“በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እስከ ቶፕ 4 ውድድሩን ለማጠናቀቅ አቅደናል”
“በእግር ኳሱ ምርጥ ጥምረቴ ከጌታነህ ከበደ ጋር የነበረኝ ነው”
ሄኖክ አየለ /ወልቂጤ ከተማ/
ወልቂጤ ከተማ አዳማ ከተማን በሄኖክ አየለ ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ በጅማ በመካሄድ ላይ ያለውን የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በድል ሊወጣ ችሏል።
ወልቂጤ ከተማ የ7ኛ ሳምንት ጨዋታውን በማሸነፉም ከነበረበት 7ኛ ደረጃ ወደ 5ኛ ሊመጣም በቅቷል።
ወልቂጤ ከተማ አዳማ ከተማን ከረታ በኋላ ለቡድኑ የድሉን ግብ ያስቆጠረውን ሄኖክ አየለን በተለያዩ ጥያቄ ዙሪያ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮታል። ተጨዋቹም ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ ስለነበራቸው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው
“በውድድሩ ላይ የነበረን ቆይታ በጣም ጥሩ እና ደስ የሚል ነበር። በውጤት ደረጃ ሲታይ ደግሞ የሚያስከፋ ስኬትን አላስመዘገብንም። እንደዛም ሆኖ ግን ከሲዳማ ቡናና ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በተጫወትንባቸው ግጥሚያዎች ላይ ጥሩ ተንቀሳቅሰን እንደ ቀልድ ያጣናቸው ውጤቶች የጠበቅናቸው አልነበሩምና ያ ባይሆን በደረጃ ሰንጠረዡ አሁን ካስመዘገብነው በተሻለ በሚባል ደረጃ ላይ መቀመጥም እንችል ነበር”።
- ማሰታውቂያ -
ለቡድናቸው አስቆጪ ስለነበረው ጨዋታ
“አስቆጪው ጨዋታችን የመጀመሪያው ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረግነው እና የተሸነፍንበት ነበር። በመቀጠል ደግሞ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያደረግነውና ነጥብ የተጋራንበት ጨዋታ። በተለይ ከሀዲያ ጋር በነበረን ፍልሚያ እነሱ ቀድመው ጎል ቢያገቡብንም እኛ በእንቅስቃሴ የተሻልን ነበርን። ጎል ጋርም እንደርስም ነበርና ይሄ ጨዋታ በእኛ አሸናፊነት መጠናቀቅ ሲገባው አቻ ስለወጣንበት ልንቆጭ ችለናል”።
ስለ ቡድናቸው ወቅታዊ አቋም
“ወልቂጤ ከተማ በሜዳ ላይ ያለው ወቅታዊ አቋም በግለሰቦች ላይ ጥገኛ በመሆን የሚንቀሳቀስ ሳይሆን እንደ ቡድን በጋራ በመከላከልም ሆነ በማጥቃት የሚጫወት ቡድን ነው። ከዛም በተጨማሪ ሁሉም ተጨዋች ስራውን ጠንቅቆ ያውቃል። በህብረት እያጠቃ በመጫወትም የየስፍራው ተጨዋቾች ጎልም እያገቡ ይገኛል። ይሄን ስንመለከት ቡድናችን በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ልናውቅ ችለናል”።
እንደ ቡድን ስላለባቸው ክፍተት
“በተወሰነ መልኩ ጎሎች ቀድመው ይገቡብናል። ከዛ አቻ ሆነን ግጥሚያውን ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት በምናደርግበት ሰዓት ላይ በስነ ልቦና የተጎዳንበት ጊዜ ስለነበር ቀድሞ ጎል የሚቆጠርብንን ችግር ልንቀርፈው ይገባል። ሌላው እኛ ላይ ጎል እንዳይገባና ቀድመን ጎል ማስቆጠር እንዳለብንም ነው ከቡድናችን አቋም የተረዳሁት”።
አዳማ ከተማን ጅማ ላይ ስለማሸነፋቸው እና በሜዳ ላይ ስለነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ
“ከአዳማ ከተማ ጋር የነበረንን የጨዋታ እንቅስቃሴ በተመለከተ እነሱ ከሽንፈት መልስ በመምጣት ያደረጉት ስለነበር ለእኛ ጠንከር ብለውብን ነበር የመጡት። የድሉን ግብ በእነሱ ላይ ለማስቆጠር በጣም ተቸግረን ነበር። ዘግይተንም ነው ጎል ማስቆጠር የቻልነው። አዳማ አሁን ላይ ውጤት ይራቀው እንጂ ትልቅ የሆነ ቡድን ነው። እየተሻሻሉም ነበር የመጡት። በዕለቱ ግን እኔ ባስቆጠርኩት ግብ ግጥሚያውን ስናሸንፍ በጣም ነው የተደሰትኩት”።
በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የቡድናቸው እቅድ
“ወልቂጤ ከተማ የእዚህ ዓመት ተሳትፎው ላይ ሊያስመዘግብ ያሰበው ውጤት በቶፕ አራት ውስጥ ሆኖ ሊጉን መጨረስ ነው። ይሄንንም ያሳካል ብዬ አስባለሁ”።
በእግር ኳስ ተጫውቶ ስላሳለፋቸው ጊዜያቶች
“በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ምንም እንኳን በአንድ አንድ ክለቦች ውስጥ በጉዳት የተነሳ አልፎ አልፎ ከሜዳ በመራቅ አስቸጋሪ የሆነን ጊዜያቶች ባሳልፍም እንደ አጠቃላይ ግን ለደቡብ ፖሊስ፣ ለአዳማ ከተማ፣/ሁለት ጊዜ/ ለሲዳማ ቡና እና ለሐዋሳ ከተማ ስጫወት በነበረኝ የኳስ ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነኝ። ይሄ ሊሆን የቻለበትም ምክንያትም ኳስን ከልጅነቴ እድሜ አንስቶ ወድጄ እና አፍቅሬውም እየተጫወትኩ በመምጣቴ ነው”።
በእግር ኳስ ዘመን ቆይታው ምርጥ ጥምረቴ ስለሚለው
“ለደቡብ ፖሊስ ስጫወት በነበረበት ሰዓት ላይ ነው ከጌታነህ ከበደ ጋር የነበረኝን ጥምረት ምርጥ የምለው። በጥምረታችንም በጣም ደስተኛም ነበርኩ። በተለይ ደግሞ ያኔ ቡድናችን በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው /ሞውሪኖ/ ነበር የሚመራውና እሱም ነው እኔንና ጌታነህን ጨምሮ በሌሎችም ታዳጊ ተጨዋቾች ላይም ከፍተኛ እምነት ስለነበረው ሁለታችንን በጋራ እንድንጫወት አድርጎም ነው ብዙ ጎልም እንድናስቆጥር ያደረገው እና ከጌታነህ ጋር የነበረኝን ጥምረት ዛሬም ድረስ በአቻነትም ወደር የማላገኝለት ነው”።
በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ጎሎችን ስታስቆጥር ቁጥሮቹን የመመዝገብ ዲያሪ አለህ…ካለህ ምን ያህል አስቆጥረሃል?
“የጎሎቼን ብዛት በተመለከተ ብዙ ጊዜ ለመመዝገብ ሀሳቡ ቢኖረኝም በቁጥር ደረጃ ግን ይህን ያህል ነው ብዬ ለመናገር የፃፍኩት ወይንም ደግሞ ያስቀመጥኩት ነገር ስለሌለ ብዙ ነገርን ማለት አልችልም። በተወሰነ መልኩ ግን ከማስታውሳቸው መካከል በደቡብ ፖሊስ እያለው ከ20 በላይ በአዳማ ከተማ ቆይታዬም እስከ 20 የሚደርሱ ጎሎችን ማስቆጠሬ ነው። ለሌሎቹ ቡድኖች ስጫወት ደግሞ ከአጥቂ ይልቅ የመሀል ተጨዋች አድርገው ይጠቀሙብኝ ስለነበር ብዙ ጎል ማስቆጠር አልቻልኩም እና እንደ አጠቃላይ ግን በኳስ ዘመኔ ብዙ ጊዜ ነገሮችን አስብ የነበርኩት በጉዳት ከሜዳ እርቅ ስለነበር ተጎድቼ በነበርኩበት ሰዓት ስለአጠዋቸው ነገሮች እና ከጉዳቴ አገግሜና ወደ ጤንነቴ ተመልሼም ወደ እግር ኳሱ ስለመመለስ ነበር ስጨነቅ የነበርኩት”
ለወልቂጤ ከተማ ግቦችን ማስቆጠር ስለመጀመሩ እና ለቡድኑ በቀጣይነት ሊሰጠው ስላሰበው ግልጋሎት
“እንደ አጥቂ ጎሎችን ወደ ማስቆጠሩ መመለሴ በጣም እያስደሰተኝ ነው። ይበልጥ የሚያስደስተኝ ደግሞ በአዳማ ከተማ ላይ እንዳስቆጠርኩት አይነት ቡድናችን ለድል የሚበቃበትን ግብ ሳስቆጥር ነው። ለወልቂጤ ከተማም እስካሁን ሁለት ጎሎችን በቡድኔ ተጨዋቾች እገዛ በጋራ በመጫወት አስቆጥሬያለሁ እና ከእዚህ በኋላም በሚኖረኝ የቡድኑ ቆይታ ጠንክሬ ሰርቼ ቡድኔን ለውጤት የሚያበቁ ግቦችን አስቆጥራለው”።
ስለ ወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው
“አሰልጣኛችንን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በእሱ ስር የሰራሁት። አስቀድሞ እሱን መጀመሪያ ላይ የጠበቅኩት እና ወደ ዝግጅት ላይ ገብተን በሚያሰራው ልምምድ ላይ እንዳየሁት ልዩነት አለው። ጥሩ የአሰለጣጠን ብቃት እና ልምድ ያለው ጎበዝ አሰልጣኝ ነው። አሰልጣኛችን ኳስን እንዴት አድርገን መጫወት እንዳለብን ቀለል ባለ መልኩም ነው የሚያስረዳንና ይሄን ተመልክቼበታለው። ጥሩም አሰልጣኝ ነው ያለን”።
በመጨረሻ
“ወልቂጤ ከተማን በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ጥሩ ደረጃ ላይ ማድረስ ዋንኛ ዓላማችን ነው። ቡድናችን እንደ ህብረት እንዲጫወትም ሁሌም እየተጋን ይገኛል። ፈጣሪ ረድቶን ጥሩ ውጤትን እንድናመጣም ምኞቴም ነው። ይህን ካልኩ ለቡድናችን ተጨዋቾች ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክትም ለእግር ኳስ የሚበጀው የእኔነት ስሜት ኖሮ መጫወት ሳይሆን ስራን በህብረት መስራት ነውና በእዚሁ አካሄዳችን እና ጉዞአችን ነው አሁንም ልንቀጥልበት የሚገባን”።