ይህ ዋንጫ ለእኔ ሳይሆን ለባለቤቴ ነው የሚገባው

“ይህ ዋንጫ ለእኔ ሳይሆን ለባለቤቴ ነው የሚገባው

“ደጋፊ ገብቶ ጃኖ ማልያችንን ለብሰው ደጋፊዎችን ማየት ለእኛ ትልቅ ክብር እና ደስታ ነው”

“አቡበከር ናስር በድጋሚ እንኳን ደስ አለህ”

“አሰልጣኝ ስዩም ከበደ አባት ነው” መጂብ ቃሲም /ፋሲል ከነማ/

አፄዎቹ በዛሬው ዕለት የሊጉን የመጀመሪያ ዋንጫቸውን ከፍ አድርገው ሲያነሱ የፊት መስመር አጥቂው ሙጂብ ቃሲም ሚና የሚዘነጋ አይደለም ።

ከ በረኝነት እስከ ተከላካይነት አልፎም አሁን ላይ በአጥቂነት በተጫወተባቸው ክለቦች ቁልፍ ድርሻን የተጫወተው ሙጂብ ቃሲም ሀያ ጎሎችን ለአፄዎቹ በማስቆጠር ፋሲላውያንን ዘንድሮ ላይ ሲያስፈነጥዝ ዘልቋል ።

የአፄዎቹ የፊት መስመር ፊት አውራሪ ሙጂብ ቃሲም ሻምፒዮናነታቸውን ፣ የውድድር ዓመቱን ጉዞ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ ከሀትሪክ ስፖርት ፀሀፊው ቅዱስ ዮፍታሄ ጋር ቆይታን አድርጓል ።

” የዘንድሮው የውድድር ዓመት ደስ ይላል ፣ ለእኛ ልዩ ነበር ። ትልቅ ድል ያስመዘገብንበት ለዛውም ዲ ኤስ ቲቪ ባለበት ነው ዋንጫውን ያነሳነው ከዚህ ባለፈም ብዙ ጨዋታዎችን ሳንሸነፍ ( 19 ጨዋታዎች ) ቆይተን ነው በስተመጨረሻ በድሬደዋ ልንሸነፍ የቻልነው ።

ለእኛ ለፋሲላውያን ትልቅ የውድድር ዓመት ነበር ፣ ለፋሲልም የዘንድሮው ፉክክር የተለየ ጊዜ ነበር ።

የፋሲል የዘንድሮው ግስጋሴ በጣም ልዩ ነበር ፣ የነበረው ጊዜ ካለፉት አመታት የሚለየው ከዚህ በፊት ለዋንጫ ስንፎካከር የነበረው እያሸነፍን እየተሸነፍን ነበረ ፣ ዘንድሮ ግን ጥቂት ጨዋታዎችን አቻ ወጥተን ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ተሸንፈናል ።

በተከታታይ ጨዋታዎች አለመሸነፋችን የዘንድሮውን ውድድር ዓመታትችንን ልዩ ያደርገዋል ፣ ያም ነው ለውጤታችን ትልቅ አስተዋፅኦ የነበረው ለፋሲል ዓመቱ ልዩ ነበር ።

ፋሲል ካስቆጠራቸው ግቦች ግማሹን ከመረብ ማሳረፍ ችያለው ፣ እንደ ግል ትልቅ ደስታ ነው የሚሰማኝ ምክንያቱም አንድ ቡድን ዋንጫ በልቶ ከፍተኛውን ጎል በዛ መሐል ማስቆጠር ማለት በጣም ትልቅ ነገር ነው ።

ግማሹን ማስቆጠር ማለት ደግሞ አብዛኛውን አስቆጥር የነበረው እኔ ነኝ ማለት ነው ፣ ይህ ማለት ደግሞ ቡድናችን ዋንጫ እንዲበላ ትልቅ ነገር ነው በግሌ ይህንን በማድረጌ የምፈልገውም ነገር ስለሆነ ለእኔ ትልቅ ድል እና ስኬት ነው ።

ፍላጎቴ የነበረው ፋሲል ዋንጫ እንዲያነሳ ማድረግ ነው ፣ ያንንም በምችለው አቅም የምችለውን ነገር አድርጌያለው ለእኔ ትልቅ ትልቅ ስኬት ነው ።

ስለ ስዩም ለመናገር በአንድ ቃል ነው የምገልፀው ስዩም አባት ነው ብዬ ነው ልገልፀው የምችለው ፣ የተጫዋቹ እና የአሰልጣኛችን ግንኙነት ልክ እንደ አባት እና እንደ ልጅ ነው ።

ይህም ነው ለስኬት ያበቃን ፣ ኳስ ላይ ደግሞ ጤነኛ የሆነ ግንኙነት ካለህ ሁሌም ውጤታማ ትሆናለህ ፣ ይህ ግንኙነታችን ነው ለዚህ ይበልጥ ለድል ያበቃን እና ስዩም እንደ አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆን እንደ አባትም ነው ለሁሉም ተጫዋች ነው ፣ ስዩምን ልገልፀው የምችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው ።

የቡድናችን አዝናኝ ተጫዋች ከጨዋታ በፊትም ሆነ በኋላ ሽመክት ጉግሳ ነው ፣እርሱ ነው የቡድናችን አዝናኝ በመሆን ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል ።

ደጋፊ በሌለበት መጫወት ብዙም ደስ አይልም ፣ ደጋፊ ሲኖር እና ሳይኖር እግር ኳስ ራሱ ልዩነት አለው ፣ ይህ ደግሞ የሆነው በኮቪድ ምክንያት በግዴታ ነው ። ደጋፊ በሌለበት መጫወት ብዙም አይጥምም ማለት ይቻላል ፣ ምክንያቱም ኳሱ ትልቁን ነገር የሚወስደው ደጋፊው ነው እና ያም ባለመኖሩ ቅር ብሎናል ።

ደጋፊ ያለ ኳስ ምንም አይደለም ኳስም ያለ ደጋፊ እንደዛው ነው ፣ ደጋፊዎቻችን ባለፉት ጊዜያት አለመኖራቸው ቅር ያሰኛል ደስም አይልም ፣ ወደ ፊት የተሻለ ጊዜ መጥቶ ደጋፊዎች የሚገቡበት መንገድ ከፈጣሪ ጋር ይኖራል ብዬ አስባለው ።

ደጋፊ ገብቶ ጃኖ ማልያችንን ለብሰው ደጋፊዎችን ማየት ለእኛ ትልቅ ክብር እና ደስታ ነው ። ይህን ክብርም ደስታም ለማግኘት ነው ስንጫወት የነበረው እና የተወሰኑ ደጋፊ ተፈቅዶ ያም ሆነ በደጋፊዎቻችን ፊት ዋንጫ ያነሳነው ፣ ይህ ለእኛ በጣም አስደስቶናል እኛ እንደውም ከዚህ በላይ ደጋፊ ገብቶ ዋንጫ ማንሳት ነበር ፍላጎታችን የነበረው እና በነበረውም ነገር ቢሆን ግን በጣም ደስተኞች ነን ።

በጎል አግቢነቱ ላይ እኔ ከጅምሩም ስል የነበረው ከግብ አግቢነቱም ባሻገር ፋሲልን ዋንጫ ማስበላት እና እኔም በግሌ ዋንጫ በጣም የማግኘት ጉጉት ነበረኝ ያንን አሳክቻለው ፣ ለእኔ ትልቅ ድል ነው ፣ ያም ደግሞ ሆኖ ያንን ሳደርግ ፋሲል ዋንጫ ሲበላ ብዙ ጎል አስቆጥር የነበረው እኔ ነኝ ፣ ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው ።

በአቡኪ እና በእኔ መካከል ፉክከሩ ያው ጎል ስታስቆጥር እሱም በግሉ እኔም በግሌ ሳስቆጥር ተቀራራቢ የሆነ ነገር ሲመጣ ፉክክር ነው የሚባለው ዞሮ ዞሮ፣ ጥሩ ጊዜ ነበረን ብዬ አስባለው ዘንድሮ ላይ እሱም ሪከርዱን ሰብሯል ።

ይህ ደግሞ በጣም ትልቅ ትልቅ ነገር ነው ፣ በጣም ደስ ይላል ፣ በዚህ ዕድሜ ሪከርድ መስበር በጣም ትልቅ ነገር ነው እንደውም ገና አልሰራም ብዬ ነው የማስበው ምክንያቱም ከዚህ በላይ የመስራት አቅም አለው ።

ሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጭ በሌላም ሀገር በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ነገር መስራት የሚችል አቅም አለው ። ብዙ አቅም ያለው ተጫዋች ነው እና አበረታትቼ ማለፍ እፈልጋለው ።

በዚህ አጋጣሚ እንደውም እንኳን ደስ አለህ ! ከዚህ በፊት ብዬዋለው ግን እንኳን ደስ አለህ ማለት እፈልጋለው ።

ለእኔ ሁሉም ጎሎች ምርጥ ናቸው ፣ ምክንያቱም ማንኛውንም ጎል አግቢ ጎል ሲያስቆጥር ደስ ይለዋል ፣ ያንን የደስታ ስሜት ደግሞ የሚፈጥሩልኝ ደግሞ ጎሎቼ ናቸው ። ለእኔ ሁሉም ጎል ልዩ ናቸው ግን ይበልጥ ደግሞ በጣም የወደደኩት ከጅማ አባጅፋር ጋር ባህርዳር ላይ ስንጫወት ያስቆጠርኳቸው ሁለት ጎሎች እንዲሁም ሲዳማ ቡና ላይ ያስቆጠርኳቸው ጎሎች በጣም የምወዳቸው ናቸው ።

ለማስቆጠር ከባድ የነበሩ ጎሎች ናቸው ትንሽ ማሰብ የሚጠይቅ ነበር ፣ ለእኔ ልዩ የሆነችው ጎል ጅማ ላይ በጭንቅላት ያስቆጠርኩት ጎል ነው ።

ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው ፣ ምክንያቱም በልጅነቴም በ አጥቂ ቦታ ላይ ነበር የምጫወተው መሀል ላይ ነው በአሰልጣኞች ተከላካይ የሆንኩት ፣ ከመሐል ተከላካይ በአንዴ ወደ አጥቂነት መጥተህ እንዲህ አይነት ነገር መስራት በራሱ ከባድ እና በግሌ ትልቅ ነገር ነው ።

ሶስት ዋንጫ ከፋሲል ጋር አንስቻለው ዛሬ አራተኛውን አሳክቻለው ፣ እንሻላህ ወደፊት ይበልጥ ከዚህ የተሻለ ነገር ከፋሲል ጋር እሰራለው ።

ለእኔ ዘንድሮ ላይ ልዩ የሆኑብኝ ተጫዋቾች ሁለት ናቸው ፣ አንዱ አቡበከር ናስር ነው ሌላኛው የቡድን አጋሬ ፋሲል ላይ ያለው እና አምበላችን ያሬድ ባየህ ነው ።

አብሬ ብጫወት ብዬ የማስበው የባህር ዳር ከተማው ፍፁም አለሙ ነው ፣ ከዚህ በፊት በፋሲል ቤት አብረን ተጫውተን ለእኔ ልዩ ነበር ።

ከፍፁም ጋር አብሬው ብጫወት እኔም የተሻለ ይሆናል ብዬ አስብ ነበር እና ከፍፁም ጋር በድጋሚ ብጫወት በጣም ደስ ይለኛል ።

በድሬደዋ ስንሸነፍ ከአቅም በታች ተብለናል ፣ እሱን አልቀበለውም ፣ ምክንያቱም ከአቅም በታች ማለት ኳስ ላይ ሌላ ነገር ነው ። ይህንን በፍጹም አልቀበለውም ፣ እኛ እየተጫወትን የነበረው ሶስቱን ጨዋታዎች ዋንጫ ከበላን በኋላ ነው ያ ደግሞ ሁሉም ተጫዋች ጋር አንድ አይነት ስሜት ይኖራል ማለት አይደለም ።”

ስለ ባለቤቴ ኢማን ሱርር በቀላሉ ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም ፣ ሙሉ የእግር ኳስ ህይወቴ ታሪኬን ታቀዋለች ። ትልቁ ስኬቴ ላይ እርሷ ኖራ ዋንጫ በማንሳቴ ትልቅ ደስታ ተስምቶኛል ፣ የዚህ ውጤት 75% ለእኔ እዚህ መድረስ የእሷ አስተዋፅኦ ጠንካራ እና ትልቅ ሴት መሆን ነው ።

ይህ ዋንጫ ለእኔ ሳይሆን ለእሷ ነው የሚገባው ፣ የእሷ ትልቅ መሆን እኔን ለዚህ ደረጃ አድርሶኛል ፣ ሁሌም ከጎኔ ሆና ስታበረታታኝ እንደ እናት እንደ ወምድም ስትመክረኝ ለዚህ ስታበቃኝ ትልቅ ክብር ደስታ ይሰማኛል ።

ስለ እሷ እንዲህ ብዬ መናገር ቃላቶች ያጥረኛል በአጭሩ ባለቤት ኢማን ሱርር እንኳን ደስ አለሽ ፣ ዋንጫውንም ሆነ ሜዳልያውን ለእሷ ነው የሰጡሁት ይህ ሙሉ ለሙሉ የእሷ ስኬት ነው ።

ይህን ዋንጫ ስንበላ በቀላሉ አልነበረም በጣም ብዙ ውጣውረዶችን አሳልፈናል ብዙ መከራዎችን አይተናል ፣ ዋንጫ መብላት በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም በጣም ትልቅ ድል እና ታሪክ ነው ፣ በዚህ አጋጣሚ ሁሉንም የፋሲልውያን ቤተሰብ እንኳን ደስ አላችሁ ።

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor