“ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣሁት አዲስ ታሪክ የማፃፍ ትልቅ ህልምን ሰንቄ ነው” ጋቶች ፓኖም

የጋምቤላው ጥቁር ወርቅ

ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣሁት አዲስ ታሪክ የማፃፍ ትልቅ ህልምን ሰንቄ ነው”
ጋቶች ፓኖም

በእርግጥ አሁን የያዝነው የክረምት ወር ለጋምቤላው ጥቁር ወርቅ በጣም ቢዚ የሆነበት ወቅት ይመስላል፤ በትልቅ ክለብ ውስጥ ገብቶ የመጫወት ህልሙን ዳር ለማድረስ ደፋ ቀና ሲል ከርሞ በመጨረሻም ጋቶች ፓኖም አዲሱ ፈረሰኛ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

የጋምቤላ ምድር ያበቀለውና 1 ሜትር ከ9߀ የሚረዝመው ጋቶች ፓኖም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገው ዝውውር በብዙዎች ያልተጠበቀ ሲሆን የሁለቱን የሀገሪቱ ተቀናቃኝ ቡድኖች የሆኑትን የኢትዮጵያ ቡናና የቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያን በመልበስ የሌላ አዲስ ታሪክ ባለቤትም ሆኗል፡፡
በእርግጥ ቴዎድሮስ በቀለ (ቦካንዴ)፣ አሰግድ ተስፋ፣ አንተነህ ፈለቀ፣ አንተነህ አላምረው፣ ደብሮም ሐጎስ፣ አሸናፊ ግርማ፣ ሚኬኤሌ ሽፈራው፣ ሠለሞን ግርማ (ልምጭ)፣ ሳምሶን (ጆሮ)፣ ዮሴፍ ተስፋዬ፣ አወቀ አሰፋ፣ ሳምሶን ጥላሁን፣ ኤልያስ ማሞ፣ በኃይሉ ደመቀና የቅርብ ጊዜው አብዱልከሪም መሐመድ (ተርሚኔተር) የሁለቱን ባላንጣና ተቀናቃኝ ክለቦች ማልያን ለብሰው በመጫወታቸው አዲሱ ፈረሰኛ ጋቶች ፓኖም የመጀመሪያው ተጨዋች ባይሆንም ይሄ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ግን የመጨረሻው ፈራሚ ሆኖ ተወስዷል፡፡

የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስክዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የጋምባላውን ጥቁር ወርቅ ጋቶች ፓኖምን ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስላደረገው ዝውውር፣ በክለቡ ማሳካት እፈልጋለሁ ስለሚለው ህልሙ፣ ስለቤተሰቡ፣ የሁለቱን ኃያላን ክለቦች ማልያ መለያን የመልበስ እድል ስለማግኘቱ፣ የቀድሞ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ግብ የማስቆጠር እድል ቢያገኝ ደስታውን ለመግለፅ ስላሰበበት መንገድና በሌሎች ጉዳዮች ላይ አነጋግሮት ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቅርቦታል፤ እንደተለመደው ጊዜያችሁን አውሱን፡፡

ሀትሪክ፡- …ጋቶች እንዴት ነህ….? ሁሉ ሠላም ነው…?…

ጋቶች፡- …እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ሠላም ነው…?…

ሀትሪክ፡- …ክረምቱ እንዴት እያደረገህ ነው…?…

ጋቶች፡- …ክረምቱ አሁን ትንሽ ጠንከር እያለ ነው፤ግን ያው እንደ ወቅቱ እየኖርኩ ነው…(ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …እኔ የምልህ ጋቶች የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች ሆንክ በቃ…?…

ጋቶች፡- …(እንደመሣቅ እያለ)…ምነው ተጠራጠርክ እንዴ…?…የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች መሆኔን በፊርማዬ አረጋግጫለሁ…በአዲሱ የውድድር ዘመን በፈረሰኞቹ ማልያ ነው የምታየኝ…(አሁንም ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስለመጫወት ማልያውን ስለመልበስ…ግን…ቆይ…ቆይ…ጋቶች…ከዚህ ጥያቄ በፊት በግል ህይወትህ ዙሪያ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ…?…

ጋቶች፡- … ምን…?…

ሀትሪክ፡- …ከሁለት አመት በፊት ነው ትዳር የመሰረትከው..ወለድክ…?…ከበድክ…?…

ጋቶች፡- …አዎን እግዚአብሔር ይመስገን…ከባለቤቴ ኛሮት ቤታችንን የምታሞቅ የአንድ አመት ከስድስት ወር ሴት ልጅን አኝቼያለሁ…በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ….

ሀትሪክ፡- …የአንተም የባለቤትህ ኛሮት ስምም ለየት ያለ ነው…የልጃችሁንስ ማን አልከው…?…

ጋቶች፡- …ልጃችን ከነን ትባላለች….?…

ሀትሪክ፡- …ከነን…?…በጋምባሌ ነው…?…ትርጉሙ ምን ማለት ነው…?…

ጋቶች፡- … (እየሳቀ)…ከነን ማለት ትርጉሙ በእሱ ፈቃድ እንደ ማለት ነው…የልጅ አባት የሆንኩት… ለዚህ ክብር የበቃሁት በአምላክ ፍቃድ በመሆኑ የእሱን ውለታ ለማንሣትና ለማመሰገን ነው ልጃችንን “ከነን” ያልናት…

ሀትሪክ፡- …እስቲ አሁን ደግሞ ስለ አዲሱ ክለብህ ቅዱስ ጊዮርጊስ እናውራ…?…ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስለመጫወት ማልያውን ስለመልበስ ከራስህ ጋር ያወራህበትን ጊዜ ታስታውሳለህ…?…

ጋቶች፡- …እንደምታውቀው ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመጫወት ተጉዤ ነበር…ከዛ ስመለስ በውስጤ የሚመላለስ አንድ ትልቅ ሃሣብ ነበር…ከሳውዲ እንደ መጣሁ ግማሽ የውድድር አመት ከወላይታ ድቻ ጋር በመጫወት ነበር ያሳለፍኩት…እዛ እያለሁ ግን አንድ ነገር አስብ ነበር.. ትልቅ ቡድን ውስጥ ገብቼ መጫወት አለብኝ የሚል…ከታፊችን የአፍሪካ ዋንጫም ስላለ በትልቅ ቡድን ውስጥ ገብቼ ራሴን በደንብ ማሳየት ራሴን የምገልፅበት ትልቅ ታሪክና ስም ያለው ክለብ መግባት አለብኝ የሚል ነገር በውስጤ ይመላለስ ነበር…ያ ሃሣቤ አሁን ምላሽ ያገኘ ይመስለኛል…ያ ክለብም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆኖ ተገኝቷል…

ሀትሪክ፡- …በቅዱስ ጊዮርጊስ እንደምትፈለግ ወይም እንድትጫወት ማነው ቀድሞ ያናገረህ…?…

ጋቶች፡- …በወሬ ደረጃ አንዳንድ ነገሮችን እሠማ ነበር…ነገር ግን በቀጥታ ስልክ ደውሎ “ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደትጫወትለት ይፈልጋሃል” ብሎ ያናገረኝ ምክትል አሠልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ ነው…

ሀትሪክ፡- …ለቅዱስ ጊዮርጊስ መፈረም የተለየ ስሜት አለው…?…

ጋቶች፡- …ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም…በጣም የተለየ የደስታ ስሜት እንዲሠማህ ያደርጋል… ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀገራችን ውስጥ ካሉት ታላላቅ ክለቦች አንዱ ነው…ክለቡ ታሪክም ውጤት ያለው ክለብ ነው…ለዚህ ቡድን መጫወት በራሱም ትልቅ ታሪክ ነው…ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችም የተሰባሰቡበት ቡድን ነው…ይሄ ደግሞ አቅምህን አውጥተህ እንድትጫወት ያደርግሃልና…ጥሩ ስሜት በውስጥህ እንዲፈጠር ያደርጋል…

ሀትሪክ፡- …በእርግጥ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፊርማህን ካኖርክ በጣም አጭር ጊዜ ነው…በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ስለ ክለቡ ይበልጥ እንድታውቅ…እያገዘህ፣እየረዳህ ያለ ተጨዋች ማነው…?…

ጋቶች፡- …የሚገርምህ አብዛኛው የቡድኑ ተጨዋቾች ጓደኞቼ ናቸው…በቅርበት እንተዋወቃለን…እናወራለን… አሁን በተናጠል ስም መጥቀስ ባልፈልግም ከብዙዎቹ ጋር አወራ እገናኝ ነበር…አሁን ብቻ ሣይሆን በብ/ቡድን ደረጃም ስንገናኝ ስለ ክለቡ አደረጃጀት፣ስለ ህልሙና ስለ ሌሎች ጉዳዮች እናወራ ነበር…

ሀትሪክ፡-… ከሌሎች ለክለቦች ጋር አንድም ድርድር ሳትጀምር በቀጥታ የመጀመሪያ ምርጫህን ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው ያደረገው የሚል ነገር ሰምቻለሁ እውነት ነው…?…

ጋቶች፡- …አዎን እውነት ነው…!…ከየትኛውም ክለብ ጋር ንግግር አልጀመርኩም…ከሀገር ውስጥ ክለቦች ይልቅ ወደ ውጪ ወጥቼ የምጫወትበት እድል ሁሉ ነበረኝ…ነገር ግን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ወጥቶ መጫወቱን አልፈለኩም…ቢያንስ ይህን አመት በሀገሬ ትልቅ ቡድን ውስጥ ገብቼ መጫወት አለብኝ የሚል ስለነበር ስሜቴ…በአሁን ሰዓት ሊጋችንም በDSTV መታየት ጀምሯል… ጨዋታዎቻችንንም የሚከታተሉት ብዙዎች ናቸው…ቢያንስ የተሻለ ቡድን ውስጥ ገብተህ አቅምህን ማሳየት ከቻልክ ወደ ተሻለ ሊግ ሄደህ ለመጫወት እንደ በፊቱ የሚከብድ ነገር የለም…ከዛ አንፃር እዚሁ ለመጫወት ወስኜያለሁ…

ሀትሪክ፡- …ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያና ብቸኛ ምርጫህ እንዲሆን ያስገደደህ ምክንያት ምንድነው…?…

ጋቶች፡- …ብዙ ምክንያቶች አሉ…ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ትልቅ ታሪክም ውጤትም ካላቸው ክለቦች የመጀመሪያው ነው…በሀገር ውስጥም በኢንተርናሽናል ደረጃ ከፍተኛ ስም ያለው ክለብ ነው…የክለቡ አደረጃጀትም…አያያዝም ፕሮፌሽናል ክለብ መሆኑን የሚጠቀም ነው…ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በክለቡ አቅምህን አውጥተህ እንድትጫወት የሚያግዙ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቹ አሉ…እነዚህ እነዚህ ምክንያቶች ተደማምረው ነው…ክለቡን እንድመርጥ ያደረገኝ…

ሀትሪክ፡- …በሀገርውስጥኢት.ቡና፣መቐለ 70 አንደርታና ለወላይታ ድቻ ተጫውተሃል…ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጣህ በኋላ ምን የሚያስገርም (Surprise) የሚያደርግ ነገር አየህ…?…

ጋቶች፡- …እንግዲህ ገና ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ስላልገባን ስለ ክለቡ ብዙ ነገሮችን በተግባር እንዳይ አላደረገኝም…ነገር ግን በጥቂቱም ቢሆን ባየሁት ነገር በጣም ተደስቼበታለሁ…

ሀትሪክ፡- …በክለቡ የተደረገልህን አቀባበልስ እንዴት አገኘኸው…?…

ጋቶች፡- …የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አብነት ገ/መስቀል ጭምር ነው የተቀበሉን…ጊዜ ሰጥተው ሁላችንንም አነጋግረውናል…የማስታወሻ ፎቶም አብረን ተነስተናል…ደጋፊውም በተለያየ መንገድ ስሜቱን እየገለፅልኝ ነው…በዚህ ደግሞ በጣም ነው የተደሰትኩት…ለክለቡ የበለጠ እንድትሠራ የሚያነሳሳ ሆኖም አግኝቼዋለሁ…

ሀትሪክ፡- …ለክለቡ የፈረማችሁት አዳዲስ ተጨዋቾች እንዳልከው ከክለቡ የቦርድ ሊቀመንበር ጋር የመገናኘትና ፎቶ አብሮ የመነሣት አጋጣሚ ነበራችሁ…ከአንተ ጋር በግል ወይም በጋራ ያወራችሁበት አጋጣሚ ነበር…?…ከነበረስ ምን ምን ተባባላችሁ…?…

ጋቶች፡- …በግሌ የተለየ ምንም ያሉኝ ነገር የለም…በቡድኑ ዙሪያ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት በሚለውና ከእኛ ብዙ በሚጠበቅበት ዙሪያ ነው ያወራነው…ፕሬዚዳንቱ ስለክለቡና ለእግር ኳስ ያላቸውን ፍቅርም በደንብ አይቼ አረጋግጪያለሁ…

ሀትሪክ፡- …በርካቶች ጋቶች ለቅዱስ ጊዮርጊስ መፈረም ከሚገባው ጊዜ በጣም ዘግይቶ ነው የፈረመው ይሉሃል…አንተስ እንደዘገየህ ይሰማሀል…?…

ጋቶች፡- …አይሰማኝም..ምክንያቱም ለእኔ አልዘገየሁም…ሁሉም የሆነው በሠዓቱ ነው…ከዚህ በፊት ከሀገር ውጪ ነበርኩ…ወደ ሀገር ቤት የመጣሁት ሊጉ ከተጋመሰ በኋላ ነው…ሊጉ አጋማሽ ላይ መጥቼም ቀሪውን ጊዜ ያሳለፍኩት በሊጉ ለወላይታ ድቻ እየተጫወትኩ ነው ያሳለፍኩት…እንደውም በልምድም፣በችሎታም፣በእድሜም በበሰልኩበት ሰዓት ነው ለቅዱስ ጊዮርጊስ የፈረምኩት…ዘግይተሃል የሚለውን አልቀበልም የምለውም ከዚህ አንፃር ነው…

ሀትሪክ፡- …ጥያቄዬን ሸፋፍኜ ከማቀርብ ይበልጥ ግልፅ እንዲሆንልህ ጋቶች አቋሙ በወረደበት ሰዓት ነው ለቅዱስ ጊዮርጊስ የፈረመው ብለው የሚሠጉ አሉ…አንተ አቋሜ ባልወረደበት፣በጥሩ ብቃትና ጥንካሬ ላይ ባለሁበት ሰዓት ነው የፈረምኩት ትላለህ…?…

ጋቶች፡- …ከላይም ብዬሃለሁ…በሀገር ውስጥም በውጭም የተሻለ ልምድን ችሎታና እውቀትን በቀሰምኩበት…በበሰልኩበት ሰዓት ነው ለቅዱስ ጊዮርጊስ የፈረምኩት…ወደ ሊጉ የመጣሁት ግማሽ ላይ ከደረሰ በኋላ ነው…በድቻ በነበረኝ ቆይታ ያሳየሁት ብቃት ለእኔም ለብዙዎችም በጣም በቂ ነበር…አቋሜ አለመውረዱንም አሳይቼበታለሁ ብዬ አስባለሁ…ለቅዱስ ጊዮርጊስም እንድፈርም ያደረገኝ በወቅቱ ባሳየሁት ብቃት እንደሆነም እረዳለሁ…በኮሮና ምክንያት ተቀምጬ ከመምጣቴ አንፃር በአጭር ጊዜ ነው ወደ ተሻለ ብቃት የመጣሁት…አሁን ደግሞ ገና የዝግጅት ጊዜ ስላለን የበለጠ ወደ ተሻለ ነገር መምጣት ይቻላል…ከዚህ ውጪ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣሁት አቋሜ በወረደበት ሣይሆን በተሻለ ብቃት ላይ ባለሁለበት ሰዓት መሆኑን መግለፅ እወዳለሁ…

ሀትሪክ፡- …በወላይታ ድቻ ጥሩ ጊዜን አሳልፈሃል እንደ አጠቃላይ…?…

ጋቶች፡- …አጭር ቢሆንም በጣም ጥሩ የሚባል ጊዜን አሳልፌያለሁ…ቡድኑ ከፍተኛ የሆነ የመውረድ ስጋት አንዣቦበት ነበር…ነገር ግን ሁላችንም ተረባርበን በሊጉ እንዲቆይ አድርገናል…የአሰልጣኝ ዘላለም (ሞሪንሆ) እጅ ከፍተኛ ነበር ላለመውረዱ…ዘላለምም ባይኖር ወደ ድቻ ላልሄድ የምችልበት ሁኔታ ሁሉ ሊፈጠር ይችል ነበር…

ሀትሪክ፡- …የሀገሪቱን ሁለት ኃያልንና ተቀናቃኝ ቡድኖች የሆኑትን የኢት.ቡናና የቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያን ለብሶ የመጫወት እድል ማግኘትህን እንዴት ነው የምትገልፀው…?…

ጋቶች፡- …ኡው…!…በጣም የተለየ እድለኛ የሆንኩ ያህል ራሴን እንድቆጥር ነው ያደረገኝ…የብዙ የሀገራችን ተጨዋቾች ምኞት ከሁለቱ ኃያል ክለቦች የአንዱን ማልያ ለብሶ መጫወት ነው…ያም ቢሆን የአንደኛው ቢሳካልህ የአንደኛው ብዙውን ጊዜ ሲሳካልህ አይታይም…እኔ ግን በጣም እድለኛ ነኝ የሀገሪቱ ትልቁ ደርቢ ተፋላሚ የሆኑት የሁለቱም ክለቦች ማልያን ለብሶ የመጫወት እድል አግኝቼያለሁ…በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ…

ሀትሪክ፡- …አሁን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች መሆንህ ተረጋግጧል…የቀደሞ ክለብህን ኢት.ቡና በተቃራኒ ስለመግጠም ስታስብ ፍራቻ በውስጥህ ይፈጠራል…ይጨንቅሃል…?…

ጋቶች፡- …በፍፁም…ምንም አያስጨንቀኝም…የሚያስፈራኝም ነገር የለም…ኢት.ቡና ያደኩበት የታወኩበት ክለብ ነው…ከቡና ከወጣሁና ከተለያየሁ አራት አመታት ተቆጥረዋል…ኢት.ቡና እያለሁ ለክለቡ ውጤታማነት አንድም ነገር ሳልሰስት የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ…አሁን ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ንብረት ሆኛለሁ…ለውጤታማነቱ ያለኝን ሁሉ ስለመስጠት ብቻ ነው የማስበው…ከቡና ጋር ስንጫወት መጨነቅና መፍራት ሳይሆን ኳሱ የሚፈቅደውን ሁሉ ስለማድረግ ነው የማስበው…ለክለቡ ውጤታማነት የምችለው ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም…ማሸነፍ ካለብኝ ለማሸነፍ ብቻ ነው የምጫወተው…

