“እንደ አሰልጣኝ ስራ ላይ አሰሪ፤ ከስራ ውጪ ግን ለተጨዋቾቼ ወንድም ነኝ” ዘላለም ሽፈራው (ሞውሪንሆ) የሰበታ ከተማ አሰልጣኝ

“ለካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ጠንክሮ መስራትና መፀለይ የግድ ነው”

“እንደ አሰልጣኝ ስራ ላይ አሰሪ፤ ከስራ ውጪ ግን ለተጨዋቾቼ ወንድም ነኝ”
ዘላለም ሽፈራው (ሞውሪንሆ)
የሰበታ ከተማ አሰልጣኝ

በርካታ ክለቦች ላይ አሻራውን አሳርፏል… ቢያንስ በትንሹ ወደ 7 ክለቦችን አሰልጥኗል… በደቡብ ፖሊስ የ6 አመት ቆይታው የሚገራርሙ ገጠመኞቾን አስተናግዷል… ከሙሉ ስሙ በላይ ቅጽሉ መገለጫው ሆኗል። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው /ሞውሪንሆ/ ይሰኛል… ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለአሰልጣኝነቱ ህይወት፣ ስለትዳሩ፣ ስለ ምክትል ኮማንደርቱ፣ በደቡብ ፖሊስ ስለገጠመው ቂጣና ጎመን፣ ከራዕይና ከገንዘብ ለየቱ ቅድሚያ እንደሰጠ፣ስለ አሰልጣኞች ማህበር፣ ስለ ወላይታ ድቻና ሰበታ ከተማ ፣ስለ ዋሊያዎቹ እንዲሁም ስለ ሌሎች ጉዳዮች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል።

ሀትሪክ:- አመሠግናለሁ…ዘላለም ሽፈራው ከሚለው ስምህ በላይ “ሞውሪንሆ” በተሰኘው ቅጽል ስም ትታወቃለህ..ስያሜው ከየት መጣ..?

ዘላለም:- ስሙን ያወጣው የቀድሞው የኢንተር ስፖርት ባልደረባ ኤርሚያስ አማረ ነው ያወጣው…መነሻው በምሰጠው ውሳኔና በያዝኩት የዲሲፕሊን አቋም ይመስለኛል ዋናው ግን ጆዜ ሞውሪንሆ በክለብ ደረጃ ኳስ ተጫውቶ አላለፈም አለም ላይ ግን ወርልድ ክላስ አሰልጣኝ ነው እኔም በተጨዋችነት የሚነገር ታሪክ ሳይኖረኝ በአሰልጣኝነቴ ጥሩ ታሪክ አለኝ ከታች ጀምሮ ጥሩ ስራ ሰርቻለሁ ያንን መነሻ አድርገው ነው ስሙን ያወጡልኝ

ሀትሪክ:- ስያሜው ታዲያ ተመቸህ..?

ዘላለም:- በርግጥ ዘላለም ነኝ ዘላለምን ስሆን ነው የሚመቸኝ…ግን በአለም ላይ ተጽእኖ በፈጠረ አሰልጣኝ ስምን ሲያጋሩኝ ደስ ይላል በጣም ተመቸኝ ባልልም አልጎረበጠኝም

ሀትሪክ:- ቤተሰቦችህ ጋርስ ተጽእኖ ፈጥሯል..?

ዘላለም:- /ሳቅ/ በሚገባ…ልጆቼ ኳስ ሲያዩ የጋዜጠኞችን ዘገባ ሲሰሙ በጣም ወደውታል በፕሪሚየር ሊግ ሞውሪንሆ ያለበትን ቡድን ነው የሚደግፉት..እኔም እርሱ ባያውቀኝም የርሱ አድናቂ ነኝ../ሳቅ/

ሀትሪክ:- እስቲ ደግሞ የአሰልጣኝነት ጉዞህን መለስ ብለህ አስታውሰኝ..?

