“የኢትዮጵያ ቡናና ካሳዬን ወድጄ፣ መርጬና ፈቅጄ ነው የመጣሁት”
“ነገሮች እየሄዱ ያሉት በአላህ እንጂ በኔ ሀሳብ አይደለም”
ነስረዲን ሃይሉ/ ኢት.ቡና/
ለአመታት የዘለቀው የኢትዮዽያ ቡና ፍቅሩ በመጨረሻም የሚወደውን ማሊያ እንዲያደርግ አድርጎታል ካሳዬና ቡና ፈልገውህ እንቢ ማለት ይከብዳል ሲልም ይናገራል ከ130-150 ሺህና ብር የተጣራ ደመወዝ ቀርቦለት አሻፈረኝ ብሎ 100ሺህ ብር ወዳቀረበለት ኢትዮዽያ ቡና አምርቷል። ተወልዶ ያደገው አዳማ ቢሆንም ልቡ የፈቀደው ለኢትዮዽያ ቡና መጫወት ነው በማለትም ከቀጣዮቹ 3 አመታት የቡናማዎቹ የኋላ ደጀን ላደረገው ካሳዬ ያለውን ፍቅር የሚገልጸው የመሃል ተከላካዩ ነስረዲን ሃይሉ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ከታች ያለውን ይመስላል።
…..
ሀትሪክ:- ነስረዲን በህይወቱ ደስተኛ ነው?
ነስረዲን:- /ሳቅ/በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ አላምዲሊላሂ….ባለኝ ነገር በሁሉም ደስተኛ ነኝ
ሀትሪክ:- ኳስ ተጨዋች የሆንከው በድንገት ነው… ? እንደዚህ የሚል መረጃ አግኝቻለሁ
ነስረዲን:- አዎ በህይወቴ ውስጥ ኳስ ተጨዋች እሆናለሁ ብዬ በፍጹም አስቤ አላውቅም…2007 ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በሂዩማን ኒዩትሬሽን ተመርቄ ስራ ፈላጊ ነበርኩ…
ሀትሪክ:- ከዩኒቨርስቲ ወደ ካምቦሎጆ እንዴት መጣህ ታዲያ?
ነስረዲን:- /ሳቅ/ አጋጣሚው የተቀየረው ስራ በምፈልግበት ጊዜ ለምን እግርኳስ አትጫወትም ብሎ አሰልጣኝ ሄኖክ ታኬታ ሰጥቶኝ አዲስ አበባ ፖሊስ ለሙከራ መጣሁ…በዚህ አጋጣሚ ሄኖክን ከልብ አመሰግናለሁ።
ሀትሪክ:- ፍላጎትና ህልም ሳይኖርህ ሙከራ ማድረግህ አይጋጭም?
ነስረዲን:- ከዚህ በፊት ኤፍሬም የሚባል አዳማ ላይ ያሰራ የነበረ ልጅ ነበር..ሁልጊዜ ትምህርት ጨርሼ ክረምቱን ወደ አዳማ ስሄድ ሁሌ በክረምት ጨዋታ ይደውልልኝና ሙሉ የትራንስፖርት ወጪዬን ችሎኝ እነሱ ላሉበት ቡድን እጫወታለሁ.. ኳሱ አንድ ሁለት ብሎ የጀመረው ያኔ ነው
ሀትሪክ :- የሙከራው ውጤት ምን ሆነ ?
ነስረዲን:- ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ መመላለሱ ከበደኝ ገንዘብም አልበቃኝም ቻሌንጁም በዛ…በዚህ ጊዜ ባሌ ነገሌ ቦረና ብሄራዊ ሊግ ወደ የሚወዳደረውና አሰልጣኝ ወንደሰን ሮባ ወዳለበት ቡድን ሄጄ ለአንድ አመት ብጫወትም አልተሳካም ያለው ክፍያ ማነስ ቤተሰብ ከሚጠብቀው ጋር ባለመሄዱ ጫና ሲበዛ ተውኩት…ከዚያ ግን ስሙን የማልጠቅስልህ ሰው የሆነ ቡድን ጋር እልክሃለሁ ቅድሚያ ግን መክፈል አለብህ አለኝ አካሄዱን አላወኩም ገንዘብም የለኝም ግራ ገባኝ…

ሀትሪክ:- ከፈልክና ሄድክ ታዲያ…?
ነስረዲን:- ምን እከፍላለሁ? የምከፍለው ምንም አልነበረኝም ቡድኑን ከነገረኝ ለምን ራሴ አልሄድም አልኩ ሲስተሙን ገና አላወኩትም…እንዳሰብኩት ሄጄ ሞከርኩ ጥሩም ነበርኩ…ነገር ግን በወቅቱ የጠጣሁት ውሃ አልተስማማኝምና በጣም ታመምኩ… አልቻልኩም ወደ ናዝሬት ተመለስኩ በህይወቴ መቼም የማልረሳውን መጥፎ ጊዜአሳለፍኩ… ግን አንድ ነገር አጽናናኝ አላህ የተሻለ ነገር ለካ አስቀምጦልኝ ነበር.. ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሳገግም ሰው ጠቁሞኝ ሀዋሳ ላይ በተዘጋጀ ሲቲ ካፕ ላይ በአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ በሚሰለጥነውና ከፍተኛ ሊግ ላይ በሚካፈለው ቡራዩ ከተማ ተካትቼ ጥሩ ጊዜ በማሳለፌ ከባሌ ወደ ቡራዮ ያደረኩት ጉዞ ተሳክቶ ለ2 አመት ልጫወት ቻልኩ። ከዚያ በአሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ የሚሰለጥነው ለገጣፎ ለገዳዲ ለአንድ አመት ተጫወትኩ.. ከዚያ መከላከያ አንድ አመት ከግማሽ ተጫውቼ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ገባሁ እዚህ 6 ወር ተጫውቼ ዘንድሮ ስመኘው ወደነበረው ኢትዮዽያ ቡና ገባሁ… ጉዞዬ ይህን ይመስላል።
ሀትሪክ:- ተወልደህ ያደከው አዳማ ተምሳሌት የሆነህ ተጫዋች የለም ማለት ነው?
ነስረዲን:- በኳስ የምጠራው ተጨዋች የለኝም .. ነገር ግን ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስማር የውበቱ አባተ ሀዋሳ ከተማን እመለከት ነበረና ያየሁትና ጥሩ ነገር ገፋፍቶኛል ብዬ አስባለሁ። በርግጥ ያን ባይም ወደኳሱ ሳይሆን በተመረኩበት ሙያ ስራ ፍለጋ ነው ፊቴን ያዞርኩት የውበቱን ቡድን ሳይ ለካ መጫወት እችላለሁ የሚል ነገር የጫረብኝ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ አዳማና ሀሮማያ ላይ በተዘጋጀው የዩኒቨርስቲዎች ውድድርን ላይ ለሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተጫውቻለሁ/ሳቅ7
ሀትሪክ:- የመሃል ተከላካይና ነህ…ለምን ቦታውን መረጥክ?
ነስረዲን:- በነገራችን ላይ ለዩኒቨርስቲው ስጫወት ሁለቱም ከተማ ላይ አጥቂ ሆኜ ነው… የዩኒቨርስቲው ሰው ሁሉ የሚያውቀኝ በአጥቂነቴ ነው መሃል ተከላካይ የሆንኩት ባሌ እያለሁ አሰልጣኝ ወንድወሰን ሮባ መሃል ተከላካይ አድርጎ አጫወተኝ.. ተመቸሁት ጥሪ አቋም አሳየሁ.. በተለያየ ጨዋታዎች ላይ ለዛሬ ብቻ እየተባልኩ በመጫወቴ ቦታዬ የመሃል ተከላካይ ሆኗል። አሰልጣኙ በፐርፎርማንሴ ወደደኝ.. በቃ ከዚያው በኋላ ቦታዬ ሆኖ ቀረ ማለት ነው
ሀትሪክ:- የመሃል ተከላካይ ከሆንክ በኋላ ከሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ ማነው ምርጫህ?
ነስረዲን:- ሀገር ውስጥ ዘንድሮ ለፋሲል ከነማ የፈረመው አስቻለሁ ታመነ ከውጪ የሊቨርፑሉ ቨርጂል ቫንዳይክ ምርጫዬ ናቸው
ሀትሪክ:- ምንይሉ ወንድሙስ ላንተ ምን ትርጉም አለው?
ነስረዲን:- በብዙ ጥሩ ነገሩ ምንይሉ ወንድሙ ደስ ይለኛል አጥቂ ነው ነገር ግን የእግርኳስ ህይወቴ ስኬት ላይ የርሱ ምክር ቦታ አለው… መከላከያ እያለሁ የሚመክረኝ እንዴት አቅጣጫ መያዝ እንዳለብኝ አጨዋወቴ ምን መምሰል እንዳለበት የሚመክረኝ እርሱ ነበረ አመሰግነዋለሁ
ሀትሪክ:- መከላከያ የቆየህበት አንድ አመት ተኩል መለስ በልና አስታውሰን?
ነስረዲን:- መከላከያ ትልቅ ክለብ ነው እንደ ስሙ መከላከያ የሆነ ምርጥ ቡድን ነው በግሌ ግን ደስተኛ ያልነበርኩበት ጊዜ አሳልፌያለሁ… አልተመቸኝም ነገር ግን ጥሩ ቡድን ነው…. ለኔ ፈታኝ ጊዜ ያኔ ነበር
ሀትሪክ:- ከአጨዋወት ጋር በተያያዘ ከአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ጋር አልተስማማችሁምኮ..?
ነስረዲን:- አዎ.. አልተግባባንም እውነት ነው የራሱ ፍልስፍናና አጨዋወት ስለነበረው የኔ አጨዋወት አልተመቸውም ይመስለኛል…
ሀትሪክ:- የደስታህን 12 ወራቶች እናስታውስ..የለገጣፎን ቆይታ አስታውሰን?
ነስረዲን:- ዋው ምርጥ ቡድን ነበረን.. ሙሉ ቡድንና አሪፍ ህብረት የነበረበት ቡድን ውስጥ ነበርኩ..ደስታን አጣጥሜያለሁ… አሁን ድረስ የምደዋወላቸው ተጨዋቾች አሉ..አሰልጣኝ ዳዊት ብዙ ነገርን አድርጎልኛል.. እንዴት መጫወት እንዳለብኝ መስመሮችንና አጨዋወቴን ያሳየኝ ከኳስ ህይወት እንዳልወጣ ያደረገኝ ባለውለታዬ ነው.. በዚህ አጋጣሚ ከልብ አመሰግናለሁ
ሀትሪክ:- የኢትዮ ኤሌክትሪክ የ6 ወራት ቆይታህስ ምን ይመስላል?
ነስረዲን:- አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ከወደኩበት ያነሳኝ ያህል ይሰማኛል.. ውስጤ በነገሮች በተወጠረ ጊዜ ደርሶ መልሶ ያነሳኝ አሰልጣኝ ነው.. አሰልጣኝ ክፍሌንም አመሰግናለሁ
ሀትሪክ:- ለኢትዮዽያ ቡና በመፈረምህ ምን ተሰማህ?
ነስረዲን:- በጣም ነው የተደሰትኩት.. በፊትም የመግባት እድል አግኝቼ ነበር በኔ ጥፋት ሳይሳካ ቀርቷል በማጥፋቴም ቅጣቴን ተቀብዬበታለሁ… አሁን ላይ ደግሞ እድሉ ሲመጣ በርካታ አማራጭ ክለቦች ከጥሩ ክፍያ ጋር ቢመጡም አልጓጓሁም በዚያ ላይ አሰልጣኝ ካሳዬ አናግሮኝ እንቢ ማለት አልቻልኩም በስልክ ስናወራ እንኳን ይመስጥሃል.. በቃ ኢትዮዽያ ቡናና ካሳዬን ወድጄ መርጬና ፈቅጄ ነው የመጣሁት… ለኢትዮዽያ ቡናም ስፈርም ደስተኛ እሆንበታለሁ ብዬ ነው …
ሀትሪክ:- ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ምን ለማሳካት አቅደሃል..?
ነስረዲን:- ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ጠንክሬ ሰርቼ ክለቡን ውጤታማ ማድረግና የሊጉ ሻምፒዮን እንዲሆን ያለኝን ለመስጠት
ተዘጋጅቻለሁ..በዚያውም ለብሄራዊ ቡድን የመመረጥ እቅድ አለኝ፡፡ ማንኛውም ተጨዋች ቅድሚያ ለብሄራዊ ቡድን መመረጥን ያልማል እኔም ይህን አስባለሁ ከቡና ጋር ጥሩ ሆኜ ቡድኑ ሻምፒዮን ከሆነ ብሄራዊ ቡድን እንደምመረጥ አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ:- ካለ ኢትዮዽያ ቡና ተሰላፊነት ሲፈልጉህ ለነበሩት ለሲዳማ ቡና፣ ለወላይታ ድቻ፣ ለሰበታ ከተማና ለድሬዳዋ ከተማ ብጫወት ለብሄራዊ ቡድን አልመረጥም እያልክ ይሆን?
ነስረዲን:- /ሳቅ/ በፍጹም አላልኩም.. እንደዛም አላሰብኩም.. ለኢትዮዽያ ቡና መፈረሜ ያጎላኛል.. ከዚህ በፊት ገንዘብ መርጬ የሆንኩትን አውቃለሁ እስቲ አሁን ደግሞ ከአጨዋወቴ ጋር ይሄዳል ያጎላኛል ለምለው ልፈርም ብዬ ቡናና ካሳዩን መርጫለሁ ዋና ሀሳቤ ይሄ ነው…
ሀትሪክ:- በአቋራጭ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተፋላሚነት ማደግህ አልገረመህም?
ነስረዲን:- /ሳቅ/ ገርሞኛል ተደስቼበታለሁም.. ከመጀመርያውኑ የሆነው አስቤ ሳይሆን የአላህ መንገድ ሆኖ ነው..ነገሮች እየሄዱ ያሉት በአላህ እንጂ በኔ ሀሳብ አይደለም ስለ ሁሉም ነገር አላምዲሊላሂ ነው የምለው…
ሀትሪክ:- የኤጀንቶች የስልክ ጥሪ ፈርምልን ከኛ ጋር ስራ የሚል ጥያቄ አልቀረብልህም…?
ነስረዲን:- ከነገሮች ከሰው ሳይሆን ከራሴ ስህተት ነው የተማርኩት.. ገንዘብ ብለህ ስትሄድና ደስታን የት ነው የማገኘው ብለህ መርጠህ መፈረም ይለያያል እኔ ከቀድሞ የራሴ ምርጫ ተምሬያለሁ.. በዚያ ላይ እድለኛ ነኝ ከጎኔ ሆኖ በኤጀንትነት የሚሰራው ዘላለም በቀለ/ዞላ/ ነው … መከላከያ ስገባ ጀምሮ ኤጀንቴ ነው በነገሮች መበላሸት ግን የተወሰነ ጊዜ ከፍዬው ክፍያውን ሳቋርጥ ተቀይሞኝ ደውሎ ሰድቦኝ አያውቅም፡፡ በተቃራኒው እንዴት መሄድ እንዳለብኝ እየደወለ ይመክረኛል..
በዚህ ባህሪው አስገርሞኛል…. አሁንም ኢትዮዽያ ቡና የገባሁት በርሱ ነው ..ከጎኔ ሆኖ እያደረገ ላለው ድጋፍና አርአያነት ላለው ስራው ዞላን ከልቤ አመሰግናለሁ።
ሀትሪክ:- ለኢትዮዽያ ቡና ከፈረምክ በኋላ የተደረገልህ አቀባበል ምን ይመስላል?
ነስረዲን:- አሪፍ ነገር ነው ያለው…ባለፉት ሁለት አመታት ስሜ በመያያዙ እንደ ቤቴ ነው ያየሁት..አቀባበሉ ደስ ብሎኛል
ሀትሪክ:- ስለ ደጋፊውስ የምትለው ነገር አለ?
ነስረዲን:- የቡና ደጋፊ ምርጥ ነው..ሁሌ ከቡድኑ አጠገብ መገኘቱ ያስደስታል። የተሻለ ነገር ሰርቼ ደጋፊውን እንደማስደስት ተስፋ አደርጋለሁ።
ሀትሪክ:- አጨዋወትህ ለካሳዬና ለቡና እንደሚመች ርግጠኛ ነህ?
ነስረዲን:- አዎ.. እንደ ሀሳብ ሰው ከሚሰጠው ምክር ተነስተህ የተሻለውን ትመርጣለህ የኔም እንዲህ ነው የሆነው.. ወደፊት ባለው ነገር ዙሪያ ርግጠኛ መሆን አይቻልም ነገር ግን የተሻለ ነገር አደርጋለሁ አጨዋወቱ ከኔ ጋር ይሄዳል ብዬ አስባለሁ
ሀትሪክ:- ገንዘብ ከሆነ ይደርሳል አሁን ቅድሚያ ራሴን ማሳየት ላይ የማተኩረው ብለሃል የሚል ነገር ሰማሁ…እውነት ነው?
ነስረዲን:- አዎ ብዙዎች ደውለው ውሳኔዬን ሲሰሙ እንደሞኝ ነው ያዩኝ እጅህ ላይ 1.2 ሚሊዮን ብር ይዘህ እንጂ ያሉኝ ብዙ ናቸው አላምዲሊላሂ በቡናም ያገኘሁት ማንም ያላገኘውን ነው አብረውኝ የተማሩ ቀን ከሌት ሲለፉ የነበሩ አሉ.. አሁንም ያለኝ ነገር ብዙ ነው..እሱን ይባርክልኝ/ሳቅ/
ሀትሪክ:- ከሌሎች ክለቦች የተጣራ ወርሃዊ ደመወዝ እስከ 140 እና 150 ሺ ብር የቀረበለት ነስረዲን ለቡና በ100 ሺህ ብር ፈረመ መባሉ ያነጋግራል.. በዚህ ላይ ለተጨዋቾች የምትለው ነገር አለ?
ነስረዲን:- በነገራችን ላይ ማንም ሰው ገንዘብ ለማግኘት ይሰራል..ይሄ እውነት ነው ቡናም ግን ከፍሎኝ እንጂ በነጻ አልፈረምኩም..ያንሳል ሲባል ግን እንደ መነሻችን ይለያያል 130 ሺህ ተከፍሎኝ ማድረግ አለብኝ የምለውን 100ሺህ ብርም አሳካዋለው ከኔ የሚጠበቀው መበርታት ብቻ ነው….ማሳካት ያለብንን ለማሳካት የቱ ይመረጣል የሚለውም መታየት አለበት ብዬ አስባለሁ.. በኮንፌዴሬሽን ካፕኮ ላልጫወት እችላለሁ.. የመጫወት እድል ላይኖር ቢችል በርትቼም በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ልጫወት እችላለሁ ዋናው ደመወዜን ከፍ ዝቅ ማድረግ ሳይሆን ላሳካ የፈለኩትን የት አሰካለሁ የሚለው ነው ዋናው.. በግሌ በ3 አመት ውስጥ ለማሳካት ያሰብኩት ላይ መጣሬን እቀጥላለሁ።
ሀትሪክ:- በከፍተኛ ሊግ ቆይታህ ከባዱ የትኛው ነበር?
ነስረዲን:- በከፍተኛ ሊግ ከባዱ ፍልሚያዎቹ ታክቲካል አይደለም ስፔስ የላቸውም ተዘጋጅተህ የምትመጣበት ቡድን የለም ይሄኛው ቡድን እንዲህ ነው የሚጫወተው ብለህ ስትዘጋጅ ሌላ ሆኖ ይመጣል የዚህ ቡድን አጨዋወት ይሄ ነው ማለት አትችልም በፕሪሚየር ሊጉ ግን ጨዋታ ስታይ እያንዳንዱ ቡድን መገለጫ አለው ትንተና ስሰማም ይሄንን ነው የሚያረጋግጥልኝ.. ከፍተኛ ሊግ ግን ይሄ አለመኖሩ ከባድ ያደርገዋል፡፡
ሀትሪክ:- በፕሪሚየርሊጉ የመጀመርያ አመትህን እንዴት ትጠብቀዋለህ?
ነስረዲን:- የመጀመርያው አመት ፈተና ሊሆንብኝ ይችላል ፈተናውን በብቃት ለመወጣት ግን እጥራለሁ .. ከፍተኛ ሊግ ሆኜ በወዳጅነት ጨዋታ ላይ ከፕሪሚየር ሊጉ ቡድኖች ጋር ተጫውቻለሁ። ቀላል ባይሆንም ጫናው ቀለል ያለ ከከፍተኛ ሊጉ ስፔስ አልባ ጨዋታ በላይ ደግሞ ክፍተት እንዳለው ተረድቻለሁ፡፡

ሀትሪክ:- በህይወቴ ላይ ምርጥ ነገር ጨምሯል የምትለው አሰልጣኝ ማነው?
ነስረዲን:- በዚህ ደረጃ የለገጣፎውን አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙና የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ክፍሌ ቦልተናን ነው። ሁለቱንም በደንብ አመሰግናለሁ ልባቸውን ሰጥተውኝ ነው ያጫወቱኝ..ሁለቱንም አመሰግናለሁ
ሀትሪክ:- ትዳር መስርተሃልና አስቲ ባለቤትህን አስተዋውቀን የምትላት ካለ እድሉን ልስጥህ?
ነስረዲን:- አዎ ዘንድሮ አገባሁ…ባለቤቴ ዙማራ በቀለ ትባላለች ብቻውን የሆነ ኳስ ተጨዋች ችግር ሲገጥመው ሀሳቡ ወደ ሌላ ቦታ ሊሄድ ይችላል..ወደ ትዳር ስትገባ የሚያበረታህ የሚያጽናናህ ነገሮችን የምታጋራው አጋር ታገኛለህና ጉዳትህ ጉዳቷ የሚሆነው ባለቤትህ ናትና ደስ የሚል ስሜት ይኖርሃል በዚህ አጋጣሚ ስለሁሉ ነገር ባለቤቴን አመሰግናለሁ እወድሻለሁ አፈቅርሻለሁ ማለት እፈልጋለሁ..
ሀትሪክ:- የመጨረሻ ምስጋና ካለህ….?
ነስረዲን:- ቤተሰቦቼን፣ ባለቤቴን፣ ወንድሜን አመሰግናለሁ.. አሰልጣኝ ሄኖክና ኤፍሬምን አመሰግናለሁ የሰፈሬ እናቶች ጸሎትና ዱአ ነው ያቆመንና የሰፈር እናቶችንም አመሰግናለሁ..ጓደኞቼን አሰልጣኞቼን ኤጀንቴን ዞላን ያገዙኝን በሙሉ አመሰግናለሁ..
አስተያየት ይስጡ