ሩቅ አላሚው አሰልጣኝ “አሁን ወደምገኝበት ሙያ የመጣሁት በአቋራጭ ሳይሆን ብዙ ዋጋ ከፍዬ ነው” ፋሲል ተካልኝ (አዳማ ከተማ)

ሩቅ አላሚው አሰልጣኝ
“አሁን ወደምገኝበት ሙያ የመጣሁት በአቋራጭ ሳይሆን ብዙ ዋጋ ከፍዬ ነው”
ፋሲል ተካልኝ (አዳማ ከተማ)

የዛሬ እንግዳዬ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን አስጨንቄዋለሁ፤ ኮስተር ኮስተር ያሉ ጥያቄዎችን ብወረውርበትም ለመመለስ ብዙም አልተቸገረም፤ እንደውም ቃለ-ምልልሳችንን ከጨረስን በኋላ ስለነበረን ቆይታና ስላነሳኋቸው ጥያቄዎች ሳነሳበት “ያልተለመዱ ነገሮች ቢመስሉም እኔን ብዙም አልጎረበጠኝም” በማለት አለመገረሙን ገልፆልኛል፡፡

የቀድሞው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የባህር ዳር ከነማ የአሁኑ የአዳማ ከተማ ዋና አሰልጣኝ የሆነው ፋሲል ተካልኝ ግራጫ የሆነ ቲ-ሸርት፣ ነጣ ባለ ጅንስና ከቲ-ሸርቱ ጋር ለመቀራረብ የሚሞክር ፍላት ጫማ አድርጎ በተለምዶ ሰባ ደረጃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ኢንሀስ ሕንፃ 4ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኩዮቲቭ ኤዲተር ቢሮ ውስጥ ያደረግንለትን ጥሪና የጋዜጣችንን አንባቢዎች አክብሮ ተገኝቷል፡፡

ፍፁም ትሁት፣ ቀናና ትልቅ ሕልም በውስጡ ሰንቆ ወደ እግር ኳሱ ከፍታ እየተንደረደረ ያለው ወጣቱ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጥሪያችንን አክብሮ በሀትሪክ ዝግጅት ክፍል ቢሮ መገኘቱ ቢያስከብረውም በሚነሳለት ጥያቄ በኩል ግን ርህራሄ አልተደረገለትም፡፡

የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዮቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ አንዳችም ሳይራራ ፋሲልን ኮስተር ባሉ ጥያቄዎች ወጥሮ ይዞት የሰጠውን መልስ ለተከበሩ አንባቢዎቻችን በሚመች መልኩ አጠናክሮ አቅርቦታል፤ አብሮነታችሁን አውሱን፤ የተለመደው የአክብሮት ግብዣችን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ፋሲሎ አንባቢዎቻችንንም ጋዜጣችንንም አክብረህ ወደ ሀትሪክ ቢሮ እንኳን ደህና መጣህ…?

ፋሲል፡- …እንኳን ደህና ቆያችሁኝ…እንግዳ አድርጋችሁ ቢሮአችሁ ስለጋበዛችሁኝ በጣም ደስ ብሎኛል…በጣም አመሰግናለሁ…

ሀትሪክ፡- …ቢሮአችንን እንዴት አገኘኸው ብልህ ለእኔ ሳታዳላ ትመልስልኛለህ…?…

ፋሲል፡- …(በጣም ሣቅ)…እውነት ለመናገር ከጠበኩት በላይ ነው…በጣም ጥሩ ተደራጅታችኋል…የፀሐፊዎቹም የአንተም ቢሮ ትክክለኛ የጋዜጠኞች ቢሮ እንደሆነ በራሱ ይናገራል…በእጭሩ በጣም አሪፍ ቢሮ አላችሁ…

ሀትሪክ፡- …ለአስተያየትህ በጣም እናመሰግናለን…ፋሲሌ ዛሬ ከአንተ ጋር የሚኖረኝ ቆይታ ኮስተር ባሉ ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ነው…ለመመለስ ተዘጋጅተሃል…?…

ፋሲል፡- …አመጣጤ ለምትጠይቀኝ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ስለሆነ ኮስተር ያለም ይሁን ሌላ…የፈለከውን ጠይቀኝ…ችግር የለብኝም…

ሀትሪክ፡- …አሁን አሁን አሰልጣኞች…“ለሙያው ከመስራት ይልቅ…ለጤፍ መስራትን አስቀድመዋል“ በሚል ትታማላችሁ…?…ትቀበለዋለህ..?…

ፋሲል፡- …እንደዚህ ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ ከባድ ነው…እኔ እንደዚህ ነኝ ሌሎች ደግሞ እንደዚህ ናቸው ማለትም እንደዚሁ ከባድ ነው…አሰልጣኞች ለስልጠናው ለሙያው ዋጋ ሳይከፍሉ፣ስልጠናውን ሳይወዱ ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል ብዬ አላምንም…ምንም ጥያቄ የለውም የአሰልጣኝነት ህይወት እንደ ሌላው ሙያም ሥራ ነው፣ ህይወት ነው…በሙያው በምታገኘው ነገር ህይወትህን ትመራበታለህ፣ቤተሰብህንም ታስተዳድርበታለህ…

ሀትሪክ፡- …ይሄንን ማንም የሚያውቀው ነው…አንተ ራስህን በድፍረት ልጠይቅህ ለጤፍ ስትል ብቻ ነው የምትሰራው…?…

ፋሲል፡- …የእኔን የግሌን አስተያየት ከሆነ የምትጠይቀኝ እንድዋሽህ አታድርገኝ ለሁለቱም ነው የምንሰራው…አንተ ባቀለልከው ደረጃ ለጤፍ ነው ባልልም ህይወትን ለመምራትና ቤተሰብን ለማስተዳደር እንዲሁም ባለኝ እውቀት ህይወትን ለመምራትና ቤተሰብን ለማስተዳደር እንዲሁም ባለኝ እውቀት የሀገሬን እግር ኳስ ለማገዝ ነው የምሠራው…ከዚህ አንፃር ለሁለቱም የሚለው ያስማማናል…ይሄንን ስልህ ግን አጠቃቀምክ ወይም አስተሳሰብህ ይወስነዋል…ለጤፍ ብለህ ሙያህን የምትረግጥ አሳልፈህ የምትሰጥ ከሆነ ይሄ በጣም አደጋ አለው…ግን ሙያውን በታማኝነት የምታገለግል ከሆነ የጤፍ ነገር በራሱ ጊዜ ይመጣል…እኔ በዚህ ሙያ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ…ዝም ብዬ በአቋራጭ መጥቼ አሰልጣኝ አልሆንኩም…ከት/ቤት ከወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እግር ኳስ ውስጥ ነኝ…ለአራት አመታት ወጣት ቡድንን ከማሰልጠን ተነስቼ በሂደት (Process) ወደምፈልገው ደረጃ እየመጣሁ ነው ብዬ አስባለሁ…በተጫዋችነት፣በአሰልጣኝነት ብዙ ሂደቶችን አሳልፌያለሁ…ራሴንም በእውቀት ለማስታጠቅ ብዙ ዋጋዎችን ከፍያለሁ…ይሄንን ሁሉ ያደረኩት ወይም ስልጠናና እግር ኳስ ውስጥ ያለሁት ገንዘብ ስለማገኝ ብቻ ነው ብዬ አላስብም…ለሙያው ስልም ነው…ሙያዬን አክብሬ ከሠራሁ የጤፍ ነገር ይከተላል…በማገኘው ገንዘብ ህይወቴን እመራለሁ ቤተሰቤንም አስተዳድራለሁ…

ሀትሪክ፡- …ብዙ አሰልጣኞች የጤፍ ነገር አሳስቧቸው ሙያቸውን ሙያተኛ ባልሆኑ ሰዎች እንዲጣስ ሲፈቅዱ ይታያል…በዚህ በኩል የፋሲል አቋም ምንድነው…?…ሙያው ሙያተኛ ባልሆኑ ሰዎች እንዲጣስ ይፈቅዳል…?…

ፋሲል፡- …በፍፁምም አልፈቅድም…እስካሁን ባለው ሁኔታ የራሴን ኃላፊነት ጠንቅቄ የምረዳ አሰልጣኝ ነኝ ብዬ ነው የሚስበው…ይሄንን እምነቴን ለማንም ሸራርፌ አልሰጥም…እንዲጣስም አልፈቀድም…የማይገባኝ ቦታ አልገባም… የእኔ ያልሆነ ቦታ አልደርሰም፤ሰዎችም የእነሱ ባልሆነ ነገር እንዲደርሱብኝም አልፈቀድም…በዚህ መንገድ ነው ስጓዝ የነበረው…ወደፊትም ይሄንኑ አቋሜን አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብዬ አስባለሁ…

ሀትሪክ፡- …እግር ኳሱ አካባቢ መሞዳሞድ የተለመደ ነው ይሄንንስ ታውቃለህ…?…በሚሞዳሞዱ አመራሮች ወይም ተጫዋቾች ተፈትነሃል…?…

ፋሲል፡- …በዚህ ዙሪያ ምንም የማውቀው ነገር የለም…የተሞዳሞድኩትም፣የሚሞዳሞደኝ ሰውም እስከአሁን አላጋጠመኝም…

ሀትሪክ፡- …የሚሞዳሞድህ የክለብ አመራር ወይም ተጫዋች ቢመጣ እንዴት ነው የምታስተናግደው ብልህ የልብህን ትነግረኛለህ…?…

ፋሲል፡- …አንድ የጠነከረ አቋም አለኝ…እኔ በሁሉም ነገር የራሴ የሆነ ልክ አለኝ…በልኬ ነው መንቀሳቀስ የምፈልገው…ሙያው የሚፈቀደውን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ…ከሙያው ውጪ የሚደረጉትን ነገሮች ለመቀበል ፍቃደኛ አይደለሁም…ይሄንን ጥሶ የሚመጣ ካለ መጀመሪያ መሳሳቱንና እሱ ባሰበው ደረጃ ላይ እንዳልሆንኩ ለማስረዳት እሞክለራለሁ… ይሄንን ሁሉ አድርጌ የማይለወጥ ከሆነ አልታገሰውም…የእኔንም ስብዕና የሚነካ እግር ኳሱን የሚጎዳ ተግባር ላይ አለመሆኔን ማሳየት ብቻ ሣይሆን ከቦታው ዞር እስከማለት መስዋዕት እስከመክፈል ሁሉ ልደርስ እችላለሁ…

ሀትሪክ፡- …አሁን አሁን አሰልጣኞች ክለብ ለመያዝ የሚሄዱበት የተለየ መንገድ አላቸው ይባላል…ፋሲል ክለብ የሚይዝበት የራሱ የሆነ የተለየ መንገድ አለው…?…

ፋሲል፡- …የምን የተለየ መንገድ…?…እኔ የራሴ የተለየ የምለው መንገድ የለኝም…ባህር ዳርም የገባሁት አንተ የተለየ ባልከው መንገድ ሣይሆን በቀጥተኛው መንገድ ነው…ባህር ዳሮች ፈልገውኝ ነው የገባሁት…ባህርዳር ለመግባት የተለየ መንገድ አላስፈለገኝም… አሁን አዳማም ስገባ እንደዛ ነው… “አንተ አብረኸን እንድትሠራ መርጠንሃል፤ከእኛ ጋር መስራት ትፈልጋለህ ወይ?” …ተብዬ ነው የገባሁት…ክለብም ለመግባት በተለየ መንገድ አልሄድኩም…የተለየ የሚባለው መንገድ ራሱ የት ነው ያለው? የት እንዳለም አላውቅም…የሚገርምህ እኔ እንደውም ራሴን በማስተዋወቅና ሌላ መንገድ በመጠቀም በኩል በጣም ደካማ ነኝ…ራሴን ማስተዋወቅ ግንኙነት መፍጠር ላይ ደካማ እንደሆንኩ ብዙዎች ይነግሩኛል…ከደካማ ጎኖች አንዱ እንደሆነ የማስበውም ይሄንኑ ነው…

ሀትሪክ፡- …ብዙዎች በኔትወርክ ክለብ ይይዛሉ…ውጤት ባይኖራቸው ኔትወርክ ካላቸው ከክለብ ክለብ ለመገለባበጥ ችግር የለባቸውም… ፋሲልም ኔትወርክ አላቸው ተብለው ከሚታሙት አንዱ ነው ይሉሃል…ምን ትላለህ… ?…

ፋሲል፡- …እዚህ ጋር ኔትወርክን (ግንኙነትን) በተመለከተ መደበላለቅ እንዳይኖር ስለምሰጋ መለየት ቢኖር ደስ ይለኛል…ኔትወርክ (ግንኙነት) መፍጠር ጤነኛ በሆነ መልኩ የምትጠቀምበት ከሆነ ጉዳት አለው ብዬ አላስብም…አደጋው በሙያው ለመጠቀም ሌላውን ሙያተኛና እግር ኳሱን በሚጎዳ መልኩ የምትጠቀምበት ከሆነ ነው…ይሄን አይነቱን ኔትወርክ አልደግፈውም ብቻ ሳይሆን በጣምም ነው የምጠየፈው…ኔትወርክ (ግንኙነት) በትክክለኛው መንገድ እስከሆነ ድረስ ሁሉም ቢኖረው ክፋት የለውም…ኔትወርክ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት ከዋለ ነው ችግሩ…የውጪም አሰልጣኞች እኮ በዋናነት የሚሠሩት በኔትወርክና በማናጀሮቻቸው ነው…ያለ ኔትወርክ ነገሮችን ብቻህን ለማሳካት ከባድ ይመስለኛል…

ሀትሪክ፡- …ከውጤት ይልቅ ገንዘብ የሚሰጡ አሰልጣኞች በክለብ አመራሮች የመጀመሪያ ተመራጭ እንደሆኑ ፀሐይ የሞቀው አደባባይ የወጣ ነገር ነው…ስለዚህ ነገርም ሰምቼ አላውቅም ልትል ነው…?…

ፋሲል፡- … (ሣቅ)…አላውቅም የሚል ቃል አልወጣኝም…እኔም እንደማንኛውም ሰው በወሬ ደረጃ ሲባል እሰማለሁ… ግን በጣም የማዝነው በወሬ ደረጃ ከመነጋገር በዘለለ በተጨባጭ የቀረበ ነገር እስከአሁን አለመታየቱ ነው… ከውጤትና ከስራህ ይልቅ በገንዘብ የሚደረግ ነገርን ትክክለኛ ነገር እንዳልሆነ ነው ውስጤ የሚያምነው…እንደዚህ አይነት አሰራርንም እቃወማለሁ በግሌ…አንድ አሰልጣኝ ክለብ ለመያዝ…ተጨዋች ክለብ ለመግባት መመዘኛው የሚሰጠው ገንዘብ መሆን አለበት ብዬም አላምንም…ክለብ ለመቀጠር በሠራው ልክና በሜሪቱ (በእውቀቱ) መሆን አለበት ባይ ነኝ…ማንኛውም ሰው በሠራው ባለው ልክ ነው ማግኘት ያለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ…

ሀትሪክ፡- …አሁን አሁን በጣም በሚገርምህ ሁኔታ የኮሚቴ አመራሮች አሰራራቸውን አሻሽለዋል…እነዚህ ለኪሳቸው እንጂ ለእግር ኳሱ ደንታ የሌላቸው የክለብ አመራሮች…አንድን አሰልጣኝ ለመቅጠር እንደ በፊቱ “ይሄን ያህል ብር ታመጣለህ…?…“የሚለው የሌብነት አሰራራቸው ተቀይሮ…“በዚህን ያህል ሚሊዮን ብር እናስፈርምሃለን ስንት ብር ቀድመህ በአካውንታችን ታስገባለህ…?…“የሚል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ጀምረዋል የሚባል ነገር ሰምቼ ደንግጫለሁ…በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ…?…

ፋሲል፡- …(በጣም የግርምት ሳቅ እየሳቀ)…እንደዚህ ማለት ምን ማለት ነው…?…

ሀትሪክ፡- …አንድን አሰልጣኝ አንድ ክለብ ከማስፈረሙ በፊት ለአሰልጣኙ…“2 ሚሊዮን ብር የፊርማ እናሰጥሃለን፤ ግን በቅድሚያ 500 ሺ ብር አካውንታችን ውስጥ አስገባልን…“…በማለት በሚያሳፍር መልኩ ቅድሚያ ክፍያ መጠየቅ ጀምረዋል…ይሄንን እሺ ብለው የሚፈፅሙ አቅም የፈጠሩ ሌቦች አሰልጣኞችም አሉ ይባላል…አሁንስ ገባህ…?….

ፋሲል፡- …(አሁንም ሳቅ)…መግባትማ አሁን በደንብ ገብቶኛል…ይሄ የምትነግረኝ ነገር ለእኔ አዲስ ነገር ነው… (በድጋሚ ሣቅ)…ነገሮች እዚህ መድረሳቸውን አላውቅም…ግን ምንድነው መሰለህ እግር ኳሱ ውስጥ ማስረጃ የሌላቸው መረጃዎች ይበዛሉ…በእግር ኳሱ ዙሪያ የማይባል ነገር የለም…አሁን ደግሞ እንደዚህ አይነት ነገር መጣ እያልከኝ ነው…እውነትም ተደርጎ ከሆነ ይሄ የሚያስደነግጥ ነው…ግን እንደዚህ አይነት ወሬ በማስረጃ ቢደገፍ በጣም ጥሩ ነው…ምክንያቱም ማስረጃ የሌላቸው ያልተረጋገጡ ወሬዎች የሚጎዱት እግር ኳሱን ነውና…እኔ ወደ ሙሉ ዋና አሰልጣኝነት ከመጣሁ ገና ሶስት አመቴ ነው…ከእኔ በላይ በሙያው የቆዩ ትላልቅ አሰልጣኞች አሉ…እነሱንም መቀላቀል እንዳይሆን እሰጋለሁ…ማስረጃ ካለ ማቅረብ ለሁሉም ይጠቅማል…ማስረጃ በሌለበት ማውራት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም…ማስረጃ ካለ ይሄንን ያደረጉትን ማጋለጥና በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ይቻላል፡፡

ሀትሪክ፡- …ከኤጀንቶች ጋር ያለህ ግንኙነት እንዴት ነው…?…

ፋሲል፡- …እግር ኳሳዊ ግንኙነት ነው ያለኝ…የተለየ ግንኙነት እንደሌለኝ ነው የማውቀው…የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኤጀንቶች ከተጨዋቾች ጋር ሆነው እንዲያስፈርሙ ፈቃድ ሰጥቶአቸዋል…ኤጀንቶች እኔ የምፈልጋቸውን ተጨዋቾች ካመጡ ግንኙነት ይኖረናል…

ሀትሪክ፡- …ይሄንን ጥያቄ ያነሳውልህ ያለ ምክንያት አይደለም…አሰልጣኞችም ከኤጀንቶቼ ጋር አብረው ይሸቅላሉ የተለየ የጥቅም ግንኙነት አላቸው በሚል ትታማላችሁ…የሚፈልጉትን ተጨዋቾች እከሌ በሚባል ኤጀንት በኩል ጨርስ እያሉ የሚልኩና በዛ በኩል ሲመጣ የማስፈረም ካልመጣ ያለማስፈረም ነገር አለ ይባላል…ፋሲል እዚህ ውስጥ አለ ብዬ ብጠይቅህ እንደ ድፍረት ታይብኝ ይሆን…?…

ፋሲል፡-…በዚህ ጉዳይ እኔ ስለሌለሁበት የማውቀው ነገር የለም…አብሬ ሸቅዬም አሸቅዬም አላውቅም…

ሀትሪክ፡- …ከደሙ ንፁህ ነኝ እያልክ ነው…?….

ፋሲል፡- …አዎን በደንብ ነኝ…!…

ሀትሪክ፡- …በባህር ዳር ከነማ ቀሪ አንድ አመት እያለህ መልቀቅህ በሠራኸው ስራ ደስተኞች ስላልሆኑ ነው የለቀከው ብሎ መደምደም ይቻላል…?…

ፋሲል፡- …ወደዚህ ድምዳሜ ከመምጣትህ በፊት እነሱን ብጠይቃቸው የተሻለ መልስ ታገኛለህ…

ሀትሪክ፡-… የአንተን ምላሽ ነው ማወቅ የፈለኩት…?…

ፋሲል፡- …መጀመሪያ እኔ ለባህር ዳር የፈረምኩት ለአንድ አመት ነው…ከአንድ አመት በኋላ ግን በነበረው ነገር ደስተኛ ስለሆኑ ኮንትራቱ ለሁለት አመት ሊራዘም ችሏል…እንደውም እነሱ የሶስት አመት እንድፈርም ነበር የፈለጉት… እኔ ነኝ ሁለት አመት በቂ ነው ብዬ የፈረምኩት እንጂ ፍላጎታቸው ለሶስት አመት ነበር… ይሄ የሚነግርህ ነገር አለ..ደስተኛ ባይሆኑ ኮንትራቴ አይራዘምም ነበር…
ሀትሪክ፡-…ታዲያ በኋላ ላይ ምን ተፈጥሮ ቀሪ አንድ አመት እያለህ ልትለያዩ ቻላችሁ….?…

ፋሲል፡- …በጣም የሚገርምህ ወደ መለያየት ውሣኔ ከመምጣታችን በፊት እኔም ክለቡም በጉዳዩ ዙሪያ ቁጭ ብለን አውርተናል…እነሱ ናቸው የመለያየት ጥያቄውን ያመጡት…ለዚህም እንደ ምክንያት የተቀመጠው የእኔ የብቃት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ሣይሆን ክለቡ በሊጉ የመጨረሻው ሣምንታት ባሳየው አቋም ደስተኞች አለመሆናቸው ነው… ደጋፊውም፣ኮሚቴውም ከነበረው የበለጠ የተሻለ ነገር ይፈልጉ ነበር…በዚህ ጉዳይ ላይ ረዡም ጊዜ ተወያይተንበታል…የመለያየት ጥያቄው ከእነሱ መጣ…ጥያቄያቸውን መቀበል ነበረብኝ…አክብሬ ተቀብዬ መልካም ነገር ተመኝቼ ተለያይተናል…

ሀትሪክ፡- …መለያየታችሁ የተሰማው በመጨረሻው ሰዓት ነው…ቀሪ ኮንትራት እያለህ ሳትዘጋጅበት ስትለያዩ በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ተፈጠረ…?…

ፋሲል፡-… በባህርዳር ላሳካቸው የምፈልጋቸው ብዙ ህልሞች ነበሩኝ…ቡደኑን በጊዜ ሂደት እየገነባሁ እየመጣሁ እንደነበር አስባለሁ…ያለፈውን አመት ውድድር ገምግመናል…ለቀጣይ የውደድር አመትም ሪፖርት አቅርቤያለሁ… ከዚያ በኋላ ነው ሃሣቦች የተቀየሩት… ይሄ በእግር ኳስ ይኖራል…ከተፈጠረው ነገር ይልቅ በባህር ዳር በነበረኝ የሁለት አመት ቆይታ ያገኘሁትን ነገር ነው ማየት የምፈልገው…እንዳልኩህ በሊጉ መጨረሻ ላይ የቡድኑ ውጤት እየወረደ መጥቷል…ውስጣዊም ውጫዊም ችግሮች ውጤትን ዝቅ ያደረጋሉ…እኔ በባህሪዬ ውጪያዊ ችግሮችን ብዙ ማየት አልፈልግም…በሜዳ ላይ ምንድነው የተሳሳትኩት…?… የሚለውን ነው ማየት የምፈልገው…በመጨረሻ ጨዋታዎች ላይ ለምን አላሸነፍንም…?…የሚለውን እማርበታለሁ…ደግሞም ተምሬበታለሁ…ሜዳ ላይ ለተፈጠረው መጥፎም ይሁን ጥሩ ነገር ኃላፊነቱን የምወስደው እኔ ነኝ …

ሀትሪክ፡- …አንተን ተክቶ ባህር ዳር የገባው…በብ/ቡድን አብሮህ የሠራው ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ነው… በባህር ዳር ምን ይገጥመዋል ትላለህ…?…ባህር ዳሮችስ ትክክለኛውን ሰውስ አግኝተዋል…?…

ፋሲል፡- …በእግር ኳስ አስቀድሞ ይሄ ይገጥማል…ወይም አይገጥመውም…ብሎ መገመት አይቻልም…የተለመደም አይደለም… ከዚህ አንፃር እንደዚህ ነው ማለት ይቸግረኛል…ይሄን ብልህም…ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የተሻለ ደረጃና የተሻለ የሥራ ልምድ ያለው ለቦታው ተገቢው ሰው እንደሆነ ግን…መናገር አይከብደኝም…

ሀትሪክ፡- …ከባህር ዳር ስትለቅ…አዳማ ስትገባም ነገሮች ድንገተኛ ነበሩ…አዳማን የማሰልጠን እቅዱ ነበረህ…?…

ፋሲል፡- …ከባህር ዳር ጋር መለያየቴ ከተሠማ በኋላ ከበርካታ ክለቦች ጥያቄዎች ይቀርቡልኝ ነበር…ፍላጎቶች በብዛት ነበሩ…ጥያቄውን በትክክለኛው መንገድና ሰዓት ገፍቶ ያቀረበው አዳማ ስለነበር…ጥያቄያቸውን ደስ ብሎኝ ተቀብያለሁ…ከዚህ በፊት አዳማን የማሰልጠን እድሉ ባይኖረኝም….ስጫወትም ሳሰለጥንም የማየትና በተቃራኒው የመግጠም እድሉ ነበረኝ…አዳማዎችን የማውቃቸውን ያህለ አውቃቸዋለሁ…ኃላፊቱን ስረከብም ከዚህ መነሻነት ነው…ምናልባት ባለፈው አመት ከነበረው የአቋምና የውጤት መዋዥቅ ውጪ…አዳማ በሊጉ ከነበሩ ጠንካራ ቡድኖች አንዱ እንደነበር ሁሉም የሚያውቀው ነው…ናዝሬትን በተጫዋችነት፣በአሰልጣኝነት፣በብ/ቡድን ተጨዋችነትም ጭምር በደንብ የማየትና የመታዘብ እድሉ ነበረኝ…የአዳማ ነዋሪ ለእግር ኳስ ከፍተኛ ስሜት ያለው… ምርጥ የሆኑ ደጋፊዎችም ያሉት ክለብ እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ…እንደዚህ አይነት ድባብ ያለበት አካባቢ የመስራት ፍላጎት ስለነበረኝ…ጥያቄውን ለመቀበል አላመነታሁም…

ሀትሪክ፡- …ለአዳማዎች ምን ልታሳካላቸው ነው የተስማማኸው…?…

ፋሲል፡- …እንግዲህ አዳማ ከተማ ባለፈው አመት ወርዶ በተገኘው እድል ነው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተመለሰው…ከዚህ አንፃር ቡድኑን በዝግጅት ብቻ ሣይሆን በስነ-ልቦና አጠናክሮ ወደ ውጤት ለመመለስ ብዙ ሥራ ይጠብቀናል፤ብዙ ተጨዋቾች ክለቡንም ለቀዋል…ከዚህ አንፃር ስራዬን ከምንም (ከዜሮ) ነው የምጀምረው…አሁን አዲስ የቡድ ግንባታ ጀምረናል…ከደጋፊው፣ከክለቡ አመራርና ከተጫዋቾቼ ጋር በመሆን አዳማ ተለይቶ የሚታወቅበትን የጠንካራ ተፎካካሪነት ስሜትን ለመመለስ ነው የመጀመሪያ ዓላማዬ…

ሀትሪክ፡- …ብዙ አሰልጣኞች ክለባቸውን በተመለከተ አስተያየት ሲሰጡ አንድ በጣም የሚያስቀኝ ነገር አለ…ዘንድሮ እቅድህ ወይም ለማሳካት የምትፈልገው ምንድነው…?…ተብለው ሲጠየቁ “…ቡደኑን በሊጉ ማቆየትና ጠንካራ ተፎካካሪ ለማድረግ ነው ይላሉ…ዋንጫ ለማንሳትም ነው ስትሉ አይሰማም እንደዚህ የማትሉት ከፍርሃት በመነጨ ነው…?

ፋሲል፡- …መፍራት ሳይሆን…ጦርና ጋሻ ሳይዙ መፎከር አይሆንም…?…ለእኔ እንደዛ ነው የሚታየኝ…?…

ሀትሪክ፡-? …ይሄ ሁሉ ሚሊዮን ብር ፈሶ፣አመት ሙሉ ተወዳድሮ ክለቡን ለማቆየት ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን መጫወት በሂሣብ ስሌት እንደ ኪሣራ አይታይም…?…

ፋሲል፡- …የዛሬ አመት ወይም ሁለት አመት ባህር ዳር ስገባ በጠየከኝ ጊዜ እንደዚህ አላልኩም…አሁን ገና አዳማን ከመያዜ ከመሬት ተነስቼ ቡድኑን ዋንጫ በዋንጫ ነው የማደርገው…ብልህ አንተ ራስህ አትታዘበኝም…ሰውም ይታዘብኛል…ደግሞም ጀብደኝነት ባዶ ፉክራ ነው የሚሆነው…እግር ኳስ ፕሮሰስ (ሂደት) ነው…አዳማ ከባለፈው ችግር በተለይ በስነ-ልቦናው በኩል መረጋጋት አለበት…አዲስ የቡድኑን ግንባታ እያደረኩ ነው…ይሄንን እያወኩ ፉከራ ባበዛ ሙያዊ አይመስለኝም…ይሄንን ተወውና በገባሁበት አመት አስገራሚ ውጤት ልመጣም ትችላለህ…ያ ግን ሠርተህ በጊዜ ሂደት አስበህበት ያመጣኸው ውጤት ነው ብዬ አላስብም…ቡድኑን ዋንጫ በዋንጫ አድርገዋለሁ ብሎ መናገር ያን ያህል ከባድ ወይም የሚያስፈራ ነገር ሆኖ አይደለም…ቡድን የሚገነባው በሂደት ነው…ከሂደቶች በኋላ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል…?…

ሀትሪክ፡- ስም መጥራት እችላለሁ ብዙ አሰልጣኝ ከአንዱ ክለብ ወደ ሌላ ክለብ ሲዛወሩ እንደ ከባድ መኪና ፉርጎ (ተጎታች)አብሮዋቸው እየጎተቷቸው ይዘዋቸው የሚሄዱ ተጨዋቾች አሉ…ከችሎታቸው ነው?…ወይስ የአሰልጣኛቸው ጆሮ ጠቢ ስለሆኑ ነው…?… አንተም በዚህ መልኩ ተጨዋቾች ይዘህ ስትሄድ ስላየሁ ነው ተሳሳትኩ…?…

ፋሲል፡- …የምትጠይቀኝ እኔን ከሆነ እኔ በዋና አሰልጣኝነት ገና ሶስት አመቴ ነው…በዚህ ደረጃ የሚያሳማኝ ነገር አለ ብዬ አላስብም…በዚህ ደረጃ ይዤው የሄድኩት ተጨዋች ቢኖርም ምንድነው ክፋቱ…?…አብረን በሰራንበት አመት ጥሩ ብቃት ካሳየኝ አዲስ ለገባሁበት ክለብም ሆነ አጨዋወት ጠቃሚ ነው ብዬ ካመንኩና ችሎታውን ብቻ መሠረት አድርጌ ይዤው ብሄድ ክፋቱ ምንድነው…?…የተጨዋቹ ብቃት ወርዶ ወይም ካሉት ተጫዋቾች የማይሻል ሆኖ ይዤው ከሄድኩ ሊያሳየማህ ይችላል…ከዚህ ውጪ ክለብ በቀየርክ ቁጥር አብሮህ የሚዞር ተጨዋች ካለም ይሄም የሚደገፍ ነው አልልም…በትክክለኛው መንገድ ችሎታውን ማዕከል አድርገህ የምትወስደው ከሆነ ግን ክፋቱ አይታየኝም…

ሀትሪክ፡- …ከአዳማ በፊት ስምህ ከቀድሞ ክለብህ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተያያዞ ሲነሣ ነበር…ለምን ተነሣ…?…ለምንስ ሳይሳካ ቀረ…?…

ፋሲል፡- …(በጣም እየሳቀ)…ለምን ተነሣ…?…ለምንስ ቀረ…?…ብሎ ጥያቄ አለ እንዴ…?…ጋዜጠኛው አንተ አይደለህ…?…አንተነህ መመለስ ያለብህ…(አሁንም ሳቀ)…

ሀትሪክ፡- …የእኔን ተወው…አንተ በግልህ ለምን ስምህ ከቅ.ጊዮርጊስ አሰልጣኝነት ጋር ተያይዞ የተነሣ ይመስልሃል…?…

ፋሲል፡- …ብዙ ቅዱስ ጊዮርጊሳዊያን ክለባቸውን እንዳስለጥን ይፈልጋሉ…ደጋፊዎች በተለያየ መንገድ ፍላጎታቸውን ሲገልፁልኝ ነበር…የክለቡን ማልያ ለብሶ ተጫውቶና አሰልጥኖ ያለፈ በመሆኑ ለክለቡ አንድ የሚያበረክተው አቅም አለ ብለው ማመናቸው ይመስለኛል ወሬው እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው…

