የአንደኛ ዙር ድል ይደገማል አቡበከርም ሀትሪክ ይሰራል” ሬድዋን ናስር /ኢት.ቡና/

አሁንም ድረስ የደርቢው ግለቱ አልበረደም ፋሲል ከነማ ሁለቱንም የሸገር ደርቢ ድምቀቶች በርቀት እየመራ መገኘቱ የክለቦቹን ደጋፊዎች ሙቀት አላበረደውም…. ፈረሰኞቹ ከቡናማዎቹ….ነገ ምሽት 1 ሰዓት በድሬደዋ የሚፋጠጡት ሁለቱ ክለቦች ጠንካራ ትግል እንደሚያደርጉ ይጠበቃል የፈረሰኞቹ የመሀል ሜዳ ታጋይ በደጋፊዎቹ አጠራር ደግሞ “ጄኔራል” የሚሰኘው ሙላለም መስፍን /ዴኮ/ እና የኢትዮጵያ ቡናው ወጣቱ ታጋይ ሬድዋን ናስር ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበራቸው ቆይታ ይህን ጨዋታ በጉጉት እንደሚጠብቁትና ከፍልሚያው 3 ነጥብ እንደሚወስዱ እርግጠኛ የሆኑበትን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሁለቱም በየፊናቸው ለሀትሪክ የሰጡት ምላሽ ከታች ያለውን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና የ18ቱ ሳምንት አቋምን እንዴት አገኘኸው?

ሬድዋን፡-ጥሩ አቋም እንዳለን ነው የማውቀው የሚቀሩን ጥቃቅን ነገሮች ቢኖሩም… እንደአጠቃላይ ግን በ18ቱ ሳምንት ጥሩ ብቃት እንደነበረን ይሰማኛል በቀጣይ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለሁ….

ሀትሪክ፡- በደርቢ ጨዋታ ምን ውጤት ይጠበቅ…?

ሬድዋን፡- ማሸነፍ የግድ ይኖርብናል ለኮንፌዴሬሽን ካፕ ነው የምትጫቱት የሚሉ አሉ በእኛ በኩል ግን ለዋንጫውም እድል አለን…እስከመጨረሻ ድረስ እንታገላለን በደርቢ ጨዋታውም ድሉ የኛ ነው ለዚህ ደግሞ ተዘጋጅተናል፡፡

ሀትሪክ፡- የአንደኛው ዙር ድል ይደገማል እያልክ ነው…?

ሬድዋን፡- አዎ… ለዚህ ደግሞ ጥርጥር የለኝም፡፡ በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጀን እንደመሆኑ ከጨዋታው 3 ነጥብ እንፈልጋለን፤የአንደኛ ዙር ድል ይደገማል አቡበከርም ሀትሪክ ይሰራል በያዝነው አቋምም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ብዙኃኑ የስፖርት ቤተሰብ ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫውን ለፋሲል ከነማ ሰጥተዋል ብለው ያምናሉ… አንተስ ትስማማለህ…?

ሬድዋን፡- በፍፁም አልስማማም፤ ልዩነታችን 9 ነጥብ ቢሆንም ተስፋ አንቆርጥም ለፋሲል ከነማም ዋንጫውን አልሰጠንም በኛ በኩል ቀጣዮቹን ተጋጣሚያዎቻችንን ለማሸነፍ እንጥራለን እንደሚሳካም እርግጠኛ ነኝ….ፋሲል ከነማ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ነጥብ መጣሉ ስለማይቀር በደንብ እንጠጋለን ብዬ አስባለሁ፤ ዋንጫውን የማግኘት እድሉም ለኛ ክፍት ነው ብዬ ስለማምን ቀጣዮቹ ጨዋታዎችን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡

ሀትሪክ፡- ከፋሲል ከነማ በ9 ነጥብ ለመረቃችሁ ዋነኛ ምክንያት የፋሲል ከነማ ጥንካሬ ወይስ የኢትዮጰያ ቡና ድክመት…?

ሬድዋን፡- በርግጠኝነት መናገር የምችለው እኛም መጣል የሌለብንን ጨዋታ ላይ ነጥብ መጣላችን ነው የጎዳን… የፋሲል ከነማም ጥንካሬ መረሳት የለበትም… ዋንኛ ምክንያት እኛ የጣልናቸው ነጥቦች ናቸው ርቀቱን የፈጠሩት ባይ ነኝ፤ ለማንኛውም ቀጣዮቹ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ ላለመጣል እንጥራለን፡፡

ሀትሪክ፡- በ33 ነጥብና 15 ግብ 2ኛ ናችሁ ከተከታያችሁ ባህርዳር ከተማ በ3 ነጥብ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በ6 ነጥብ በልጣችሁ መገኘታችሁን ስታይ 2ኛ ሆናችሁ ለኮንፌዴሬሽን ካፕ እንደምታልፉ መገመት ይቻላል…?

ሬድዋን፡-በዋናነት ለፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ነው የምንፎካከረው እያልኩህ እንዴት ስለ ሁለተኛነቱ እንሰጋለን? በቻልነው መጠን ፋሲል ከነማ ላይ ጫና አድርገን የሊጉን ዋንጫ ለማሸነፍ እንጥራለን ነገር ግን ሁለተኛ ሆነን የኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎ ማግኘታችን የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡናና ደጋፊዎቹ ይሄ ሲያንሳቸው ነው እያልኩህ ነው…

ሀትሪክ፡- የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ተጨዋች ላንተ ማነው…?

ሬድዋን፡-/ሳቅ/ ይሄማ ቀላል ጥያቄ ነው በእስካሁኑ የሊጉ ምርጥ ተጨዋች አቡበከር ናስር ነው በ22 ግብ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል የግብ አግቢነቱን ሪከርድ የማሻሻል አቅምም አለው ብዬ መናገር እችላለሁ…

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን እንዴት አገኘኸው…?

ሬድዋን፡- ምርጥ አሰልጣኝ ነው… ለወጣቶች እድል የሚሰጥና ወጣቶች ላይ የሚያምን አሰልጣኝ ነው፤ ሁሉም ተጨዋች በካሳዬ ላይ እምነቱ አለው ለኛ ክብር ያለው ጥሩ አሰልጣኝ መሆኑ ያስደስታል… በርሱ ስር በመሠልጠኔ ደስተኛ ነኝ፤

ሀትሪክ፡-የ2013 ፕሪሚየር ሊግ ከተካሄደባቸው ከአራቱ ከተሞች ላንተ ትልቅ ታሪክ ያለው የትኛው ነው?

ሬድዋን፡- ባህርዳር ላይ ነዋ… ምርጥ ስታዲየም አሪፍ የልምምድ ሜዳ ያለው በመሆኑ ሜዳ ላይ በጥሩ ሁኔታ አሳልፈናል ከዚያም ውጪ በውጤትም ካየነው የባህርዳሩ ቆይታችን የተሻለ ነበር

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ቃል… ?

ሬድዋን፡-ደጋፊዎቻችን ማመስገን እፈልጋለሁ በነርሱ ደስተኞች ነን የነርሱ ድጋፍ ያስፈልገናል እንደ ሁሌውም ከጎናችን ሆነው እንደሚደግፉን እርግጠኛ ነኝ… በተቻለ መጠን በአፍሪካ ደረጃ ለመሳተፍና እነሱን ለማስደሰት እንጥራለን…፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport