“ኢትዮጵያ ቡና ወደራቀበት የአፍሪካ መድረክ ለመመለስና ታሪክ ለመስራት ዝግጁ ነን” ኃይሌ ገ/ተንሳይ/ ኢት.ቡና/

ሀትሪክ፡- ሀዋሳን እንዴት አገኘሃት…?

ኃይሌ፡- በጣም አሪፍ ከተማ ናት ዘና ብያለሁ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ከውጤትስ አንፃር ስኬታማ ጊዜ በሀዋሳ አሳልፋችኋል ማለት ይቻላል…?

ኃይሌ፡- አይ አይ እንደዚያ ስኬታማ ነበርን ለማለትማ እንቸገራለን ሁለተኛነትን ለማስጠበቅ ግን ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ሌሎች ክለቦችም ነጥብ መጣላቸው ጠቀማችሁ እንጂ ኢትዮጵያ ቡናኮ ተደጋጋሚ ጊዜ ነጥብ ጥሏል ምክንያቱ ምንድነው…?

ኃይሌ፡- አዎ… ካሸነፍን መቆየታችን እውነት ነው ጫና ውስጥ እንዳለን ይሠማኛል የጫናው ውጤት ይመስለኛል… ጎል ለማስቆጠር ስንሄድ ግብ ሲቆጠረብን የመረበሽ ነገር አለ ያ ደግሞ ጫናው የፈጠረብን ይመስለኛል፡፡ ለማሸነፍ ካለን ጉጉት አንፃርም ነጥብ እየጣልን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ከሀድያ ሆሳዕና ጋር እሁድ ላለባችሁ ወሳኝ ጨዋታ ተዘጋጅታችኋል…?

ኃይሌ፡- ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያለን ጨዋታ ለኛ የፍፃሜ ያህል ነው በራሳችን እጅ ያለውን እድል ለመጠቀም ተዘጋጅተናል ካሸነፍን አንድ ጨዋታ እየቀረን ልዩነቱ በ5 ነጥብ ስለሚሰፋ ማሸነፋችን 3 ነጥብ ብቻ ሳይሆን ለኮንፌዴሬሽን ካፕ ማለፋችንን ያሳያልና ለማሸነፍ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ እንጥራለን… ኢትዮጵያ ቡና በአፍሪካ መድረክ ከተሳተፈ ረጅም ጊዜ ስላስቆጠረ ዘንድሮ ያን ሕልማችንን የምናሳካበት ጨዋታ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የማሸነፍ ፍላጎትና ጉጉት መኖሩ ጫና ውስጥ አይከታችሁም…?

ኃይሌ፡- እውነት ነው ሊከተን ይችላል አሁን ግን ጫና ውስጥ እንዳለን አውቀው አሰልጣኛችን ከጫና የማላቀቅ ስራ እየሠራ ነው ሙሉ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ እናንተ የምትችሉትን ብቻ አድርጉ በማለት ከጫና የሚላቀቅ ሥራ እየሠራ ነው ይህም በደንብ ስለሚጠቅመን እንደሌላው ጨዋታ ጫና ውስጥ ሆነን እንገባለን ብዬ አልሰጋም በጥሩ ሁኔታ ልምምዳችንን እየሠራን ነው የጫናው ስጋት የለብንም ማለትም ይቻላል፡፡

ሀትሪክ፡- የሀዲያ ሆሳዕና ወጣቶች ቅዱስ ጊዮርጊስን ረተዋል ይሄስ ለናንተ ስጋት አይፈጥርም፡፡ ?

ኃይሌ፡-ስጋት ይፈጥራል ግን ስጋቱ የሚያደርገን በደንብ ተዘጋጅተን በጥሩ በራስ መተማመን እንድንጫወት እንጂ ፍርሃት አይፈጥርም በራሳችን እድላችንን እንደመወሰናችን ያለምንም ጥርጥር እናሸንፋለን ሀዲያ ሆሳዕና ረትተን በኮንፌዴሬሽን ካፕ አገራችንን መወከላችን አይቀርም፡፡

ሀትሪክ፡- በወጣት የተሞላ ቡድን እንደመሆኑ በኮንፌዴሬሽን ካፕ የማለፍ እድል ስላላቸውም ግጥሚያው አይከብድም?

ኃይሌ፡-ምንም ጥርጥር የለውም ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን አውቃለው በነርሱ በኩል ለወጣቶች እድል መሰጠቱ ወጣቶቹም እድሉን ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት ያስደስታል ከጫና ውጪ ሆነው የሚጫወቱ መሆኑ ለነርሱ ይጠቅማቸዋል ነገር ግን እኛም በቀላሉ እጅ አንሰጥም ጥንካሬያቸውን አውቀን ስለምንገባ ማሸነፋችን አይቀርም፡፡

ሀትሪክ፡- የሁለታችሁ ልዩነት አቡበከር ናስር አይመስልህም…? እነርሱ አቡኪ የላቸውም ቡና ግን አለው ይሄንንስ እንዴት አገኘኸው…?

ኃይሌ፡-/ሳቅ/ ምርጥ አጥቂ አለን የአገሪቱን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሪከርድን ሰብሮ በጥሩ ሞራል ላይ ይገኛል አቅምም አለው ከሀገር ወጥቶ የመጫወት እድል እንደሚያገኝና እንደሚሳካለት መገመት አይከብድም ልዩነት ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ እንደ ኢትዮጵያ ቡና ግን አንቅስቃሴው እንደ ቡድን ነው የአቡኪ አቅም እንዳለ ሆኖ ቡድናችን ነው ጠንክሮ የሚወጣው የቡድን ስራ እንደመሆኑ ሁሉም ዋጋ አለው፡፡

ሀትሪክ፡-በኢትዮጵያ ቡና በኩል አቡበከር ናስር በሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ዳዋ ሁቴሣ ተወድረዋል… የአጥቂዎት ፍልሚያ ነው ማለት ይቻላል…?

ኃይሌ፡- አዎ ሁለቱም ልዩነት ፈጣሪ ናቸው ቡድኖቻቸውን በድል ለማስጨፈር እንደሚጥሩ አምናለው በዋናነት ግን ልዩነት የሚፈጥረው ክለቦቹ እንደ ቡድን የሚኖራቸው አቋም ይመስለኛል እኛም ለዚህ ጨዋታ ድል ተዘጋጅተናል ኢትዮጵያ ቡና ወደራቀበት የአፍሪካ መድረክ ለመመለስና ታሪክ ለመስራት ዝግጁ ነን፡፡

ሀትሪክ፡- እንደ ሙያና እንደ ግለሰብ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን እንዴት ትገልፀዋለህ…?

ኃይሌ፡- የሚገርም ሰው ነው፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ካሳዬን የመሰሉ ሰዎች ቢኖሩት የሚለወጥ ይመስለኛል በጣም የሚደነቅ ሰብዕና አለው በቃ አባት በለው ለሁሉም ፍቅር አለው ተስፋ አድርጎህ ያምንብሀል በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እፈልጋለው፡፡ ዳኛ በደለ ብለን እንጮሃለን… እርሱ ጋር ይሄ የለም.. ከዚህ በፊት በነበሩ አመታቶች ውጤት ሲጠፋ ሰበብ የምናደርገው ዳኞችን ነበር አሁን ግን የለም በርትተን ዳኞችን ሳይቀር ማሸነፍ እንዳለብን ይናገራል እኛ ሀገር ይሄ አልተለመደም በዚያ ላይ በታዳጊዎች አምኖ እድሉን ይሰጣል ይሄ ትልቅ መገለጫው ነው በዚህ ሃሣብ ሀገራችን ተቸግራለች እንዲህ የሚያስብ ዋጋ የሚከፍል አሰልጣኝ የለም፡፡

ሀትሪክ፡- ሀድያ ሆሳዕና ወጣቶቹን ያመጣው ተገዶም ቢሆን በታዳጊ ማመን ከተቻለ እንዲህ ማድረግ ይቻላል የሚል መልዕክት ያስተላለፉ አይመስልህም…?
ኃይሌ፡-ታዳጊ ተተኪ አጥተን ተቸግረናል ብሔራዊ ቡድናችን ላይ ተመሳሳይና አንድ አይነት ፊት እየየን ያለነው ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ነው ይሄ ታዳጊ ላይ ባለመሰራቱ ያለውን ክፍተት ያሳያል ሀዲያ ሆሳዕና ውስጥ እያየን ያለነው ደስ የሚል ነገር ነው በሁለት ጨዋታ ታዳጊዎቹ ያሣዩት አቋም በክለቡ ውስጥ 4 አመት የቆዩ ያስመስላቸዋል ይሄ የሚያስተላልፈው ትልቅ

መልዕክት፡ አለው ከዚህ አንፃርም ካሳዬ አራጌ በቀጣይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብዬም አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና እንቅስቃሴና የካሳዬ ፍልስፍና ለሀገር ይጠቅማል የሚሉም አሉ በተቃራኒው ደግሞ አይ የትም አይደርስም የሚሉም አሉ አንተስ ምን ትላለህ…?

 

ኃይሌ፡-ለሀገር ጠቃሚ ነው ወይ? ምንም ጥያቄ የለውም ለኛ ሀገር የሚሆን ፍልስፍና ነው ብሔራዊ ቡድኖቻችን ለተቸገሩበት መፍትሔም ይመስለኛል አቅማችንን ያማካለ ነው ሌሎች ሀገራትን በፍጥነትም ይሁን በአቅም አንበልጣቸውም በኳሱ ግን በቅብብሉ ማሸነፍ እንችላለን ባለን መስራት ይገባል ለሚለው ኢትዮጵያ ቡና ምሣሌ መሆን ይችላል… ኳስ መስርቶ መጫወት የኛን አቅም አውጥቶ ለመጫወት ይጠቅማል …ያለንም ይሄ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 ወረርሽኝ አልተቸገራችሁም …?
ኃይሌ፡-በጣም የፈተንን ድሬዳዋ ላይ በነበረን ቆይታ ነው ሁሉም የተቸገረው እዚያ ነው ድሬዳዋና ሀዋሳ በኮቪድ መጠቃታቸውን ሰምተን ስለነበር ፈተና ቢኖረውም ለማለፍ ሞክረን ተሳክቶልናል የምንችለውን ጥንቃቄም እያደረግን ነው አሁን ሃዋሳ ላይ እንደ ድሬዳዋው ጫና አልተፈጠረብንም ይህም ጊዜ አልፎ ጥሩ ጊዜ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ለደጋፊው የምትለው የመጨረሻ ቃል…?
ኃይሌ፡- ደጋፊው ኢትዮጵያ ቡናን በአፍሪካ መድረክ ለማየት ጓጓቷል እነርሱን ለማስደሰት የምንችለው እናደርጋለን ማለት እፈልጋለሁ ከጎናችን እንደነበሩ አሁንም ከጎናችን እንደሚሆኑ እተማመናለሁ ከኛ ጎን ስለሆናችሁም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team