ወልቂጤን አሸንፈን ዋንጫውን እናነሳለን፤የሻምፒዮኖቹም ቡድን አምበል መሆኔም እየተሰማኝ ነው”ያሬድ ባዬ /የፋሲል ከነማ አምበል/

“ወልቂጤን አሸንፈን ዋንጫውን እናነሳለን፤የሻምፒዮኖቹም ቡድን አምበል መሆኔም እየተሰማኝ ነው”

“ቅዱስ ጊዮርጊስን ስናሸንፍ ወታደራዊ ሠላምታ ያቀረብኩት የፋሲል ከነማ ወታደሮች ስለሆንን ነው”
ያሬድ ባዬ /የፋሲል ከነማ አምበል/

ተወልዶ ያደገው ባህርዳር ከተማ ውስጥ ነው እያየሁ አድጌያለው የሚለው ተምሣሌት ግን የለውም ያለኝን አቅም አውቄ… አውቄ ብቻ ሳይሆን ደግሞ ብቃቴን አውጥቼ እንድጠቀም አድርጎኛል በማለት ኢንተርናሽናል አርቢትር ዶ/ር ኃ/የሱስ ባዘዘውን ያመሰግናል በክለቡ ደጋፊዎች የሚታወቀው በቅፅል ስሙ ነው “ገብርዬ” ይሉታል… የአፄ ቴዎድሮስ ታማኝ ጄኔራል የሆነውን ገብርዬን በቅፅልነት ሰይመውት ከዋናው ስሙ ባላነሰ መለያው ሆኗል…ታማኙ ገብርዬ… የሬድ ባዬን…፡፡ ለሴንትራል ዩኒቨርሲቲ፣ ለባህርዳር ከተማና ለአውስኮድ በሱፐር ሊጉ ከተጫወተ በኋላ ባለፉት 6 አመታት በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ይገኛል…አንድ አመት ለዳሽን ቢራ ከተጫወተ በኋላ ከ2009 ጀምሮ ባለፉት 5 አመታት በተጨዋችነት፣ባለፉት 3 አመታት ደግሞ በአምበልነት ፋሲል ከነማን እየመራ ለዋንጫው ከጫፍ ደርሷል፡፡

ፋሲል ከነማ በቀጣዩ ቅዳሜ ወልቂጤ ከተማን ማሸነፍ የሚችል ከሆነና ከክልል ክለቦች የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳ 4ኛው ክለብ መሆኑን ካረጋገጠ ከዕለቱ የክብር እንግዳ ዋንጫ የመቀበልን ምርጥ ታሪክ የሚሰራው አምበሉ ያሬድ ባዬ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ምን ያልተነሳ ጉዳይ አለ… ስለ ፋሲል የዋንጫ ድል አድራጊነት፣ለርሱ ኮከብ ስለሚላቸው፣ ስለ ኮቪድ- 19፣ስላለፉት 20 ጨዋታዎች፣ለአፍሪካ ዋንጫ ስለማለፋችን፣የፋሲል ድል ስለሚያመጣው መልካም ነገር፣ስለተደሰተባቸውና ድል ስላደረጉባቸው ጨዋታዎች፣ፋሲል ከነማን ከስነ ምግባር መጓደል ጋር ተያይዞ ስሙ ስላለመጠራቱ፣ስለ ትዳሩና ልጁ… ለተሰነሱለት በርካታ ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ምርጥ አምበል ነኝ ብለህ ታምናለህ…?

ያሬድ፡- /ሳቅ/ ገና ነኝ እየተማርኩ ነው፡፡ ጥሩ አምበል ለመሆን እየጣርኩ ነው ከዚህ በፊት የቡድናችን አምበል ከነበረው ሙሉቀን አባይ አሁን አሰልጣኝ ነው ከርሱ ብዙ ተምሬያለው፤ ባለፉት 3 አመታት የቡድኑ አምበል ሆኜ አገልግያለሁ ጥሩ አምበል ለመሆን እየጣርኩ ነኝ፡፡ አሰልጣኝን ከተጨዋቾቹ ጋር ማገናኘት፣ ቡድኑን በሜዳ ውስጥ መምራት፣ ተጨዋቾቹን ማነቃቃት የሚለውን የአምበል ተግባር በተቻለኝ መጠን እየተገበርኩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከስነ ምግባር መጓደል ጋር ተያይዞ የፋሲል ከነማ ስም የማይጠራው በአንተ ጠንካራ አመራርነት ይሆን?

ያሬድ፡- ይሄ ስራ በተለይ የቡድን መሪው ነው…እርሱ ደግሞ ስራውን በደንብ ያውቃል በደንብ ቡድኑን እየመራ ነው በዋናነት የሚመለከተው እሱን ነው ነገር ግን ጥያቄውን ካነሳኸው አይቀር ተጨዋቾቹን በተመለከተ ወጣ ያለ አስቸጋሪ ባህሪ ያለው ተጨዋች የለም ብዙ አልተቸገርንም ቢኖር እንኳን ያለው የቡድን መንፈስ ይመልሰዋል ብዬ አስባለው ለዋንጫ ጉዟችንም ጥሩ የነበረው የነበረንን የቡድን መንፈስ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ዋንጫ እንዳያነሳ የሚያደርግ ኃይል አለ ብለህ ታምናለህ…?

ያሬድ፡- አሁን ላይ ሁሉንም የሚያውቅ ፈጣሪ ብቻ ነው ኳስ በመሆኑ የሚሆነው አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ያን ያህል ዋንጫ እናጣለን የሚል ስጋት የለብኝም ለምሣሌ ኢትዮጵያ ቡና የዛሬውን ጨዋታ ጨምሮ 6ቱም ማሸነፍ አለበት (ቃለ ምልልሱን የሰራነው ረቡዕ ጠዋት ነው) ማሸነፍ ባንችል እንኳን ቡና ነጥብ ይጥላል ብዬ አምናለሁ ለማንኛውም 1 ጨዋታ ማሸነፍ ወይም 3 አቻ ውጤት እናጣለን ብዬም አልሰጋም፡፡ በቀጣይ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነው የምንጫወተው ሁሉንም እንደ ዋንጫ ጨዋታ ነው የምናየው.. ወልቂጤን አሳንሰን እነ ጊዮርጊስን አክብደን አንገባም የመጣንበት ጉዞም የሚያሳየን ይሄን ነው ሁሉንም ጨዋታ ለማሸነፍ ነው የምንገባው ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ አንመለስም ወልቂጤን አሸንፈን ዋንጫውን እናነሳለን የባለድል ቡድን አምበል መሆኔም እየተሰማኝ ነው 3ቷን ነጥብ አግኝተን ዋንጫውን እናነሳለን የባለድል ቡድን አምበል መሆኔ እየተሰማኝ ነው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- በጨዋታው ሂደት ላይ ስኬታማ ለመሆንህ የቤተሰብህ ድጋፍ ምን ይመስላል?

ያሬድ፡- ሙሉ ቤተሰቦቼ ለዚህ ለመድረሴ ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው እነሱን ማመስገን እፈልጋለሁ ባለቤቴ ሳምራዊት እንዳለም ትልቅ ሚና አላት ለስኬቴ ትልቁ አስተዋፅኦ የእሷ ነው… ያው ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነኝ ልጄ ሄሜን ያሬድ ትባለለች የስሟ ትርጉም “እግዚአብሔር ልመናችንን ሰማ” ማለት ነው… በዚህ አጋጣሚ ባለቤቴ ሳምሪን በጣም እንደምወዳትና እንደማፈቅራት መናገር እፈልጋለው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- በእስካሁኑ ጨዋታዎች ድል በማድረጋችሁ የተደሰትክበት ጨዋታ የትኛው ነው…?

ያሬድ፡- በድል ከተወጣናቸው ጨዋታዎች መሀል ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ሀድያ ሆሳዕናን የረታንባቸው ይበልጡብኛል የመጀመሪያዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡናን የረታንባቸው ጨዋታዎች በይበልጥ ይጠቀሳሉ የእኛ ተከታዮች ስለነበሩ አሸንፈናቸው ከነርሱ የራቅንበት ጨዋታ አይረሳኝም… ተከታይ ሆነው ማሸነፋችንና ከእነሱ መረቃችን ብቻ ሣይሆን ግቦቹ የገቡበት ደቂቃዎች የበለጠ ደስታችንን እጥፍ ድርብ አድርጎታል ሊያልቅ ነው በተባለበት ሰዓት የማሸነፊያ ግቦችን ማስቆጠር ያስደስታል ሌላው ጅማ ላይ ሀዲያ ሆሳዕናን የረታንበት ግጥሚያ የሚረሳኝ አይደለም በእርግጥ እነኚህን ጠቀስኳቸው እንጂ አሸንፈን 3 ነጥብ ያገኘንባቸው ጨዋታዎች በሙሉ አስደስተውኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የ20 ጨዋታዎቹን ጉዞ እንዴት አየኸው? ምንስ ስሜት ፈጠረብህ?

ያሬድ፡-ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል 15 ድል 4 አቻና 1 ሽንፈት ሪከርድኮ ነው… ምርጥ ጊዜ እንዳሳለፍንም የሚያሳይ ነው የሚገርም ተፎካካሪነት ነበረን…. የቡድን መንፈሱም ልዩ ነበር… ለማሸነፍ ያለው ተነሳሽነት ጠንካራ ነበር… ከዚህ አንፃር ጠንካራ ሆነን ቀርበን ጥሩ ውጤት አስመዝግበናል የሁላችንም የጋራ ውጤት ሙሉ የአሰልጣኞች ቡድን፣ ተጨዋቾቹ፣ አመራሮቹና መላው ደጋፊያችን የጋራ ድምር ውጤት በመሆኑ ለሁሉም ክብር ይገባቸዋል ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን 1ለ0 ስትረቱ ግቡን በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠርከው አንተ ነህ…ሙጂብ ቃሲም ተቀይሮ እንደወጣ ማስቆጠርህ እድለኛነትህን አያሳይም…?

ያሬድ፡- ሙጅብ ባይወጣም የፍፁም ቅጣት ምቱን የምመታው እኔ ነበርኩ፤ በዚህ በኩል የሚያመጣው ለውጥ የለም የቡድኑ ዋነኛ የፍፁም ቅጣት ምት መቺ እኔ ነኝ… በርግጥ በኮከብ ግብ አግቢነት እየተፎካከረ ነው ያም ቢሆን 94ኛ ደቂቃ ላይ የተገኘ እንደመሆኑ መምታቴ አይቀርም ነበር በኔ ግብ በማሸነፋችን ደስ ብሎኛል፡፡

 

ሀትሪክ፡- ግቧን አስቆጥረህ… ወታደራዊ ሠላምታ አቀረብክ …ምንድነው ምክንያቱ …?

ያሬድ፡- /ሳቅ/ ሁላችንም ተጨዋቾች የፋሲል ከነማ ሠራተኞችና ታዛዦች ነን ቅዱስ ጊዮርጊስን ስናሸንፍ ወታደራዊ ሠላምታ ያቀረብኩት የፋሲል ከነማ ወታደሮች ስለሆንን ነው የፋሲል ከነማ ወታደሮች መሆናችንን ለማሳየት ያደረኩት ነው በግቧ ደስታዬ ወደር አልነበረውም፡፡

ሀትሪክ፡- በቦታህ አይተኸው እያደነቅክ ያደከው ተከለካይ አለ? ከሀገርህ ውስጥና ከውጪስ ምርጡ ተከለካይ ላንተ ማነው…?

ያሬድ፡- ብዙ ተጨዋቾችን የማየት እድሉ ስላልገጠመኝ አይቼ ያደኩት የመሀል ተከለካይ የለም ነገር ግን በክለብ ደረጃ መጫወት ከጀመርኩ ወዲህ ግን ደጉ ደበበ ምርጫዬ የሆነ ጎበዝ ተከላካይ ነው ከውጪ ደግሞ የሊቨርፑሉ ቨርጂል ቫንዳይክ ምርጫዬ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ የዋንጫ አሸናፊነት ለሊጉ ይሰጣል የምትለው ጥቅም ምንድነው…?

ያሬድ፡-በደንብ የሚፈጥረው ለውጥማ አለ፡፡ ብዙ ጊዜ ዋንጫ ይወስዳል ተብሎ የሚታመነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው ደጋግሞ ወስዶ አሳይቷል፡፡ የእኛ ዋንጫ መውሰድ ይሄን የስነ-ልቦና እምነትን ያስቀራል ባለፉት 4 አመታትም ሌሎች ክለብ ዋንጫ መውሰድ መጀመራቸው ያመጣው ለውጥ አለ በስነልቦና ተሸንፎ ዋንጫውን ለአንድ ክለብ ብቻ መስጠቱን እያስቀረን ነው ይሄም ትልቅ ለውጥ ነው አሁን ዋንጫው ለሁሉም ክለቦች ክፍት መሆኑን አሳይተናል፡፡

ሀትሪክ፡- ከክፍያ ጋር ተያይዞ የክለቡ ስም በመጥፎ አለመነሳቱ ለዋንጫው አስተዋፅኦ ነበረው ማለት ይቻላል?

ያሬድ፡- አስተዋፅኦ ካላቸው ጉዳዮች አንዱ ይሄ ነው ተጨዋች ሁሉም ነገር ሲሟላለት ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል በፋሲል ከተማ የታየውም ይሄ ነው ደሞዝም ይሁን ጥቅማ ጥቅሞች በጊዜው ነው የሚሰጠን… ፋሲል ከነማ ጋርም የክፍያ ችግር አልተፈጠረም በዚህም ደስተኞች ነን፡፡

ሀትሪክ፡- 2011 ባለቀ ሰዓት ዋንጫ አጣችሁ …. 2012 ደግሞ የኮቪድ 19 ስርጭት ሊጉን አቋረጠው ሁለቱ አመታት የፋሲል ከነማ የቅሬታ ዘመን ነበር ማለት ይቻላል?

ያሬድ፡- አዎ አዎ… ደባሪ ጊዜ ነበር በይበልጥ 2011 ደግሞ አሳዛኝ ጊዜ ነው ዋንጫ ያጣንበት ተበልጠን እግር ኳሳዊ በሆነ ጉዳይ ባለመሆኑ ተከፍተን ነበር… 2012 ግን እየመራን ቢሆንም የተፈጠረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አለምን ያስቸገረ በመሆኑ ያን ያህልም አልተከፋንም ራስን መከላከል ማዳን ላይ ያተኮረ በመሆኑ እንደ 2011ዱ አልጎዳንም አልቆጨንም… ሀገር ሠላም ህዝቡ ጤነኛ ሲሆን ነውና ኳሱ የሚካሄደው በ2012 ብዙም ቅር አልተሰኘንም፡፡

ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 ለፋሲል ከነማ አባላት ስጋት አልነበረም…?

ያሬድ፡- በኮቪድ 19 መከላከል ፋሲል ከነማ ከሁሉም ክለቦች የተሻለ ነበር የትም ቦታ አንታይም ከሆቴላችን አንርቅም የሚወጣ የለም እንደ ክለብ ጥሩ መከላከል አድርገናል፡፡ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ መያዝ በርግጥ በተወሰነ መልኩ ረብሾናል ያኔ ከባህርዳር ጋር ስንጫወት የተወሰነ ጥሩ ያልሆነ ስሜት ነበረው የኛ ቡድንም የኮቪድ ውጤት ጥሩ ስላልነበረና ውጤት በፈለግንበት ሰዓት የተፈጠረ በመሆኑ ጥሩ ስሜት አልተሰማንም የኮቪድ ውጤቱ ከሁለት ቦታ የተከናወነ መሆኑ በራሱ ትንሽ ከበድ ብሎን ነበር. የባህርዳር ከተማ ተጨዋቾችም ጥሩ ስለነበሩ የጨዋታውን ውጤት በፀጋ ተቀብለነዋል፡፡

ሀትሪክ፡- የዲ.ኤስ.ቲቪ መምጣትም ለውጥ አምጥቷል ውድድሩን አጠናክሮታል የሚሉ አሉ… አንተስ ?

ያሬድ፡- አዎ በሚገባ አጠናክሮታል… በደንብ ተዘጋጅተን እንድንመጣ አድርጎናል ጨዋታውን ግልፅ አድርጎት ሁሉንም ፊት ለፊት እንድናይ አድርጓል ጥሩ ፉክክር እያየን መጥተናል ራሳችንን ለመሸጥ ጠንክረን እንድንጫወት አድርጎናል ለዚህም ነው ፉክክሩ ከፍ ያለው ማለት ይቻላል፡፡

ሀትሪክ፡- እንደ አምበልና ተጨዋች ሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪ ያለህ ማህበራዊ ግንኙነት ተመሳሳይ ነው…?

ያሬድ፡- /ሳቅ/እኔ የምሰማው እንደውም ያሬድ አያወራም የሚል ነው ሜዳ ላይ ቡድኔን እመራለው እናገራለሁ ያ አይቀርም ጨዋታው ሲያልቅ ዳኛን አልናገርም በቃ የሚለወጥ ነገር የለም ብዬ ስለማስብ ዝም ብዬ ነው ከሜዳ የምወጣው… ከሜዳ ውጪ ግን አይናፋርም ተናጋሪም የምባል አይነት ሰው አይደለሁም እንደ ሁኔታው ነው ቀልድ ካለ ልቀልድ እችላለው ዝምታም ካለ ዝም ነው የምለው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ የዘንድሮ የውድድር አመት ኮከብ ማነው ?

ያሬድ፡- ሁሉም ናቸዋ… ሁሉንም መምረጥ ይቻላል? ልዩ ነበርንኮ… አብዛኛው ተጨዋቾ ወጥ አቋም ነው ሲያሳይ የነበረው ሁሉም ተጨዋች ለኔ ኮከብ ነው እንደ ቡድንም ምርጥ የነበርነው ለዚህ ነው ከሊጉ አንፃር ካየን ግን አቡበከር ናስርና ሙጅብ ቃሲም የተለየ አመት አሳልፈዋል፡፡

ሀትሪክ፡-ዋሊያዎቹ ከ8 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፋቸው ውስጥ አንዱ ባታሪክ ሆነሀልና ምን ተሰማህ… ?

ያሬድ፡- በጣም ተደስቻለሁ ለኔ ብቻ ሳይሆን ለመላው ህብረተሰብ ደስታን የፈጠረ ታሪክ ሰርተናል፡፡ አሁን ብቅ እያለ ያለ ወጣትም ተስፋ የሚያደርገው የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን ማገልገል ነውና ለነርሱም መነሳሳት ፈጥራል ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ከሆነ ከታች ያለውም ይበረታልና በማለፋችን ደስ ብሎናል፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ደግሞ በፋሲል ከነማ አሰልጥነውሃልና… እስቲ ስለሁለቱ የምትለን ነገር ካለ…?

ያሬድ፡- ሁለቱም ምርጥ አሰልጣኝ ናቸው፤ ስኬታማ ጊዜ አሳልፈዋል አጨዋወታቸው በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይነት አለው…. እንግዲህ ሁለቱም ድላቸውን ያጣጥሙት ማለት ነው የምፈልገው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ከኳስ ውጪ ሌላ ዘና የምትለው በምንድነው?

ያሬድ፡- ከኳስ ውጪ ብዙ ጊዜ ባይሆንም ፊልምና ቲያትር ማየት ደስ ይለኛል አዲስ አበባ ስመጣ ደግሞ ቲያትር ማየት እመርጣለሁ እሱንም ጊዜ ካለኝ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የውጪ ኳስ ታያለህ.. የማን ደጋፊ ነህ…?

ያሬድ፡- ብዙ የውጪ ኳስ ተመልካች አይደለሁም ሲያጋጥመኝ ነው የማየው… በፊት ደጋፊ ነበርኩ.. አሁን ግን የምደግፈው ቡድን የለኝም፡፡

ሀትሪክ፡- ብዙ ኳሶችን የማታይ ከሆነ ለመለወጥ ለማደግ ያለህን እድል አያጠበውም፤… ?

ያሬድ፡-አይ የማየቱ ፍላጎቱ የለኝም ምን ማድረግ ይቻላል…? አሁን ላይ ጊዜ ካገኘሁ ብቻ ነው የማየው…

ሀትሪክ፡- ከኢንተርናሽናል አርቢትር ዶ/ር ኃ/የሱስ በዛዘው ጋር የተለየ ግንኙነት አላችሁ የሚባል ነገር ሰማሁ… እውነት ነው…?

ያሬድ፡- ለዚህ ለመድረሴ ትልቁን አስተዋፅኦ እሱ ይወስዳል፤ትልቅ ድጋፍ አድርጎልኛል…ያለኝን አቅም እንዳውቅና አውጥቼ እንድጫወትም አድርጎኛል፤እንደምወደውና እንደማከብረው መግለፅ እፈልጋለው፡፡

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ.. የምታመሰግነው ካለ እድሉን ልሰጥህ?

ያሬድ፡- በኔ ህይወት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉትን በሙሉ አመሰግናለሁ…ቤተሰቦቼን፣ባለቤቴን፣ የቅርብ ጓደኞቼን፣ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች፣የፋሲል ከነማ አመራሮችና ደጋፊዎችን አመሰግናለሁ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport