“እግር ኳሱ ጋር ያለው ሽኩቻና መጠላለፍ መቆም አለበት” “የእኛ ተጨዋቾች እንደ ኢትዮጵያ ብር ለሀገር ውስጥ ብቻ ነው የሚያገለግሉት እንደ ዶላር ከሀገር ውጪም መስራት አለባቸው”ግርማ ሳህሌ ከፈረንሳይ

 

እግር ኳሱ ጋር ያለው ሽኩቻና መጠላለፍ መቆም አለበት”

“የእኛ ተጨዋቾች እንደ ኢትዮጵያ ብር ለሀገር ውስጥ ብቻ ነው የሚያገለግሉት እንደ ዶላር ከሀገር ውጪም መስራት አለባቸው”

ግርማ ሳህሌ ከፈረንሳይ

 

ዛሬ ሀትሪክ ባህር፣ድንበርና ርቀት ሳይገድባት አህጉር አቋርጣ ወደ ምዕራብ አውሮፓዊቷ የወቅቱ የአለም ሻምፒዮና ወደ

ሆነችው ፈረንሣይ አንድ የቀድሞ የእግር ኳሱን ባለውለተኛ ፍለጋ ጎራ ብላለች፤ በፋሽን ኢንዱስትሪው፣በወይን ምርቶቿና

በቱሪስት መስህብነቷ ተለይቷ በምትታወቀው ፈረንሣይ በፓሪስ ከተማ ላለፉት 28 አመታት ኑሮውን ያደረገውን የቀድሞ

የመብራት ኃይል፣የመኩሪያ፣የመቻል፣የፔፕሲ፣የሸዋ ምርጥና የኢትዮጵያ ብ/ቡድን ተጫዋች የነበረውን ግርማ ሳህሌን

ፍለጋ፡፡

በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በዋናነት ከመሠረቱት አንደኛውና ፌዴሬሽኑን ላለፉት 16 አመታት

በቴክኒክ ዳይሬክተርነትና በህዝብ ግንኙነት በመምራት ፌዴሬሽኑ አሁን ለደረሰበት ስኬታማ ጉዞ ስሙ በዋናነት ከፍ ብሎ

የሚነሣው የቀድሞው ባለውለተኛ ተጫዋች ግርማ ሣህሌ የኢትዮጵያ እግር ኳስ መቼም ከማይዘነጋቸው በድንቅ

ጥበባቸውና በውለታቸው ስማቸውን ከፍ አድርጎ ከሚያነሳቸው ተጫዋቾችም አንዱ ነው፡፡

የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ባህርና ድንበር ሳይገድበው ሀገር አቋርጦ በስልክ

ሞገድ አሳብሮ በአየር በረራ ከ5,575.09 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን…በሰው ሀገር ቢኖርም ሁሌም የሀገሩ

እግር ኳስ ጉዳይ የሚያንገበግበውን ግርማ ሳህሌን አግኝቶ ትናንትን በዛሬ መነፅር ሊያስቃኘን የ The Big Interview

እንግዳ አድርጎ አቅርቦታል፡፡

ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ከግርማ ሳህሌ ጋር በነበረው የስልክ ቆይታ በተጫዋችነት ስላሳለፈባቸው ክለቦች፣ስለነበረው

ፉክክርና ስለገጠመኙ ብቻ ሣይሆን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ይበጃል ያለውን ሃሣብ በነፃነት አንስተው ያደረጉትን ቆይታ

ከዚህ በታች ባለው መልኩ ተቀናብሮ ቀርቧል፤ አብራችሁን ወደ ፈረንሣይ ዝለቁ፡፡


ሀትሪክ፡- …በመጀመሪያ ድንበርና ርቀት ሳይገድበን…ሀገር አቋርጠን ላቀረብነው ጥያቄና ለቃለ- ምልልሱ ፍቃደኛ

ስለሆንክ…በአንባቢያን ስም ማመስገንን አስቀድሜያለሁ…?

 

ግርማ ሣህሌ፡- …እናንተም ካለሁበት አፈላልጋችሁ…ለሀገሬ የሰራሁትን ትንሽ ነገር አስታውሳችሁ…ዋጋ

ሰጥታችሁ…የሀገርህ እግር ኳስ ይመለከትሃል ብላችሁ…ሃሳቤን እንዳካፍል መድረኩን ስለሰጣችሁኝ እኔም ሀትሪኮችን

ከልብ አመሰግናለሁ…ጥሩ ነገር እየሰራችሁ ነው…በርቱ ለማለትም እወዳለሁ…፡፡

ሀትሪክ፡- …ኮስተር ወደ አለ ጥያቄ በቀጥታ ከምንገባ…ለማሟቅ…አንባቢን ዘና ለማድረግ ያህል …ከገጠመኞችህ እንጀምር

እስቲ…?

 

ግርማ ሣህሌ፡- …በጣም ደስ ይለኛል…

ሀትሪክ፡- …መቻል እያለህ…ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስትጫወቱ…የቅዱስ ጊዮርጊሱ አለማየሁ ኃይለስላሴ(ፊኛ)…በመቻል

ተጨዋች ተገጭቶ የተናገረው ቀልድ ዛሬም ድረስ ብዙዎች በግርምት ያነሱታል…እስቲ እሱን አጋጣሚ በማንሣት…ቆይታችንን

በይፋ እንጀምረው… ?

 

ግርማ ሣህሌ፡- …(በጣም ሳቅ)… ይሄንን ደግሞ ማነው የነገረህ…(አሁንም ሳቅ)…እንዳልከው እኔ መቻል

እየተጫወትኩ ነው…ጨዋታችን ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነው…ብዙ ተመልካች በእኛ የጨዋታ ጊዜ ሜዳ ውስጥ

ዝም ብለን የምንጫወት ይመስለዋል…ግን አይደለም…ሜዳ ውስጥ ያለው ተረብ፣ምላስ ከጨዋታው የበለጠ የከበደ

ነበር…(ሣቅ)…የቃላት ጦርነቱን ልነግርህ አልችልም…ታዲያ አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰለህ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት

የሚመራው ጋሽ ተስፋዬ ገ/የሱስ ነው…በወቅቱ ደግሞ ደርግ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል መፈክር

ነበረው…አንድ የመቻል ተጫዋች ጋሽ ተስፋዬ ገ/የሱስ ሳያይ አለማየሁ (ፊኛን) ይገጨዋል…በዚህን ጊዜ የአለማየሁ

(ፊኛ) ከንፈሩ ደም በደም ይሆናል… በኃላ ፊኛ ደሙን እየዘራ ወደ ዳኛው ይሮጥና…“…ጋሽ ተስፋዬ…ጋሽ

ተስፋዬ…ተመልከት ደም በደም እንዳደረገኝ…እነዚህ ሰዎች መፈክራቸው [ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም]

ነው…እዚህ ግን የሰው ደም ያፈሳሉ ሲለው…(ያላባራ ሳቅ)…ጋሽ ተስፋዬም ሁላችንም ብንደነግጥም ሳቃችንን

መቆጣጠር ግን አልቻልንም…ሁኔታውን በቅርበት ሲከታተል የነበረው አምበላችን ሙሉጌታ ብርሃኔ…አለማየሁ ተናግሮ

ሳይጨርስ ምን ቢለው ጥሩ ነው… (ሳቅ)…

 

ሀትሪክ፡- …ምን አለው…?

 

ግርማ ሣህሌ፡- …(ሳቅ)…ስሟ አለማየሁ…ይህቺን የተናገርክበትን ምላስህን ከጫወታው በኋላ ቀበሌ ወርደህ ስትታሰር

ትደግማታለህ…ጨዋታው ሲያልቅ እንገናኝ…ሲለው…አለማየሁ ምን ውስጥ ይግባ…(በጣም ሣቅ)…ምክንያቱም

አምበላችን ሙሉጌታ በወቅቱ መቶ አለቃ ነበረ… መቶ አለቃ ደግሞ ያኔ የፈለገውን ሰው ወስዶ ቀበሌ ውስጥ ያስር

ነበር…ያ አጋጣሚ በተነሳ ቁጥር ሁሌም እንደ አዲስ ነው የሚያሰቀን…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …የመብራት ኃይል አሰልጣኝ የነበሩት…አመለ ሸጋውና ስኬታማው አሰልጣኝ ሀጎስ ደስታ ጋር…(ነፍሳቸውን

ይማረው)…በጨዋታ ዘመናቸው ከአንተ ጋር ገጠመኝ እንዳላቸውም ሰምቼ ስቄያለሁ…እስቲ እሱንም እናንሳ…?

 

ግርማ ሣህሌ፡- …(በጣም ሳቅ)…ማነው ይሄን ሁሉ መረጃ የሰጠህ…?…(አሁንም ሳቅ)…ትክክል ነህ…ይሄ ደግሞ

ከአየር ኃይል ጋር ስንጫወት ነው…ለአየር ኃይል በተከላካይ ቦታ ሀጎስ ደስታ የሚባል ተጨዋች ነበር…እንዳልከው በኋላ

ላይ የመብራት ኃይል አሰልጣኝ ሆኖ ብዙ ሥራ ሠርቷል…እንዳልኩህ ሐጎስ ተከላካይ ነው…እኔ ደግሞ የምጫወተው

በክንፉ በኩል ነው…ኳስ አግኝቼ በተደጋጋሚ ላጠቃ ስል…እንዴት ያንቀሳቅሰኝ…ወጥሮ ያዘኝ…ወጥሮ መያዝ ብቻ

አይደለምበዚያ ላይ ይኮረኩመኛል…ይገጨኛል…ሲገጨኝ ደግሞ እንዲህ ቀላል ግጭት መሰለህ…ልክ በብረት የመታኝ ያህል

በጣም ያመኝ ይደነዝዘኝ ነበር…እየገጨም እየመታም አላንቀሳቀስ ማለቱ በጣም አበሳጨኝ…በኳስ አታልዬ

 

እንዳላልፈው አልቻልኩም…በጉልበትም ልቋቋመው አልቻልኩም…ብቻ ምን አለፋህ ከጨዋታ ውጪ አደረገኝ…በዚህን

ጊዜ ይሄንን ሰውዬ እንዴት ነው ማለፍ የምችለው…?…ብዬ ራሴን ስጠይቅ አንድ ሃሣብ መጣልኝ…

 

ሀትሪክ፡- …ምን አይነት ሃሳብ…?

ግርማ ሣህሌ፡- …ሐጎስ ኤርትራዊ ነው…ለምን ኤርትራዊነቱን አንስቼ አላበሳጨውም እልና…ጠጋ ብዬ…ስማ

አንተ…!…ኤርትራዊ ዘመዶችህ እዛ ለአናት ሀገራቸው ይዋጋሉ…አንተ እዚህ ቂጥህን ገልበህ ትሮጣለህ…አንተ የማትረባ

ስለው…(በጣም ሳቅ)… አበደ…“ቧ…አንተ… ምናምን…ብሎ በትግርኛ ተሳደብ…በጣም ነርቨስ ሆነ…ከዚያ በኋላ

ጨዋታው ሁሉ ጠፋበት…(ሳቅ)…እኔም ስጫወት የነበረው በ7 ቁጥር ቦታ ነበር ወደ 11 ቁጥር ቦታ ቀየርኩ… እሱ

በብስጭት እኔን ሲፈልግ…የእኛ ተጨዋቾች በእሱ ቦታ የማጥቃት እድል አገኙ…ይሄም አጋጣሚ መቼም

አይረሳኝም…ከሜዳ ላይ ጨዋታ በተጨማሪ የጭንቅላት ጨዋታም እንደምንጫወት የሚያሳይ ነው…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …በክለብ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ታቅፈህ የተጫወትከው በወቅቱ “መኩሪያ” በሚል ለሚጠራው እግር ኳስ ክለብ

ነው…?

 

ግርማ ሣህሌ፡-  ጃንሜዳ አስፓልት ላይ እንጫወት ነበር፤ያኔ ወታደሩ እንዳለ ከቦን ነበር ጨዋታችንን የሚከታተለው ነበር…እዛ ስንጫወት ጨዋታችንን ሲከታተሉ የነበሩት የግርማ አስመሮም እህት ባል የነበሩት ሻምበል

ተክለሃይማኖት ይባላሉ…እሣቸው ስጫወት ያዩኝና በጣም ያደንቁኛል…በዚህም ሳያበቁ…በመሀል ይጠሩኛል “…አንቺ

ልጅ…በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነሽ…አንቺ መጫወት ያለብሽ እኛ ጋ ለመኩሪያ ቡድን ነው…”…ይሉኛል…በዚህን ጊዜ

በውስጤ በጣም ደስታም…በጣም ፍርሃትም ተፈጠረ…

 

ሀትሪክ፡- …ለምን…?

 

ግርማ ሣህሌ፡-…ለመኩሪያ ቡድን እንድጫወት በመምረጣቸው ትልቅ እድል ስለሆነ በጣም ተደሰትኩኝ…ነገር ግን

መኩሪያ የወታደር ቡድን ስለሆነ…እንዴ ወታደር ልንሆን…?…ልዘምት…ነው እንዴ…?…ብዬ…በልጅነት አዕምሮዬ

ፈራሁ…በዚህ የተነሳ እሺም እምቢ ስላላልኳቸው የተዘበራረቀ ስሜት በውስጤ መፈጠሩን ተረድተው ነው መሰለኝ

“…አይዞሽ በወታደርነት ተቀጥረሽ አይደለም፤በሲቪል ተቀጥረሽ ኳስ ለመጫወት ብቻ ነው…” ሲሉኝ መናገር አቅቶት

የነበረው አንደበቴ ተከፈተ…በወታደርነት ተቀጥሬ…ኳስ ለመጫወት ብቻ ከሆነማ በጣም ደስ ይለኛል

አልኳቸው…እሳቸውንም በመገናኛ ክፍል ገብተህ ኳስ ብቻ ትጫወታለህ አሉኝ…ባሉት መሠረትም ለመኩሪያ

ለመጫወት ተስማማሁ…ገባሁ…ግን ስገባ የገጠመኝና የተፈጠረውን ነገር ተወው…(ሣቅ)…

 

ሀትሪክ፡- …ምን… ተፈጠረ…?

 

ግርማ ሣህሌ፡- …እንዳልኩህ የገባሁት በተጫዋችነት ለኳስ ብቻ ነው ተብዬ ነበር…ስገባ ግን ነገሮችን እንደነበረ ሣይሆን

እንዳልነበረ ሆኖ ነው ያገኘሁት…በተጫዋችነት ለኳስ ነው የተቀጠርከው የተባልኩትን ልጅ ደብረብርሃን ወስደው ለ6 ወር

በስልጠና ልባችንን አጠፉት…ለ6 ወር ደብረብርሃን ለስልጠና ሲወስዱኝ…እንዴ ምን እየሰራችሁ ነው…?…ለኳስ ነው

የምትገባው ለወታደርነት አይደለም አላላችሁኝም እንዴ? ለእግር ኳስ ተጫዋች ወታደራዊ ስልጠና ያውም ለ6 ወር ምን

ያደርግለታል? ስንላቸው.. “አይ ኳስ ተጨዋች ብትሆኑም የምትጫወቱት ለወታደር ቡድን በመሆኑ ወታደራዊ ስነ-

ሥርዓት ማወቅ ስልጠና መውሰድ አለባችሁ” አሉን…ምንም ማድረግ አልቻልንም…6 ወር ሙሉ ወታደራዊ ስልጠና

ወሰደን… ስልጠናውን ግን አልነግርህም…በጣም ከባድ ነበር…ግን በጣም ነው የተማርንበት…ከስልጠና ስንመለስ

የመኩሪያን ቡድን ተቀላቅዬ መጫወት ጀመርኩ…፡፡

ሀትሪክ፡- …ወደ መብራት ኃይልስ እንዴት ተዛዋወርክ…?

ግርማ ሣህሌ፡- …የመኩሪያ ቡድን እንዳልኩህ የወታደር ቡድን ነው…የወታደር ቡድን ከሲቪል ቡድኖች ጋር ታቅፎ

መጫወት የለበትም የሚል ሕግ ስለነበር ከሌሎች ክለቦች ጋር ታቅፈን በስታዲየም የመጫወት እድሉ

አልነበረንም…በዚህ የተነሣ ሌላ ክለብ ተዘዋውሮ የመጫወት ሃሣብ በውስጤ ነበር…ለዚህ ደግሞ የቅርብ አማራጬ

የነበረው መብራት ኃይል ነው…መብራት ኃይሎች በወቅቱ ልምምድ የሚሰሩት ጃንሜዳ ነበር…መጫወት እንደምፈልግ

ጠየኳቸው… ሳያመነቱ ወዲያው ተቀበሉኝ…መብራት ኃይል ቢ ቡድን ገባሁ…ግን መብራት ኃይል ቢ ቡድን አንድ አመት

ያህል እንደተጫወትኩ…አንድ ያልታሰበ ሌላ ነገር ተፈጠረ…

 

ሀትሪክ፡-…ምን ተፈጠረ…?

 

ግርማ ሣህሌ፡- …መብራት ኃይል ጥሩ እየተጫወትኩ ሳለ…የወታደር ቡድን ከሲቪል ቡድኖች ጋር አብሮ መጫወት ይችላል

የሚል ሕግ ወጣ…በዚህን ጊዜ መኩሪያዎች በድጋሚ ወደ ክለቡ እንድመለስ ፈለጉ…በተለይ ሻምበል ደነቀው መንግሥቱ

የሚባሉ ሰው ነበሩ…እሣቸው ያቺ 12 ቁጥር ጎበዝ ናት…ለምን እሷን ከመብራት ኃይል መልሰን አንወስዳትም አሉ…እኔ

ግን መመለሴ ቢያስከፉኝም መብራቶች ያኔ በወቅቱ ዘመናዊ ትጥቅ ለተጨዋቾቻቸው ይስጡ ነበር… ለእኔም አዲዳስ

ጫማ፣አዲዳስ ቦርሣና አዲዳስ ቀይ ቱታ ተገዝቶ ሊሰጠኝ ሲል ነበር መኩሪያዎች

የጠየቁኝ፤ያንን የመሰለ ትጥቅ ሳልወስድ ብዬ በጣም ተበሳጨሁ፤ ምክንያቱም የአዲዳስ ትጥቅ መልበስ በወቅቱ

በጣም ብርቅ ነበር፤በቃ በትጥቁ እንደጎመዥሁ ሳይሳካልኝ ሙከሪያ ገባሁ፡፡

 

ሀትሪክ፡- የመኩሪያ የመጀመሪያ ጨዋታህ እንዴት ነበር?

 

ግርማ ሣህሌ፡- የሚገርምህ የመጀመሪያ ጨዋታችን ከመቻል ጋር ነበር፤በጣምም ከባድ ጨዋታም ነበር፡፡ ግን ለእኔ

የእግር ኳስ ህይወት ትልቅ በር የከፈተም ነው፤ መቻልን 4ለ3 ስናሸንፍ የመጀመሪያውንም የመጨረሻውንም ግብ

ያስቆጠርኩት እኔ ነኝ፤ በዚህ ጨዋታ ጥሩ በመንቀሳቀሴ ለሸዋ ምርጥ በተደጋጋሚ የመመረጥ እድልም አግኝቼበታለሁ፡፡

በነገራችን ላይ ለሸዋ ምርጥ ከአራት ጊዜ በላይ የተመረጥኩት መኩሪያ እያለሁ ነው፤ በእኛ ጊዜ ለሸዋ ምርጡና

ለብ/ቡድን ለመመረጥ የነበረው ተጋድሎ እንዲህ ቀላል አይመስልህ…

ሀትሪክ፡-.. ያን ያህል በጣም ከባድ ነበር ማለት ነው?

 

ግርማ ሣህሌ፡-በጣም ከባድ ብቻ?…. በሳር የተሠራ ጎጆ ቤት ታውቃለህ…?

 

ሀትሪክ፡- … አዎን አውቃለሁ…?

 

ግርማ ሣህሌ፡-ከዚያ ጎጆ ቤት ውስጥ ካሉት ሣሮች ውስጥ አንዷን መዞ የማውጣት ያህል ነው፤ እንደው የእድል ሎተሪ

በለው… በቃ እንደዛ ነው፤ ምክንያቱም በየቦታው ያሉት ተጨዋቾች ፉክክር በጣም ከባድ ነበር፤ አሰልጣኞች ሁሌም

ችግራቸው የትኛውን መርጠን የትኛውን እንተወዋለን የሚለው ነው፤ ካሳሁን ተካ፣ ሰለሞን ሽፈራው፣ አስራት ኃይሌ፤

ቀፀላ፣ ስዩም አባተ፣ መሐመድ ሸርዳድ፣ ፍቃደ ሙለታን የመሳሰሉ ምርጥ ተጨዋቾች አሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ

ለመሆን መቻልና ለብ/ቡድን መመረጥ መታደልም ነው፤ ለዚህ ነው ከሳር ጎጆ ውስጥ አንድ ሳር የመምዘዝ ያህል ነው

የምልህ፡፡

 

ሀትሪክ፡-መኩሪያ እያለህ በጦር ሠራዊት ቡደኖች መካከል የላይ ቤት የታች ቤት በሚል የምትጠራሩበት ነገር ነበር አሉ፤…

እሱስ…?

 

ግርማ ሣህሌ፡-… (በጣም ሳቅ).. እውነት ነው የላይ ቤት የምንባለው እኛ ነን… ምክንያቱም እኛ የጃንሆይ ጠባቂዎች

ክቡር ዘበኞች ነን፤ በየቀኑ በግና በሬ እየታረደልን የምንቀለብ ነን፤ የታች ቤት የሚባሉት ደግሞ ጦር ሠራዊቶች

ናቸው…እንደ እኛ አይቀለቡም፤በኋላ ላይ እነ ቼንቶ ግብፅ ላይ ሲጠፉ…መቻል የመግባት እድል አገኘሁ፤የ68ቱ ውድድር

ወደ 69 ተዛወረ፤ መቻል ከቅ/ጊዮርጊስ ለነበረበት ጨዋታ ተመርጬ ለዝግጅት ወደ ደብረዘይት ሄዱኩኝ፤ ዝግጅታችንን

ጨርሰን ለጨዋታ መጣን፤ እንዳልኩህ ጨዋታዎችን ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ነው…ተሰለፍኩኝ በዚህ ጨዋታ ሶስት ፔናሊቲ

ነው ያሰገኘሁት፤ ጨዋታውን የሚመራው ደግሞ አየለ ጅቦ ነበር፤ በጨዋታው 30 ደቂቃ ተጨምሮ 3ለ3 በመለያየታችን

ወደ መለያ ምት (ፔናሊቲ) ስናመራ እኔ አልመታም አልኩኝ…

 

ሀትሪክ፡- …ለምን…?

 

ግርማ ሣህሌ፡- …አንደኛ እኔ ለመቻል አዲስ ነኝ…ከእኔ የበለጡ ሲኒዬሮች አሉ…ሁለተኛ ብስት እንኳት ሞራሌ ይነካል ብዬ

ፈራሁ…አልመታም ስል የሰማው አምበላችን ሙሉጌታ ብርሃኔ “…እኛ እኮ ያመጣንሽ ልትጫወቺ እንጂ ልትቀልጂ

አይደለም…” ሲሉኝ ደነገጥኩ…የስንት አመት ልምድ ያለው ጌታቸው (ዱላ)ግብ ክልል ውስጥ መቆሙ ራሱ

ያስፈራል…ብፈራም ግን አልቀረልኝም የግድ መምታት አለብህ ስለተባልኩ…ያበጠ ይፈንዳ ብዬ ለመምታት ወሰንኩ፤

በዚህን ጊዜ የጊዮርጊሱ አለማየሁ (ፊኛ) ለአምበላችን ምን ይለዋል “ኳሱን አላገባውም፤ እስተዋለሁ” ብሎኛል ብሎ

ይነግረዋል…በዚህን ጊዜ አዕምሮዬ ተሰረቀ…ኳሱን ስመታ የፈራሁት አልቀረም….

 

ሀትሪክ፡-…ሳትከው…?.

 

ግርማ ሣህሌ፡- …(ሣቅ)…የፈራሁት አልቀረም…ጌታቸው (ዱላን) ብሸውደውም…በእግሩ እንደምንም ብሎ አዳነብኝ በቃ

በዚያን ሰዓት ሰማይና ምድሩ ዞረብኝ፤ሜዳ ላይ ተዘረርኩ የጊዮርጊስን ደጋፊዎች ተደስተው ችቦ አበሩ (ጋዜጣ ለኮሱ)

ስታዲየሙ የተቀጣጠለ መሠለ፤ ቀጣይ መቺ ጊዮርጊሶች ነበሩ…መቼው ደግሞ ስዩም አባተ ነበር…ስዩም ኳሱን

ሲመታው ሳተው…ይሄ ሁሉ ሲሆን እኔ አላይም…የእኛ ሲመታ ደግሞ አገባ…የጊዮርጊሱ ተስፋዬ የሚባል ተጨዋች

ነበር…እሱ ደግሞ አንዴ ሲለው ሰማይ ሊነካ ምንም አልቀረው…ኳሱ ወጣ…ቀጣዩ የእኛ መቺ አረፋይኔ ምትኩ

ነበር…እሱ ሲመታው ጌታቸው (ዱላን) በግራ ልኮ ኳሱን በቀኝ ከተተው…ጊዮርጊስን አሸንፈን ዋንጫውን

ወሰድነው…በጣም ተደሰትኩ…ለቅሶዬም ጠፋ…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …እንደዚህ አይነት ደስታን ካገኘህበት መቻልስ እንዴት ወጣህ ታዲያ…?

 

ግርማ ሣህሌ፡- …ለክፉ ቀን ብዬ ትምህርት እማር ነበር…ማታ ማታ ተምሬ 12 አጠናቀቅኩ…ከዚያ ኮሜርስ (ንግድ ሥራ

ት/ቤት) ገባሁ…እዛም ሶስት አመት ተምሬ ጨረስኩ.. መቻል አምስትና ስድስት አመት ያህል ተጫውቻለሁ፤የተሻለ

ነገር ፍለጋ መውጣት አለብኝ አልኩና አንድ ዘዴ ዘየድኩኝ…አንድ የማውቃት ልጅ ነበረች…እናቷ ሆስፒታል ነው

የሚሠሩት…አባቷ ደግሞ ጄኔራል ናቸው…በኋላ ይህቺን ልጅ ቀጠርኳትና ከጦሩ መውጣት እፈልጋለሁ…ለዚያ ደግሞ

የአንቺና የቤተሰቦችሽ ድጋፍ ያስፈልገኛል አልኳት…ልጅቷም ባልኳት መሠረት እናቷን ጠየቀችልኝ…ባሰብኩት መሠረትም

ተባብረውኝ ቦርድ ወጣሁ…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …ከመቻል ወጥተህ ፔፕሲ ነው የገባኸው ፤የፔፕሲ አገባብህስ…?

 

ግርማ ሣህሌ፡-…ከመቻል ከወጣሁ በኋላ ECA ነው ሥራ የገባሁት፤ በቃ ኳሱን ተውኩትና እዛ ተቀጠርኩ…ምክንያቱም

እዛ ደሞዙ ጥሩ ነበር…በወር ወደ 230 ብር አካባቢ አገኝ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ይሄ ትልቅ ደሞዝ ነው…12ተኛ

ክፍልም…ኮሜርስም ተምሬ በመጨረሴ የሚሰባበር ቢሆንም በእንግሊዘኛ ስለማልታማ (በጣም ሳቅ) እዛ ገባሁ፤

ECA ውስጥ የአግሪካልቸር ኃላፊ የነበረች ሴት አለች የእሷ ሾፌር ነበርኩ፤ በጣም ቆንጆ ቀይ ፔጆ መኪና ይዤ ነበር

በከተማው የምፈሰው፤ በዚህ መሀል አንድ ቀን ከአለማየሁ (ፊኛ) ጋር መንገድ ላይ እንገናኛለን፤ እሱ ያኔ የፔፕሲ

አሰልጣኝ ነበር…“እንዴ አንቺ አለሽ እንዴ? ለምንድነው ኳስ የማትጫወቺው?” ሲለኝ አይ እኔ እንኳን ጫካ ገብቻለሁ

ስለው…“ነይ እኛ ጋ ተጫወቺ?” ሲለኝ ደሞዝ ስንት ነው የምትከፍሉት?…“125 ብር ነው፤በጣም ብዙ ብር ነው”

ሲለኝ አይ ተወው ECA 230 ብር ነው የሚከፍለኝ አልኩት…“ችግር የለም ለገንዘቡ፤ከደሞዝሽ ሌላ መኪና ተሰጥቶሽ

ከሽያጭ ከመኪና ዘጠኝ ብር ታገኝያለሽ እሱ ሲጠራቀም ብዙ ነው ይለኛል” እንደዚህ ከሆነማ እልና ኳስም በጣም

ስለምወድ ደመዜን ቀንሼ 125 ብር ክፍያ ፔፕሲ ገባሁ፤ወር ላይ ደመወዜን አያለሁ አለማየሁ ቃል የገባልኝ የሽያጩ

ብር የለም…ከዛሬ ነገ ይጨምሩልኛል ብዬ ባይ ባዬ ምንም ነገር የለም፤ በዚህም በጣም ተበሳጨሁ፤

 

ሀትሪክ፡-…ለምን ሳይጨመርልህ ቀረ…?

 

ግርማ ሳህሌ፡- …አላውቅም ብቻ በዚህ መሀል እያለን ከቅ.ጊዮርጊስ ጋር ሱሉልታ ጨዋታ ነበረን፤ኦኬሎ የሚባል የእነሱ

ተጨዋች ሲያገባ እኔም አገባለሁ…እሱ ሲደግም እኔም እደግማለሁ…በዚህ መሀል እያለን የመጨረሻ አንድ ኳስ

አገኛለሁ…እኔ ብዙ ጊዜ የምታወቀው በቴስታ ግብ በማስቆጠር ነው…ኳስ ስትመጣ ከማግባት ይልቅ ለመሣት

የምትከብድ ኳስ አገኘና ሁሉም አገባት ብሎ ሲያስብ እንዴት እንደሣትኳት እስከአሁን ባላወቅሁት ሁኔታ ኳሷን

ሳትኳት…በዚህ ጊዜ አለማየሁ (ፊኛ) “አንተ የማትረባ እንዴት ይሄንን ያለቀለት ኳስ ትስታለህ? “ ብሎ ሲጮህብኝ

ከመደንገጥ ይልቅ ውስጤ ያለው ብሶት ገንፍሎ ምን እንዳልኩት ታውቃለህ…?

 

ሀትሪክ፡-…ምን አልከው…?

 

ግርማ ሳህሌ፡- …(በጣም ሳቅ)…ዞር አልኩና…ስማ በ125 ብር ደሞዝ ከዚህ በላይ እንዴት ነው የምዘለውና

የማገባው?…(አሁንም ሳቅ)…በ125 ብር ከዚህ በላይ አያዋጣም አልኩት…እሱም በምላሹ ከመቆጣት ይልቅ

ደነገጠና ወዲያውኑ አስተዳደር ቢሮ ገብቶ “ይሄ ልጅ እኮ ጉድ አደረገኝ ቶሎ ጨርሱለት ብሎ” አነጋግሮ መኪናውም

ተሰጠኝ ደሞዜም ወደ 600 ብር አደገ፤

 

ሀትሪክ፡- 600 ብር ከገባህ በኋላ ግብ ማግባት ጥሩ መጫወት ጀመርክ…?

 

ግርማ ሳህሌ፡- በጣም እንጂ..ደሞዜ ወደ 600 ብር ካደገ በኋላ ባደረግናቸው ጨዋታዎች ላይ በጣም

ጥሩ…ለማሸነፋችንም ምክንያት ነበርኩ፤አንድ ጊዜ መልበሻ ቤት ውስጥ ሰብስቦን በየተራ ስማችንን እየጠራ “እከሌ

በጣም ጥሩ ነህ… እከሌ ደግሞ ዛሬ አልተቻልክም፤ ሌላውን ተጨዋች ደግሞ አንተ ዛሬ እንደጠበኩህ አይደለህም… እያለ

እየመከረ እኔጋ ይደርሳል.. ከዚያ የእኔን ስም ይጠራና ግርማ ሳህሌ ዛሬ በጣም ልዩ ሆነህ ነው የዋልከው” ሲለኝ እንዴ

አለማየሁ ትቀልዳለህ እንዴ 600 ብር ደሞዝ ገባሁ እኮ… 600 ብሩ ነው ይሄንን የሰራው አልኩት (በጣም ሳቅ)

 

ሀትሪክ፡- በጨዋታ ዘመንህ ከእግርህ ይልቅ በጭንቅላት (በቴስታ) የምታስቆጥራቸው ጎሎች ይበዙ ነበር ይባላል እውነት ነው?

 

ግርማ ሣህሌ፡-… እውነት ነው፤ ያገባኋቸውን ጎሎች ብታይ አብዛኛው በእግር ሣይሆን በጭንቅላት የተቆጠረ ነው፤

የሚቀናኝም እሱ ነው፡፡

 

ሀትሪክ፡- የዚህም ምክንያት ምንድነው ማለት እንችላለን?

 

ግርማ ሳህሌ፡- በዚህ በኩል እንደ ሮል ሞዴል የማያቸው በቴስታ የተካኑ ተጨዋቹ ነበሩ፤ እነ ሰለሞን ሸፈራው ተስፋዬ

(ወሎ) እና ቀፀላ በጣም በጭንቅላት ግብ በማስቆጠር የሚታወቁ ተጨዋቾች ናቸው፤ ሠለሞን ሽፈራው ሲጫወት

ብታየው በቴስታ እንኳን ፊት ለፊት ወደ ጎን ሁሉ የሚመታ የተለየ ተሰጥኦ ያለው ተጨዋች ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ

እንደ እነሱ አይነት በቴስታ ግብ የሚያገባ ተጨዋች አላየሁም…ወደፊትም ስለመፈጠሩ አላውቅም፡፡ ከእነደዚህ አይነት

ተጨዋቾች በተጨማሪ በወቅቱ “ቢግ ሊግ ሶኮር” በሚል ከሚተላለፈው የእንግሊዝ እግር ኳስ ተጨዋቾች የተማርኩት

ነው፤የቴስታውን አነሳሁልህ እንጂ እኔ ክሮስ በማድረግም ነው የምታወቀው፤ለተከላካዮች ፈተና…ለአጥቂዎቻችን ግን

ለግብ የተመቻቸ… ጣጣውን የጨረሰ ክሮስ ነበር የማደርገው…ገና ኳስ አግኝቼ ወደ ክንፍ ስወጣ…የእኛ አጥቂዎች

የማደርገውን ስለሚያውቁ ተመቻችተው ነው የሚጠብቁት…ቦታቸውን እኔም አውቀዋለሁ… እነሱም የት

እንደምጥልላቸው ያውቃሉ…ክሮስ የምታደርገው ዝም ብለህ በአቦ ሰጡኝ ሳይሆን በመናበብ ነው…በተለይ አህመድ

አብደላ በዚህ በኩል ከእኔ ጋር በጣም ይናበብ ነበር፡፡

 

ትሪክ፡- በጨዋታ ዘመንህ መቼም የማልረሣት የምትላት ግብ…?

 

ግርማ ሳህሌ፡- …ቅድም አንስቼልሀለሁ…ከመቻል ጋር ስንጫወት ያስቆጠርኳቸው የመጀመሪያና የመጨረሻ ሁለት ግቦች

የተለየ ቦታ አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- …የጨዋታ ዘመንህ ምርጥ ተጨዋች የምትለውስ…?

 

ግርማ ሳህሌ፡- …ውይ ማንን ጠርቼ ማንን ልተው…?ሁሉም ምርጦች ነበሩ…አህመድ አብደላ…?…አንዱን

ነጥዬ እንዳልጠራ ሁሉም በየቦታቸው ምርጦች ናቸው፤ለማንሣት ያህል ሰለሞን ሽፈራው፣ተስፋዬ (ወሎ) ካሳሁን

ተካ፣ኧረ ብዙ ናቸው ይቅርብኝ…እንደው በደፈናው በጣም ምርጥ ምርጥ ተጨዋቾች ነበሩ ብል ይሻለኛል፤ከአሁኖቹ ግን

የጌታነህ ከበደ አድናቂ ነኝ፡፡

 

ሀትሪክ፡- …አላንቀሳቅስ ብሎ ሲያስቸግርህ የነበረ ተጨዋችስ…?

 

ግርማ ሳህሌ፡- …ሐጎስ ደስታ…በኋላ ላይ የመብራት ኃይል አሰልጣኝ የነበረው…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …በአሳዛኝነት የምታነሣው ገጠመኝህ…?

 

ግርማ ሳህሌ፡- …በጣም ብዙ ገጠመኞች አሉኝ…ግን አሁን ድንገት ትዝ ያለኝን ገጠመኝ ልንገርህ…ለብ/ቡድን ተመርጠን

ወደ ግብፅ ለመሄድ ሁለት ቀን ቀርቶናል…በወቅቱ አውሮፕላን ላይ ወጥቼ ስለመሄዴና ስለሚሰጠን ዶላር እያወጣን

እያወረድን ባለበት ሰዓት እኔና ታምራት የሚባል ከአንበሳ የተመረጠን ተጨዋች በአለማየሁ (ፊኛ) ሲቀንሱን

የተበሳጨንበትን ጊዜ በአሳዛኝነቱ የማነሳው ነው…እንደውም በጣም ከመበሳጨቴ የተነሣ ያኔ አንድ የአሜሪካን ዶላር

በ2.50 ሳንቲም ነበር የሚመነዘረውና በጣም ከመበሳጨታችንም የተነሣ እንዴት ልክ እንደ ዶላር ሁለት ተጫዋቾችን

በአንድ አለማየሁ ትመነዝሩናላችሁ ብለናቸዋል፤ምክንያቱም እኛ ወደ ግብፅ ለመሄድ በጣም ጓጉተናል፤በዚያ ላይ በቀን

5 ዶላር በወር 150 ዶላር አካባቢ ታገኛለህ በዚያን ጊዜ ትልቅ ገንዘብ ስለነበር በጣም ተበሳጨን፡፡

 

ሀትሪክ፡- …በጨዋታ ዘመንህ የፊርማ ገንዘብስ ተቀብለህ ታውቃለህ…?

 

ግርማ ሳህሌ፡- …የምን የፊርማ ገንዘብ…?

 

ሀትሪክ፡- …አሁን ለምሳሌ ከአንድ ክለብ ወደ ሌላ ስትዛወር ወይም እዛው ስትፈርም የፊርማ ገንዘብ ተብሎ ተዘግኖ የሚሰጥ

በሚሊየን የሚቆጠር ብር አለ…እንደዛ ማለቴ ነው…

 

ግርማ ሳህሌ፡- …(ባጣም ከት ብሎ እየሳቀ) የፊርማ ገንዘብ…?…እንዴ ይስሀቅ ትሣደባለህ እንዴ…?…ይሄ እኮ

ትልቅ ስድብ ነው…በእኛ ጊዜ የመጫወቻ ቲሴራ ወይም ደሞዝ ለመውሰድ ከምንፈርመው ውጪ ፊርማ የሚባለውን

ቃል አናውቀውም…ምናልባት ክቡር ዘበኛ ስንቀጠር ፈርመናል…ከዚህ ውጪ ትልቅ ክለብ መጫወት፣ለሸዋ ምርጥና

ለብ/ቡድን መመረጥ ነው ለእኛ የፊርማ ገንዘባችን…ከዚህ ውጪ የፊርማ ተብሎ ያገኘነው ሣንቲም የለም…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …በተለያየ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለእረፍት እንደምትመጣ አውቃለሁ፤ ያም ቢሆን ከሀገር ከወጣህ ረዘም ያለ ጊዘ ነውና

እግር ኳሱን በቅርበት ትከታተላለህ?

 

ግርማ ሳህሌ፡- ..በጣም እከታላለሁ…እድሜ ለቴክኖሎጂ የእናንተም ዌብሳይት አለ…በሌላ መንገድም መረጃ

አገኛለሁ…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …ብ/ቡድኑ ከ31 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ ስሜትህ እንዴት ነበር…?

 

ግርማ ሳህሌ፡- …በጣም ነው የተደሰትኩት…በጋሽ ሰውነት ቢሻው አሰልጣኝነት ብ/ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ

እንቅልፍም አልወሰደኝም…በውስጥህ ኢትዮጵያዊ ደም ስላለ ድሉ ከውስጥህ ደስታ ፈንቅሎ እንዲወጣ የማድረግ

አቅምም ነበረው፤እኛ ባለንበት ሀገር ራሳቸው ፈረንሣዊያን፣ አረቦችና አፍሪካዊያኖች ሳይቀሩ “የእናንተስ ብ/ቡድን

መቼ ነው የሚያልፈው” እያሉ ይጠይቁናል…ያበሽቁናል…እንደውም የአፍሪካ እግር ኳስ መስራች መሆናችንን ተወው

እግር ኳስ ሁሉ የምናውቅ አይመስላቸውም፤እንደዚህ አይነት ስሜቶች በጣም ስለሚያበሳጩን ብ/ቡዱኑ ሲያልፍ የተለየ

የደስታ ስሜት ነው የተሰማን፤ በእውነት ነው የምልህ ቡድኑ ምንም ይሁን ምን በጋሽ ሰውነት ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ

አልፈን መሳተፋችን ለእኛም ለዓለም ትልቅ መልዕክት ነው ያስተላለፉት፡፡

ሀትሪክ፡- ብ/ቡድኑ ከ31 አመት በኋላ ካለፈ አሁን ስምንት አመት ሞልቶታል፤ በድጋሚ ለማለፍም አልቻልንም የዚህ ችግሩ

ምንድነው ትላለህ?

 

ግርማ ሳህሌ፡- የእግር ኳስ ስርዓታችን ወይም መዋቅሩ አልተቀየረም…የአለም እግር ኳስ ምስጢርም

አልገባንም…በአካዳሚ ላይ የማያምን…ለጊዜያዊ ውጤት የሚሮጥ እግር ኳስና መዋቅር ነው ያለን…የብዙ ሀገሮች ስኬት

ፈረንሣይን ጨምሮ ምስጢሩ የአካዳሚው ውጤቶች ናቸው…እኛ ሀገር ግን እየደከምን ሀብት እያፈሰስን ያለነው እንደዛፍ

ተንጋደው ባደጉ ተጨዋቾች ላይ ነው…ታዳጊዎች ላይ በአካዳሚ ደረጃ መዋቅር ቀይሰን ካልተንቀሳቀስን ሟርተኛ አትበለኝ

እንጂ ሌላ 31 አመት መቁጠራችንም አይቀርም…ሲስተሙ ስርዓቱ መቀየር አለበት…አካዳሚ ላይ መልፋት

አለብን፤ከዚህ ውጪ ደግሞ የእኛ ሀገር ተጨዋቾች ይቅርታ አድርግልኝና እንደ ኢትዮጵያ ብር ናቸው…

 

ሀትሪክ፡- …እንደ ኢትዮጵያ ብር ናቸው ስትል ምን ማለት ነው…?

 

ግርማ ሳህሌ፡- …የኢትዮጵያ ብር የሚሰራው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው አይደለም…?…እዚህ ጎረቤታችን ሱዳን ውስጥ

እንኳን አይሰራም ብሩ እዚሁ ሀገር ውስጥ ብቻ ነው የሚሠራው… የእኛም ሀገር ተጨዋቾች ልክ እንደ ብሩ ሀገር ውስጥ

ብቻ ነው የሚሠሩት…እንደ አሜሪካ ዶላር ሌላ ሀገር ሄደው አይሠሩም…ሌላ ሀገር ሄደው ለመጫወት እንኳን አይናቸውን

አይከፍቱም፤እነ ባዩ ሙሉ ምንም በሌለበት ዘመን ቤልጂየም ድረስ ሄደው ተጫውተዋል፤ አሁን አሁን እነ ሽመልስ

እየሞከሩ ነው…ሙከራው ጥሩ ቢሆንም ከአፍሪካ እንኳን አልወጡም፤ ስለዚህ ተጫዋቾቹን እንደ የኢትዮጵያ ብር

አገልግሎታችሁ ሀገር ቤት ብቻ አይሁን…እንደ ዶላር ሌላ ሀገር ላይም መስራት አለባችሁ ብዬ ነው የምመክራቸው…ሌላው

ሳላነሳው የማላልፈው ታዳጊዎች ያሉት ት/ቤት በመሆኑ እዛ ላይ መሰራት አለበት…የወታደሮች ውድድር

ካልዘረጋን…አካዳሚ ላይ የሚያተኩር ሲስተም ከሌለ እድገቱን መናፈቅ የለብንም፤ የፌዴሬሽን አመራሮች ወደ ስልጣን

ሲመጡ መዋቅሩን በዚህ መልኩ መቃኘት አለባቸው፤ ከዚህ ውጪ 4 አመታቸውን ቆጥረው ቢወጡ አባከኑት እንጂ

ሰሩበት ለማለት ይቸግራል፤ ቢያንስ እነሱ ወደ ስልጣን ሲመጡ የ15 አመት ልጅ ቢይዙ ከስልጣን ሲወርዱ 19 አመት

ይሞላዋል፤ ለU-20 የሚጫወት ልጅም ይሆናል፤ የዚህ አይነት አምስት ወይም አስር ልጅ ማፍራቱ ይቅር…ቢያንስ ሁለት

ልጅ እንኳን ቢገኝ እግር ኳሱ ይጠቀማል፡፡

 

ሀትሪክ፡- የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ያቀረበው ባለ 9 ነጥብ ምክረ ሃሣብ አስተዳደራዊ ሥራን በሚሰራው አመራር ውድቅ

መደረጉ እንደ አንድ የስፖርቱ ባለድርሻ እንዴት አገኘኸው?

 

ግርማ ሳህሌ፡- ይሄ እኮ ነው የእግር ኳሳችን ችግር፤ በመጀመሪያ ደረጃ የባለሙያ ሃሣብ መከበር አለበት፤ በእናንተ ጋዜጣ

ላይ የወጣው የአቶ ሰለሞን አባተን ኢንተርቪው አንብቤዋለሁ፤ ቴክኒክ ኮሚቴ እኮ የሙያተኞች ስብስብ ነው፤ እንዴት

ሙያተኛ ያልሆኑ ሰዎች የሙያተኛን ሃሣብ ውድቅ ያደርጋሉ?አስተዳደር ማለት ለፊርማና ለስፖርቱ ልማት ነው መቀመጥ

ያለበት፤ አስተዳደራዊ እየተባለ የሚሰራው ስህተት አደጋም አለው፤ሙያተኞች ናቸው ቦታው ላይ መቀመጥ ያለባቸው፤

ሰውነት ቢሻውን ብትወስድ ትልቅ አሰልጣኝ ነው እግር ኳሱንም ያውቀዋል፤ እንደእነሰ አይነት ሰዎች ናቸው ወደ ስልጣን

መምጣት ያለባቸው፤ ሰውነት ፕሬዚዳንት መሆንም ይችላል፤ ፕላቲኒን ብትወስድ ከአገሩ አልፎ የUEFA ፕሬዚዳንት

እስከመሆን ደርሷል፤ ቦታው ለሙያተኞች መተው አለበት፤ እኛ የያዝናቸው ግን ያልተጠቀምንባቸው እነ ጋሽ ሰውነት፣

አስራት ኃይሌ፣ ሁለቱን አብረሃሞች አልተጠቀምንባቸውም እንጂ ቢያንስ ብናስጠጋቸው ስፖርቱን ይጠቅማሉ ስልጣኑ

የእኔ ነው ብለህ አስተዳደሪ ነኝ ብለህ ቴክኒክ ውስጥ ከገባህ ችግር አለ፡፡

ሀትሪክ፡-የቴክኒክ ኮሚቴው አባል አቶ ሰለሞን አባተ ከሀትሪክ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ተጨዋቾች ወፍረዋል ዳሌ አውጥተዋል”

ብለው ያላቸውን ስጋት ወይም ሙያዊ አስተያየት በመስጠታቸው ፌዴሬሽኑ ለቅጣት እንዳዘጋጃቸው እየተሰማ ነው ይሄንንስ

ታዝበሃል?

 

ግርማ ሳህሌ፡- እንዳልኩህ አቶ ሰለሞን የሰጠውን አስተያየት አንብቢዋለሁ፤ ከአቶ ሰለሞን ጋር ፔፕሲ አብረን

ስለተጫወትን በቅርበት አውቀዋለሁ፤ የሰጠው አስተያየት ችግሩ ምን እንደሆነ የሚያስረዳኝ አላገኘሁም፡፡ ተጨዋቾቹ

ወፍረዋል፤ ዳሌ አውጥተዋል ማለት ችግሩ ምንድን ነው? ሰው እንዴት እንደተረዱት አልገባኝም እንጂ ሰባት ወር

ስለተቀመጡ፣ ስፖርት የለመደ አካላቸው ከዚያ ውጪ ስለሆነ ሰውነታቸው ላይ ለውጥ ይመጣል፤ ይወፍራሉ ነው ሃሳቡ፤

ይሄ ደግሞ የሚያሳግድ፣ የሚያስቀጣም አይደለም፤ ምክንያቱ እንኳን እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ተጨዋቾችን ተወውና

ማንኛውም ሰው 7 ወር ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆኖ ቢቀመጥ መወፈሩ አይቀሬ ነው፤ እኔ እንደገባኝ ሰለሞን ለማለት

የፈለገው ይሄንን ነው፡፡

 

ሀትሪክ፡- በአውሮፓ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ለብ/ቡድን እንዲጫወቱ በማገዝ በኩል ስትሳተፉ ብዙም

አትታዩም፤ በእዚህ በኩል ምን ትላለህ…?

 

ግርማ ሣህሌ፡- እኛ ሁልጊዜም የሀገራችንን እግር ኳስ ለማሳደግ በሚረዱ ነገሮች ወደ ኋላ ብለን

አናውቅም…ጉልበታችንን፣ እውቀታችንንም አንሰስትም፤ እንዳልከው አውሮፓ ውስጥ ሀገራቸውን በብቃት መጥቀም

የሚችሉ ተጨዋቾችን አድነን ለሀገር እንዲጠቅሙ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን ስናደርግ ነበር…አሁንም እምነት

የሚጥልብንና ተባብሮን የሚሰራ የፌዴሬሽን አካልና አሰልጣኝ ካለ እኛ ለማገዝ ዝግጅዎች ነን፤ በተለይ ለU-17 ብዙ

ጥሩ ጥሩ ልጆችን ማግኘት ይቻላል…በማንኛውም ጊዜ የሚያነጋግረን ካለ ከመርዳት ወደ ኋላ አንልም፡፡

 

ሀትሪክ፡- ለነበረን ጊዜ አመሰገንኩህ፤ Merci ብዬ ከመለያየታችን በፊት ግን ቀረ የምትለው ካለ?

 

ግርማ ሣህሌ፡- …ቀረ ሣይሆን አንድ መልዕክት ባስተላልፍ ደስ ይለኛል፤ በእግር ኳሱ አካባቢ ያለ ሽኩቻ መቆም አለበት

እላለው፤ እግር ኳሱ አካባቢ አንዱ አንዱን ጠልፎ ለመጣልና ቦታውን ለመያዝ የጦፈ ሽኩቻ አለ፤ ይሄ መወገድ አለበት፤

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ተጨዋቾችን፣ አሰልጣኞችን፣ ጋዜጠኞችንና የሙያ ማህበራትን በአንድ ጠረጴዛ ቁጭ አድርገው

በማወያየት ችግሩ እንዲወገድ መስራት አለባቸው፤ ከዛ ውጪ በሀገራችን ያሉ ሙያተኞች እርስ በርስ መከባበር

አለባቸው፤ አንዱ አንዱን ማጣጣል ሳይሆን አብሮ ስለመስራት በማሰብ ለእግር ኳሱ ቢሰሩ ጥሩ ነው፤ ከዚህ ሌላ ክብር

ላለኝ ጋዜጠኞች አስተያየት ሰጥቼ እንዳልፍ ብትፈቀድልኝ በጣም ደስ ይለኛል…በዚህ በኩል በተለይ ገነነ መኩሪያ(ሊብሮ)

ለእኔ የስፖርት ጋዜጠኛ ሳይሆን የስፖርት ዲክሽነሪ ብዬ ሰይሜዋለሁ፤ ከእሱ ሌላ ሁሌም ለአገራቸው ጥሩ የሚሰሩትን

ሰይድ ኪያርንና መኳንንት በርሄን እንዲሁም አንተን (የሀትሪክ ጋዜጣ አዘጋጅና ባለቤትን) በዚህ አጋጣሚ ሳላደንቅና

ሳላመሰግን አላልፍም፤በተቃራኒ ደግሞ አንድ ሰዓት ሙሉ አስለፍልፈውህ ነገር ግን አንዳች የሚታይ ስራ የማይሰሩ

ጋዜጠኞችን ከዚህ ስህተታቸው እንዲታረሙ ለመምከር እወዳለሁ፤ የሚታይ ለሀገር የሚጠቅም ስራ እንዲሰሩ ወንድማዊ

ምክሬን እለግሳለሁ…አመሰግናለሁ፡፡

 

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.