ሀትሪክ፡- …ለምን የቀረ ይመስልሃል…የሚለውን አልመለስክልኝም…?…

ፋሲል፡- …ስሜ አብሮ ተያይዞ የተነሳበትን ምክንያት ገልጬልሃለሁ…ለምን ቀረ…?…ለሚለው የሚቀረው እኮ ክለቡ ወይም የሚመለከታቸው ሰዎች ጥያቄ አቀርቦውልኝ ሲቀር ነው…ከዚህ አንፃር አንድም የክለቡ አመራር ያናገረኝ ነገር ስለሌለ የቀረ ነገር የለም…(ሣቅ)…ቀረም…አልቀረም ለማለት ጥያቄው መጀመሪያ ወደ እኔ መምጣትና መነጋገር ነበረብን…ይሄ ግን ስላልሆነ በተለይ የምናገረው ነገር የለም…

ሀትሪክ፡- …በቅዱስ ጊዮርጊስ በተጨዋችነትም በአሰልጣኝነት በወርቅ ቀለም የተፃፈ የደመቀ ታሪክ አለህ…አንድ ቀን ተመልሰህ ይሄንን ክለብ የምታሰለጥን ይመስልሃል…?…

ፋሲል፡- …አትጠራጠር…!…ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ህይወቴን ትልቁን ታሪክ የያዘ በጣም የምወደው የማከብረው ክለብም ነው…በጊዮርጊስ ቤት አድጌያለሁ…ታላላቅ ስኬቶችንም አግኝቼበታለሁ…ለዛሬ ማንነቴ በደንብ አርጎ የቀረፀኝ ክለብ ነው…ሁልጊዜም እንደምለው ለጊዮርጊስ መስራት ለእኔ መታደልም ክብርም ነው…አንድ ቀን ይሄ ህልሜ እውን እንደሚሆን እምነቱ አለኝ…

ሀትሪክ፡- …አዳማ አንተን በአሰልጣኝነት ከመቅጠሩ በፊት ተጨዋቾችን ሲያስፈርም ነበር… ባልመረጥካቸው ተጨዋቾች መጫወት በውጤትህ ላይ ችግር አይመጣም…?…

ፋሲል፡- …ወቅቱ የተጨዋቾች ዝውውር ወቅት ስለነበር የተሻሉ ተጨዋቾችን ለክለቡ ለማምጣት በማሰብ የተወሰኑ ተጨዋቾችን አዘዋውረዋል እንዳልከው…ተጨዋቾቹን ባልመረጣቸውም ለእኔ አጨዋወት የሚሰማሙና ክለቡን የሚጠቅሙ ናቸው ያልኳቸውን ተቀብያቸዋለሁ…በአብዛኛው ያነነገርኳቸው የሚጠቀሙኝ በመሆኑ ችግር አልፈጠረብኝም…ክለቡ ወደ ዝውውር የገባው በጣም ዘግይቶ ስለነበር…ገበያው ውስጥ የተሻሉ ተጨዋቾች ቀድሞለማግኘትና በሌላ እንዳይያዙ በመስጋት የተደረገ በመሆኑ ተገቢ ውሳኔ ነው…

ሀትሪክ፡-.. ምክትል አሰልጣኝህን ክለቡ መርጦ ነው ያዘጋጀው… በምክትል አሰልጣኝ ዙርያ አለመግባት ሁሉ ተፈጥሮ የራሴን ኮቺንግ ስታፍ ይዤ እመጣለሁ ብለህ በሁለት ረዳት አሰልጣኝ የምትሰራበት ሁኔታ እስከመፈጠር ደርሶ ነበር…ይሄንን አምነህበት ነው የተቀበልከው…?…

ፋሲል፡- …ምክትል አሰልጣኝ ለመቅጠር የእኔ ይሁንታ ያስፈልግ ነበር…በዛ መሰረት ተመርጧል…

ሀትሪክ፡- …ፋሲል ተሳስተሃል ካላልከኝ በስተቀር…ምክትል አሰልጣኙ ይታገሱ እኮ ባልተለመደ መልኩ አንተ ከመቀጠርህ በፊት እሱ ተቀጥሮ ጨርሶ እኮ ነው የጠበቀህ…?…

ፋሲል፡- …አንተ ስለምትለው ነገር እኔ መረጃው የለኝም…ምክትል አልጣኘ ሲቀጠር ሙሉ በሙሉ የእኔ ይሁንታ ነበረበት…ባህርዳር ይሄደል ተብሎ ተጠብቆ ነበር…እንደማይሄድ ሲታወቅ ከእኔ ጋር ረዥም ሠዓት ቁጭ ብለን ተነጋግረን፣ተሰማምተን በመጨረስ…አብረን ለመስራት ፍቃደኛ በመሆኑና ክለቡም የእኔን ይሁንታ አግኝቶ ነው የተቀበለው…ከዚያ በፊት አንተ እንዳልከው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጭምጭምታዎች ነበሩ…

ሀትሪክ፡- …ፋሲል ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ…?…

ፋሲል፡- …እኔም በተመሳሳይ አመሰግናለሁ…

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.