መርጧል“የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ለዚህ ውድድር ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት አድርጓል፤ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ አፍስሷል” የሚለው አቶ ክፍሌ ውድድሩ ከችግሮች የፀዳ ለማድረግ እየጣረ ነው ብሏል፡፡
የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስክዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በስፖርት ሳይንስ የመጀመሪያ ድግሪ፣በፉትቦል ኮቺንግ ሁለተኛ ዲግሪ ያለውን ትምህርትን ከልምድ ጋር ያጣመረ 17 አመታትን የዘለቀ ሥራ ልምድ ያለውን አቶ ክፍሌ ሠይፈን ድሬደዋ ላይ ምነው ቅሬታው በረከተ? የሚል ጥያቄን በዋናነት በመምዘዝ በርካታ ተጨዋቾች በኮቪድ 19 ተያዙ እየተባለ በኋላ ነፃ ናቸው ስለመባላቸው፣ስለ ልምምድ ሜዳ ችግር፣ስለ ስታዲየም መብራት (ፓውዛ) እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የብቻ ለብቻ ቃለ-ምልልስ አድርገዋል አብራችሁን ሁኑ፡፡

ሀትሪክ፡- …የድሬዳዋ ሙቀት፣የልምምድ ሜዳ ችግርና አመቺ አለመሆን፣ተጨዋቾች፣ዳኞች፣አሰልጣኞች በኮቪድ-19 መጠቃት፣የስታዲየም መብራት (ፓውዛ) በበቂ አለመኖር እነዚህ ሁሉ ተደምረው ሊግ ካምፓኒው የተፈተነበት ወቅት ነው ማለት እንችላለን…?…

አቶ ክፍሌ፡- …ለእኛ እንግዲህ የድሬዳዋው ውድድር ፈተና ሣይሆን በሀገራችን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ታሪክ ወደ 30 የሚጠጉ የማታ ውድድሮችን የማዘጋጀት ለየት ወደ አለ የመጀመሪያ ምዕራፍ የተሸጋገርንበት አጋጣሚ ነው ብለን ነው የምንወስደው፤በድሬደዋ ከዚህ በፊት ከነበሩት ጠንከር ያሉ ሥራዎች ተሰርተዋል…ብዙ ኢንቨስትመንት ፈሶበታል…በተለይ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ውድድሩ ያማረና የተሻለ እንዲሆን ብዙ ገንዘብ አውጥቶበታል…

ሀትሪክ፡- …እስቲ ችግሮቹን በተናጠል እንያቸው የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤትን የምትቀበሉበትን አሠራር አስረዳኝ….?

አቶ ክፍሌ፡-…ኮቪድ-19ን በተመለከተ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይሄንን ወረርሽኝ አስመልክቶ ምርመራ እንዲሰጡ ፍቃድ የሰጣቸው ተቋማት አሉ…ከእነዚህ የጤና ተቋማት የሚመጣውን ውጤት በማየት ነው ውድድር ውስጥ የምናስገባቸው…ከዚህ በፊት ከነበረው አሰራር በተለይ አዲስ አበባ በጣም ከተለያዩ ተቋማት ነበር የሚመጣው…ጅማ፣ባህር ዳር ላይ የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤት የሚመጣው ከአንድ ቦታ ነበር…ድሬደዋ ደግሞ ከሁለት ቦታ የሚመጣበት አጋጣሚ ነው የነበረው…ክለቦች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፈቃድ ከተሰጣቸው የጤና ተቋማት ማህተም ተመቶበት ይዘው የሚመጡትን የመጨረሻውን ውጤት አይተን ፖዘቲቭ የሆነው አይወዳደርም…ኔጌቲቭ የሆነው ደግሞ ወደ ውድድር ይገባል…በዚህ መልኩ ነው እየሰራን ያለነው…ማህተም ተመቶበት የሚመጣው የመጨረሻው ስለሆነ በዚህ በኩል የተፈተንበት ነገር የለም በእኛ በኩል…

ሀትሪክ፡- …አሁን በደንብ እንድናወራበት የምፈልገው ብዙ ሪፖርቶችን ስንሰማ ጠዋት 27 ተጨዋቾች ተያዙ ይባልና ከሰዓት በኋላ ደግሞ ድጋሚ ተመርምረው ሶስት ተጨዋቾች ብቻ ናቸው የተያዙት ሌሎቹ ነፃ ሆኑ ይባላል…አሁን አንተን መጠየቅ የምፈልገው መጀመሪያ 27 ተያዙ…ከዚያስ 24ቱ ነፃ ሆነው እንዴት ወደ ሶስት ወረደ…?…እንደዚህ አይነት የሚዋዥቅ ሪፖርት የሚመጣው ከአቅም ችግር ወይስ ከመመርመሪያው ድክመት…?…አሊያስ ኮቪድ-19 ባህሪውን እየቀያየረ በመምጣቱ ነው እንደዚህ አይነት ተለዋዋጭ ሪፖርቶች የምንሰማው…?…

አቶ ክፍሌ፡- …እንግዲህ እንደዚህ አይነቱን ኢንፎርሜሽን እኛም እንደ እናንተው ነው የምንሰማው… አሁን እንደዚህ ነው እንደዚህ ለማለት በመጀመሪያ ሙያተኛ መሆን ይጠይቃል…በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የራሱን ምርመራ (Investigation) ይጠይቃል…በእርግጥ ይሄ የእኛ ሥራ አይደለም፤የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይሄንን የመስራት ብቃት አላችሁ ብሎ ፍቃድ የሰጣቸው ተቋማት ሥራ ነው…የእኛ ሥራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፍቃድ ከሰጠው ከተረጋገጠ ተቋም በማህተም ተደግፎ የመጣ ደብዳቤን ይዘው ሲመጡ ማወዳደር ነው…እንዳልከው እኛም በኢንፎርሜሽን ደረጃ እንሰማለን…23 ተጨዋቾች ተያዙ የተባለበት ክለብ በሌላ ቀን ወደ ሁለትና ሶስት ወርዶ ታገኘዋለህ…ግን ይሄንን ከመስማት በዘለለ ቁጥሩ ለምን ወጣ?ወይም ለምን ወረደ? ማለት አንችልም…ምክንያቱም እዚህ ውስጥ ገብተን ለምን እንዲህ ሆነ ለማለት ሙያችንም ኃላፊነታችንም አይደለም…

ሀትሪክ፡-…ይሄ ለእኔ ድፍን መልስ ነው…ይሄ ሁሉ ውጣ ውረድና ውዥንብር ሲፈጠር እግር ኳሱን እየመራ ያለው ሊግ ካምፓኒ ኃላፊነታችንም ሙያችንም አይደለም በማለት ዝም ብሎ መቀመጥ…. ኃላፊነትን ካለመወጣትስ አያስስቆጥርም…?…

አቶ ክፍሌ፡- …እኔ ለማለት የፈለኩት ይሄ የሙያ ጉዳይ ነው…ለዚህ ደግሞ ኃላፊነት ያለው አካል አለ ለማለት ነው…የኢትዮጵያ የህብረተሰብ የጤና ኢንስቲቲዩት አለ…እሱ ምርመራውን (Investigation) እየሠራ ነው…እሱ ነው ዋናው ኃላፊነት ያለበት…ስለዚህ እነሱ በሚሠሩት ምርመራ (Investigation) ይሄኛው ተቋም ልክ ነው…ያኛው ልክ አይደለም ብለው እስከመዝጋት የደረሰ እርምት ሊሰጥ የሚችል አካል ያ ነው ለማለት ነው…ከዚህ የዘለለ እና ይሄኛው ልክ ነው ልክ አይደለም ለማለት ስልጣኑም፣ እውቀቱም፣ክህሎቱም የለንም ለማለት ነው…ምክንያቱም ይሄ ሙያዊ ጉዳይ ነው…ልክ ነው ልክ አይደለም ለማለት ማረጋገጫ ያስፈልግሀል…ጥናትም ይጠይቃል…አልያም ሙያተኛ መሆን አለብህ…

ሀትሪክ፡-…ሌላው ክለቦች በሚመረምሩት ባለሙያዎችም…ምርመራውን በሚያከናውነው ተቋም እምነት በማጣት በራሳቸው ውጪ በድጋሚ የመርመር ነገር ውስጥ ሲገቡ ይታያሉ…አንዳንድ ክለቦች እንደውም የሚሸተን ነገር አለ…ሆን ተብሎ እኛን ለመጉዳትና ውጤት ለማሳጣት ወሳኝ ተጨዋቾቻችንን ሳይያዙ ተይዘዋል በማለት የህክምና ስህተት ወይም ማጭበርበር እየተፈጠረ ነው በማለት ውስጥ ለውስጥ የሚያማርሩ አሉ ትቀበለዋለህ…?…

አቶ ክፍሌ፡- …በወሬ ደረጃ እኛም እንሰማለን…በዚህ ደረጃ የሙያ ዝቅጠት ውስጥ ይገባል የሚል እምነት የለንም…ሁሉም ሙያውን አክብሮ በታማኝነት ለእውነት ይሠራል ብለን ነው የምናምነው.. በጉዳዩ ላይ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ለማለት የተረጋገጠ ማስረጃ ያስፈልጋል…ከእኛ አቅም በላይ ነው…ልክ ነው አይደለም ለማለት ማረጋገጫ ያስፈልጋል…እንዳልኩህም ሙያተኛ መሆንም ይጠይቃል….

ሀትሪክ፡- ይሄንን የክለቦች ቅሬታንና በውጤቱ ላይ ያለውን ጥርጣሬ ለማስቀረት በእናንተ በኩልስ ምን እየሠራችሁ ነው…?…

አቶ ክፍሌ :- መንገዶችን ለመከተል ነው የምንሞክረው፤ለዚህ ትክክለኛ መልስ የሚገኘው ከEHI (የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ነው) ምክንያቱም የላብራቶሪውን ኳሊቲ አቅሙን የሚያረጋግጠው፣ የሚያጣራው አካል በዋነነት እሱ ነው…እኔ ግን አሁን የተነሣውን ሀሜት ልክ ነው አይደለም ለማለት ይከብደኛል…በቅርቡ ይሄን መሰል ችግሮች ለመቅረፍ ከዋናው መ/ቤት ሙያተኞች ወደ ድሬደዋ ከተማ ይሄዳሉ…ችግሩ የክህሎት ነው…?…ወይስ የላብራቶሪ መመርመሪያ መሳሪያው…?…የሚለውን ለማረጋገጥ፣የችግሩን ምክንያት ለመፈተሽና ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል…

ሀትሪክ፡- …በድሬደዋ ላይ በቅሬታ መልክ ከሚነሱ…ክለቦች ከሚያማርሯቸው ነገሮች አንደኛው በቂ የሆነ የልምምድ ሜዳ አለመዘጋጀቱ ይጠቀሳል…በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ…?…

አቶ ክፍሌ፡- …የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከዚህ ቀደም የሚካሄድባቸው ቦታዎች እናንተም እኛም እናውቃቸዋለን…በሀገር ውስጥ ያሉት ስታዲየሞች ሁሉም ኳሊቲያቸው አንድ አንድ አይደለም…ባህር ዳር ላይ ያለው ኢንፍራስትራክቸር ድሬደዋ ላይ…ጅማ ላይ ያለው ሐዋሳ ላይ ይኖራል ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው እንደ ከተሞቹ ሁሉም ነገር ይለያያል…ሁሉም የየራሱ ጠንካራና ደካማ ጎንም አለው… ለምሣሌ ጅማ ላይ ሁለት የትሬይኒንግ ቦታ ብቻ ነው የነበረው…ያንን አጣበው በተራ ነበር ሲጠቀሙ የነበረው…

ሀትሪክ፡- …በሜዳ በኩል ከሚነሱት ቅሬታዎች አንዱና ዋነኛው ሜዳው አሸዋማና ለጉዳት የሚዳርግ ምቹ አይደለም የሚለው ይነሳል…ይሄን ቅሬታ ትቀበለዋለህ…?…

አቶ ክፍሌ፡- …እዚህ ጋ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ድሬደዋ ልምምድ ሳር ላይ ይደረጋል የሚል መረጃውም እውቀቱም ያለው ሰው ይኖራል ማለት ይቸግረኛል… ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ውድድሩ ድሬደዋ እንደሆነ ስንነጋገር ድሬዳዋ ሜዳዎቿ አሸዋማ እንደሚሆኑ ሁሉም ክለቦች ያውቃሉ…ሜዳዎቹ አሸዋማ በመሆናቸው የከተማው አስተዳደር ዝም ብሎ አላየም…ሜዳዎቹ ምቹ እንዲሆኑና ከጤና ጋር የተያያዘ ችግር እንዳያመጡ በቀን 1,500 ብር እያወጣ ሜዳውን ውሃ የማጣጣት ስራን በመስራት ችግሩን ለመቀነስ ሲጥር ታይቷል…አንድ መታወቅ ያለበት የከተማው አስተዳደር ሜዳዎቹን ያቀረበው ያለ ክፍያ ነው…በሌሎች ከተሞች ግን ክለቦች ገንዘብ እየከፈሉ ሲሰሩ እንደነበር ይታወቃል…ሜዳው አሸዋ ነዋ አይመችም የሚሉ ካሉ ሌላ አማራጭ አላቸው… በክፍያ የግለሰብ አርቴፊሻል ሜዳ አለ እሱን መጠቀም የሚችሉበት አማራጭም ነበር…
የትም ሀገር ብትሄድ ሁሉም አንድ አይነት ሊሆን አይችልም…አፍሪካ ዋንጫ፣ኦል አፍሪካን ጌምስም ይሁን ሌሎች ውድሮች ሲካሄዱ ሁሉም ነገር እንደየሀገሮቹ ሀገሮቹ ይለያያል…ይሄ የሚጠበቅ ነው…ችግሮች ቢኖሩም ችግሮቹን ለመፍታት የከተማው አስተዳደር ትልቅ ጥረት አድርጓል…ኮሚትመንታቸው በጣም የተለየ ነው…ብዙ ኢንቨስት አድርገዋል…ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ለዚህ ውድድር ማማር አፍስሰዋል… በአጠቃላይ ግን የተለያዩ ድክመቶች ሊኖሩ ይችላሉ…እየተማርንባቸው፣እያረምናቸውና እየተስተካከሉ ይሄዳሉ ብዬ አምናለሁ…

ሀትሪክ፡- …የድሬደዋ ሙቀት ለተጨዋቾቹ አመቺ አይደለም የሚለው ሌላኛው ወቀሳ ነው…ለዚህስ የምትሰጠኝ መልስ ምንድነው…?…

አቶ ክፍሌ፡- …የድሬደዋ የመወዳደሪያ ሰዓት እና አየሩ እንደውም ከእስከዛሬው ለተጨዋቾቹ በጣም አመቺው ነው…ተጨዋቾች ሙቀቱ አያሰጋቸውም….

ሀትሪክ፡- …(ድንገት አቋረጥኩት)…አቶ ክፍሌ ቅሬታው እኮ የቀረበው ከተጨዋቾቹ ነው…በተለይ ወደ ሜዳ ለመግባት የሚያሟሙቁበት ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ያለው ሙቀት በጣም ከባድ ነው እያሉ ነው የሚያማርሩት…አንተ ደግሞ በተቃራኒው ምቹ ነው ትላለህ…?…

አቶ ክፍሌ፡- …የሰዓት ለውጥ ያደረግነው ይሄን መሰሉ አቤቱታ እንዳይቀርብ ነው…የመረጥናቸው የጨዋታ ሰዓቶች ለተጨዋቾቹ ምቹ ናቸው ሙቀት አያሰጋቸውም ስል በማስረጃ ነው… …. ምክንያቱም የሚጫወቱት በ16 እና 17 ድግሪ ሴንት ግሬድ ውስጥ ነው…ይሄንን አየር ደግሞ በየትኛውም ከተማ አግኝተውት አያውቅም…ግን በደፈናው የማማረር ነገር አለ…ከዚህ በፊት በሌሎች ከተማ ከነበረው የተሻለ ነው ማለት አችላለሁ…ደግሞም ሙቀት ነው ብሎ ማማረር አይገባኝም… የኢትዮጵያ ብ/ቡድን እኮ ኮትዲቯር ላይ በ36 እና 37 ድግሪ ሴንትግሬድ ውስጥ ነው የተጫወተው… ይሄንን ለምንድነው መሄድ ያለብን…ደግሞም ሙቀት አንድና ሁለት ክለቦችን ብቻ አይደለም የሚመለከተው ለሁሉም እኩል ነው…እያንዳንዱ ነገር የተሟላ (Perfect) እንዲሆን ከፈለግን የሀገሪቱና የክለቦች የስፖርት ደረጃ ከፍ ማለት አለበት…በሚቀጥለው አመት ኮቪድ-19 የሚጠፋ ከሆነ ክለቦች በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጪ ነው የሚጫወቱት…ከዚህ አንፃር ክለቦች ቢያንስ እንኳን ሜዳ ማዘጋጀት አለባቸው…እኛ የክለቦችን ቅሬታ ለማስወገድ ወርደን ሜዳ እስከማስተካከልና ውሃ እስከማጠጣት ሁሉ ደርሰናል…ይሄንን የምናደርገው ለክለቦች ምቹ እንዲሆን…ጨዋታው የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ስለሚያገኝ የተሻለ ገፅታ እንዲኖር በማሰብ ከሥራችን ውጪ እስከመስራት ደርሰናል…

ሀትሪክ፡-…የመብራት (ፓውዛ) ጉዳይም አንደኛው በችግር መልክ ሲነሣ የነበረ ነገር ነው…በዚህ ችግር የተነሣም ጨዋታ ያልተላለፈበት ሁኔታ ነበር…ይሄስ አያስወቅስም ትላለህ…?…

አቶ ክፍሌ፡- …በመጀመሪያ ለመውቀስ ብቻ ሣይሆን የተሠራ መልካም ነገር ካለ መልካሙን ነገር እናወድስ…በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ የምሽት ጨዋታ ተካሄዶ አያውቅም…አልፎ አልፎ የተካሄደበት አጋጣሚ ቢኖርም መብራት የሚጠፋበት ጊዜም ነበር…በድሬደዋ ግን ፕሪሚየር ሊጉ በምሽት (በመብራት) ተካሄዶ አዲስ ታሪክ ተፅፏል…የመብራት (ፓውዛ) ጉዳይ ችግር የነበረው ለአንድ ቀን ነው…እሱም በነጋታው ተፈቷል…የስታዲየም መብራቱ (ፓውዛው) በጣም ምርጥ ነው…በስርጭት ባለሙያዎች ተፈትሾ ማረጋገጫ ተገኝቶበት ነው ወደ አገልግሎት የገባው…ለምሣሌ የአዲስ አበባ ስታዲየምን ብትወስድ ተለክቶ በስርጭት ሙያተኞች ብቁ ነው ብለው ያረጋገጡት አይደለም.. የድሬዳዋውን ብትወስድ ግን…ሱፐር ስፖርት የታወቀ የብሮድካስት (የቀጥታ ስርጭት) ተቋም ነው… የእነርሱን የቀጥታ ስርጭት ደረጃ (ስታንዳርድ) አሟልቶ ብቁ ሆኖ ያለፈ ነው…የመጀመሪያው ያልተላለፈው እኮ ስታንዳርዱን ስላላሟላ ነው…በመሣሪያ መለካትና ተጨዋቾች እየተጫወቱበት ማየት የተለያየ ነው…በሰዓቱ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን ባይኖርም ተቀርጾ በነጋታው አየር ላይ የዋለበት ሁኔታ ነው የነበረው…ከዚህ ከመብራት ጋር በተያያዘ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና የስፖርት ኮሚሽኑ በጣም ሊመሰገኑ ይገባል…ችግሮችን በመቅረፉ በኩል ትልቅ ጥረት አድርገዋል…

ሀትሪክ፡- …ድሬዳዋ በኮቪድ ስርጭት ከሀገሪቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ተከትሎ እንዲሁም በርካታ ተጨዋቾች፣ዳኞች፣አሰልጣኞች በተደጋጋሚ የኮቪድ 19 ምልክት የሚገኝባቸው ከመሆኑ አንፃር ሊግ ካምፓኒው ለምን አንድ ነገር አያደርግም…?…በዚህ ሁሉ የኮቪድ ሥጋት ውስጥ ሆኖ ውድድር እንዴት ያካሄዳል…?…በሰው ህይወት ለምን ቁማር ይጫወታል…?…ሰው እስኪሞት ነው የሚጠብቀው…?…በማለት አምርረው የሚወቅሷችሁ አሉ…ወቀሳውን ትቀበለዋለህ…?…

አቶ ክፍሌ፡- …በፍፁም አልቀበለውም…በዚህ ደረጃ ያውም እስከሞት በሰው ህይወት ላይ እስከመጫወት ያደረሰ አንድም ነገር አላጋጠመም…ማጋጣም አይደለም ህይወትን እስከማጣት ደረጃ የሚያደርስ ምልክት እንኳን አላየንም…እንደ እኔ እንደ እኔ…እንደዚህ አይነት የተጋነነ ነገር ውጥ እናንተም መግባትም ማራገብም የለባችሁም…በኮቪድ የሚያዘው ተጨዋች፣አሰልጣኝ ወይም ዳኛ ብቻ አይደለም… ኮቪድ እኮ ስፖርት ላይ ብቻ አይደለም የመጣው…የሚያጠቃውም እነሱን ብቻ አይደለም…የአንተ አነጋገርና ጥያቄ ግን እንደዛ የሆነ ያህል ነው..ኮቪድ ካልተጠነቀቁ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍልን እንደሚያጠቃው ተጨዋቾችም፣ዳኞችም፣አሰልጣኞችም ካልተጠነቀቁ ሊጠቁ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል…እኛ ከዚህ በፊትም በተለያየ መድረክ ደጋግመን ገልፅናል…ስፖርተኞች ራሣቸውን የመጠበቅ ከቫይረሱ የመከላከል ስራን መስራት አለባቸው…ማንኛውም ህብረተሰብ ማስክ እንደሚያደርገው፣ርቀቱን እንደሚጠብቀው፣በውሃና በሳኒታይዘር እንደሚጠቀመው እነሱም መጠቀም… ቫይረሱን መከላከል አለባቸው…እኛ ይሄንን ነው የምንመክረውና ማድረግ የምንችለው…እንደውም በዚህ ዙሪያ አንድ ነገር ልንገርህ…?…

ሀትሪክ፡- …ምን….?…

አቶ ክፍሌ፡- …እንደውም ከኮቪድ-19 ፕሮቶኮል አንፃር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በጣም ጠንካራ ሥራ የሠራና ለሌሎች ተቋማትም ልምድ የሚሆን ነው…

ሀትሪክ፡- …(ድንገት አቋረጥኩትና)…ጭራሽ…?…በርካታ ዳኞች፣ተጨዋቾች፣አሰልጣኞች ሳይቀሩ በኮቪድ ተያዙ የሚል ዜና ብርቅ ባልሆነበት ሁኔታ እንደዚህ ብሎ መናገር አያስገምትም…እንደዚህ ለማለየት ያበቃህ ምንድነው…?…

አቶ ክፍሌ፡- …በመጀመሪያ ደረጃ የኮቪድ-19 ጭርጭትን ለመከላከል ተመልካች ወደ ስታዲየም አይገባም…ሁለተኛ ተጨዋቾች በየጨዋታው ይመረመራሉ…በቫይረሱ መጠቃት አለመጠቃታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አቅርበው ነው ወደ ውድድር የሚገቡት…ፕሪሚየር ሊጉን የሚመሩ 100 የሚሆኑ ዳኞች አሉን…እነሱም በተመሳሳይ ተመርምረው ነፃ ሲሆኑ ነው ወደ ውድድር የሚገቡት… በምርመራ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ራሳቸውን እንዲያገሉ ይደረጋል…የሀኪም ውጤት ሲያመጡ ወደ ውድድር ይመለሳሉ…በዚህ ደረጃ የሠራው ማነው…?…በላ መልስልኛ…?…

ሀትሪክ፡- …የኮቪድን ፕሮቶኮል በአግባቡ በመተርጎሙ በኩል ከእኛ ውጪ የለም እያልክ ነው…?…

አቶ ክፍሌ፡- …ከእኛ ውጪ የሚል ቃል አልወጣኝም…አንድ ያለው እውነት ግን ሌሎች መጥተው ከእኛ ልምድ መውሰድ በሚችሉበት ደረጃ ላይ ነን…እውነት እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ ትላልቅ ውድድሮች ሲካሄዱ በቴሌቪዥንም በአካልም እናይ የለም እንዴ…?…ድሬዳዋስ ሌላ ውድድር እየተካሄደ አይደለም እንዴ…?…የትኛው ነው የኮቪድ ፕሮቶኮልን ጠብቆ የተካሄደው…?…ብትል መልስ የሚሰጥህ የለም… ከዚህ አንፃር እኛ በጣም የተሻልን ነን…ይሄንን የምናገረው በድፍረት ነው…

ሀትሪክ፡- …ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ሲዳማዎች 27 አዳማ ከ11 በላይ ተጨዋቾች በኮቪድ በመያዛቸው አነስተኛ ተጨዋች ለተያዘበት አዳማ ፎርፌ ሊሰጥ ነው በሚል ሲናፈስ ነበር…በድጋሚ ምርመራ የሲዳማ ተጨዋቾች ነፃ ባይሆኑ ኖሮ ፎርፌ ነበር የሚሰጠው…?…

አቶ ክፍሌ፡- …አንድ ክለብ አብዛኛው ተጨዋቹ በኮቪድ በመጠቃቱ ተሟልቶ ወደ ሜዳ መግባት ካልቻለ ከፎርፌ ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም…ይሄንን አስመልክቶ 13ቱም ክለቦች በተገኙበት የፀደቀ ደንብ አለ…የእኛ ብቻ አይደለም በፊፋ ህግም አንድ ቡድን በኮቪድ ምክንያት ከሰባት ተጨዋቾች በታች ይዞ ከቀረበ ፎርፌ ነው ይላል…ስለዚህ ፎርፌ ነው…ይሄንን የምለው እኔ ሳልሆን ደንቡ ነው…

ሀትሪክ፡-…ኮቪድ ባለመጠንቀቅ ብቻ የሚመጣ አይደለም…የተጠነቀቁ ከቤታቸው ሳይወጡ የተያዙ እንዳሉ እያየን እየሰማን ነው…ከበሽታው ተለዋዋጭነትና ባህሪ አንፃር እንዲሁም የፊፋን ህግ እንዳለ በመተርጎም ወደ ፎርፌ መሄድን ለምን መረጣችሁ…?…ጨዋታውን ማራዘም የሚቻልበትን አማራጭ መከተልን ለምን አልመረጣችሁም…የሚል ጥያቄን ባስከትል መልስህ ምንድነው…?…

አቶ ክፍሌ፡- …መጀመሪያ ደንቡን 13ቱም ክለቦች ባሉበት ስናፀድቅ ያየነው ባልኩህ እይታ ነው…እኛ ደንቡን አዘጋጅተን 13ቱን ክለቦች ባሉበት ተወያይተንበት ይሄ ያስኬደናል ብለው ደንቡ ፀደቀ…አሁን ለምን ይሄ አይሆንም…?…ለሚለው ይሄን ማድረግ የእኛ ስልጣንና ኃላፊነት አይደለም…13ቱም ክለቦች ተሰብስበው በድጋሚ ማስተካከያ ያላደረጉበት ነገር ላይ እኛ አንገባም…በእኔ ስሜት ወይም በአንድ አመራር ፍላጎት እንደዚህ ይደረግ ማለት አይቻልም…ምናልባት መስተካከልም አለበት ከተባለ ሊስተካከል የሚችለው ክለቦች የጉዳዩን አሳሳቢነት አሳማኝ በሆነ መልኩ በደብዳቤ አቅርበው እንደገና ሲታይ ነው እንጂ…አሁን ላይ ምንም የሚደረግ ነገር የለም…በደንቡ መሠረት ነው የምንሄደው…ከዚህ ይልቅ ክለቦች ተጨዋቾች ራሣቸውን እንዲጠብቁ መምከር፣ማስተማርና መከታተል አለባቸው…

ሀትሪክ፡- …አሁንም በርካታ ዳኞች፣ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ተያዙ የሚለውን ዜና ከድሬዳዋ መስማት ብርቅ አይደለም…ይሄን የታዘቡ ሊጉ ድሬደዋ ላይ በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቁ ላይ ጥርጣሬውና ሥጋቱ አላቸው…አንተስ እንደ ሊግ ካምፓኒ የድሬዳዋው ውድድር ሊቋረጥ ይችላል የሚል ስጋት በውስጥህ አለ…?…

አቶ ክፍሌ፡- …በፍፁም…!…እኛ በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት ያልቃል ብለን ነው የምናምነው… ደግሞም ሥራ የምትሰራው በሥጋት አይደለም…በሥራ ሂደት ችግር ቢመጣ አንኳን መፍትሔ ትፈልጋለህ እንጂ ዝም ብለህ አትቀመጥም…ከዚህ በኋላ ሶስት ዙር ጨዋታ ወይም 10 እና 12 ቀን አካባቢ ነው የቀረን…ከዚህ አንፃር ላይጠናቀቅ ይችላል ብለን አንሰጋም…

ሀትሪክ፡-…ከድሬዳዋ ቀጥሎ የሊጉን ውድድር የማስተናገድ ኃላፊነትን የምትረከበው ሀዋሳ ናት…ሀዋሳ ደግሞ ኮቪድ-19 በስፋት የተስፋፋባትና ከሀገሪቱ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ናት…በድሬዳዋ የተፈጠረው መተራመስ እዛም እንዳይከሰት ምን አይነት የጥንቃቄ እርምጃ እየወሰዳችሁ ነው…?…

አቶ ክፍሌ፡- …የድሬዳዋው ትልቅ ልምድ የወሰድንበት ነው…እስከ አሁን በአዲስ አበባ፣ጅማና ባህር ዳር ባደረግናቸው ውድድሮች ኮቪድ ለእኛ ፈተና አልነበረም…ድሬዳዋ ላይ ግን በዚህ በኩል ክፍተት አይተናል…ስለዚህ ከኢትዮጵያ የማህበረሰብ ጤና ጋር በመሆን የተሻለ ነገር እንሠራለን…ከዚህ ሁሉ በፊት ግን ተጨዋቾች፣ዳኞች፣አመራሮች፣አሰልጣኞች ሁሉም ራሣቸውን መጠበቅ ነው ያለባቸው… በተለይ ተጨዋቾች ዋነኛ ተዋናዮች ከመሆናቸው አንፃር ራሣቸውን መጠበቅ አለባቸው…በድሬደዋ ብዙ የታዘብኳቸው ነገሮች አሉ…በድሬደዋ ብዙ ማህበረሰብ አለ…ተጨዋቾቹ ሶስት አራት ቀን ያለ ማስክ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቀለው ያየሁበት አጋጣሚ አለና ይሄ በጣም መታረም አለበት…ስለዚህ ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን ማስተማር፣ራሣቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ አለባቸው…በድሬደዋ ካለው የተሻለ ሥራ ለመስራት እየተዘጋጀን ነው…በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ቡድን ከወዲሁ ወደ ሀዋሳ ሄዶ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያየ ነው…ሥራውን ቀድመን ጀምረናል…የተነሱትን ችግሮችም እንቀርፋለን ብዬ አስባለሁ…

ሀትሪክ፡-ሌላው በዚህ አጋጣሚ ልጠይቅህ የምፈልገው የውድድር ኮሚሽነሮች ፕሮቶኮልን በተመለከተ ነው…የኮሚሽኖሮች ፕሮቶኮል ወጥነት ይጎለዋል…አንዳንዱ በጃኬት፣አንዳንዱ በሸሚዝ፣አንዳንዱ ደግሞ ሙሉ ሱፍ ለብሶ በተዘበራረቀ መልኩ ይታያሉ…ከዚህ አንፃር የተሻለ ፕሮቶኮል እንዲኖር ያሰባችሁት ነገር አለ…?…

አቶ ክፍሌ፡- …የሚገርምህ ነገር ይሄንን እኛም አስበንበታል…ጨዋታው የቀጥታ ስርጭት ከመሆኑ አንፃር በተሻለና ወጥነት ባለው ፕሮቶኮል መቅረብ መልካም ነው…ይሄንን ታሳቢ በማድረግ በአገራችን ከሚገኝ አንድ የሙሉ ልብስ አምራች ድርጅት ጋር ግንኙነት በማድረግ ውይይት ጀምረን ነበር…ለእነሱም ትልቅ ማስታወቂያ ነው…ነገር ግን እኛ ካለብን የተደራረበ ሥራና ውስን የሰው ኃይል አንፃር ብዙም አልሄድንበትም እንጂ እየሞከርን ነው…በቀጣይ ይበልጥ ገፍተን በመሄድ የምንደርስበትን የምናሳውቅ ይሆናል…፡፡

ሀትሪክ፡- …ክፍሌ ለነበረን ጊዜ አመሰግናለሁ…?…

አቶ ክፍሌ፡- …እኔም እንግዳ ስላደረጋችሁኝ ምስጋናዬ የበዛ ነው…

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.