“በፕሪምየር ሊጉ ሰበታ ከተማን ለውጤት ለማብቃት እና የሀገሪቱንም የግብ ሪከርድ ለመስበር እየተዘጋጀው ነው” ቡልቻ ሹራ /ሰበታከተማ/

አዳማ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎው በርካታ ወጣት ተጨዋቾችን በማፍራት ይታወቃል፤ ከእዚህ ቡድን
የሚወጡ ተጨዋቾችም እስከ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ በመድረስም ሀገራቸውን እያገለገሉም ይገኛል፤ አዳማ ከተማ
በእዚህ የቅርብ ጊዜ የሊጉ ተሳትፎውም እንደ እነ ከነዓን ማርክነህን፣ ሱራፌል ዳኛቸውን፣ በረከት ደስታን እና
የመሳሰሉትን ተጨዋቾች ለእውቅና ያበቃ ሲሆን ሌላው ተጨዋች ቡልቻ ሹራም ከእዚህ ቀደም ጉዳት በሳበበት ደረጃ ላይ
ባያደርሰውም በአሁን ሰዓት ግን ይህ ተጨዋች በመልካም ጤንነት ላይ ካለፈው ዓመት አንስቶ የሚገኝ በመሆኑ አዲስ
በፈረመበት የሰበታ ከተማ ቡድን ውስጥ ጥሩ ብቃቱን በሜዳ ላይ በማሳየት የሌሎቹን ጓደኞቹን ፈለግ በመከተል ለጥሩ
ተጨዋችነት እንደሚበቃም እየተናገረ ይገኛል፤ የአዳማ ከተማ የቀድሞ ተጨዋች ከነበረው እና በአሁን ሰዓት ለሰበታ
ከተማ ፊርማውን ካኖረው ከቡልቻ ሹራጋር ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በኳስ ዙሪያ አጠር ያለ ቆይታን ያደረገ ሲሆን
የተጨዋቹ ምላሽም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡

ሀትሪክ፡- በዝውውር መስኮቱ ወደ ሰበታ ከተማ ባታመራ ኖሮ የአንተ ማረፊያ ክለብ የት ይሆን ነበር?

ቡልቻ፡- በአዳማ ከተማ ውስጥ የነበረኝን የውል ጊዜዬን ካጠናቀቅኩኝ በኋላ የእኔ ፈላጊ የነበሩት ክለቦች በርካታዎች
ነበሩ፤ከእነዛም መካከል ለሰበታ ከተማ ፊርማዬን አኖርኩ እንጂ ወደዛ ባልገባ ኖሮ የእኔ አዲሱ ክለቤ ሊሆን ይችል
የነበረው ከሲዳማ ቡና፣ ከባህርዳር ከተማ እና ከወልቂጤ ከተማ ቡድኖች አንዳቸው ነበሩ፡፡

ሀትሪክ፡- ሰበታ ከተማ የአንተ የመጀመሪያ ምርጫህ የሆነው በምን መስፈርት ነው?

ቡልቻ፡- በአጋጣሚ ወደዛ ለማምራት ቡድኑ የመጀመሪያ ምርጫዬ ሊሆን የቻለው የእኔ ፈለጊ ከሆኑት ቡድኖች አንፃር
ሰበታ ከተማ ለቤተሰቦቼ ቅርብ ስለሆነ ነው፤ሌላው ደግሞ የቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አሁን ወደ ብሔራዊ ቡድኑ

ተጓዘ እንጂ በእሱ ስር መሰልጠንን በጣም እፈልግ እና የተሻለም ስልጠናን ማግኘትን እፈልግም ስለነበር ያ ሁኔታ ነው
ወደ ቡድኑ እንዳመራ ምክንያት እና መንገድ የሆነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ለሰበታ ከተማ ለመጫወት ፊርማህን አኑረሃል፤ የእዚህ አመት ዋነኛ ግብህ እና እቅድህ ምንድን ነው?

ቡልቻ፡- በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ እግርኳስ ተጨዋቾች የአሁን ሰዓት ላይ ወደ ልምምድ የተመለሱበት ሁኔታ
ቢኖርም እኔ ግን ካለፉት በርካታ ወራቶች አንስቶ ለአንድም ጊዜ ያረፍኩበት ሁኔታ ስላልነበርና ዘንድሮም በጥሩ ብቃት
ላይ ሆኜ መገኘትን ስለፈልግኩ የእዚህ አመት ላይ በሚኖረኝ የውድድር ተሳትፎ የእኔ ዋነኛ እቅድ በተሻለ ብቃት እና
አቋም ላይ በመቅረብ የምጫወትበትን አዲሱን ቡድኔን በጥሩ ሁኔታ ማገልገልነው፤ ከእዛም በተጨማሪ በርካታ
ጎሎችንም ለቡድኔ ማስቆጠርንም እፈልጋለሁ፤ እነዚህ ግቦቼም ቡድኔን ለአሸናፊነት የሚያበቁ እና የሀገሪቱንም የግብ
ሪከርድ የሚሰብሩ እንዲሆኑም ነው የምፈልገው፡፡

ሀትሪክ፡- ለአዳማ ከተማ ስትጫወት እንደ አንድ አጥቂ በርካታ ጎሎችን አላስቆጠርክለትም፤ በዛ የቁጭት ስሜት አለ?

ቡልቻ፡- አዎን፤ አንድ አጥቂ ምንጊዜም ለሚጫወትበት ቡድን ተደጋጋሚ ጎሎችን ማስቆጠር ይኖርበታል፤ በአዳማ
ከተማ ክለብ ቆይታዬ እኔ እነዚህን ነገሮች በተለያዩ ምክንያቶች በተለይ ደግሞ አልፎ አልፎ ይደርስብኝ በነበረው ጉዳት
ምክንያት ላሳካቸው አለመቻሌ በጣም ይቆጨኛል፤ ስለዚህም ይህን ቁጭቴን መሻር የምችለው የእዚህ አመት ላይ
ለምጫወትበት ቡድን ብዙ ጎሎችን ማግባት መቻል ነውና ለዛ የውድድሩን መጀማመር እየተጠባበቅኩኝ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ ተጫውተህ ስታሳልፍ የአንተ ምርጥ ጥምረቶችህ የነበሩት ተጨዋቾች እነማን
ነበሩ?

ቡልቻ፡- ምርጥ ጥምረቴ የምለው ከበረከት ደስታ እና ከዳዋ ሆቴሳ ጋር ሆኜ የተጫወትኩበትን ነው፤ እኛ ጋር የነበረው
የሶስትዮሽ ጥምረታችንም በጣም የሚያምርም ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- በአጥቂ ስፍራ የእግር ኳስን ተጫውተህ ስታሳልፍ ተቃራኒ ሆነው ከገጠሙህ ውስጥ አንተን አላፈናፍን ብሎ
ያስቸገረ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ማን ነው?

ቡልቻ፡- በእዚህ በኩል ያስቸገረኝ ተጨዋች የራሳችን ቡድን ተከላካይ ወናፍ ነው፤ ይሄ ተጨዋች በልምምድ ሰዓት ብዙ
ጊዜ ላልፈው ስሞክር የማይቀመስ አይነት ተጨዋች የሚሆንብኝ ጊዜ አለና በእዚህ አጋጣሚ ላደንቀው እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዲ. ኤስ. ቲቪ ሊተላለፍ ከጫፍ ደርሷል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?

ቡልቻ፡- ይሄ ሊሆን መቻሉ ለእግር ኳሳችን እድገት አንድ እርምጃ ነው የሚሆነው፡፡ እኛ ተጨዋቾችም ራሳችንን
የምናሳይበት እና ከሀገር ወጥተንም ወደ አፍሪካ እና ወደተቀረው አለምም በመምጣት በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ
የምንጫወትበትም ሁኔታ ይፈጠርልናልና ጨዋታው በዲ ኤስ ቲቪ መተላለፉ በጣም ጥቅም አለው፡፡

ሀትሪክ፡- ሰበታ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ተሳትፎ ምን ውጤትን ያመጣል?

ቡልቻ፡- የሊጉ ተሳትፎአችንን በተመለከተ አሁን ላይ ሆኜ በእዚህ ደረጃ ላይ ሆነን ሊጉን እናጠናቅቃለን ባልልም ቡድኑ
በወጣት ተጨዋቾች እየተገነባ ከመሆኑ አንፃር ግን ምንአልባት ከእዚህ በፊት ከነበረበት ደረጃ ግን የተሻለ ውጤት
የሚያስመዘግብበት ሁኔታ ሊያጋጥመው እንደሚችል አስባለውኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ አስደሳች እና አስከፊ ጊዜያቶቼ የምትላቸው የትኞቹን ነው?

ቡልቻ፡- አስደሳች የምለው ምንም እንኳን ክለቤን በተደጋጋሚ ጊዜ በስኬት ደረጃ ለውጤት አብቅቼው ለማገልገል
ባልችልም የ2010 ላይ ገንብተነው በነበረው ቡድን ውስጥ አባል ስለነበርኩ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፤ ይሄ ቡድን ያን
ታምረኛ የተጨዋቾች ስብስብን ይዞ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት አለመቻሉ ደግሞ ሁሌም እንድቆጭበት ያደርገኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ራስህን ምን አይነት አጥቂ ነኝ ብለህ ታስባለህ?

ቡልቻ፡- በጣም ፈጣን፣ አግሬሲቭ፣ እና ሹተር፤ በእዚህ ደረጃ የምገለፅ ተጨዋች ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ከእግር ኳስ መጫወት ውጪ የአንተ መዝናኛዎች ምንድን ናቸው?

ቡልቻ፡- ሙዚቃ መስማት እና ፊልም ማየት በጣም እወዳለው፤ ከዛ ውጪም ከቤተሰቦቼ ጋር ማሳለፍ የእኔ
መዝናኛዎች ናቸውና ይሄን ነው ለማለት የምፈልገው፡፡

ሀትሪክ፡- በዘመንህ የወደድከው ሙዚቃ እና ፊልም የትኛው ነው?

ቡልቻ፡- ከሙዚቃ በጣም የወደድኩት የቴዲ አፍሮን ዘፈኖች ነው፤እሱንም ከሚገባው በላይ እወደዋለሁ፤
ከተመለከትኩት ፊልሞች ደግሞ የእኔ ቀዳሚ ምርጫዬ እና የወደድኳቸው ረቡኒ እና ላምባ የሚባሉትን ፊልሞች ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ሰበታ ከተማ ከማምራትህ አኳያ አዲሱን ቡድንህን ቶሎ የምትላመድ ይመስልሃል?

ቡልቻ፡- በአንዴ እና በፍጥነት እላመዳለው ብዬ ፈፅሞ አላስብም፤ያም ሆኖ ግን በሊጉ የተሻለ ተጨዋች መሆንን
እያሰብኩ ስለሆነ በሂደት ከቡድኑ ተጨዋቾች ጋር እንደምግባባ እና እንደምላመድ አውቃለውኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያለ ተመልካች ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሊከናወን ስለመሆኑ ምን ትላለህ?

ቡልቻ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ያለ ተመልካች መከናወኑ በጣም ደስ አይልም፤ በተለይ ደግሞ በደጋፊዎች መጫወት
ለለመደ ቡድን ያን ማየት የእግር ኳስ ጨዋታን ጣህም እንዲደበዝዝም ያደርገዋልና ይሄን ነው ማለት የምፈልገው፤
ሆኖም ግን ይሄ ሊሆን የቻለው ከኮቪድ ወረርሽኝ የተነሣ ለሁላችንም ጤንነት ታስቦ ስለሆነ ደስተኛ ሆነን ልንጫወት
ባንችልም ሁኔታውን መቀበሉ ግን የግድ ነው የሚለን፡፡

ሀትሪክ፡- ትዳር መመስረትህን እናውቃለን፤ ባለቤትህ ማን ትባላለች…? ከእግር ኳስ ህይወትህ ጀርባስ እሷ ምን
የምታደርግልህ ነገር አለ?

ቡልቻ፡- የእኔ ባለቤት እየሩሳሌም ስዩም ትባላለች፤ የአራት ወር እድሜ ያላትንም ኤምራኬል ቡልቻ የተባለች ሴት
ልጅንም ከአብራካችን በማፍራት ልትሰጠኝም ችላለች፤ እሷ ለእኔ ስለምታደርግልኝ እገዛ ሁሌም ነው ከአጠገቤ ሆና
በምፈልገው ነገር ሁሉ እየረዳችኝ ያለው፤ ከእዛ ውጪም ቤታችንን በመቆጣጠርም የወደፊት ህይወታችን የሰመረ
እንዲሆንም ከፍተኛ ጥረትን እያደረገችም ትገኛለችና በእዚህ አጋጣሚ በጣም ላመሰግናት እወዳለው፡፡

ሀትሪክ፡- ከባህር ማዶ የሚያደንቀው ተጨዋች እና የሚደግፈው ቡድን?

ቡልቻ፡- የማደንቀው ክርስቲያኖ ሮናልዶን ነው የምደግፈው ቡድን ደግሞ ሪያል ማድሪድን እና ቼልሲን ነው፤ በተለይ
ቼልሲን በቀድሞ ጊዜ ለመደገፍ ምክንያት የሆነኝ ድሮግባ እና ላምፓርድ በሚጫወቱበት ዘመን ላይ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- የአንተ ባህሪህ ሲገለፅ?

ቡልቻ፡- በጣም ዝምተኛ ነኝ፤ ከሰዎች ጋር ቶሎ አልግባባም፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?

ቡልቻ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ አሁን ለመጣሁበት መንገድና እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ እንድችል ትልቁን
የጥርጊያ መንገዱን ያመቻቹልኝ ቤተሰቦቼ ናቸው፡፡ በእዚህም በጣም አመሰግናቸዋለሁ፤ ከእዛ ውጪ ደግሞ ለመናገር
የምፈልገው ከኮቪድ ወረርሽኝ መግባት በኋላ አሁን ላይ በፈጣሪ እገዛ ወደ ቀድሞ ስራችን እየተመለስን መሆኑ በጣም
ነው ደስ የሚለው፤ ያ ደስታ አብሮን ቢኖርም አሁንም ግን ራሳችንን ከኮቪድ መጠበቁን ፈፅሞ መርሳት እንደሌለብን
ልንረዳ ይገባናል፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website