“ኢትዮጵያ ቡና በአንደኛ ዙር ያሳካውን ድል በፍፁም አይደግመውም” ሙላለም መስፍን /ዴኮ/ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

አሁንም ድረስ የደርቢው ግለቱ አልበረደም ፋሲል ከነማ ሁለቱንም የሸገር ደርቢ ድምቀቶች በርቀት እየመራ መገኘቱ የክለቦቹን ደጋፊዎች ሙቀት አላበረደውም…. ፈረሰኞቹ ከቡናማዎቹ….ነገ ምሽት 1 ሰዓት በድሬደዋ የሚፋጠጡት ሁለቱ ክለቦች ጠንካራ ትግል እንደሚያደርጉ ይጠበቃል የፈረሰኞቹ የመሀል ሜዳ ታጋይ በደጋፊዎቹ አጠራር ደግሞ “ጄኔራል” የሚሰኘው ሙላለም መስፍን /ዴኮ/ እና የኢትዮጵያ ቡናው ወጣቱ ታጋይ ሬድዋን ናስር ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበራቸው ቆይታ ይህን ጨዋታ በጉጉት እንደሚጠብቁትና ከፍልሚያው 3 ነጥብ እንደሚወስዱ እርግጠኛ የሆኑበትን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሁለቱም በየፊናቸው ለሀትሪክ የሰጡት ምላሽ ከታች ያለውን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስን የ18 ሳምንት ጨዋታ እንዴት አገኘኸው?

ሙላለም፡- ክለባችን ሊያሳካ ፈልጎ ከተነሳበት አላማ አንፃር ካየነው አልተሳካም ከሽፏል ማለት ይቻላል በርግጥም የአመቱ ፍፃሜ ገና ቢሆንም እስካሁን ባለው ጉዞ ያልተሳካ አመት ልንለው እንችላለን ግብ የነበረው ዋንጫ ማሸነፍ ነው ባለፉት 3 አመታት ምንም ዋንጫ ካላማንሣታችን ጋር ተያይዞ ከአፍሪካ መድረክ በመራቃችን 2013 በድል የማጠናቀቅ አላማ ነበረው ያንን ለማሳካት ትንሽ ከበድ የሚል ሁኔታ ላይ ነው የምንኘኘውና ያልተሳካ ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሀትሪክ፡- እሁድ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባላለባችሁ የደርቢ ጨዋታ ላይ ምን ውጤት ትጠብቃለህ…?

ሙላለም፡- ኢትዮጵያ ቡና በአንደኛ ዙር ያስመዘገበውን ድል በፍፁም አይደግመውም ብዬ ነው የማስበው በኛም በኩል በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅተናል ተቀራራቢ ነጥብ እንደመያዛችን የሚቻለንን አድርገን በኢትዮጵያ ቡና ላይ ያለንን የበላይነት ለማስመለስ እንጥራለን፡፡

ሀትሪክ፡- ከኮቪድ 19 መከላከል ጋር ተያይዞ አሁን ያለው የመከላከል አቅማችሁ ምን ይመስላል…?

ሙላለም፡- ካምፕ ውስጥ ነው ያለነው ወደ ውጪ የምንወጣበት አጋጣሚም የለም፡፡ ደብረዘይት የሚገኘው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ካምፕ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ ከግቢው ባለመውጣታችን ከኮቪድ 19 ስጋት ነፃ ሆነን ነው ልምምዳችንን ስንሰራ የነበረው፡፡

ሀትሪክ፡- ዋንጫው ለፋሲል ከነማ ሰጣችሁ….?

ሙላለም፡-/ሳቅ/ አልሰጠንም… መጨረሻ ላይ ግን ሊግ ካምፓኒው ነው ሊሰጥ የሚችለው /ሳቅ/ እኛ በቁጥር ስሌት ዋንጫውን አንስቷል እስኪባል ድረስ የምንችለውን እናደርጋለን፡፡ በርግጥ የፋሲል ከነማ ጥንክሬም ይሁን የኛ ድክመት አመቱ ለኛ ጥሩ አልነበረም፡፡ በርግጥ ፋሲል ዘንድሮ ጠንካራ ሆኗል ከኛ ብቻ 6 ነጥብ ወስዷል መጣል የሌለብንን ብዙ ነጥቦች ጥለናል ይህም ጎድቶናል የፋሲል ጥንካሬና የኛ ተዳክሞ መቅረብ ለፋሲል ከነማ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖለታል፡፡

ሀትሪክ፡-ለጣላችሁት ነጥብ መጣል ኃላፊነቱ የማን ይሆናል?

ሙላለም፡- አብዛኛው ነገር የተወሳሰበ ነው፤ ብዙ ጊዜ ቁጭ ብለን ለመነጋገር ሞክረናል ጉዳዩ ምንም ይሁን አብዛኛው ድርሻ የተጨዋቹ ነውና ኃላፊነቱ የኛ ነው… በተወሰነ መልኩ የአሰልጣኞቹ ቅይይርና ቋሚ ቡድን አለመኖሩ እንደምክንያት ይቀርባል በየጨዋታው ስትገባ ነው ለውጥ የሚኖረውና በየጨዋታው ተጨዋች መቀያየሩ ወጥ የሆነ ነገር ማሳየት አልቻልንም፡፡ ለተፈጠረው የውጤት ማጣት ግን የአብዛኛው ተጨዋች ኃላፊነት ይመስለኛል?

ሀትሪክ፡- 2ኛ መሆን ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ የመካፈል እድል ይፈጥራልና ቢያንስ መፅናኛ አለን ትላለህ….?

ሙላለም፡- ብዙም አልራቅንም ከእጃችንም አልወጣም እድሉ አለን ብዬ አስባለው በርግጥም አንደኝነትን ለሚፈልግ 2ኛነት መፅናኛ ነው ደርቢውን ደግሞ የግድ እናሸንፋለን፡፡

ሀትሪክ፡- የ2013 የሊጉ ምርጥ ተጨዋች ማነው….?

ሙላለም፡- በዘንድሮ የውድድር አመት ብዙዎችን እንዳስገረመው ልዩ ተጨዋች የሆነብኝ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ነው… ልዩ ብቃቱን እያሳየ ነው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ ማነው ኮከቡ?

ሙላለም፡- በኔ በኩል ሄኖክ፣ ጌታነህና ግብ ጠብቂያችን ባሩህ አሪፍ ነበሩ… አንድ ምረጥ ካልከኝ ግን ሄኖክ አዱኛ ጥሩ አመት አሳልፏል፡፡

ሀትሪክ፡- አዲስ አበባን ጨምሮ 4 ከተሞችን አይታችኋልና ይሄ አገርህን እወቅ አልተመቸህም…?

ሙላለም፡-/ሳቅ/ ሀገርህን እወቅ ይመቻል ሌላ ክልል ሄደን 1 ወር መቀመጥ አልተለመደም በእርግጥ ትንሽ የማሰልቸት ነገር አለው ከአራቱ ከተሞች የተሻለ የነበረው በየትኛውም መመዘኛ ባህርዳር ነው በመጫወቻው ሜዳም ሆነው በልምምድ ሜዳ ባህርዳር ስታዲየም ብዙ ነገር ተሟልቶለታል ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡-ለደጋፊዎቹ የምትለው ነገር አለ…?

ሙላለም፡- ለደጋፊዎቹማ ብለን ብለን ደከመን አሁን ላይ ምንም ለማለት ይከብዳል ብዙ ነገር አልናቸው እንከሳችኋለን አልን ሌላም ሌላም… ግን አልሆነምና ምንም ማለት ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ሻምፒዮንስ ሊጉ ቢቀር ኮንፌዴሬሽን ካፑ ላይ ለመገኘት የሚቻለንን እናደርጋለን በርግጥ ደጋፊዎቻችን ሁለተኝነትን በምንም መንገድ የሚቀበሉ አይደሉም የሚዋጥላቸውም አይደሉም፡፡

ሀትሪክ፡- ዘንድሮማ ሁለተኝነት ትርጉም አለው…. ከሌላው ጊዜ አንፃር ሁለተኝነት ዘንድሮ የሚጠላ አይመስለኝም?

ሙላለም፡- አዎ በርግጥ በጣም ትርጉም አለው በእጃችን ያለው ሁለተኝነትን ለማሳካት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን በተወሰነ መልኩ መካሻ ከሆነም ቡድኑን እንደገና ወደ አፍሪካ መድረክ ለመመለስ እንጥራለን፡፡

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ጥያቄ… ትዳርን እንዴት አገኘኸው… ባል የመሆን ትርጉሙስ…?

ሙላለም፡- /ሳቅ በሳቅ/ ምን ባክህ የባልነት ኃላፊነቴን አላየሁትም ማለት ይቻላል ለማውራትም ይከብደኛል ከባለቤቴ ጋር ተጋባን… በሳምንቱ ወደ ቡድኑ ተቀላቀልኩና እስካሁን አልተመለስኩም እረፍት የነበረውም ትንሽ ስለነበር በሚገባ ስለባልነት ላወራ አልቻልኩም ባለቤቴ አዜብን በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ በጣም እንደምወዳት መናገር እፈልጋለሁ ትዳር ውስጥ የገባችሁ ይህን ሁሉ አውቃ ነውና መውደዴን ማክበሬን ልገልፅ እፈልጋለሁ /ሳቅ/

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport