የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ ረዳት ካፒቴንና ጠንካራው የኋላ ማገር ተጨዋች የሆነው አስቻለው ታመነ ቡድናችን ከጋና አቻው ጋር ላለበት የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታው እንዲረዳው ከሴራሊዮን አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ግጥሚያን አድርጎ ያለ ግብ ካጠናቀቀ በኋላ ስለዚህ ጨዋታ፣ ስለ ዋልያዎቹ ዝግጅት፣ ከጋና ጋር ስለሚያደርጉት የዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ፣ ለአፍሪካ ዋንጫው ጨዋታ ከአስተናጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር ስለመደልደላቸውና ሌሎችንም ተያያዥ ጥያቄዎች አጠር ባለ መልኩ አቅርበንለት ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል፤ አስቻለው ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ያደረገው ቆይታም ይህን ይመስላል፡፡
ሀትሪክ፡- በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በቅርቡ የጋና ብሔራዊ ቡድንን /ብላክ ስታሮቹን/ ትገጥማላችሁ፤ ለእዚህ ጨዋታ እያደረጋችሁት ያለው ልምምድ ምን ይመስላል?
አስቻለው፡- እስካሁን ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ጥሩ ልምምድን ነው እያደረግን የሚገኘው፤ ይሄ ዝግጅታችንም ምንም እንኳን ከጋና ጋር ላለብን የቅርቡ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ቢሆንም ለሌሎቹም የእዚህ ምድብ ግጥሚያዎቻችንና በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደውም የዋናው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድራችን ሊጠቅመንም የሚችል ነው፤ ከሁሉም በላይ በዚህ ዝግጅት ወቅት እኔን ያስደሰተኝ ነገር ቢኖር ደግሞ ለእኛ ዋልያዎቹ የራሳችንን አቅም ለመለካት የምንችልበትና ለዋናው ውድድሮቻችንም ሊጠቅሙን የሚችሉ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ተዘጋጅቶልን ያንን ግጥሚያ ማድረግ መጀመራችን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ ጋናን ከመግጠማችሁ በፊት ሴራሊዮንን በአቋም መለኪያ ግጥሚያ ተፋልማችሁ ያለ ግብ ጨዋታውን ልታጠናቅቁ ችላችኋል፤ ግጥሚያው ምን መልክ ነበረው? ጨዋታውን ስላላሸነፋችሁም እየተተቻችሁም ነው በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
አስቻለው፡- እኛ ሀገር አሸነፍክም፣ ተሸነፍክም፣ አቻ ወጣክም ትችት አይጠፋም፤ ትችት አስተማሪና አንተን የሚያሳድግህና የሚያሻሽልህ ሲሆን ነው በጣም ደስ የሚለው፤ እዚህ ግን ጨዋታዎችን አሸንፈህ ስትወጣ በእድል ነው ያሸነፍከው፣ በአጋጣሚም ነው ውጤታማ የሆንከው ትባላለህና ሁሌም የእኛ ስራ ሊሆን የሚገባው ከምናደርጋቸው ጨዋታዎች በመነሳት የቱ ነው ክፍተት እና ደካማው ጎናችን በሚል ስራችንን መመርመር ይገባናልና ሌላ ምላሽ ውስጥ ልንገባ አይገባም፤ በእግር ኳስ ጨዋታ ኳስ እስከሆነ ድረስ ማሸነፍ፣ መሸነፍና አቻ መለያየት አለ፤ እግር ኳስን በአጋጣሚ ጎል ጋር ደርሰህ የምታሸንፍበትም ወቅት አለ፤ ደርሰህም ደግሞ እድለኛ ሳትሆን ትቀርና ላታሸነፍም ትችላለህና የእኛም ቡድን ከሴራሊዮን ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ሆኖና ጎልም ጋር ደርሶ እነሱን ለማሸነፍ ያልቻለው ዕድለኛ ስላልነበር ነው፤ በዚህ ጨዋታ የእኛ ቡድን ግጥሚያውን ባለማሸነፉ ብዙ ነገር እየተባለ ይገኛል፤ ቡድኑም እየተተቸ ይገኛል፤ ግን ለምን አላሸነፉም በሚለው ነገር ላይ ነው ልንነጋገር የሚገባን፤ ከሴራሊዮን ጋር ያደረግነው ጨዋታ የመጀመሪያችንና የአቋም መለኪያም ግጥሚያ ነው፤ በዛ ላይ ደግሞ ከጌም ርቀን በመምጣትም ያከናወነው ነው፤ ውጤት የሚመጣው ተደጋጋሚ የሆኑ ግጥሚያዎችን ስታደርግም ነው፤ አሁን እያደረግን ያለነው የአቋም መለኪያ ግጥሚያ አሰልጣኙ ለዋናዎቹ የማጣሪያ ግጥሚያዎች በቋሚ ተሰላፊነት የሚጫወቱትን ልጆች ለመለየት የሚያይበት ነው፤ ( እሁድ ከኡጋንዳ ጋር ለሚኖረ ሌላውም ጨዋታ በጉዳት ላይ የነበሩትን እነ ጌታነህንጨምሮ ና አቡበከርን እንዲሁም ሌሎቹንም የሚመለከትበት ስለሆነም ለእኛ እንዲህ ያሉ ግጥሚያዎችና እሁድ ከኡጋንዳ ጋር የምናደርገው ሌላው የአቋም መለኪያ ጨዋታም እኛን በጣም የሚጠቅሙን ናቸው፡፡ ቃለ ምልልሱ ከእሁዱ የወዳጅነት ጨዋታ በፊት የተደረገ ነው።

ሀትሪክ፡- የዋልያዎቹን የተጨዋቾች ስብስብ በተመለከተ ምን አልክ? ይሄ ቡድን የት ድረስስ የሚጓዝ ይመስልሃል?
አስቻለው፡- አሪፍ ስብስብ ነው ያለን፤ 80 ፐርሰንቱም የበፊቱም ቡድን ነውና ጥሩ ምርጫም ነው የተደረገው፤ ሌላው ቀደም ሲል የነበረው ቡድን ሳይፈርስ ባሉት የተጨዋቾች ስብስብ ላይ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አሰልጣኙ ለሚከተለው አጨዋወት ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳዩ የነበሩትን ልጆችና ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾችም ውስጥ አንድአንድ ልጆችን ሊያካትት መቻሉም በጥሩ መልኩ የሚጠቀስለት ነው፤ አሰልጣኝ ውበቱ የዋልያዎቹን ስብስብ ሳያፈርስ የሄደበት መንገድ ወደፊትም ሊለመድ ይገባል፤ የተሰራ ቡድን መፍረስ የለበትም፤ አሁን አሁን እንኳን ከቅርብ ጊዜያቶች ወዲህ በእኛ ሀገር ደረጃ ይህን እየተመለከትንም ነው፡፡
ዋልያዎቹን በሚመለከት አሁን ላይ የአቋም መለኪያ ግጥሚያን እያደረግን ስለሆነ ራሳችንን እየፈተሽን ነው፤ ቀጣይ ጨዋታም አለን፤ በዛ ላይም መሻሻሎች እንደሚኖረን እናምናለን፤ ከዛ ውጪም ከቡድኑ ጋር በጉዳትና በሌላ ምክንያቶችም ያልነበሩ እነ ጌታነህ፣ አቡበከርና በግብፅ ሊግ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለን የመሳሰሉ ተጨዋቾችም ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ ሲቀላቀሉ የተሟላም ቡድን ይኖረናልና ይሄ ደግሞ ለዋናዎቹ ውድድሮች በጣሙን ይጠቅሙናል፡፡
ሀትሪክ፡- በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ከአስተናጋጇ ሀገር ካሜሩን፣ ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር ተደልድለናል፤ የዕጣ መውጣቱን እንደሰማህ ምን አልክ?
አስቻለው፡- እኛ ከማንም ሀገራት ጋር ቢደርሰን ያለውን ሁኔታ እናውቀዋለን፤ ሌሎቹ ሀገራት ግን ለእኛ ከሚሰጡን ዝቅተኛ ግምት በመነሳት ከእኛ ጋር እንዲደርሳቸው ይፈልጋሉ፤ ይሄ በፊት የነበረ ሁኔታ ነው፤ አሁን ላይ ግን እኛ ዋልያዎቹ በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚኖረን ተሳትፎ ወደ ውድድሩ ስፍራ የምናመራው በደቡብ አፍሪካ ከነበረን ተሳትፎ አንድ ደረጃ ወደላይ ከፍ ከማለት ባሻገር የውድድሩ ክስተትም ለመሆን ነውና ያን እልማችንን እናሳካለን፡፡
ሀትሪክ፡- ዋልያዎቹን በካፒቴንነት መምራት መቻልህን በተመለከተ ምን ትላለህ?
አስቻለው፡- ከዚህ ቀደም የመራሁበት ጊዜም ነበርና ይሄ ለእኔ አዲስ አይደለም፤ አሁን ጌታነህ ጉዳት ላይ ስለነበር የእሱ ረዳት ሆኜ ነው ቡድኑን በሀላፊነት እየመራውት የምገኘው፤ ብሔራዊ ቡድንን በሃላፊነት መምራት ከአንተ ብዙ ነገር ይጠበቅብሃል፤ ሀላፊነቶችን ስለምትሸከም ጫናም አለውና አሰልጣኙ በእኔ እምነት ጥሎብኝ ነው ሀላፊነቱን የሰጠኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?
አስቻለው፡- ኳስም ማንኛውም ነገር የሚኖረው ሰላም ሲኖር ነው፤ ፈጣሪ ውዲቷ ሀገራችንን ሰላም እንዲያደርጋትም እመኛለው፤ ፀሎታችንም አይቋረጥ፡፡
አስተያየት ይስጡ