“ግለሰቦች ዕውቅና ቢነፈጉኝም ውለታ አዋቂው የስፖርት ቤተሰቡና ህዝቡ ቀድሞ ስለሸለመኝና ዕውቅና ስለሰጠኝ እጅ እነሳለሁ”
“ከ12ቱ ክለቦች በበለጠ ፈተናዎቻችንና ኮቪድ ጠንካራ ተጋጣሚዎቻችን ነበሩ”
ኢንስ. አብርሃም መብራቱ
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንና የስፖርት ኮሚሽን በሐዋሳ ሌዊ ሆቴል ከስምንት ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ የበቁትን ዋልያዎቹን ሸልመዋል፤ ከዋልያዎቹ ሽልማት በላይ የፌዴሬሽኑ አመራሮች በራሳቸው ድግስ ራሳቸውን መሾም መሸለማቸው የብዙዎቹን ትኩረት ስቧል፡፡ አንድም ቀን ስብሰባ ላይ ተገኝተው የማያውቁ አመራሮች ሳይቀሩ የሽልማቱ አካል ሆነው ጠንካራውን የኮትድቭዋር ብ/ቡድን በማሸነፍ ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፉ የራሱን አሻራ ያሳረፈው ኢንስ. አብርሃም መብራቱ ከሽልማቱም ከእውቅናም ውጭ መሆኑ ብዙዎቹን አላስደሰተም፡፡ አብርሃም አለመሸለሙና እውቅና መነፈጉን ብቻ ሳይሆን በሽልማት ስነ ስርዓቱም ላይ እንዳይገኝ መደረጉ ብዙዎቹን ቅር አሰኝቷል፡፡
ጉዳዩ ቀልቡን የሳበውና የሕዝቡን ቅሬታና አስተያየት አንግበው ወደ ኢንስ. አብርሃም የእጅ ስልክ የመታው የሀትሪክ ስፖርት ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ለመሆኑ በሽልማቱ ስነ ስርዓት ላይ ያልተገኘኸው አኩርፈህ ነው? ሲል ጠይቆት ኢንስትራክተሩም “ለምን አቃርፋለሁ? ሳልጠራ፣ ሳልጋበዝ እንእት በአዳራሹ እንድገኝ ትጠብቃለህ?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሶለታል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ኢንስ. አብርሃም መብራቱ ከሀትሪኩ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር በነበረው የ6ዐ ደቂቃ ቆይታ ስለ ሰበታ፣ ስለቀጣይ ቆይታው ከፋሲል ውጭ ደሞዝ የከፈለውም ያልከፈለውም፤ ዝግጅት ያደረገውም ያላደረገውም እኩል ሆነው ማየቴ አስገርሞኛል ስለማለቱም፣ እውቅናና ሽልማት መነፈጉ ሀገሩን እንዳያገለግል ያደርገው ይሆን? የሚሉና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዩች ዙሪያ የሰጠው ሰፊና አነጋጋሪ ምላሽ ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡ እንደተለመደው ጊዜያችሁን አውሱን፡፡
ሀትሪክ፡- …ተበሳጭተሃል…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …ለምን እበሳጫለሁ…?…1ለዐ አሸንፈን ወጣን እኮ….!…ማሸነፍ ያበሳጫል እንዴ…?…(እየሳቀ)…(ያነጋገርኩት ባለፈው ማክሰኞ አዳማን ካሸነፉ በኋላ ነበር)…
ሀትሪክ፡- …እኔ እንኳን ተበሳጭተሃል ያልኩህ ባለመሸለምህ ነው…አሁን ደግሜ ልጠይቅህ… ብ/ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ አብርሃም አስተዋፅኦ አለው…ከዚህ አንፃር ሊሸለምና ዕውቅና ሊሰጠው ሲገባ…አልተሸለመም በማለት…ብዙዎች አለመሸለምህ አበሳጭቶአቸዋል… አንተስ ተበሳጭተሃል…?…
ኢንስ አብርሃም፡-…(እንደ መሣቅ እያለ)…ለዚህ ጥያቄ መልስ የለኝም…ከአንተ ጋር ቀጠሮ የያዝነው በሽልማት ዙሪያ ለማውራት ሣይሆን በክለቤና በሊጉ ዙሪያ እንድናወራ ስለሆነ… የማላስቸግርህ ከሆነ ይሄን ጥያቄ ብትዘለው ደስ ይለኛል…(በአንደበቱም በፊትም እየተናገረ)…
ሀትሪክ፡- …መዝለል እንኳን አልዘለውም…ለጊዜው ግን የጥያቄውን አቅጣጫ ልቀይረውና… ፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ሻምፒዮን…(ፋሲል ከተማን)…በማግኘቱ ምን አልክ…?…ብልህ ምን ትመልስልኛለህ…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …ፕሪሚየር ሊጉ እንዳልከው አዲስ ሻምፒዮንስ አግኝቷል…ይሄ በጣም የሚያስደስት ብቻ ሣይሆን ፕሪሚየር ሊጉም ተገማች አለመሆኑን ያሳያል…ይሄ መሆኑ የሊጉ የፉክክር መጠን ከፍ እያለ፣እየጠነከረ፣እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው…የሊጉን ዋንጫ የማንሣት እድል ለአንድና ለሁለት ወይም ለጥቂት ክለቦች ያልተተወ…አዲስ ቡድንም የሚያነሳበት አጋጣሚ እንዳለ የሚጠቁም ነው…አዲስ ቡድን ዋንጫውን ማንሣቱም ለሊጉ ተጨማሪ ውበት ነው…
ሀትሪክ፡- …እናንተ አሰልጣኞች ጋር “እንኳን ደስ አለህ” ያለመባባል፣ለድሉ እውቅና ያለመስጠት የዘመናት መጥፎ ችግር አለ…አብርሃምስ ከዚህ አሮጌ ታሪክ ለማምለጥ የሊጉ ሻምፒዮን የሆነውን ስዩም ከበደን “እንኳን ደስ አለህ” ብሎት ይሆን…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …(በጣም ሳቅ)…እኔን እንግዲህ አንተም ስለምታውቀኝ በደንብ መናገር ትችላለህ…ንፉግ የምባል አይነት ሠው አደለሁም…እንኳንስ ስዩም ከበደ የቅርብ ጓደኛዬን ተወውና ለሌሎችም ወደ ኋላ አልልም…ፋሲሎች ሻምፒዮንስ መሆናቸውን እንዳረጋገጡ “እንኳን ደስ አለህ” ለማለትም አልዘገየሁም…ወዲያውኑ ነው ለዚህ ትልቅ ስኬት በመብቃትህ ተደስቻለሁ እንኳን ደስ አለህ ያልኩት…የስዩምን ተወውና እኛ ከምንወዳደርበት ሊግ ውጪ ያሉትንና ፕሪሚየር ሊጉ የተቀላቀሉትን የመከላከያ፣የአዲስ አበባና የአርባ ምንጭ ክለብ አሰልጣኞችን…በቴክስትም ስልክ በመደወልም …በደስታቸው መደሰቴን ገልጬላቸዋለሁ…ይሄ ባህል መለመድ አለበትም ብዬ አስባለሁ…
ሀትሪክ፡- …ፕሪሚየር ሊጉ ትክክለኛውን ሻምፒዮን አግኝቷል…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …በጣም…!…ከነበራችው ዝግጅት፣ከነበራቸው ፐርፎርማንስ (ብቃት) እንዲሁም ባለፉት ሁለት አመታት ዋንጫው እየደረሱ ከመመለሳቸው፣በየአመቱ እየተገነባ… እየተገነባ ከመምጣቱ አንፃር…በእርግጥም የሊጉ ሻምፒዮን መሆን የሚበዛባቸው አይሆንም… ፋሲል ከተማ ሁሉንም ያሰማማ ትክክለኛው የሊጉ ሻምፒዮን ነው ለእኔ…
ሀትሪክ፡- …በአንተ የሚሰለጥነው ሰበታ ከተማ ግን ለዋንጫ ከመፎካከር ይልቅ ላለመውረድ በመታገል ነው አመቱን ያሳለፈው…አብርሃም በየመን፣በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣በፊፋና በካፍ ካለህ ከፍ ያለ ብራንድ አንፃር የሚመጠንህ ነው…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …አንዳንድ ጊዜ የሚያጋጥምህ ቡድን የምትፈልጋቸውን ነገሮች ወይም ለውጤታማነት የሚረዳህን በሙሉ ማሟላት ካልቻለ ጋርዲዮላም ሆነ ሞውሪንሆ ቢመጣ እኔ በሰበታ ያጋጠመኝ ነገር ማጋጠሙ አይቀርም…እኔ ወደ ሰበታ ስመጣና በመጀመሪያው ውይይታችን ሁሉም ነገር የተሟላ እንደሆነና ያልተሟላው ተሟልቶ ለስራው ምቹ የሆነ ከባቢ እንዳለ ነበር የተነገረኝ…ነገር ግን ወደ ሥራ ከገባሁ በኋላ የተባለውም ሆነ የጠበኩትን ነገር ማግኘት አልቻልኩም…ይሄ በራሱ ትልቅ ፈተና ነበር…ያም ቢሆን ከችግራችን አንፃር የተሻልን ለመሆን ሞክሬያለሁ…
ሀትሪክ፡- …ወደ ኃላፊነት ስትመጣ አሳካለሁ ያልከውን አሳክተሃል…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …ወደ ክለቡ ኃላፊነት ስመጣ ከአመራሮቹ ጋር የተነጋገርነው በተቻለኝ መጠን የቡድኑን እስትንፋስ በሊጉ ማቆየት ነበር…ይሄን ደግሞ ቡድኑ ገና ቀሪ ሶስት ጨዋታዎች እያሉት ማሳካት ተችሏል…ይሄ ብቻ አይደለም…ከዚህም አልፈን የአመቱን ውድድር ከሊጉ ምርጥ አምስቱ ቡድኖች አንዱ ሆኖ ለመጨረስም እየታገልን ነው…ከተሰጠኝ ግብ (ታርጌት) አንፃር ግባችን በጣም የተሳካ ነበር ማለት እችላለሁ…ይሄ ስኬት የመጣው ዝም ብሎ ሳይሆን በብዙ ፈተናዎችና መሰናክሎች ውስጥ ሆነን ነው…
ሀትሪክ፡- …በሰበታ አሰልጣኝነትህ ብዙ ፈተናዎችን ያስተናገድክ ይመስለኛል…የተጫዋቾች ደሞዝ አለመከፈልን አስመልክቶ አንዴ ልምምድ የማቆም…በሌላ ጊዜ የመጀመር…ጨዋታ ያለ በቂ ልምምድና የስነ ልቦና ዝግጅት የማድረግ ነገሮችን አስተናግደሃል…በዚህ መልኩ በፈተና የተከበበን ቡድን ማሰልጠንና ለውድድር ቀርቦ ውጤታማ መሆን አይፈትንም…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …(እንደ መሳቅ እያለ)…በእርግጥ ትኩረትህ ሁሉ በሜዳ፣በልምምድ ላይ እንዳታደርግ የሚገፋህ እንደሆነ መደበቅ አልፈልግም…ግን እኔ በፈተና ውስጥ አልፎ ፈተናዎችን ተቋቁሞ የመስራት ልምዱ አለኝ…ያ በፈተናው እንዳልንበረከክ ጠቅሞኛል… ፈተናዎችን ተጋፍጦ አሸንፎ ማለፉ ያስደስተኛል…በባህሪዬ ፈተናዎችንና ችግሮችን ወደ መጥፎ (Negative Energy)ሣይሆን ወደ መልካም ነገር (Postive Energy) የመለወጥ ለጥሩ ነገር የመጠቀም ልምድ አለኝ…ከዚህ በፊት ከሠራሁባቸው…እንደ ጉምሩክ አይነቱ ክለብ ጀምሮ…የመንም ስሄድ ከዚህ የበለጠ ፈተናዎችና መሰናክሎች አጋጥመውኝ እንደ አመጣጣቸው ለመቋቋም ሞክሬያለሁ…በየመን የብ/ቡድኑ ተጨዋቾች አመቱን ሙሉ ሳይከፈላቸው…ኳታር ሞግዚት ሆና የሆቴልና የውድድር ቁሳቁሶችን ብቻ እየሸፈነችልን ነበር ስንጫወት የነበረው… ከድላችን በኋላ ግን ተጨዋቾቹ ማግኘት የነበረባቸውንን ገንዘብ ሙሉውን አግኝተዋል… ተሸልመዋል…ከዚህ አንፃር በሰበታ የገጠመኝ የተሻለ ነገር እንዳልሠራ ቢታገለኝም በፊት ካጋጠሙኝ የተየለ አልነበረም…እንደ አጋጣሚ ደግሞ በቡድኑ ውስጥ በሰል ያሉ ተጨዋቾች እንደ ዳዊት፣መሰዑድ፣ፍፁም ገ/ማርያምና ቢያድግልኝ ኤልያስ አይነት ተጨዋቾች መኖራቸው ነገሮች ቀለል እንዲሉ አድርጓል፤እነሱን ከወጣቶች ጋር አጣምረን አሁን ያለንበት ደረጃ መድረስ ችለናል…እዚህ ጋ ግን…
ሀትሪክ፡- …እዚህ ጋ…ምን…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …እዚህ ጋ ግን አንድ እንዲሰመርበትና ለክለቦች መናገር የምፈልገው ቡድኖችን በሚያቋቁሙበት ጊዜ በትክክል አቅማቸውን አውቀው ከተጨዋቾችና ከአሰልጣኞች ጋር በግልፅ መፈራረም ይኖርባቸዋል…አንዴ ውድድር ከተጀመረ በኋላ ወገቤን የማለት ነገር ማቆም አለባቸው…ይሄ ከዚህ ዘመን ጋርም የሚሄድ አይደለም…
ሀትሪክ፡- …ተጨዋቾች ደሞዝ ሳይከፈላቸው…በቂ ነገር ሳይቀርብላቸው…ማሰልጠንና ውጤት እንዲያመጡ መጠበቅ ከተጋጣሚ ቡድን የበለጠ አደገኛ ተጋጣሚ አይሆንም…?…
ኢንስ አብርሃም፡- … በጣም እንጂ…(ሣቅ)…እንኳንም ይሄንን አነሳኸው…ከተጋጣሚዎቻችን በላይ የፈተነን ይሄው ውጪያዊ ችግራችን ነው…በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ለእኔ ተጋጣሚዎቻችን የነበሩት 12ቱ ክለቦች ብቻ ሣይሆኑ…ውጪያዊ ችግሮቻችንና ፈተናዎቻችንም ጭምር ነበሩ…የበረቱ ተጋጣሚዎችን እንደውም እነዚሁችግሮቻችን ነበሩ ብል አላጋነንኩም… .ኮቪድን ጨምሮ እነዚህ ሁሉ የበረቱ ችግሮችን ይዘን ነው በሚገባ የተደራጀ፣ቅርፁን የያዘ፣ የተመልካች ቀልብ ሰቅዞ ለመያዝ የሚሞክር ቡድን ይዤ ለመቅረብ የሞከርኩት…
ሀትሪክ፡- …በፈተና፣በመከራ ውስጥም ሆኜ…ለሰበታ አደረኩት የምትለው ምንድነው…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …የመጀመሪያው ትልቅ ታሪክ ያለው የሰበታ ቡድን ከሚመጥነው ሊግ እንዳይወርድ መታገሌ ነው…የቡድኑን ስምና ታሪክ በዚህ መልኩ መጠበቅ አንደኛው ነገር ነው ብዬ አስባለሁ…ምክንያቱም ሰበታ ቢወርድ ምንአልባትም ታሪኩ ሌላ ሊሆን ይችል ይሆናል… ከዚህ ውጪ ኳስን ሳያበክን ለረዥም ጊዜ መስርቶ መጫወት የሚችል፣ማራኪ እግር ኳስ መጫወት የሚችል ቡድን ለመግንባትም ሞክሬያለሁ… በእርግጥ ይሄ የቡድን ግንባታ ቀደም ሲል የነበረው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ይከተለው የነበረ አጨዋወት ስለነበር…ማስቀጠሉ ላይ ብዙም እንዳልቸገር አድርጎኛል…ያንን በማስቀጠሉ፣በማዳበሩ በኩል ግን ተሳክቶልኛል ብዬ አስባለሁ…ከዚህ ሌላ…
ሀትሪክ፡- …ከዚህ ሌላ ምን…?…
ኢንስ አብርሃም፡– …ከዚህ በተጨማሪ በሰበታ ቡድን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣት፣ የተተኪ ቡድን አልነበረም…ነገር ግን የነገ የክለቡ መሰረቶች ወጣቶች ናቸው በማለት ከ38ዐ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ሰብስበን የተወሰኑትን ወደ ዋናው ቡድን አሳድገን…የተቀሩትን ደግሞ ሌሎች አሰልጣኞች ተመድበውላቸው እንዲሰሩ ማድረጋችን…በወጣቶች ላይ የመስራት ባህልን መፍጠራችን ሌላው በትልቁ የሚጠቀሰው ሥራችን ነው…አንተም ታውቃለህ ከኒያላ አሠልጣኝነቴ ጀምሮ ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የመስራት ልምዱ አለኝ…ይሄንን ወደ ሰበታ በማሳደግ ደፍረን እየሞከርን እየተሳካልንም ነው…
ሀትሪክ፡- …ክለቡ ከስፔኑ ባርሴሎና ከመጣው ካምፓኒ ጋር ያደረገውን ስምምነት በአንደበትህ ግለፅልኝ እስቲ…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …ከስፔን ባርሴሎና ከመጣው ካምፓኒ ጋር ስምምነት ማድረጋችን መልካም ጎን ነው…ከካምፓኒው ጋር በጣም ብዙ ውይይት ነው ያደረግነው…በተለይ ለታዳጊ፣ ለወጣቶችም ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ላይ…ዋናው ቡድንን ደግሞ በቴክኖሎጂ የታገዙ የልምምድ መሳሪያዎችን ማቅረቡ ላይ…ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ትጥቅ በማቅረብ ረገድ… ከሁሉም በላይ ደግሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ ስልጠናዎችን ለታዳጊ፣ህፃናትና ወጣቶች አሠልጣኞች ላይ የአቅም ግንባታ ስራ እንዲሠራ ከስምምነት መድረሱ በጣም ትልቁ ሌላኛው ስራችን ነውና በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ….
ሀትሪክ፡- …ከሰበታ ጋር ያለህ ኮንትራት በያዝነው አመት ይጠናቀቃል፤የአብርሃም የሰበታን መጨረሻ አሁን መናገር ይችላል…?…
ኢንስ አብርሃም፡-…(ሣቅ)…ይሄንን አሁን መመለስ አልችልም…አሁን ስራዬን በስምምነቴ መሠረት እስከ አስራ አንደኛው ሰዓት ድረስ በአግባቡ መስራት ብቻ ነው…መጨረሻህ ምን ይሆናል…?…ላልከኝ ጥያቄ መልስ የምሰጥህ ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ግራና ቀኙን አይቼ እንጂ አሁን የመልህ ነገር የለም…
ሀትሪክ፡- …ምናልባት ክለቡ ከስፔን ባርሴሎና ከመጣው ካምፓኒ ጋር ግንኙነት መጀመሩ ኮንትራትህን እንድታራዝም ጫና ሊፈጥርብህ ይችላል…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …ግንኙነቱ መልካም ቢሆንም…የእኔን ቆይታ፣የመቀጠል ወይም አለመቀጠሌን የመወሰን አቅም ይኖረዋል ብዬ አላምንም…ምናልባት በዚህ ጉዳይ ላይ ተሳትፎ ማድረጌ እንደዚህ አይነቱን ስሜት ፊጥሮ ከሆነ አላውቅም…እኔ የማምንበት ነገር ምንድነው…?…ከአንድ ክለብ ጋር ኮንትራት ካለኝ ለምን አንድ ቀን አይደለም…አንድ ደቂቃ እስኪቀር ድረስ ህዝቡን ክለቡን አክብሬ መስራት ነው…በሰበታ እኔ ብኖርም ባልኖርም ይሄ ለሰበታ የተውነው ትልቁ ሌጋሲያችን ይሆናል ማለት ነው…ነገ ሌላ ክለብም ብሄድ ተመሳሳይ ነገር ነው የማደርገው…ክለቦችን ማዘመን፣በልማት ስራ ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ ከእኛ ከአሰልጣኞች የሚጠበቅ ነው ብዬ አምናለሁ…ከዚህ ውጪ ከክለቡ መቀጠል አለመቀጠል ጋር ይሄ ጉዳይ አይያያዝም…
ሀትሪክ፡- …ወደ ሱዳን አል-ሜሪክ ትሄዳለህ መባሉ ይሆን እንዳትወስን ያደረገህ…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …ሱዳን አልሜሪክ ትሄዳለህ በማለት ለተወራው ነገር…በእርግጥ በቃል ደረጃ አወራን…ፍላጎታቸውን አሳዩ እንጂ መሬት ላይ የወረደ ነገር ለጊዜው የለም…ይሄንን በተመለከተ ወደፊት የምናየውና የምንወስነው ይሆናል…
ሀትሪክ፡- …ከታች ያሳደከው ዱሬሳ ሹቢሻ ሁሌም ጎል ካስቆጠረ በኋላ ሮጦ ወደ አንተ ጋር በመምጣት አንተን በማቀፍ ነው ደስታውን የሚገልፀው…ምናልባት የተለየ ምክንያት ይኖረው ይሆን…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …ከእሱ ይልቅ አንድ እንዲሰመርበት የምፈልገው…እኛ አሰልጣኞች በወጣቶች ላይ በጣም መድፈር አለብን…ለወጣቶች የመጫወት እድል ደፍረን በመስጠት ኃላፊቱን መውሰድ ይኖርብናል…በሰበታ ለዱሬሳ ሹቢሻ ብቻ አይደለም ለብዙ ወጣቶች ደፍረን እድሉን ሰጥተናል….አብዱልባሲጥ፣አብዲልሀፊዝ፣ፉአድና ሹሬ እነዚህ በሙሉ ወጣቶች ናቸው…ወደፊት ክለቡን ለረዥም ዓመት ማገልገል የሚችሉ አቅም ያላቸው ልጆች ናቸው… በተለይ ዱሬሳ ሹቢሻ ተቀይሮ እየገባ ወሳኝ የሆኑ ጎሎችን በማስቆጠር ወርቃማ ነጥቦች እንድናገኝ ረድቶኛል…በዚህ በጣም ደስተኞች ነን…ወጣቶች ላይ እምነት መጣል መልካም እንደሆነና እድሉን ካገኙ ክለባቸውን በደንብ መጥቀም እንደሚችሉ ማሳያ ይሆናል…ደስታቸውን እኔ ጋ መጥተው መግለፃቸውን በተመለከተ…እነሱን ብትጠይቃቸው ትክክለኛውን መልስ ታገኝ ነበር…የእኔን አረዳድ ከሆነ የምትጠይቀኝ በዚያ ደረጃ መጥተው ደስታቸውን መግለፃቸው ግንኙነታችን የአሰልጣኝና የሰልጣኝ ሣይሆን ቤተሰባዊ እንደሆነ ማሳያ ነው…በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ…እግዚአብሔር ያክብርልኝ ማለት ነው የምፈልገው…
ሀትሪክ፡- …ከሰበታ አሰልጣኝነትህ ጋር በተያያዘ…በተለይ መጀመሪያ አካባቢ እምነት ያጡ ደጋፊዎች የጠነከረ ተቋውሞ ሲያቀርቡብህ ነበር…ዛሬ ይሄ ነገር ተለውጧል…?…እነዛ ደጋፊዎችስ ቸኩለው ነበር ብሎ መናገር ይቻላል…?…
ኢንስ አብርሃም፡- ….(ፈገግ እያለ)…በጣም እንጂ…!…ችኩልነት በጣም ያጠቃቸው ደጋፊዎች ነበሩ ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም…እኔ ቡድኑን የተረከብኩት ባልመረጥኳቸው፣ለአጨዋወቴ የሚሆኑ ልጆችን ባልያዝኩበት ሁኔታ ነው…ከዚህ ውጪ 12 ቀን ብቻ ዝግጅት አድርገን ያለ በቂ የወዳጅነት ጨዋታ ነበር ወደ ውድድር የገባነው…በዚያ ላይ በውጪያዊ ነገር የክለቡ ተጨዋቾች ስነ-ልቦና በጣም በወረደበትና…ከሜዳ ላይ ይልቅ በውጪያዊ ችግር በተከበበት ሰዓት ነው ተቃውሞዎች የመጡብኝ…በእርግጥ ደጋፊዎቹ ቡድናቸው እንዳይሸነፍ ከመፈለግ አንፃር ሊሆን ይችላል የተቃወሙት…ግን በእኔ እይታ ለመቃወም ትክክለኛው ጊዜ ነበር ለማለት ይቸግረናል…ችኩልነት የበዛበት፣ያለ ጊዜው የተወለደ ተቃውሞ ነበር ማለት እችላለሁ…እውነታው ይሄ እንደሆነ ባውቅም…ተቃውሞውን በፀጋ ነበር የተቀበልኩት…
ሀትሪክ፡- …ዛሬስ ይሄ ነገር ተለውጧል…በመፀፀትስ ይቅርታ የመጠየቅ ሁኔታ አጋጥሞሃል…?…
ኢንስ አብርሃም፡-…እውነት ለመናገር ይቅርታ አልጠየቁም…ይቅርታ እስከመጠየቅ ያለባቸውም አይመስለኝም…ነገር ግን በፊት የነበሩት አመለካከቶች አሁን ሙሉ በሙሉ ተለውጠዋል ማለት እችላለሁ…በተለይ ቡድኑ በአስተማማኝ ሁኔታ በሊጉ ውስጥ መቆየቱን፣በሂደት ኳስን አደራጅቶ የመጫወት፣በውጤትም እየተለወጠ የመጣ ቡድን መሆኑን ሲያረጋግጡ ደስታቸውንና ድጋፋቸውን በተለያየ መንገድ ገልፀውልኛል…የሰበታ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ብርሃኑ፣አቶ ቶሎሳ ፕሬዚዳንቱ፣ደጋፊዎቹ፣የሰበታ ነዋሪዎች ጭምር ደስታቸውን በስልክ ገልፀውልኛልና ሁሉንም አመሰግናለሁ…ሰበታ በ2ዐ14 በሊጉ ውስጥ የከተማቸው ወኪል ሆኖ እንዲቀጥል አድርገሃል በሚል አመስግነውኛል…
ሀትሪክ፡- አሁን ደግሞ በዋናነነት አንተን መጠየቅና ስሜትህን ማወቅ ወደፈለኩት…ነገር ግን ፈርቼህ ወደ ደበኩህ ጥያቄ አመራለሁ…ብዙ የስፖርት ቤተሰቦች…የዋሊያዎቹን ሽልማት በተመለከተ አብርሃም መብራቱ ለድሉ የራሱን አሻራ ያሳረፈ በመሆኑ ሊሸለም፣እውቅና ሊሰጠው ይገባል ብለው ይሞግታሉ…ባለመሸለምህም ይቆጫሉ…አንተስ ባለመሸለምህ፤እውቅና ባለማግኘትህ ተበሳጭተሃል…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …(እየሳቀ)…ይሄንን የማልፈልገውን ጥያቄ አዙረህ አዙረህ አመጣኸው…?… (አሁንም ሳቅ)…ይሄንን ጥያቄ ከዋናው አጃንዳችንና ከተሰማማንበት ውጪ ነው የጠየቀኝ… በዚህ ዙሪያ ምንም ባልል ደስ ይለኛልና…በሌላ ካልተረጎምከብኝ ይሄንን ጥያቄ እንዝለለው…
ሀትሪክ፡- …ይዤ የመጣሁት የህዝብ ጥያቄ ነው…ሁሉም የአንተን ምላሽ መስማት ይፈልጋልና…ከይቅርታ ጋር ይሄንን ጥያቄ አልዘለውም…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …(ኡፉ…በረጅሙ እንደመተንፈስ እያለ)…ለዚህ ጥያቄ መልስ የምሰጥህ የብስጭት ስሜት በውስጤ ኖሮ ሣይሆን ምናአልባት የምንማማርበት ከሆነ ከሚል ቅንነትን በውስጡ ከያዘ ስሜት በመነሣት ነው…ብ/ቡድኑ ላስመዘገበው ውጤት መንግሥትና ፌዴሬሽኑ ያዘጋጁት ሽልማት እዚሁ ሊጉ በሚካሄድበት ሀዋሳ ነበር…
ሀትሪክ፡- …(ድንገት አቁረጥኩትና)…ግን..ቆይ…ቆይ…አብርሽ ወደ መልስህ ከመግባትህ በፊት …በሽልማት ስነ-ሥርዓቱ ወቅት በአዳራሹ አልታየህም…ተጠርተህ የቀረኸው ለምንድነው…?… አኩርፈህ ነው…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …አትሳሳትም…ማንም የጠራኝም፣የጋበዘኝም የለም..ከሽልማቱና ከእውቅናው ይልቅ ቅር ያለኝ ይሄ ነው…ሌላውን ሁሉ ተወው እንደ አንድ የቀድሞ የብ/ቡድን አሰልጣኝ እንኳን ባይሆን እንደ አንድ የስፖርት ቤተሰብ ብጋበዝና የልጆቹን ደስታ ሲሸለሙ ባይ በጣም ደስ ይለኝ ነበር…ግን ይሄንን አድል እንዳገኝ እንኳን አልተፈቀደልኝም…
ሀትሪክ፡- …ለምን እንዳልተጠራህና እንዳልተጋበዝክ ለመጠየቅስ ሞክረሃል…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …ለምን እጠይቃለሁ…?…ደግሞስ ካለፈ በኋላስ መጠየቁ ምን ትርጉም ያመጣል…?…እኔን ያልጠሩበትና ያልጋበዙበትን ምክንያት የሚያውቁት እነሱ ናቸው…
ሀትሪክ፡- …ወደ አቋራጥኩህ…አለመሸለምህን፣እውቅና መነፈግህን ተከትሎ እየሰጠህ ወደ አለኸው ምላሽ ልመልስህ…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …እንዳልኩህ የሽልማቱ ሥነ-ሥርዓት እዚሁ ሀዋሳ ነው የነበረው…ብዙዎች የጠበቁት ነገር ነበር መሰለኝ ከሽልማቱ ስነ-ሥርዓት ጀምሮ፣ከተጠናቀቀም በኋላ የእጅ ስልኬ አረፍት አልነበረውም…አዳራሹ ውስጥ ያጡኝም…ከአዳራሹ ውጪ ያሉትም እየደወሉ የሆነ የማፅናናትና አይዞህ የበዛበት አስተያየት ይሰጡኝ ነበር…ከዚህ ሌላ በማህበራዊ ትስስር ሚዲያውም ብዙ ተቆርቋሪ ሰዎችን አይቻለሁ “መሸለም ነበረብህ፣ባትሸለም እንኳን እውቅና ልትነፈግ አይገባም” ከሚሉ ጀምሮ ሞራልህ በፍፁም እንዳይነካ እስከሚሉ ቃላቶች ድረስ የቁጭት ስሜቶች ይገለፁ ነበር…አንድ የማልደብቀው ነገር የሰው ቁጭት ወደ አላሰብኩት ስሜት ውስጥ ከቶኝ ነበር…እዚህ ጋ የእኔ መሸለም አለመሸለም ወይም እውቅና ማግኘት አለማግኘት አይደለም ትልቁ ቁም ነገር…የሠራኸው ትንሽም ይሁን ትልቅ ስራ የመመሰጋገን እውቅና የመስጣጠትም ባህሪ ቢኖረን በጣም ደስ ይለኝ ነበር…ከዚህ ውጪ ግን በጣም ያልጠበኩትና ያልገመትኩትን ተቆርቋሪነት ስመለከት ሽልማት ወይም እውቅና የተነፈገው አብርሃም ሳይሆን የስፖርት ቤተሰቡ ነበር የሚመስለው…በዚህ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ… እግዚአብሔር ያክብራችሁ ማለት እፈልጋለሁ…
ሀትሪክ፡- …የስፖርት ቤተሰቡና ህዝቡ በዚህ ደረጃ ተቆርቋሪነቱን ያሳያል የሚል ግምቱ በውስጥህ ነበር…?…
ኢንስ አብርሃም፡-…የደነገጥኩትም ለማመን የተቸገርኩም የጠበኩት ስላልነበር ነው…ሁልጊዜም ህዝብ አይሳሳትም የሚለው አባባል ትክክል መሆኑን ይበልጥ ያረጋገጥኩበትም ነው…በዚህ አጋጣሚ በሀገር ውስጥም በውጪም ያሉ ህዝቦች፣የስፖርት ቤተሰቦች ላሳዩት ፍቅር እጅ እነሳለሁ…እግዚአብሔር ያክብርልኝ ማለት ብቻ ነው አቅሜ…
ሀትሪክ፡- …“አብርሃም ብ/ቡድኑን ይዞ ኮትዲቯርን የሚያክል ታላቅ ቡድን አሸንፎ…በውጤቱ ላይ አስተዋፅኦቸው አነስተኛ የሆኑ የፌዴሬሽኑ ሰዎች በራሣቸው ድግስ ራሣቸውን መሸለማቸው በጣም ያማል…?…”የሚሉ አሉ…አብርሃምስ የህመም ስሜት አልፈጠረበትም…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …ይሄ የሰዎች አስተያየት ነው…በዚህ ላይ ብዙ ባልል ደስ ይለኛል… የህመም ስሜት አልፈጠረብህም…?…ላልከኝ…እኔን በፍፁም አያመኝም…ምክንያቱም ህመም እንዳይሰማኝ የሚያደርግ ፍቱን መድሃኒት አለኝ…
ሀትሪክ፡- …ማለት…?…አልገባኝም…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …ህዝብና የስፖርት ቤተሰቡ የህመም ስሜት ማርከሻና…ጥሩ መድሃኒቶች ስለነበሩ…እውነት ለመናገር አንዳችም የህመም ስሜት አልተሰማኝም…ይልቁንም ፍፁም የጤንነትና የፈውስ ስሜት ነው የተሰማኝ…ሌላው እዚህ ጋ በደንብ እንድታውቅልኝ የምፈልገው…ግለሰቦች ናቸው እንጂ እውቅናና ሽልማት የነፈጉኝ…ሀገሬና ህዝቧ ግን ያለስስት ሸልመውኛል…እውቅናም ሰጥተውኛል…ለአኔ ደግሞ ከዚህ በላይ ሽልማትም፣እውቅናም የለም…
ሀትሪክ፡- …ምናልባት አለመሸለምህ፣እውቅና መነፈግህ፣አለመጋበዝህ ተደማምረው…ሀገርህን በሙሉ ልብ እንዳታገለግል ሞራልህን ይሸራርፍብህ ይሆን…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …በፍፁም አይሸራረፍም…!…እንደውም ሀገሬን ይበልጥ እንዳገለግል የተሻለ ነገር እንድሠራ ጉልበት ነው የሚሆነኝ…ሌላው እዚህ ጋር መታወቅ ያለባቸው ሁለት ነገሮች አሉ…በካፍና በፊፋ ሀገሬን ወክዬ እያገለገልኩ ነው…የኢንስትራክተር አላማ ደግሞ ሀገር ውስጥ ያሉትን አሰልጣኞችን እግር ኳሱንም መርዳት ነው…የኢትዮጵያ ብ/ቡድንን በየደረጃው ያሉትን ማገዝ ስላለብኝ አግዛለሁ እረዳለው…እኔ ምንም ቅሬታም የለኝም…ምንም አይነት ቅሬታ በውስጤ ይዤ የምቆይ አይነት ሰው አይደለሁም…ሁሉም ነገር የሆነው ለበጎ ነው ብዬ የምቀበለው…እስከአሁን ሳደርገው እንደነበረው ዋልያዎቹን ብቻ ሣይሆን በየደረጃው የተቋቋሙትን የሴቶች ብ/ቡድንንም ጭምር አግዛለሁ…መርዳቴንም እቀጥላለሁ…ይሄንን በፊትም አርጌዋለሁ…አሁንም ይቀጥላል…
ሀትሪክ፡- …ይሄን የምትለው ከአንገትህ ነው…?…ከልብህ…?…ብልህ እንደ ድፍረት ታይብኝ ይሆን…?…
ኢንስ አብርሃም፡- …(በጣም ሳቅ)…የምን ከአንገት አመጣህ…?…ከልቤ ነው…አባባሌ ለማለት ብቻ እንዳልሆነና እንደማሣያነት ከረዳህ…ከብ/ቡድን ኃላፊነቴ እንደተነሳሁ ብ/ቡድኑ የወዳጅነት ጨዋታ ፈልጎ ያጣል…በዚህን ጊዜ አይቼ ዝም አላልኩም…ከኃላፊነት ብነሣም የሀገሬ ብ/ቡድን ስለሆነ ይመለከተኛል በማለት…ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ተነጋግረን የሱዳንን ብ/ቡድን ያመጣሁት እኔ ነኝ…አሁንም ይሄ ድጋፌና ትብብሬ ተጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ የሚሸራረፍ ነገር አይኖርም…
ሀትሪክ፡- …በሊጉ ምን ገረመህ….?
ኢንስ አብርሃም፡- …በሊጉ በጣም የገረመኝ…ቀደሞ የተዘጋጀውም፣ዘገይቶ የተዘጋጀውም፣ደሞዝ በተከፈለውም ባልተከፈለውም መሀል ልዩነት አለመኖሩና ተመሳሳይ ፉክክር ማድረጋቸው አስገርሞኛል…ምክንያቱም በዚህ በኩል መጀመሪያ ላይ ብዙ ልዩነት ይኖራል የሚል ስጋት በውስጤ ነበር…የዝግጅት ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ ልዩነት የፈጠረ ቡድን ቢኖር ፋሲል ብቻ ነው…በተረፈ ግን እንዳየኸው ብዙዎቹ ክለቦች
ተቀራራቢ ፉክክር ነው ያደረጉት፤ ይሄንን ኢንተርቪው አስካደረግንበት (ማክሰኞ ማለቱ ነው) ከፋሲል ውጪ 2ተኛ ወጥቶ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመግባት 5 ቡድኖች ያህል እድል አላቸው፤ እነዚህን 5 ቡድኖች ወደ ኋላ መለስ ብለህ ስታይ ዝግጅታቸው የተዘበራረቀ ፉክክሩ ግን ተቀራራቢ መሆኑ አስገርሞኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …. ማን ለየት ብሎ ወጣብህ…? ማን ክስተት ሆነበህ?
ኢንስ.አብርሃም፡-ሁለቱ ኮከብ ግብ አግቢዎች አቡበከር ናስርና ሙጅብ ቃሲም በዘንድሮው ውድድር ቡድናችንን ለድል በማብቃታቸውና ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፤ በጣም አስገራሚ ለውጥም ያሳዩ ናቸው፤ ይሄንን ስልህ ግን በረካታ ጥሩ የነበሩ ተጨዋቾች እንደነበሩ ሳልዘነጋ ነው፤ አምበልነቱን፣ በክለብም በብ/ቡድንም በትክክል የተወጣ በሁለቱም ትልቅ ስኬቶችን ያገኘው ያሬድ ባየህም ከነዲሲፒሊኑ ጭምር የተለየ ሆኖብኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የአቡበከር 4 ሀትሪክና የሀገሪቱ የግብ አግቢነትን ሪከርድ መስበሩ ምን ስሜት ፈጠረብህ…?
ኢንስ.አብርሃም፡- አቡበከርን እንደ አጋጣሚ ሆኖ ለብ/ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የጠራሁት እኔ ነኝ… ትልቅ አቅም ትልቅ ክህሉት ያለው ተጨዋች እንደነበርም አውቅ ነበር፤ ይሄንን ለራሱም እነግረው ነበር… እሱም ያዳምጠኛል፤ ከማዳጋስካርና ኮትዲቫር ጋር ስንጫወት ያሳየው የነበረው እንቅስቃሴ የልጁን ችሎታ ገላጭ ነበር… አራት ሀትሪኮችን መስራቱና የጎል ሪከርዱን መስበሩን በጣም አስደስቶኛል… በሀገር ውስጥ ብቻ ሣይሆን ውጪም ወጥቶ ብቃቱን ማሳየት እንደሚችል አምናለሁ… ይሄንን ሪከርድ ከመስበሩም… ከሰበረ በኋላ አግኝቼው አውሬቼዋለሁ… ያለኝን ሙያዊና ወንደማዊ ምክር ለግሼዋለሁ… የጨዋታው ሚናና ነፃነት የሰጠው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌም መረሳት የለበትም… ሚናው ከፍተኛ ስለሆነ እሱም ሊመሰገን ይገባል… አቡኪ አቅሙን አውጥቶ እንዲጫወት አድርጎታልና፡፡
ሀትሪክ፡- እንደ ገመትኩት እንደጠበኩት አላገኘሁትም የምትለውስ…?
ኢንስ.አብርሃም፡-… እውነት ለመናገር እንደ ስኳዱ ጥራትና ስብስብ እደነበረችው ዝግጅት ብዙ የተሟላለት ክለብ ከመሆኑ አንፃር ቅዱስ ጊዮርጊስን በዚህ ደረጃ አልጠበኩትም… ሌላው ወልቂጤም አጀማመሩ ጥሩ ነበር…. በጣም ማራኪ ፉትቦል የሚጫወት፣ በወጣቶች የተገነባ፣ እንደተጋጣሚው አጨዋወቱን የሚቀይር ተስፋ የጣልኩበት ቡድን ሆኖ መሀል ላይ ወገቤን በማለቱ ወለቂጤም እንደግምቴ አልሆነም…
ሀትሪክ፡- ከዚህ በላይ ላደክምህ አልፈልግም ጨረስኩ … አንተ ግን የምትለውም ካለ ይሄው መድረኩ… ?
ኢንስ.አብርሃም፡- ደጋግሜ መናገር የምፈልገው ለህዝቡና ለስፖርት ቤተሰቡ ነው… ውለታ በል ያልሆነውን ህዝቡንና ስፖርት አፍቃሪውን ለተቆርቋሪነቱና ለሰጠኝ ክብርና እውቅና አሁንም በድጋሚ ዝቅ ብዬ እጅ እነሳለሁ… ከዚህ ውጪ አብረውኝ የደከሙትን ረዳቶቼን፣ ተጨዋቾቼን፣ ውድድሩን የማስተናገድ ኃላፊነት ወስደው የደከሙትንና የሊግ ካምፓኒው በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