“ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ባህርዳር ላይ ተጀምሮ ባህርዳር ላይ ቢያልቅ ኖሮ ቡና ሻምፒዮና የሚሆንበት እድሉ ሰፊ ይሆን ነበር”ዊሊያም ሰለሞን /ኢትዮጵያ ቡና/

የኢትዮጵያ ቡናው ዊሊያም ሰለሞን በዘንድሮው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ቡድናቸው ጥሩ እንደሆነ በመግለፅ የአንድአንድ ሜዳዎች ለጨዋታ ምቹ አለመሆንና ጥቃቅን ችግሮች ለጣሏቸው ነጥቦች ምክንያት እንደሆኑ ገልጿል። ከዚህ ተጨዋች ጋር ስለ ዛሬው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ስለ ቡድናቸውና ስለ ራሱ አቋም ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ምላሹን ሰጥቷል።

ለሸገር ደርቢው ስላደረጉት ዝግጅት እና ስለሚገጥማቸው ውጤት

“ከቅዱስ ጊዮርጊስ ላለብን ጨዋታ ያን ያህል ዝግጅትን አላደረግንም፤ እንደሌሎች ግጥሚያዎችም ነው ትኩረትን ያደረግንበት። ይህ ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ በመሆኑም የበላይነታችንን በተጋጣሚያችን ላይ ለማሳየትና 3 ነጥባችንን አሳክተን በመውጣትም ሁለተኝነታችንን ለማስጠበቅ ዝግጁ ሆነናል”።

ሸገር ደርቢው ያለተመልካች

“ሸገር ደርቢን በተመልካች ከዚህ ቀደም አላውቀውም። ሲባል እንደሰማሁት ግን እነሱ ኖረው ብንጫወት የበለጠ ጥሩ ይሆንልን ነበር። አሁንም ግን ይህን ደርቢ ጨዋታ ያለ እነሱ የምንጫወት መሆኑ ቢያስቆጨንም እንዳሉ አድርገን ለመጫወትና ጣፋጭ ድልንም ለማስመዝገብ ዝግጁ ነን”።

በሸገር ደርቢ ላይ ተሰልፎ ስለ መጫወት

“በዚህ ጨዋታ ላይ ተሰልፎ መጫወትን እኔ የልምምድ ያህልን እና በጣምም አቅልዬ ነው የማየው። እርግጠኛም ነኝ ጥሩ እንቅስቃሴንም በማድረግ ክለቤን ለውጤት እንዲበቃ አደርገዋለሁ”።

የኢትዮጵያ ቡና ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጉዞ

“ዘንድሮ ምርጥ ነን፤ ጥሩ እግር ኳስንም በመጫወት እንለያለን”።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከመሪው ፋሲል ከነማ በነጥብ እንዲርቁ ስላደረጋቸው ነገር

“የአንድአንድ ሜዳዎች ምቹ አለመሆን፣ የአየር መቀያየር እና ራሳችን የምንሰራቸው ጥቃቅን ችግሮች ለጣልናቸው ነጥቦች ምክንያት ሆነው ከፋሲል ከነማ በነጥብ እንድንርቅ አድርጎናል። የሊጉ ጨዋታ ተጀምሮ እስኪያልቅ ባህርዳር ላይ ቢሆን የእኛ ቡድን ይሄኔ ሊጉን ከመምራት ባሻገር ሻምፒዮና መሆኑም አይቀርም ነበር”።

አሁንስ ሻምፒዮና አትሆኑም?

“የሊግ ውድድሩ ገና በርካታ ግጥሚያዎች ናቸው የሚቀሩት። የእኛም ዋንጫ የማንሳት እድላችን አላከተመም። እስከመጨረሻ ያሉትን ግጥሚያዎቻችንን በማሸነፍ የሚመጣውን ውጤት እንጠባበቃለን”።

በኢትዮጵያ ቡና ስላለው ቆይታ

“እስካሁን ከሚገባው በላይ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለእዚህ ቡድን መጫወት መቻሌም መታደልም ነው”።

በምርጥ አቋሙ ላይ ይገኝ እንደሆነ

“በፍፁም፤ በዛ ደረጃ ላይ አይደለሁም። አሁን ኳሱን ገና ጀመርኩ ብዬም አላስብም። አቅሜ ከዚህ በላይም ነውና ወደፊት ነው እኔን ማየት”።

በቤትኪንጉ አሁን ላይ ስላላቸው ህልም

“ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዘመን ቆይታው አሁንም ከዋንጫው ፉክክር ያልወጣ በመሆኑ እድሉን እስከመጨረሻው ግጥሚያ ድረስ ይጠብቃል። ይሄ ባይሳካ እንኳን ቡድኑ የግድ በአፍሪካ ክለቦች የኢንተርናሽናል ጨዋታ ላይ መሳተፍ ስላለበት ሁለተኝነቱን ደረጃ እያለመም ይገኛል”።

በመጨረሻ….

“ቅዱስ ጊዮርጊስን ዛሬ ምሽት አሸንፈን እንደምንወጣ እና ደጋፊዎቻችንንም እንደምናስደስት እርግጠኛ ነኝ”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website