ሀትሪክ፡- …የቀድሞ ክለብህ ላይ ግብ የማስቆጠር እድል ባገኝ ደስታዬን እንዴት እገልፃለሁ ስለሚለውስ ከወዲሁ ያስብክበት አጋጣሚ አለ…?…

ጋቶች፡- …እውነት ለመናገር ነገሮች ገና ስለሆኑ ስለዚህ አይነቱ ነገር ላይ አስቤ አላውቅም…ግን ያልከው ነገር ቢሆን እንኳን ኢትዮጵያ ቡና ያደኩበት፣የታወኩበት ክለቤ ስለነበር ለክለቡም ትልቅ ክብር ስላለኝ ብዙም የተለየ አክት ወይም የደስታ አገላለፅ ስለማሳየት በፍፁም አላስብም…ተገቢውን ክብር ሳልነፍግ ነው ደስታዬን መግለፅ የምፈልገው…እንደዚህ አይነቱ አጋጣሚ ከዚህ በፊት መቐለ 7߀ አንደርታም እያለሁ ገጥሞኝ ግብ አስቆጥሬ ደስታዬን በተለየ መንገድ አልገለፅኩም…አልጨፈርኩም… በዚህም ለቀድሞ ክለቤ ያለኝን ክብር ለማሳየት ሞክሬያለሁ…

ሀትሪክ፡- …ሉዊስ ፊጎ ከባርሴሎና ወደ ሪያል ማድሪድ ሲዛዋወር ባርሴሎናዎች “ከሃዲ፣ይሁዳ” በማለት የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመወርወር በየጨዋታው ሲቃወሙት የታየበት ጊዜ አለ…ጋቶችስ ይሄ ነገር በእኔ ላይ ይመጣል ብሎ ይሰጋል…?…

ጋቶች፡- …(እየሳቀ)…በፍፁም አልሰጋም…!…ከኢት.ቡና ብወጣም ህይወት መቀጠል አለበት…የተሻለ ነገር አልሜ መጫወት ስላለብኝ ነው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣሁት እንጂ የከዳሁትም የተከዳም የለም…በእርግጥ ለመቐለ 70 አንደርታ ስጫወት ሁሉም ባይባልም በጣም ጥቂት የሚባሉ ደጋፊዎች የመቃወም ነገር አሳይተውኝ ነበር…ተቃውሞም ደርሶብኝ ነበር…እኔ ግን ለደጋፊዎቹ ክብር ስላለኝ በወቅቱ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠሁም…አሁንም የቡና ደጋፊዎች በእንደዚህ አይነት የወረደ ተግባር ላይ ስለማይገኙ የምሰጋው ነገር የለም…ህይወት መቀጠል ስላለበት ያደረኩት ነገር እንደሆነ ስለሚገባቸው እንዲሁም የእግር ኳሱ አንደኛው ባህሪ እንደሆነ ይረዳሉ ብዬ ስለማስብ የሚያሰጋኝ ነገር የለም…

ሀትሪክ፡- …ከሀገር ውጪ የመጫወት እድል አግኝተህ በሄድክበት ጊዜ ኢት.ቡና ቤቴ ነው ስመለስ ለሌላ ክለብ ሣይሆን ለቡና ነው የምጫወተው ብለህ ቃልህን አልጠበክም ብለው የሚወቅሱህ አሉ…ወቀሳውን ትቀበላለህ…?…

ጋቶች፡- …በፍፁም አልቀበለውም…ምክንያቱም ከውጪ እንደመጣሁ ወደ ሌላ ክለብ ከመሄዴ በፊት በቃሌ መሠረት ለቡና ለመጫወት ነበር የመጣሁት…ከሌሎች ክለቦች በፊት ድርድርም የጀመርኩት ከቡና ጋር ነበር…በቃሌ መሠረት ቅድሚያ ሰጥቼ ከእነሱ ጋር አውርቻለሁ ግን መስማማት አልቻልንም…የሚገርምህ ነገር እንደመጣሁ ልምምድም ስሰራ የነበረው ከእነሱ ጋር ነው…ግን እንዳልኩህ መስማማት አልቻልንም…በወቅቱ ቅድሚያ ለእናንተ ነው የምሰጠው እንዳልኩትምሰጥቻለሁ…ግን አልሆነም…

ሀትሪክ፡- …ከቀድሞ ክለብህ ጋር መስማማት ያልቻላችሁት የማይጠየቅ ከፍተኛ ገንዘብ ጠይቀህ ነው በሚል…በገንዘብ ምክንያት ከክለቡ እንደተለያየህ የሚገልፁ ነገሮች በወቅቱ ይሰሙ ነበር…እውነት ከቡና ጋር ያጣላህ ገንዘብ ነው…?…

ጋቶች፡- …በፍፁም አይደለም…እኔ ከኢት.ቡና ጋር በገንዘብ ምክንያት እንደተጣላን ተደርጎ ሲናፈስ ነበር…ሲጀመር እኔ ክለቡን የተጋነነ ከፍተኛ ገንዘብም አልጠየኩም…የሚገርምህ ከውጪ እንደመጣሁ ለክለቡ ለመጫወት ካለኝ ፍላጎት የተነሣ ገና ሣንስማማና ሳልፈርም አብሬያቸው ልምምድ ሁሉ እሠራ ነበር…ተጫዋች የተሻለ ብቃት ላይ ባለበት…ተፈላጊ በሆነበት ሰዓት ተጠቃሚ መሆን አለበት…በዚህ ሁሉም የሚስማማ ይመስለኛል…እኔም ከዚህ መነሻነት ተጠቃሚ የምሆንበትን ያልተጋነነ ጥያቄ እንደማንኛውም ተጫዋች ጠይቄያለሁ…ግን ገና ከክለቡ ጋር እየተደራደርን ሳለ ድርድራችንም በሁለታችንም መሀል ሊቀር ሲገባ ጋቶች የተጋነነ ገንዘብ ጠየቀ ተብሎ ሚዲያ ላይ ወጣ…ይሄ ተገቢ አይመስለኝም…እንደ ተጨዋች ይገባኛል የምለውን ጠየኩ…ክለቡ ከቻለ እሺ ይላል ካልቻለ አልችልም መሆን ያለበት መልሱ…ግን እኛ ገና እየተነጋገርን እያለ ወሬው በሚዲያ ተናፈሰ…በዚህ ደስተኛ አልነበርኩም…እውነታው ይሄ ነው እንጂ በገንዘብ ምክንያት ብቻ አልተለያየንም…

ሀትሪክ፡- …የኢት.ቡና ቆይታህን እንዴት ነው የምታስታውሰው…?…

ጋቶች፡- …በኢትዮጵያ ቡና በጣም ጥሩ የሚባል ሁሌም በመልካምነት የማነሣው ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለሁ…ኢት.ቡና በእኔ የእግር ኳስ ህይወት ለእኔ እዚህ መድረስ እጁ በትልቁ አለበት…ኢት.ቡና ያሳደገኝ ባለውለተኛ ክለቤም ነው…

ሀትሪክ፡- …ደጋፊውንስ እንዴት ነው የምታስታውሰው…?…

ጋቶች፡- …የኢት.ቡና ደጋፊ በጣም ምርጥ ደጋፊ ነው…አበረታቶውኛል…አወድሰውኛል…ዘምረውልኛል…ለነበረን ጊዜ በጣም ነው የማመሰግናቸው… የተዘመረልኝ የተሻለ ለማድረግ ስለጣርኩ ነው…ሁሉም በመልካምነታቸው የማነሳቸው ደጋፊዎች ናቸው…

ሀትሪክ፡- …አሁን ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ መጥተሃል…ያኔ በተቃራኒ ስለምታውቃቸው የአዲሱ ክለብህን ደጋፊዎችስ እንዴት ነው የምትገልፃቸው…?…

ጋቶች፡- …ኢት.ቡናም ሆነ በሌሎችም ክለቦች እያለሁ በተቃራኒ ስንገጥማቸው በደንብ ነው የማውቃቸው…ቡድናቸውን ብቻ የሚያበረታቱ ምርጥ ደጋፊዎች ናቸው…በተቃራኒ ስገጥማቸው እንኳን በግሌ በደጋፊው የደረሰብኝ ነገር የለም…በፊትም አሁንም ለእነሱ ትልቅ ክብር አለኝ…

ሀትሪክ፡- …ለደጋፊው ከወዲሁ ምን ቃል ትገባለህ…?…

ጋቶች፡- …ደጋፊው ውጤት የለመደ ነው…ባለፉት 4 አመታት ግን የለመደውን ውጤትና ድል አላገኘም…በዚህም በጣም መከፋታቸውን አውቃለሁ…ከቡድን ጓደኞቼ ጋር ሆነን ወደ ቀድሞ ታሪካቸው የመመለስ…ቡድኑ የሚመጥነውን ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እንደማደርግ ነው ቃል የምገባው…

ሀትሪክ፡- …ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ካነሳ አራት አመታትን አስቆጥሯል…ይሄ ደካማ የውጤት ታሪክ በአንተ የተጫዋችነት ዘመን የሚያበቃ ይመስልሃል…?…

ጋቶች፡- …ወደዚህ ክለብ የመጣሁት በክለቡ አዲስ ታሪክ የማፃፍ ህልምን ይዤ ነው…ክለቡም ከሌሎች ተጨዋቾች ጋር ሲያስፈርመኝ ከዚህን መሰሉ ህልሙ ጋር እንድናገኘው በማሰብ ነው…ሁሉንም የሚያውቀው የሚያሳካው ፈጣሪ ቢሆንም…ምኞቴም አላማዬም ይሄንን ታሪክ መቀየር ነው…ክለቡም ደጋፊውም ከአራት አመት በላይ ዋንጫ መጠበቅ የለበትም የሚል የጠነከረ እምነት አለኝ…በጤና ያቆየንና ሁሉንም በሊጉ መጨረሻ ላይ የምናየው ይሆናል….

ሀትሪክ፡- …ባላነሳው በጣም የሚቆጨኝን አንድ ጥያቄ ልጠይቅህም የጋቶች የጨዋታ ስታይል ከቅ.ጊዮርጊስ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው…በቅዱስ ጊዮርጊስ አልቸገርም ትላለህ…?…

ጋቶች፡- …በፍፁም የምቸገርበት ሁኔታ የለም…በዚህ በኩልም እቸገራለሁ ብዬ አላስብም…በጊዜ ሂደት ከቡድኑ ተጨዋቾችና አጨዋወት…ከክለቡ ባህል ጋር እየተላመድኩ…እየተግባባሁ ስሄድ ደግሞ ነገሮች በጣም የቀለሉ ይሆናሉና በዚህ በኩል ስጋቱ የለኝም…

ሀትሪክ፡- …ጥያቄዎቼን በሙሉ ጨረስኩ…ከመለያየታችን በፊት ግን የብ/ቡድን ማልያን ከለበስክ ቆየህ ብዬ ብጠይቅህና ብትመልስልኝ በጣም ደስ ይለኛል…?…

ጋቶች፡- …ያን ያህል ብዙም የራኩ አይመስለኝም…ወደ ውጪ ከወጣሁ…ኮሮና ከገባ በኋላ ነው ከብ/ቡድኑ የራኩት…ወደ ሶስት የሚሆኑ ጨዋታዎች ናቸው ያመለጡኝ…ሀገር ውስጥ ለመጫወት የወሰንኩት የዋልያዎቹን ማልያ ለብሼ ሀገሬን የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ስላለኝ ነው…ቅዱስ ጊዮርጊስም የገባሁት ለዛ ነው…አትጠራጠር በድጋሚ በዋልያዎቹ ማልያ እታያለሁ፡፡

 

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.