ዘላለም:- በታዳጊ ፕሮጀክት ላይ ወንዶች ላይም ሴቶች ላይም በመስራተት ነው የጀመርኩት…የደቡብ ምርጥን አሰለጠንኩ ..ከ15 አመትና ከ17 አመት በታች ፕሮጀክትን አሰልጥኛለሁ..”ሚራክል” የተሰኘ የህንጻ መሸጫ መደብር ያዝኩ እነ አዳነ ግርማ ሙሉጌታ ምህረት ያሉበት ቡድን ማለት ነው… ከዚያ ብሄራዊ ትንባዎ ድርጅት ዋናው ቡድን ኒያላ አለ ድርጅቱ እሌኒ የሚባል ሲጋራ ማምረት ሲጀምር በእሌኒ ስም ቡድን ተሰራ ያንን ያዝኩ በትልቅ ክለብ ደረጃ ደቡብ ፖሊስ፣ አዳማ ከተማ፣ ደደቢት፣ሀዋሳ ከተማ፣ሲዳማ ቡና፣ድሬዳዋ ከተማ፣ወልዲያ ከተማ፣ ደቡብ ፖሊስ፣ ወላይታ ድቻ አሁን ደግሞ ለቀጣዮቹ 3 አመታት ሰበታ ከተማን ለማሰልጠን ተስማማሁ …/ሳቅ/

ሀትሪክ:- የማትረሳው ውስጥህ የቀረ ታሪክ የሰራህበት ክለብ የት ነው..?

ዘላለም:- ብዙም ማሰብ ሳያስፈልገኝ ደቡብ ፖሊስ የነበረኝ የ 6 አመታት ቆይታ ነዋ… አንድ ታሪክ ልንገርህ..እሌኒ 1200 ብር ደመወዝ እንክፈልህ ብለውኝ ተስማማሁ እሺ ግን እስከላይ ድረስ የመጓዝ ራእይ አላችሁ ወይ ስል አይ ዋናው ቡድን አዲስ አበባ ስላለ መጋቢ ቡድን ነው የሚሆነው አሉኝ… ከዚያ ደቡብ ፖሊስ…ኮሚሽነር ጌታቸው የሚባሉትን ሳናግር ዘንድሮ ምንም የለንም ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ወታደርነት ገብታችሁ ትቀጥላላችሁ ራዕያችን ደግሞ በ95 ጀምረናል በ1998 ፕሪሚየር ሊግ ነን ሲሉኝ ተደሰትኩ እሌኒ ደመወዝ ቢኖረውም ራዕይ የለውም በዚህ የተነሳ ገንዘብ ባይኖረውም ራእይ የያዘውን ደቡብ ፖሊስን መረጥኩና እዚያ ጀመርኩ…ወጣቶችን ሰበሰብኩና የደቡብ ክልል ሻምፒዮና ሆንን.. ክልሉን ወክለን ሄደን ሶስተኛ ወጣንና ብሄራዊ ሊግ ገባን…ከሶስት አመት ቆይታ በኋላ በ1999 በገንዘብ ችግር ቡድኑ እንዲፈርስ ማኔጅመንቱ ወሰነ

ሀትሪክ:- ተበተናችሁ? ራዕዩስ እንዴት ሆነ?

ዘላለም:- እንዴት ተደርጎ..? በወቅቱ ወደ ነበሩት ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወ/ሰንበት ጋር ሄጄ ሳናግራቸው ኳሱን እንወዳለን ብር ግን የለንም ሲሉኝ ደብዳቤ ይጻፍለኝ ገንዘብ ላምጣ ስላቸው ከቻልክማ በደስታ ብለው ትእዛዝ ሰጡ… ዲ ኤም ሲ የሚባል ኮንስትራክሽን ባለቤትን አናግረነው 50ሺብር ሰጠን…የቅዱስ ጊዮርጊሱ የልብ ደጋፊ ጀማል አህመድም
50 ሺህ ብር ሰጠን አንድ ግለሰብ ኮፓ ማንዴላ ጫማ ለ32 ልጆች ገዝቶ ሰጠን…ሙሉ ቲቪ ከነዲሹ አክሰሰሪ ጋር ሰጠንና ወደ ስራ ተመለስን…ይፍረስ በተባለበት አመት አንድም ጨዋታ ሳንሸነፍ የብሄራዊ ሊግ ሻምፒዮን ሆነን ፕሪሚየር ሊግ ገባን ተደሰትን የሚለው አይገልጸውም

ሀትሪክ:- 2000 ሚሊኒየም ደግሞ ሌላ ታሪክ ገጠማችሁ..

ዘላለም:- የሚገርም ገጠመኝ እንጂ… በወቅቱ ፌዴሬሽኑ ለሁለት ተከፍሎ ተወዳዳሪዎቹ ክለቦች 25 ሆንን…ግን 11 ክለብ ይወርዳል ተባለ…/በነገራችን ላይ ያኔ ፋሲል ከነማ ነበር ፕሪሚየር ሊግ ሲገባ በታሪኩ ለ2ኛ ጊዜ ነው/ አስራ አንድ ቡድን ሲወርድ እኛ እግዜር ረድቶን በግብ ክፍያ በልጠን 14ኛ ሆነን እነጥቁር አባይና መተሃራን በልጠን በሊጉ ቆየን..ደቡብ ፖሊስ በ2001 መነጋገርያ ሆነ እነ ጌታነህ ከበደ የነገሱበት አመት ነበር 7ኛ ሆነን ጨረስን…2002 ከስድስት አመታት በኋላ ደቡብ ፖሊስን ለቀቅኩ እነኚህ 6 አመታት የሚረሱ አልነበሩም…

ሀትሪክ:- ውትድርናና ኳስ እንዴት ሆነላችሁ…?

ዘላለም:- ወታደር ሆነን የተቀጠርነው ደመወዛችን 420 ብር ነበር በኋላ ግን ተቀጥረን ደመወዝ መጨመር ስላልተቻለ በማኔጅመንት እየተወሰነ ማእረግ እየተሰጠን ነው ያደግነው…ጌታነህ ከበደ ዋና ሳጅን እኔም ምክትል ኮማንደር ነበርኩ… ተጨዋቹ ቂጣ በጎመን እየበላ ነው ክለቡን ያቆየው… እኛን ለማበረታታት ሲል ኮሚሽነር ፍሰሃ ጋረደው ካምፕ መጥቶ ከልጆቹ ጋር ቂጣ በጎመን ይበላ ነበር..እነ ለአለም ብርሃኑ ግሩም ባሻዬ ሳይቀሩ የነበሩበት ቡድን ነው… ሊጥ ለማቡካት ሰው የምንቀጥርበት ብር አጥተን በየቀኑ ሁለት ተጨዋቹ ተራ ወጥቶለት ሊጥ ያቦካ ነበር…ሲቦካ በትክክል ካልተቦካ ተጨዋቾቹ 15 ቀን ከካምፕ ሳይወጡ ግቢ እንዲያጸዱ ይደረጋል../ሳቅ/
እንዲህ ነው ቡድኑ የተረፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 0 ለ 0 የተለያየነው በዚህ ጊዜ ውስጥ ነበር..ወቅቱ የገነንበት ቢሆንም ደመወዛቸው 420 የሆነና ቂጣ በጎመን የሚበሉ ተጨዋቾች የተሰባሰቡበት ነበር…ይህን ጊዜ የማልረሳው ብቻ ሳይሆን ምናልባት የማይደገም ምርጥ ዘመን ነው…

ሀትሪክ:- እስቲ ለሀገሪቷ እግርኳስ አበረከትኩ የምትላቸው ተጨዋቾች..እስቲ ዘርዘር አድርግልኝ..?

ዘላለም:- አንድ ተጨዋች ልንገርህ ሙሉ የሀዋሳ ሰው የሚያውቀው እስከዛሬ ያላየሁት ወደፊትም አላይም ብዬ
የምናገረው ግራ እግር ተጨዋች በሃይሉ ሽታው /ባቄላው/
ይባል ነበር እሱን የሚመስል ግራ እግር ተጨዋች እስከ ዛሬ አላየሁም ከዚያ ውጪ እነሙሉጌታ ምህረት ፣አዳነ ግርማ፣ ጌታሁን አሻሞ፣ ተመስገን ዳና፣ እርቅይሁን እንድርያስ፣ ጌታነህ ከበደና አዲስ ግደይ የመሰሉትን መጥቀስ እችላለሁ

ሀትሪክ:- ዘላለም ሸፈራው ቆፍጣና አሰልጣኝ ነው ማለት ይቻላል..?

