“እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፈን ከደጋፊዎቻችን ጋር ለመጨፈር ተዘጋጅተናል” ሄኖክ አርፍጮ/ሀድያ ሆሳዕና/

ሀትሪክ፡- አምበልነቱ እንዴት ይዞሃል…?

ሄኖክ፡- አምበልነት ከባድ ኃላፊነት ነው ብዙ ነገር ከአምበል ይጠበቃል ሜዳ ውስጥም ይሁን ከሜዳው ውጪ መሪነትና ሞዴል መሆን ይጠይቃል ለዚህም ኃላፊነቱን የመወጣት አቅምህ ከፍተኛ መሆን አለበት አሁን ደግሞ ቡድኑ ላይ ከተፈጠረው ችግር አንፃር ኃላፊነቴ ከበድ ያለ ሆኗል፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፋችሁ ቡድኑ ላይ የፈጠረው ስሜት ምን ይመስላል…?

ሄኖክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የሀገራችን ትልቁ ቡድን እንደመሆኑ በማሸነፋችን ደስ ብሎናል በተለይ ጠንካራና ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾችን ሳይሆን ወጣትና ከታዳጊ ቡድን የተሰባሰቡ ልጆች የበዙበት ሆኖ ጊዮርጊስ ማሸነፋችን አስደስቶናል በራስ መተማመናችንም ጨምሯል አዲሶቹ ወጣቶች ላይ ብዙ ተስፋ የሚጣለባቸው መሆናቸውን በሚገባ አሳይተዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በወሳኝ ጨዋታ ተገናኝታችኋልና ምን ውጤት ይጠበቅ?

ሄኖክ፡-ኢትዮጵያ ቡናም ትልቅ ቡድን ነው ጥሩ ተደርጎ የተሠራና የተደራጀ ቡድን እንደሆነ በሊጉ ያለበት ደረጃ አመላካች ነው፡፡ የተሻለ አቅም እንዳለውም ያሳያል ሁለታችንም ተመሳሳይ ነገር ይዘን የምንገባበት ጨዋታ እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡ ተመሳሳይ አላማ ይዘን ያሸነፈ ቡድን 2ኛ ሆኖ ወደ አፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽ ካፕ ሀገርን የመወከል እድል እንደሚኖረው አውቀን የምናደርገው ትልቅ ጨዋታ ይሆናል እኛም ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንጥራለን የዋንጫ ጨዋታ ያህል እንደሚሆን ይሰማኛል ከሰበታ ጨዋታ ጀምሮ እያደገ ያለ ነገር በኛ ልጆች ላይ ይታያል ይሄ ከቡና ጋር በምናደርገው ጨዋታም ይቀጥላል ወጣቶቹ የመግባባት አቅማቸው ለማሸነፍ ያላቸው ጉጉት አድርጉ የተባሉትን በደንብ የመፈፀም ነገር ይተያልና ተስፋ የሚጣልበት ነገር አለ ለኢትዮጵያ ቡናም የተለየ ግምት አንሰጥም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያደረግነውን በኢትዮጵያ ቡና ላይም እንደግመዋለን ፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈናል ቡናም ተረኛ ተሸናፊ ነው እያላችሁ ነው?

ሄኖክ፡-/ሳቅ/ በርግጠኝነት ቡናን ለማሸነፍ እንገባለን የሚሳካልን እንደሚሆንም አልጠራጠርም አሰልጣኛችንም ወጣቶቹ ጫና ውስጥ እንዳይገቡ ትልቅ ስራ እየሰራ ነው የማረጋጋት በጫና ውስጥ ሆነው እንዳይጫወቱ የማድረግ የስነ-ልቡና ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ተሰርተዋል ብዬ አምናለሁ የማሸነፍ ስነ ልቡና ስለመጣ ከቡና ጋር ከልክ ያለፈ በራስ መተማመን ይዘን እንዳንገባና ውጤቱ እንዳይበላሽ የማረጋጋት ስራ እየተሰራ ነው ታክቲኩና የቴክኒኩ ዝግጅት ሳይረሳ ማለቴ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የሀዋሳ የ3ለዐ ሽንፈት የሰበታ ከተማ ባለቀ ሰዓት በተቆጠረ ግብ የደረሰባችሁ ሽንፈት ቡድኑን አልጎዳም?

ሄኖክ፡- ከሀዋሳ ጋር ያደረግነው ጨዋታ በጎዶሎና በጣም አድካሚ የነበረ መሆኑ ታይቷል እስከ ረጅም ሰዓት ድረስ ታግለናል ከሰበታ ከተማ ጋር ግን ሜዳ ላይ ልናደርግ የምንችለውን ሁሉ አድርገን ነው የተሸነፍነው ይሄ አንዳንዴ ያጋጥማል ከዚህ ጨዋታ ተምረን ገብተን ነው ጊዮርጊስን የረታነው… የሰበታ ከተማ ሽንፈት የነበረንን አቅም አይገልፀውም ጥሩ ተምረንበት አልፈነዋል፡፡

ሀትሪክ፡- የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለና የ15 ልጆች ከቡድኑ መለየትስ ክፍተት አልፈጠረም..?

ሄኖክ፡-ጫናና ክፍተትማ ይኖረዋል ነገር ግን ምክትሉ ብዙ ጊዜ አብረን ስንሰራ ስለነበር አሁን በዋና አልጣኝነት ክፍተቱን ለመሙላት ጥሩ ስራዎች እየሰራ በመሆኑ ጫናው እንዳይሰፋ አድርጎታል… ቢኖሩ ጥሩ ነበር ነገር ግን እግር ኳስ ላይ የሚከሰት እንደመሆኑ ባለን መቀጠሉ የግድ ነው ማንም መጥቶ ቡድኑን ቢያሰለጥን የሚጠበቅብን መሰልጠን ብቻ ነውና ይህን እያደረግን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የነበረው ቡድን ቢቀጥል ሀድያ ሆሳዕና በኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን እንደሚወክል ቀድሞ ያረጋግጥ ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ… አንተስ ምን ትላለህ…?

ሄኖክ፡- ጥሩ ስብስብ ነበርን ጠንካራ ተፋላሚ ቡድን አሳይተናል የተፈጠረው ነገርማ ባይኖር ብለን እንቆጫለን… ይሄኔ ማለፋችንን አረጋግጠን የምናደርገው ጨዋታ ይሆን ነበር ያ ባለመሆኑ ቅር ቢለኝም ወጣቶቹ መጥተውም ቢሆን ከፉክክሩ ውጪ አለመሆናችን አስደስቶኛል፡፡ከእድሜያቸው በላይ እያደረጉ ባሉት ነገር ደስተኛ ነኝ ማድነቅም ይጠበቅብኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ቡድኑ አሁን ተረጋግቷል ማለት ይቻላል?

ሄኖክ፡-አዎ ያማ ታሪክ ተረስቷል ከነበርንበት መንፈስ ወጥተን በተሻለ ሂደት ላይ እንገኛለን ለስራችን ዋጋ የመክፈል ሂደት ላይ ነው የምንገኘው ታሪኩ አልፏል ቡድናችን ለተለየ ሌላ የድል ታሪክ ተዘጋጅቷል፡፡

ሀትሪክ፡- በርግጥ እንዳልከው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ላለባችሁ ጨዋታ ወጣቶቹ ላይ መተማመን ይቻላል..?

ሄኖክ፡- በሚገባ በጣም ልትተማመንባቸውና ተስፋህን እንድትጥልባቸው የሚያደርግ አቋም እያሳዩን ነው ለዚህ ርግጠኛ ነኝ ፍላጎትና አቅማቸው እንዳውም ቡድናችን ለካ ነገም ተስፋ አለው እንድል አድርጎኛል… በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ባየሁት በርግጠኝነት የተሻለ ነገር ይታያል ብዬ እጠብቃለሁ… ምንም ጥያቄ የለውም ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፋችን አይቀርም፡፡

ሀትሪክ፡- ደጋፊው ጋርስ ያለው ስሜት ምን ይመስላል አንተስ ለደጋፊው የምትለው ነገር ምንድነው…?

ሄኖክ፡-ደጋፊዎቹ ከኛ ጎን ናቸው በኛም ደስተኛ በመሆናቸው የምንችለውን ለማድረግና የበለጠ እነርሱን ለማስደሰት እንጥራለን፡፡ ከተሸነፍንበት የሰበታ ከተማ ጨዋታ ባሸነፍነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ላይ ባሳየነው ትግል ደጋፊው ደስተኛ ሆኖ ከጎናችን ነው ለዚህም እናመሰግናለን አሁንም አብረውን እንዲሆኑ ጥሪ አድርጋለሁ ከቡና ጋር በምናደርገው ጨዋታም ፍሬ አፍርተን ደስታችንን በጋራ እንደምናከብር ርግጠኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ለብሔራዊ ቡድን አልተመረጥክም… አሁን ብትመረጥ ዝግጁ ነህ…?

ሄኖክ፡-ወሳኙ የአሠልጣኙ እይታ ነው የትኛውም ተጨዋች የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን ማገልገል ይፈልጋል፡፡ እኔም ሀገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡ አቅሙና ዝግጅቱም በደንብ አለኝ የአሰልጣኙን ጥሪ የምጠብቅ ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- የክለባችሁ ሰርቪስ በአዳ ሲያዝ ከፍለህ ያስለቀከው አንተ ነህ… ምን አነሳሳህ… ?

ሄኖክ፡- በዚህም ደስተኛ ነኝ በዚህ ክለብ ውስጥ 5 አመት ስቆይ 3ቱን አመት አምበል ነበርኩ ለክለቤ ዋጋ ከፍዬ ይህን ተግባር በመፈፀሜ ኮርቻለሁ ነገኮ የበለጠ ዋጋ አገኛለሁ ለክለብ ሟች መሆን ማለት ለኔ በችግር ጊዜ መድረስ ነው ለክለቤ ክብር ይህን በማድረጌ አሁንም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የከፈልከው ተመለስልህ… ወይስ ታፍኗል….?

ሄኖክ፡-/ሳቅ/ አዎ በአግባቡ ተመልሶልኛል

ሀትሪክ፡- አመሰግናለሁ ተባልክ ሳይሆን ገንዘቡ ተመለሰ ወይ እያልኩህ ነው…?

ሄኖክ፡-/ሳቅ በሳቅ/ አዎ ለኔ ያወጣሁት ገንዘብ ተመልሶልኛል እያልኩ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ለደጋፊው የምትለው የመጨረሻ ቃል?

ሄኖክ፡- ርግጠኛ ነኝ ከኛ ጎን እንዳላችሁም አምናለሁ ከክለቤ ጎን በመቆማችሁ ደስታ ይሰማኛል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ የደስታ ቀናችን ይሆናል ብዬ አምናለሁ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፈን ከደጋፊዎቻችን ጋር ለመጨፈር ተዘጋጅተናል፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport