መነሻ ገጽ The BiG Interview “ከአቅም በታች የሚጫወት ቡድንም የለንም… ብናስብም እንኳን ህሊናችን እሺ አይለንም” ፍፁም ገ/ማርያም /ሰበታ ከተማ/
The BiG Interviewሰበታ ከተማቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግዜናዎች

“ከአቅም በታች የሚጫወት ቡድንም የለንም… ብናስብም እንኳን ህሊናችን እሺ አይለንም” ፍፁም ገ/ማርያም /ሰበታ ከተማ/

አጋራ
አጋራ

“በባህሪዬ መሃል ሰፋሪ ብሆንም በምወደው ሙያ እግር ኳስ ሲመጡብኝ ግን መሃል ሰፋሪ መሆን አልወድም”
“ከአቅም በታች የሚጫወት ቡድንም የለንም… ብናስብም እንኳን ህሊናችን እሺ አይለንም”
ፍፁም ገ/ማርያም /ሰበታ ከተማ/


ከሰሞኑ የሰበታ ከተማ እግር ኳስ ተጨዋቾች “አሁንስ በቃ” ያሉ ይመስላል፡፡ ተጨዋቾቹ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም አልተከበረልንም በማለት ከገና ዋዜማ ጀምሮ እስከ ባለፈው ማክሰኞ ድረስ ልምምድ ሳይሰሩ ቆይተዋል፡፡ አሰልጣኙ አብርሃም መብራቱ ደግሞ “የተጨዋቾቹ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ካልተከበረ ውጤታማ ቡድን መገንባት ይከብዳል ይሄን አስተካክሉ” በማለት ቅሬታ አዘል ደብዳቤ አስገብቷል፡፡ በሁኔታው የተደናገጡት የሚመስሉት የክለቡ አመራሮችም የተወሰነ ክፍያ ፈፅመው ቁጣውን ለማብረድ ሞክረዋል፡፡ የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ከሰበታ ከተማ ወቅታዊ ሁኔታና በተለያዩ እግር ኳሳዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከክለቡ የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ፍፁም ገ/ማርያም ጋር ያደረገው ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጊዜ ኳሱ ሲቆም እንዴት አለፍከው?

ፍፁም፡- ይሄ ጊዜ ብዙ ነገር ነው ያስተማረኝ፡፡ ኳስ ተጨዋች ሌላ ሕይወት ወይም ሙያ ላይ ማሰብ አለበት፡፡ ነገ ከኳሱ ሕይወት ከሲስተሙ ሊወጣ እንደሚችል ነው የተማርኩት…. የሚገርምህ ከኳሱ ሕይወት ወጥተህ ከሰዎች ጋር ስትቀላቀል ከባድ ቻሌንጅ ይገጥምሃል፡፡ ሰው ሁሉ ቀድሞን መሄዱን ተረድቻለው፡፡ የኛ ሕይወት ከማህበራዊ ጉዞ ጋር የተራራቀ ነው አንዴ ክልል አንዴ አዲስ አበባ መሆኑ ህይወታችንን ወስኖታል፡፡ በዚህ ጊዜ እንዳስተዋልኩት ሌላ ነገር ያስፈልገናል… በርካታ ተጨዋቾች ራይድ እየሰሩ ነበር ተጨማሪ ሕይወት የምመራበት ስራ ያስፈልጋል እንድል አድርጎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 መስፋፋት ግዜ የተስፋፋው ወንጀል የባል ሚስትን መደብደብ ነውና አንተስ አጋርህን አልደበደብካትም?

ፍፁም፡- /ሳቅ በሳቅ/ ከሚስቴ ጋር ትውውቃችን ከሃይስኩል የጀመረ ነው…ነገር ግን እሷ አሜሪካእኔ እዚህ ሆነን እንኖር ስለነበርን ተነፋፍቀን ነበረና ጊዜው እንዳጣረን ነው የተሰማን እንጂ ለፀብ ጊዜ አልነበርንም፡፡ 8 ወር አብረን ቁጭ ብለን ምርጥ ጊዜ አሳልፈናል፡፡ ጊዜ ስላገኘን በመለያየታችን ያጣነውን ለመረዳት ችለናል፡፡ በጸብ ሳይሆን አሪፍ ጊዜ ነው ያሳለፍነው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ 4ለ1 የተረታችሁበት ጨዋታ ሲታይ ምርጥ ነበራችሁ፡፡ ውጤቱ ጨዋታውን አይገልፀውም የሚሉ የሰፖርት ቤተሰቦች በርካታ ነበሩ፡፡ ከጨዋታ በኋላ የነበራችሁ ስሜት ምን ይመስላል?

ፍፁም፡- ያለ ምንም ጥርጥር የምነግርህ ሁላችንም ተሰሳጭተናልተናደናል… ከክለቡ ጋር በተፈጠረ ችግር ደመወዝ ባለመከፈሉ ልምምድ ይቋረጣል ይቀጥላል በተንጠባጠ በሂደት ልምምድ እየሰራንም ቢሆን ቡድናችን ጥሩ ነበር፡፡ በተለይ አሰልጣኝ አብርሃም ይዞ የመጣው ሃሳብ ከነበሩን ልምዶች ወጣ ያለ ስለነበር በሂደት ላይ ባለአጨዋወት ብልጫም ወስደን የማሸነፍ ጉጉታችን ባለመሳካቱ በጣም ተቆጭተን ነው የወጣነው… ወደፊት ጥሩ አቋም እንደሚኖረን ማሳያ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ተቀይረህ እየገባህም ቢሆን ግብ ታስቆጥራለህ… ተጠባባቂነትህ ግን አሳምኖሃል?

ፍፁም፡- 8 ወር ያለ ኳስ እንደመቆየቴ የመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ላይ የፊትነስ ችግር ነበረብኝ፡፡ ያም ሆኖ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለቡድኑ ኮከብግብ አግቢ እኔ ነኝ፡፡ አሁንም ተቀያሪ መሆን አይረብሸኝም፡፡ ተቀይሬም ገብቼ የሚያሳምን አቋም አሳያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ የተሻረው ግብን ጨምሮ መደዳውን 3 ግብ አስቆጥሬያለሁ፡፡ እግርኳስን የምወደው ሁሌ ልምምድም ሆነ ግጥሚያ ላይ ዕድል ስለሚሰጥ ነው፡፡ ኤልፓም፣ መከላከያም፣ ጊዮርጊስም ሙገርም ሆኜ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ፉክክር ውስጥ አለሁና ሃሳብ አስለውጬ ቋሚ ተሰላፊ እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የፊትነስ ችግር የገጠመህ በወቅቱ ዳሌ አውጥተህ ነበር እንዴ?

ፍፁም፡- አንዳንዴ በስሜት ይነገራል እንጂ ዳሌ አላወጣንም፡፡ በወቅቱ ተናድጄ ነበር ለማንኛውም ሸንቀጥ ብዬ የተወሰነ ኪሎ ጨምሬ ነበር የገባሁት በፍፁም ዳሌ አላወጣሁም፤ ያወጣም የለም፡፡

ሀትሪክ፡- በወቅቱ ያናደደህ አማርኛው ነው ወይስ ውሸት ስለሆነ ነው?

ፍፁም፡- የወፈረ እንጂ ዳሌ ያወጣ ተጨዋች? /ሳቅ/ ኧረ በፍፁም አልነበረም /ሳቅ/ ከኳሱ ውጪ ያለ ሰው ሚዲያ ላይ ያንን ቃል ሲሰማው መደንገጡ አይቀርም፡ ፡ ውድድሩን በዲ.ኤስ.ቲቪ ሲታይም ሸንቀጥ ብለን ነው የመጣነው፡፡ አጋጣሚ አያት አካባቢ ስለነበርኩ የዋልያዎቹ አባላትን ሳያቸውኮ ተጨዋቾቹ ሸንቀጥ ብለው ነው የገቡትና የተወሰነ የፊዚካል ፊትነስ መዛባቶች ሊኖር ይችል ይሆናል እንጂ ሁሉንም በሚያስመስል መልኩ የተነገረውን ሃሳብ አልቀበልም ስህተት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ከጅማ ጋር 1ለ1 ስትለያዩ የሰበታ ደጋፊዎች የጅማ ደጋፊ እስኪመስሉ ድረስ ሲሳደቡ ነበርና የተፈጠረ ቅሬታ የለም?

ፍፁም፡- ትንሽ አሳዝኖናል ጥቂት ግሰለቦች ናቸው ስም እየጣሩ ሲሳደቡ የነበሩትና ይሄ ትክክል አይደለም መታረም አለበት ውጤት የሚመጣው ተጨዋቾቹን ስታበረታታ እንጂ በስድብ አይደለም፡፡ ገና ረጅም ጉዞ ስላለ ውጤቱ ሊለዋወጥ መሪ የነበረ ዝቅ ዝቅ ያለው ደግሞ ወደ ላይ ከፍ ሊል ይችላልና ለዚህ ስብስብ ድጋፍ ብቻ ነው የሚያስፈልገው የነበረው ኃላፊነት የመሸከም አቅምም ሊበረታታ ነው የሚገባው፡፡ ደመወዙ ሳይከፈለው ከነ ሕመሙ መጫወቱ ሊበረታታ ብቻ ነው የሚገባው… ድርጊቱ ቅር ያሰኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ያለ ደጋፊ መጫወትስ ምን ስሜት ይፈጥራል?

ፍፁም፡- በጣም ነው የሚያስጠላው፡፡ በደጋፊ ታጅቦ መጫወት ለምደን በዝግ ሲሆን ይደብራል፡፡ ከጊዮርጊስና ቡና ጋር የምናደርገው ጨዋታ ላይ ያለውን የደጋፊ ሁኔታ ትናፍቀዋለህ ምንም ጥርጥር የለውም አሁን ጭር ብሎ አሞራ ሲበር ነው የምናየውና ከበድ ይላል

ሀትሪክ፡-በዲ.ኢስ.ቲቪ መተላለፉ ያለው ጥቅምስ?

ፍፁም፡- የዲ.ኢስ.ቲቪ ትልቁ ጥቅሙ ጨዋታዎቹን በማየት ስህተትን የማየትና የማረም ዕድል ይሰጥሃል… ክልል ላይ ለተጋጣሚ ክለቦች የሚሰጡ ወይም የሚፈጠሩ የዳኞች ስህተቶች ቁልጭ ብሎ እየታየ ነው፡፡ ምሳሌ ብጠቅስ የኔ ቡና ላይ ያገባሁት ግብ ተሽሯል፡፡ እነኝህ ነገሮች ዳኞችም አይተው እንዲማሩ ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ ከስህተት ተምረን የተሻለ ነገር እንድንመጣ የሚያደርግ እድል ሰጥቶናልና ደስ ይላል በተለይ ዳኝነት ላይ ካነሳን የኦፍ ሳይድ ሲስተሞች ላይም ያለውን ክፍተት በአራት ጨዋታዎች ላይም አይቻለሁና መስተካከል አለበት፡፡ ዲ.ኤስ.ቲቪ ተጨዋቹም ዳኛውም በአጠቃላይ ሁላችንንም የማረምና የማስተማር ዕድል ፈጥሯል…. ጨዋታ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ስህተቶችን የማረም ዕድል ፈጥሯል፡፡

ሀትሪክ፡- እግር ኳስ ውስጥ ያለውን ውዝግብ ስታይ አሁንስ በተማርኩበት ሙያ ብሰራ ይሻል ነበር የሚል ስሜት አልተፈጠረብህም?

ፍፁም፡- እግር ኳሱ ምንም ጥቅም ሳይኖረው የገባሁት ትልቅ ፍቅር ስላለኝ ነው… ሙያውን ስለምወደው ምንም አይነት ፈተና ሊያስቀረኝ አይችልም፡፡ ክለቦች ሲፈርሱ የምናይበት ያለሙያው እየተገባ ሃሳብ የሚሰጥበት እግር ኳስ ቢሆንም ልጠላው አልችልም፡፡ ሙሉ በሙሉ ለምን አይቀርብኝም የማልለው ለዚህ ነው፡፡ እስከምችለው እስከመጨረሻ ድረስ የምታገል ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ውዝግብ የሚሸሽ ሰው ነው አሉኝ..ይሄ ባህሪስ አልጎዳህም?

ፍፁም፡- አዎ… ብዙ ጊዜ ከአስተዳደጌ አንስቶ መሃል ሰፋሪ የምባል አይነት ሰው ነኝ፡፡ ቤተሰቤን ስታይ 4 ሴትና 4 ወንድ ሆነን በማደጋችን ብዙ ጊዜ ሃሳቦች ተነስተው ሃሳብ ስሰጥ መሀል ሰፋሪ ነው የምባለው፡፡ ያ ማለት ግን በባህሪዬ መሃል ሰፋሪ ብሆንም በምወደው ሙያ እግር ኳስ ላይ ግን ሲመጣብኝ መሀል ሰፋሪ መሆን አልወድም…ግልፅ የሆነ ነገር ይመቸኛል፡፡

ሀትሪክ፡- መሀል ሰፋሪ ትርጉሙ ኔጌቲቭ ነው መሀል ሰፋሪነት ትዳርህ ላይስ አለ?

ፍፁም፡- /ሳቅ/ ትዳሬ ላይ መሀል ሰፋሪ አይደለሁም፡፡ እንደሁኔታው ነው ነገሩን የማየው፡፡ ሴቶች ስሜታዊ በሚሆኑበት ጊዜም አብሬ ስሜቴን አልገልፅም፡፡ ትዳር ላይ የሚቀድመው መቻቻሉ በመሆኑና ባለቤቴም ጥሩ አጋር በመሆኗ በብዙ ነገር ተቻችለን ኖረናል፡፡ ከርሷ ጋር ተቻችለን ደስተኛ የሆነ ኑሮ እንኖራለን፡፡

ሀትሪክ፡- በተጫወትክባቸው 5 ክለቦች የነበረህን ቆይታ ስታስበው በስኬታማነቱ የምትጠራው ነው?

ፍፁም፡- ደስተኛ ሆኜ ነው የማስበው፡፡ ሙገር፣ ጊዮርጊስ፣ ኤልፓ… በኮከብ ግብ አግቢነት ከመፎካከር በዘለለ ሳልጎዳ በጤና መጫወቴ በራሱ እግዚአብሔር ማመስገን አለብኝ፡፡በክልል ሜዳዎች ያለምቾት ተጫውቼ አለመጎዳቴ እግዚአብሄር ታላቅ ነው እንድል አድርጎኛልለዚህም ነው ቆይታዬን በጥሩ ጎኑ የማየው፡፡

ሀትሪክ፡- በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ ያንተ ምርጡ ተጨዋች ማን ነበር?

ፍፁም፡- ያለ ጥርጥር ጥሩ ሆኖ ያገኘሁት የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስርን ነው ክለቡ ኢትዮጲያ ቡናም አዲስ ሃሳብ ይዞ የመጣ አሰልጣኝ ስላላቸው ጥሩ ነገር አይተናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ አብርሃም ለፍፁም ምን አዲስ ነገር ጨመረለት?

ፍፁም፡- ገና ነው…. በግሌ ከብዙ አሰልጣኞች ጋር እየሰራሁ ነው…ከአሰልጣኝ አብርሃም ጋር 5 ጨዋታ ብቻ ነው ያደረግን በመሆኑ ብዙም መናገር አልችልም፡፡ ምሽት ምሽት ላይ ግን በስነ ምግብና በሳይኮሎጂ የሚሰጡን ስልጠናዎች አዲስ ተሞክሮ ናቸው፡፡ አጠቃላይ አመቱን ስንጨርስ ግን የተሻለ ነገር ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ሰበታ ከተማ በ6ቱ ሳምንት ጨዋታዎች 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል… የመውረድ ስጋት አይፈጥርም?

ፍፁም፡- ይወርዳል ብዬ አልሰጋም ጠንካራ ቡድን ነው ያለን…. የኛ ቡድን ሃሳብ አለው ያን ሃሳብ እስከ መጨረሻ ደቂቃ ድረስ ይዞ ከሄደ ጥሩ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ይቺ ሃሳብ ሃሳብ የምትለውን ነገር ደጋገምከው…. የኛ ቡድን ሃሳብ አለው ስትል የሌላው ቡድን ሃሳብ የለውም አንዴ?

ፍፁም፡- /ሳቅ በሳቅ/ ሃሳብ የሌለው አለ እያልኩ አይደለም፡፡ የኛ ቡድን አንድ ሃሳብ ይዞ ነው የሚጫወተው… በተሻለ መንገድ እያደገ የሚሄድ ሃሳብ ነው ተጨዋቾቹም ወጣቶችና ሲኒየሮች ያለበት በመሆኑ ኳስን መሠረት አደርጎ የሚጫወት ቡድን ዳግም እነኚህን መሰል ተጨዋቾች ያስፈልጉታልና የሚታይ ነገር አሳይተናል ለማለት ነው…. ምናልባት አሰልጣኝ አብርሃም ተናግሮ ይሆናል 600 ኳስ የተቀባበለውየኛ ቡድን ነው ሲያድግ የተሻለ ነገር ይዘን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ጅማ አባጅፋር ከሰበታ ከተማ ጋር ሲጫወት በናንተ በኩል ከአቅም በታች አልተጫወታችሁም?

ፍፁም፡- በፍፁም… ከአቅም በታች የሚጫወት ቡድንም የለንም ብናስብም እንኳን ህሊናችን እሺ አይለንም፡፡ ለእግር ኳስ ትልቅ ፍቅር አለን ሙያውን የማያከብር ካልሆነ በስተቀር በኛ በኩል እስከመጨረሻው የተቻለንን ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡

ሀትሪክ፡- ከዋሊያዎቹ 28  ተጨዋቸች ውሰጥ ስምህ የለም….አለመመረጥህን ተቀበልከው?

ፍፁም፡- ይሄ የአሰልጣኙ ሃሳብ ነው ብዙ ጊዜ ለምን አልተመረጥንም የሚሉ ተጨዋቾች ይገርሙኛል፡፡ 100 ተጨዋች በአንዴ አይመረጥምና የአሰልጣኙ አስተሳሰብ መታየት አለበት፡፡ መመረጥ አለመመረጥ አያሳስበኝም፡፡ ነገር ግን ፍፁም ገብረ ማሪያም ጥሩ ተጨዋች ነው ግብ ያስቆጥራል…ይህ እውነት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የዘንድሮው የገና በዓል ዋዘማና በዓሉ ለሰበታ ከተማ ተጨዋቾች ደስታን አላመጣም አሉ… እውነትነው?

ፍፁም፡- አዎ ቅር ብሎናል፡፡ መታወቅ ያለበት በእግር ኳስ ሕይወት ተጨዋቹ ትንሽ ነገር ካገኘ ደስተኛ ይሆናል ያን ትንሽ ነገር ካጣ ደግም ቅር ይለዋል፡፡ በወቅቱ የክለቡ አመራሮች ደመወዝ ለበዓሉ ይደርስላችኋል ብለው መድረስ ባለመቻሉና በአል ላይ በምንፈልገው ደረጃ ማድረግ የምንችለውን ባለማድረጋችን ደስተኛ አልነበርንም፡፡ ለወደፊቱ ብዙ ነገሮች ተስተካክለው ደስተኛ እንሆናለን ብዬ ግን አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በእግዚአብሔር ይስጥልኝ ምርቃት ያለ ደመወዝ መጫወት አይከብድም?

ፍፁም፡- አምና የነበሩ አመራሮች ሳይሆኑ የአሁኖቹ አዳዲስ ናቸው፡፡ ያ ደግሞ ትንሽ ክፍተት ፈጥሯል፡፡ የሚያውቁት ነገር እንዳልነበርም ሲገልፁልን ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ተጨዋቹ በውሉ መሠረት ማግኘት ያለበት ጥቅም ሊሰጠው ይገባል፡፡ የደመወዝ ክፍያ ሲዘገይ ሁሉም ተጨዋች አንድ አይነት አስተሳሰብ አይኖረውም፡፡ ቅሬታው ሊሰፋ ይችላል፡፡ አንዳንዱ ቤተሰብ የሚረዳው ተጨዋች ያን ማድረግ ካልቻለ ቅር ይለዋል… የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉና በቀጣይ ችግሮቹ ይስተካከላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከበዓል መልስ የተወሰነ ከፍለዋል….ወደፊትም ነገሮች ተስተካክለው ጥሩ ነገር ይኖራል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ደስተኛ ካልሆነ ተጨዋች ምርጥ አቋም መጠበቅ አይከብድም?

ፍፁም፡- እንደተጨዋቹ አስተሳሰብ ይለያያል፡፡ በግሌ አልተደረገልኝም ብዬ ያለኝን አቅም ሳላወጣ ቀርቼ አላውቅም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ያልተፈቱ ችግሮች ቢኖሩም ከባድ የሆነ ችግር ይፈጠራል ብዬ አላስብም…. ለምንወደው እግር ኳስ ዋጋ መክፈል አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የውጪ ኳስ ታያለህ?

ፍፁም፡- አዎ በደምብ እንጂ….

ሀትሪክ፡-እሁድ ምሽት በአንፊልድ ማን.ዩናይትድ ከሊቨርፑል ይጫወታሉ… ድሉ የማን ይሆናል?

ፍፁም፡- እኔ የማን.ዩናይትድ በመሆኔ ድሉ የኛ ይሆናል ብዬ አምናለሁ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ከ1222 ቅናት በኋላ የሊጉመሪ መሆንያን ያህል ደስታ አይፈጠርም የሚሉ ወገኖች አሉ…. ትስማማለህ?

ፍፁም፡- /ሳቅ/ ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ እዚህ ደረጃ ለመደረስወደ 4 ዓመት ሞልቶናልና መሪነቱ ትርጉም ሰጥቶናል፡ በጨዋታው ከባድ ፉክክር ይኖራል በርግጥ ሊቨርፑል አንፊልድ ላይ ትልቅ ታሪክ ስላለው ጨዋታው ትግል ይኖረዋል የኛዎቹ ግን ተፋልመው ውጤቱን አስጠብቀው ይወጣሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- መንፈሳዊ  ሕይወቴ ጥሩ መሆኑ በጨዋነት ከሚጠሩ ጥቂት ተጨዋቾች መሃል እንድሆን አድርጎኛል ብለህ ታምናለህ?

ፍፁም፡- ድሮም ልጅእያለሁ ወደ መንፈሳዊነቱ ማዘንበሌ ጠቅሞኛል ብዬ አስባለሁ…በእርግጥም ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ቃል…?

ፍፁም፡- የማመሰግነው አለ…. ቤተሰቦቼን በጣም አመሰግናለሁ… ባለቤቴን…. በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በፊት ይጫወት የነበረ ወንድም አለኝ፡፡ ለገሠ ገ/ማርያም ይባላል እሱንም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ሌላው ዮናስ ገ/ማርያም የተባለ ወንድም አለኝ…. በየክልል እየዞረ የሚደግፈኝ ክለብ ስቀይር ማሊያ የሚቀይር ነው አሁን የሰበታ ከተማ ደጋፊ ነው፡፡ ተመላላሽ ታካሚዬ ማለት ይቻላል /ሳቅ/ ቀጣይ የምገባበትን ክለብ እንዳወቀ ማሊያ ለመቀየር በጀት መድቦ እየጠበቀ ነው /ሳቅ/ ሁሉንም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

ስለ አባይ
በመጀመሪያው የውሃ ሙሌት በጣም የተደሰትኩበት ቀንም ነበር፡፡ የመብራት ችግር ከተማ ውስጥ ብዙ ላይኖር ይችላል ገጠር ግን ሆስፒታልና ሌሎች ቦታዎች መብራት ባለመኖሩ መውለድ እየቻሉ የሚሞቱ ወገኖቻችን መኖራቸውን ስታይ ግድቡ ትልቅ ደስታን ይፈጥራልበእውነት በግድቡ ደስተኛ ነኝ ሲመረቅ ደግሞ ቦታው ድረስ ሄጄ ደስታዬን የማከብር ይመስለኛል፡፡ በ8100 ኤ በደንብ አለሁበት፡፡ በሙገርም ሆነ በብሄራዊ ቡድን ቦንድ ገዝቻለሁ፡፡ የቀረኝ በሰበታ ከተማ ነው /ሳቅ/ ሰበታ ከተማ ደመወዝ ሲከፍለኝ ደግሞ ያኔ ቦንድ እገዛለሁ፡፡ ለማንኛውም መላው ሕብረተሰቡ የሚጓጓለት በተስፋ የሚጠብቀው ጉዳይ በመሆኑ ስኬቱ ደስታን የበለጠ ይጨምራል ብዬ አምናለሁ፡፡

ስለ ኮቪድ 19
የሚያዘውና የሟች ቁጥር መጨመሩ በየቀኑ እየተነገረ ማህረበሰቡ እየተጠነቀቀ አይደለም፡፡ ለስራ የሚወጣው ሰው ሁሉም እናትና አባቱን በዚህ በሽታ ሊበክል እንደሚችል ማወቅና መረዳት ተስኖታልና ይሄ ነገር መስተካከል አለበት፡፡ ቫይረሱ በቅርብ እየጎዳ ያለው የቅርብ ቤተሰቦቻችን የሆኑት እናትና አባቶቻችንን ነው ትልቅ ትኩረት ያስፈልጋል ቸልተኝነት አያዋጣም…. በግሌ ይሄንን ቫይረስ ፈጣሪ ጨርሶ እንዲያስወግድልን እመኛለሁ… በጎን ግን የሕክምና ሰዎች የሚሰጡትን መመሪያ በመከተል ርቀት በመጠበቅ ማክስ በማድረግ እጃችንን በሳኒታይዘር በማፅዳት ራሳችን ቤተሰቦቻችንና ሕዝባችንን ማዳን አለብን ማለት እፈልጋለሁ፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

በ5 ሳምንታት 39 ጨዋታዎች፣ 72 ጎሎችና ከ22.6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተመዘገበ!

በአቤኔዘር አበበ በ2019 ዓ.ም የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያዎቹ አምስት የውድድር ሳምንታት...