ዘላለም:- እንደ አሰልጣኝ ስራ ላይ አሰሪ ከስራ ውጪ ግን ለተጨዋቾቼ ወንድም ነኝ… ቆፍጣና ነው ይቆጣል ከኔ ጋር የሰራ ሁሉ ይህን ይመሰክራል ብዬ አስባለሁ

ሀትሪክ:- ከአሰልጣኞች ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ዘላለም:- በግሌ ከየትኛውም አሰልጣኝ ጋር ጥሩ ነኝ.. ከባለሙያ ጋር ቅርበቴን በልክ አድርጌ እቀርባለሁ ችግር የለብኝም.. እንደ ታላቅ ወንድምም እንደ ሙያ ሲኒየሪቲ አክብሬው እውቀት ጭምር ያገኘሁበት አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሃይሌ ነው ከርሱ ውጪ ከጸጋዬ ኪዳነ ማርያምም እግባባለሁ እቀርባለሁ ከሌሎቹ ጋር መቅረብ ባለብኝ እቀርባለሁ

ሀትሪክ:- ከአሰልጣኝ ገብረ መድህን ሃይሌ ጋር ዋሊያዎቹን ይዘህ እንደነበር ይታወሳልና ከገብረመድህን ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ዘላለም:- ከገብረመድህን ጋር አብሬ የመስራት እድል ያገኘሁት በደደቢት ክለብ ውስጥ ነው..ገብሬ ከየመን እመጣለሁ ብሏቸው ሲቀር የደደቢቱ ኮ/ል አወል እኔን አናገረኝና ሃላፊነቱን ያዝኩ… በኋላ ሀሳቡን ቀይሮ ሲመጣ ምን ያድርጉ ጨነቃቸው እንደምንም ብለው እውነቱን ነገሩኝ ምክትል ሆኜ ብሰራ እንደሚደሰቱ ነገሩኝ እኔም ከገብረመድህን ጋር መስራቱን በደስታ ተቀብዬ አብሬ መስራት ጀመርኩ

ሀትሪክ:– ግን ግን ጥለህ ልትወጣ እንደነበረም ሰምቻለሁና ምክንያቱ ምን ይሆን?

ዘላለም:– እንዴት ሰማህ ይገርማል.. ኮሎኔል አወል መረጃ እንዳቀብለው ይፈልጋል ገብረመድህን ደግሞ ወሬ ያቀብላል ብሎ ሰጋና አገለለኝ…ሁኔታው እያስጠላኝ መጣ ታዲያ አንድ ስብሰባ ላይ እጄን አነሳሁና ውይይቱን ከመጀመራችን በፊት የምናገረው ነገር አለ ኮሎኔል አንተ መረጃ እንድሰጥህ ትፈልጋለህ ገብሬ ደግሞ ወሬ የማቀብልህ መስሎት እያራቀኝ ነው እባካችሁ ስራዬን ብቻ ልስራ ተውኝ ስል ተገረሙ ኮሎኔልም ችግር የለም አለ ገብሬም አይዞህ ብሎ አበረታታኝ ቅሬታዬ ተወግዶ አሪፍ ስራ ሰራሁ በጣም ተደሰትኩ.. በኋላ ሀዋሳ ከተማ ዋና አሰልጣኝ እንድትሆን እንፈልጋለን ሲሉኝ ኮሎኔል አወልም ገብሬም ይህን እድል አናበላሽብህም ብለው በክብር ሸኙኝ ከአመታት በኋላ ገብሬ ብሄራዊ ቡድኑን ሲይዝ ደውሎ አብረን እንስራ አለኝ ጥሪውን በደስታ ተቀብዬ አብሬው ሰርቻለሁ ጊዜው ቢያጥርም…ከገብረ መድህን ጋር ጥሩ ጓደኛሞች ነን በቅርርባችንም ደስተኛ ነኝ

ሀትሪክ:- የማህበሩስ ጉዳይ…የት ነው ያለው? ምን እየሰራ ነው?

ዘላለም:- ጥሩ ጥያቄ ነው…ማህበር የሚባል ነገር አለ እንዴ? አንዴ ፌዴሬሽኑ ውስጥ ውዝግብ በነበረ ሰአት ለምርጫ ድምጽ ሲባል በአስቸኳይ ማህበር ይቋቋም ተብሎ ከተጨዋቾች ተራማጅ ተስፋዬ፣ደጉ ደበበ፣ከአሰልጣኞች እኔ ተወክለን ስራ አስፈጻሚ ሆነን ጀመርን። ዶክተር ጌታቸው ፕሬዝዳንት፣ አብርሃም ተክለሃይማኖት ምክትል፣ እኔ የህዝብ ግንኙነት አብዲ ቡሊና ሰለሞን አባተ ተካተው ስራው ተጀመረ..ከዚያ በፊት በነአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራ ማህበር ነበር ለጠቅላላ ጉባኤው ድምጽ ለማግኘት ብቻ ሲባል በማህበር ላይ ማህበር ተመሰረተ ይሄ ልክ አልነበረም…በኋላ ላይም ምንም ስራ አልተሰራም ከቃላት የዘለለ ምንም ነገር ስላልነበር ራሴን አገለልኩ… ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ብቻ የአሰልጣኞች ማህበር ተብሎ እነ ሰለሞን እነ አብዲ ሲገቡ አያለሁ እንጂ ምንም የተሰራ ነገር አልገጠመኝም..

ሀትሪክ:- ቢኖር ኖሮ ከዚህ የተሻለ ስራ ይሰራ ነበርኮ..?

ዘላለም:- ቢኖር ኖሮ የሚባል ነገርኮ የለም..ቢኖርማ በርካታ ስራዎች ይሰራ ነበር ግን የለም..

ሀትሪክ:- እስቲ ስለወላይታ ድቻ እናውራ… አራት አመት ኮንትራት ስጡኝ ብለህ የጠየከው በምን አግባብ ይሆን..?

ዘላለም:- አቅዶ መስራትን የማይፈልግ አሰልጣኝ አለ ብዬ አላምንም..እንደ ጣራ የተለመደው 2 አመት ነው ይሄ ብዙ አያዋጣም ኢትዮጵያ ቡናን ተመልከት አራት አመት ነው ለአሰልጣኙ ኮንትራት የሰጠው…ይሄ ለኛም ትምህርት ይሆናል…ራዕይና ግብ ላለው አሪፍ ነው ወላይታ ድቻ ላይ የአራት አመት ኮንትራት ስጡኝ በየአመቱ ማሳካት የምንችለውን እንገምግም አልኳቸው ወላይታ ደግሞ በርካታ አቅም ያላቸው ወጣቶች የሚፈልቁበት ቦታ ነው ቦርዱ ጋር ቀረብኩ አራት አመት ስጠይቅ አብዛኛው ሰው የተረዳው የአራት አመቱን ክፍያ እንደጠየኩ አድርጎ ነው ግን አላልኩም አራት አመት ኮንትራት ስጡኝ የሁለቱ ይከፈለኝ ነገር ግን የመጀመርያና የሁለተኛ አመት አፈጻጸሜ ተገምግሞ እቅዱ ካልተተገበረ ሶስተኛና አራተኛ አመቱ ውል ሊቋረጥ ይችላል ይህን አብራርቼ ጠየኩ.. በእቅዱ መሠረት አራተኛ አመት ላይ ክለቡ ዋንጫ ማምጣት አለበት አካባቢው ላይ በርካታ አቅም ያላቸው ወጣቶች ስላሉ አራተኛው አመት ላይ 90 በመቶ ቡድኑን በአካባቢው ወጣቶች መመስረት አለበት የሚል ነው

ሀትሪክ:- ይህን ሁሉ ነግረሃቸው ምን አሉህ…?

ዘላለም:- ይህን አንፈልግም አሉ ለምን ስላቸው ላንተ አይጠቅምም አሉኝ /ሳቅ/ ከኔ በላይ ለኔ ማሰባቸው ግን ገርሞኛል.. አሁንም ክለቡ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ምንድነው ንገሩኝ ስል አይ ላንተ አይጠቅምም ብለው ከለከሉ.. እግር ኳስን የሚመሩ ሰዎች ግን ይህን ማረም አለባቸው… ሰዎቹ የዛው አካባቢ ነዋሪዎች ቢሆኑም የፖለቲካ ሹመት ስለሆነ ኳሱን የመረዳት አቅማቸው ደካማ ሆኖ ይመስለኛል ጥሩም ሰሩ አልሰሩ በእድገትም ይሁን በውድቀት መነሳታቸው ስለማይቀር ጫና ያለውን ስራ መስራት አልፈለጉ ይሆናል

ሀትሪክ:- እንደ አሰልጣኝ ኳሱ እንዲለወጥ አመራሮቹ ምን እንዲያደርጉ ትመክራለህ?

ዘላለም:- ባለሙያውም እቅዱን ሰፋ አድርጎ ኮንትራቱን ሰፋ ማድረግ ክለቦችም በተመሳሳይ ቢያቅዱ…አመራሮቹም ደግሞ ራእይና ግብ ይዘው ቢሰሩ ጥሩ ይመስለኛል ሁሌ የሚገርመኝ ታዳጊ ላይ ወጣት ላይ ይሰራ ይባላል ግን ማን ይስራው? ወላይታ ድቻን እንይ ቅርብ ስለሆንኩ…ለዋናው ቡድን ከፍተኛ ክፍያ ከፍለህ ታዳጊውን በጀት የለም ብሎ መበተን ምን ይባላል? ተስፋ ቡድኑ አንደኛ ሆኖ እየመራ የነበረውን ቡድን አፈረሱ ቡድኑ የሚገርመው ሁለተኛውን ዙር ሙሉ ፎርፌ ሰጥቶ እንኳን መጨረሻ አልሆነም…ወረቀት ላይ ታዳጊና ተተኪ ላይ መስራት ይላል የወላይታ ድቻ እቅድ….መሬት ላይ ግን አይወርድም… ይሄ ደግሞ ያሳዝናል…በሀድያ ሆሳእና ከደመወዝ ጋር ተያይዞ በተነሳው ውዝግብ ወቅት ወጣቶቹ የነበራቸውን ብቃት እያዩ ታዳጊ ቡድን ማፍረስ ያሳምማል። ሀዋሳ ከተማ ብቻ ነው ታዳጊ ሲያሳድግ የማውቀው..ደቡብ ፖሊስ ታዳጊ ቡድን ባይኖረውም በአካባቢው ወጣቶች ስላሉ በየጊዜው ወጣቶችን ይይዛል…በቃ ወረቀት ላይ ያለው መሬት ላይ መውረድ አለበት ባይ ነኝ..

ሀትሪክ:– ጅማ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ስትጫወቱ ኤሊያስን 42ኛ ደቂቃ ላይ ቀየርከው …ከሞራል ከስነልቦና አንጻር እረፍት ላይ ቢቀይረው ምን ችግር ነበረው የሚሉ ወገኖች ነበሩና ምን ምላሽ አለህ?ያኔ እንዳልከው ውሳኔው ታክቲካዊ ነው?

ዘላለም:-.. ተጨዋቹ ራሱ ብትጠይቀው በዚያ ሰአት ከምትቀይረኝ እረፍት ላይ ብቀር ይሻል ነበር ሊልህ ይችላል..ድሬዳዋ ላይ አሸናፊ በቀለ ቀይሮ ያስገባውን ቀይሮ አስወጥቷል ያየው ነገር ነበር ማለት ነው ዘጠና ደቂቃ አልቆ በባከነ ሰአት ላይ ሁለት ደቂቃ ሲጨመር በተቆጠረ ግብ ውጤት ሲቀየር አላየንም? ከተቀየረ ታዲያ አንድም ደቂቃ ዋጋ አለው ማለት ነው..ተጨዋቹ የምፈልገውን ባለመስራቱ ቀይሬዋለሁ ያም ተሳክቶልኝ ቡናን አሸንፈነዋል ቡና 1 ለ 0 እየመራን ሌላ ቢያክል 2 ለ 0 ይሆንና መነሳት ይከብደን ነበር ማለት ነው ነገር ግን 2 ለ1 ረተን ወጥተናል። እንደ ተመልካች 3 ደቂቃ ላይ የገባው ምንም አላመጣም ሊባል ይችላል እንደ አሰልጣኝ ግን 100 በመቶ ለውጥ አምጥቶልኛል አሰልጣኙ ደግሞ እኔ ነኝ /ሳቅ/

ሀትሪክ:- ለሰበታ ከተማ ፊርማህን አኑረሃል..ምን አቀድክ?

ዘላለም:- ሶስት አመት ለመቆየት ተስማምቻለሁ… 2016 ላይ ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን መገንባት ነው…2015 ላይ ቢያንስ ሜዳሊያ ውስጥ መግባት ታቅዷል ይሄ ከውጤት አንጻር ነው…ሌላው ዕቅድ ታዳጊዎችን ማብቃት ነው…ዘንድሮን ጨምረን በርካቶችን የማፍራት እቅድ ተይዟል..በከፍተኛ ሁኔታ ወጪን መቀነስ አንዱ እቅድ ነው ታዳጊ ላይ ስናተኩር በተዘዋዋሪ ወጪ እየቀነስን ነው ማለት ነው… በ2016 ለዋንጫ የሚወዳደር ቡድን መገንባት ታዳጊ ላይ አተኩሮ ወጪ መቀነስ በሚል ታቅዷል።

ሀትሪክ:- የባዬ ገዛኸኝን ሁለት ቦታ መፈረምን እንዴት አየኸው? ምን ርምጃ ወሰዳችሁ…?

ዘላለም:- /ሳቅ/ የባዬ ድርጊት ከመከሰቱ በፊትም ተመሳሳይ ውዝግቦች ይታዩ ነበር ድግግሞሹን ፌዴሬሽኑ ተመለከተና አንድ ህግ አወጣ ተጨዋች ስታስፈርሙ መልቀቂያ አይታችሁ መታወቂያ ተቀብላችሁ መሆን አለበት በማለቱ ባዬ ገዛኸኝን ያለ መልቀቂያ ካስፈረምኩ ህጋዊ አካሄድ ያልሄድኩትና መጠየቅ ያለብኝ እኔ ነኝ በርግጥ ከባለቤት ክለቡ ባህር ዳር ከተማ ጋር ተስማምተን ቢሆንም እጃችን ላይ መልቀቂያ አልነበረም በዚያ ላይ ተጨዋቹ በየአመቱ ሁለት ቦታ የመፈረም አባዜም አለበት ተጨዋቾች ለቃላቸው መታመን አለባቸው የባዬ ጉዳይ ይሄን ይመስላል..

ሀትሪክ:- የሙጂብ ቃሲም ዝውውርስ እንዴት ሆነላችሁ..?

ዘላለም:- ሙጂብን ለማዘዋወር ፍላጎቱ ነበረን እሱም በአማርኛና በእንግሊዘኛ የተጻፈ መልቂያውን ይዟል ነገር ግን መልቀቂያው ሲሰጠው በህግ አስረው የውጪ ጉዞው ካልተሳካ ኢትዮጵያ ውስጥ የትም ክለብ መጫወት አይችልም በሚል አስፈርመውታል..ፌዴሬሽኑም የተፈራረሙትን ጠቅሶ ዝውውሩን አይቻልም ብሏል እኛም ይህን እያየን ችክ ማለት አንችልም.. በዚህ ምክንያት ለማስፈረም አልቻልንም…

ሀትሪክ:- ዋሊያዎቹን እንዴት አገኘሃቸው?

ዘላለም:– /ሳቅ/ ይሄ ጥያቄ ይለፈኝ /ሳቅ/

ሀትሪክ:– እንደ ባለሙያ ምድቡን እንዴት አገኘኸው?

ዘላለም:–ምድቡ ከበድ ሊል ይችላል.. በጋሽ ሰውነት ጊዜም ዋሊያዎቹ ሲያልፉ ቀለል ብሏቸው አልነበረም አሁንም ለካሜሩኑ አፍሪካ ዋንጫ ጠንክሮ መስራትና መጸለይ የግድ ነው/ሳቅ/

ሀትሪክ:– ከገንዘብ ዝውውር ጋር ተያይዞ ወደ ክለብ ሲገቡ ለክለቦቹ ጉቦ የሚከፍሉ..ተጨዋች ሲያስፈርሙ ደግሞ ገንዘብ የሚቀበሉ አሰልጣኞች አሉ የሚል መረጃ አለና ሞውሪንሆ ከዚህ ነጻ ነኝ ማለት ይችላል..?

ዘላለም:– ይሄ ባይጠየቅ ይሻላል ማስረጃ ከሌለ ወሬውኮ ዋጋ የለውም..በቃ መፍትሄው ታግሎ ማስረጃ ይዞ አሳልፎ መስጠት ነው.. ሰጪም ተቀባዩም ወንጀለኛ በመሆናቸው መከሰስ አለባቸው ማስረጃ ግን የግድ ይላል..

ሀትሪክ:- ከኤጀንቶች ጋር ተግባብቶ ቢዝነስ ይሰራሉ የተባሉ አሰልጣኞች አሉ …ሰበታ ከተማስ በእገሌ ኤጀንት በኩል ካልመጣችሁ አላለም?

ዘላለም:– በኛ ክለብ እስካሁን ከፈረሙት ተጨዋቾች አንድም ተጨዋች በኤጀንት አልገባም…እኔ አናግረውና በደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ከክለቡ ሰዎች ተደራድሮ ይፈርማል አበቃ.. በግሌም እንዲህ አላደረኩም…

ሀትሪክ:– ከዳዊት እስጢፋኖስ ጋር አትግባቡም እንዴ..?

ዘላለም:- እንኳን አነሳኸው በሀትሪክ ላይ አይቼዋለሁ ..ከዳዊት ጋር ምንም ጸብ የለኝም …. በርቀት በማውቀው ደረጃ በዲሲፕሊንም ሆነ በችሎታው በጥሩ ግኑ ከሚጠቀሱ ተጨዋቾች መሃል አንዱ ነው .. ነገር ግን ከቅነሳ ጋር ተያይዞ የተናገረው ልክ አይደለም.. ድሬዳዋ ከተማ የነበረው ውል ከተጠናቀቀ በኋላ ነው የሄድኩት… መከላከያም የፈረምኩት እርሱ ከሄደ በኋላ ነው ለሰበታ ከተማም የፈረምኩት ውሉ አልቆ ከሄደ በኋላ ነው.. ሶስቱም ላይ ውሉን ጨርሶ እያለ ተቀነስኩ ማለት አይችልም ውል እያለው ሳይሆን ጨርሶ ከሄደ በኋላ ከኔ ጋር ማገናኘት ተገቢ አይደለም…በችሎታው አድንቀኸው በስራ ደግሞ ላትፈልገው ትችላለህ ይሄ ደግሞ የኮቹ መብት ነው…በግሌ ከርሱ ጋር ክፉ ደግ ተነጋግሬ አላውቅም.. ክትፎ የሚወድ ግን መብላት የማይፈልግ ሰው አለ ይሄ የሰው ባህሪ ነው.. እኔም እንደዛው…

ሀትሪክ:- ሰበታ ከተማ ላይኮ ጠብቁ ተብሎ አንተ ስትመጣ ነው ለዳዊትና መስዑድ በቃ ክለብ ፈልጉ የተባሉት…

ዘላለም:– ታዲያ እሱን እኔ አላውቅም ማወቅም አይጠበቅብኝምኮ

ሀትሪክ:- እስቲ የመሰረትከውን ቤተሰብ አስተዋውቀን?

ዘላለም:- ባለትዳርና የሁለት ሴቶች የሁለት ወንዶች ልጆች አባት ነኝ ባለቤቴ ወ/ሮ ወይንሸት እሸቱ ትባላለች ልጆቼ ደግሞ የመጀመሪያዋ ቬኔሲያ ፣ ናሆም ፣ ነህምያና ማራማዊት ይባላሉ። በስራዬ ስኬት ላይ በደስታዬ ላይ ቤተሰቤ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ሽንፈት ቢገጥመኝ ሽንፈቴን የምረሳው በቤተሰቤ ነው እናም በነሱ ደስተኛ ነኝ ለቤቴ ደግሞ ትልቁን ድርሻ ወስዳለችና ማመስገን እፈልጋለሁ ሌላው ታናሽ ወንድሜ አለ ፍጹም ሽፈራው ይባላል ሁሉንም እወዳቸዋለሁ ለማለት ነው

ሀትሪክ:- ጨረስኩ የመጨረሻ የምትለው ነገር አለ…?

ዘላለም:- የመጀመሪያ ምስጋናዬ ለቸሩ መድሃኔያለም ይሁንልኝ..ብዙ መሠናክልን አልፌ በሰላምና በጤና ለዚህ ደረጃ የደረስኩት በርሱ ነውና… ከዚያ ውጪ ቤተሰቦቼን፣ ታናሽ ወንድሜን፣ ቅድም እንዳልኩህ ብዙ ጓደኞች የሉኝም ግን ያሉትን ጥቂቶቹንም ቢሆን አመሠግናለሁ…አንተም ሀትሪክም ለሠጣችሁኝ እድል ከልብ አመሠግናለሁ።

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport