“አትሌት ቀነኒሳ በቀለና አትሌት ሙስነት ገረመው በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ይወዳደራሉ” የኢትዮዽያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ

….በአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኦሎምፒክ ኮሚቴ ሌላ ውዝግብ እንዳይነሳ ተሰግቷል

የኢትዮዽያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኢትዮዽያን በማራቶን የሚወክሉ የማራቶን ተወዳዳሪዎችን በሰበታ ከተማ ባካሄደው የመምረጫ ውድድር መለየቱ ታውቋል። አትሌት ቀነኒሳ ግን ለፌዴሬሽኑ ቅሬታውን በመግለጽ ያለው ሰአት በኦሎምፒኩ የመካፈል መብት እንደሚሰጠው በመግለጽ ማስተካከያዎችን እንዲደረግና በቀጥታ የመወከል መብት እንዲያገኝ ቢጠይቅም ተቀባይነት አጥቷል። ባለፈው ቅዳሜ ከተካሄደው የመለያ ውድድር በኋላም በሁለቱም ጾታዎች አምስት አምስት አትሌቶች የተመረጡ ሲሆን አትሌት ቀነኒሳ በቀለና አትሌት ሙስነት ገረመው ተገቢ ባልሆነ መመዘኛ ተጥለናል ብለው ያቀረቡት ቅሬታ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተቀብሎታል።

“አትሌት የመምረጥ ስልጣኑ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቢሆንም የመጨረሻው ውሳኔ ግን የእኛ ነው። ዋነኛ ፍላጎታችን የሀገራችንን ባንዲራ ከፍ የሚያደርግ ውጤት እንዲመዘገብ ነው። ተገቢ ባልሆኑ አሰራሮች ወቅታዊ ብቃታቸው ጥሩ ላይ የሚገኙ አትሌቶች ከውድድሩ እንዲቀሩ አንፈቅድም ”

በማለት የኢትዮዽያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ መናገራቸው ታውቋል።
በፌዴሬሽንና በአትሌቱ መሃል ውዝግብ ሲነሳ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጠርቶ የማደራደር ስልጣን እንዳለው ይህ የማይሆን ከሆነ የመጨረሻ ውሳኔው የኦሎምፒክ ኮሚቴ መሆኑ ታውቋል። በጉዳዩ ዙሪያ ወደ ፌዴሬሽኑ ዋናና ምክትል ጸሃፊዎች ስልክ ቢደወልም ሊያነሱት ባለመቻላቸው የፌዴሬሽኑን አቋም ማወቅ አልተቻለም

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport