“ግብፅን አሻግረን ማየት ጀምረናል”ብርሃኑ ግዛው የባንኮች አሰልጣኝ (ከኬንያ በተለይ ለሀትሪክ)

ግብፅን አሻግረን ማየት ጀምረናል

“የወንዶች ቡድንን የማሰልጠን ሕልምም ፍላጎትም የለኝም፤ ማሰልጠን ሳቆም ጥሩ ገበሬ መሆን ነው ምኞቴ”
ብርሃኑ ግዛው የባንኮች አሰልጣኝ
(ከኬንያ በተለይ ለሀትሪክ)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የሴካፋ ዞን የሻምፒየንስ ሊግ ፍልሚያ በኬንያ የግብ ዝናቡን እያወረደው ነው፤ ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች በማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከ21 በላይ የጎል ዝናብ ያወረደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዋንጫ የሚያደርገውን ግስጋሴ አጠናክሮ ቀጥሏል፤ በአዳዲስ ታሪክና የጎል ሪከርዶች አዲስ ታሪክ ለማፃፍ እየተንደረደሩ ያሉትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድንን እያሰለጠነ የሚገኘው አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ከኬንያ በተለይ ለሀትሪክ ብቻ በሰጠው ቃለ-ምልልስ እየተመዘገበ ባለው ውጤት ደስታና ኩራት እየተሰማው መሆኑን ተናግሯል፡፡

“አሁን ህልሜን መኖር ጀምሬያለሁ፤ አምላክ ህልሜን እንድኖርም ፈቅዶልኛል” የሚለው አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው “ከትንሿ ሸኖ ከተማ ተነስቼ፣ ከአስከፊ የስደት ህይወት፣ ከጎዳና ህይወት፣ ሰው ቤት ተቀጥሮ ከመስራት ወጥቼ ለዚህ ክብር በመብቃቴ የውስጤን ስሜት የምገልፅበት ቃላት የለኝም” ብሏል፡፡ “የሴቶች እግር ኳስ በዚህ ደረጃ ደርሶ የማየት ህልሜ እውን እየሆነ ነው” ሲል አሰልጣኝ ብርሃኑ ከትላንቱ ዩ ጆይንት ስታርስ ድል ከፈጠረበት የደስታ ስሜት ሳይወጣ በተለይ ለሀትሪክ ገልጿል፡፡

የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ በስልክ ሞገድ አሳብሮ ወደ አሰልጣኙ ጋር በመደወል “ኧረ ይሄ ሁሉ የጎል ናዳ ምንድነው? በእናንተ ጥንካሬ ወይስ በተጋጣሚ ቡድን ድክመት?” የሚሉና ሌሎች ወቅታዊ ጥያቄዎችን በማንሣት አነጋግሮት ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቅርቦታል፤ እንደተለመደው አብሮነታችሁን አውሱን፡፡

ሀትሪክ፡- ….ሃሎ አሰልጣኝ ብርሃኑ… ይሰማል…?…

ብርሃኑ፡-… አዎን ይሠማል… ሠላም ነው…? ሀትሪኮች ከየት ተገኛችሁ….? (እንደመሳቅ እያለ)…

ሀትሪክ፡-… በኬንያ እየሠራችሁት ያለው ገድል…. እያስመዘገባችሁት ያለው አንፀባረቂ ውጤት አስገደዶን ባህር አቋርጠን በአየር ሞገድ አሳብረን በስኬታችሁ ዙሪያ ለማነጋገር ነው የደወልንልህ… ?…

ብርሃኑ፡-.. በጣም ነው የማመሰግነው… ቀድም ሲል ለሀገር ስፖርት በተለይ ለሴቶች እግር ኳስ ለምትሰሩት ሥራ ክብር አለኝ… አሁን ደግሞ ከሀገር ውጪ መሆናችን ርቀቱ ሳይገደባችሁ ውጤታችንን፣ ስኬታችንን ለሕዝቡ ለማድረስ ላደረጋችሁት ጥረት ምስጋናዬ ከፍተኛ ነው…

ሀትሪክ፡- እየተሳተፋችሁበት ባለው የሴካፋ ዞን ውድድር ላይ የኬንያውን ቬጋ ኩዊንስን 4ለ2 የዛንዚባሩን ኒው ጄኔሬሽንን 10ለ1 በሁለት ጨዋታ 14 ጎል ይሄ ሁሉ የጎል ናዳ ምንድነው…?…

ብርሃኑ፡- ተጫዋቾቼ ከአዲስ አበባ የተነሱት አንድ ታላቅ ነገርን በዚህ ከባድ ጊዜ ለሀገራቸው አስመዝግበው የመመለስ ትልቅ ህልምን ሰንቀው ነው… የኬንያውን ክለብና የዛንዚባሩን ክለብ በሰፊ ጎል ስናሸንፍ የልጆቼ ሞራልና የማሸነፍ ስሜት ጣሪያ የነካ ነበር… በግልም በቡድንም ተጨዋቾቼ በጣም ልዩ ነበሩ… ያ ይመስለኛል የግብ ዝናብ እንዲዘንብ ያደርገው…. ?…

ሀትሪክ፡-…. ይሄን ሁሉ የግብ ናዳ ከእናንተ ጥንካሬ ወይስ ከተቃራኒ ቡድን ድክመት…?…

ብርሃኑ፡-… በሁለቱም ነው ብዬ የማስበው… የእኛ ጥንካሬ መሆኑ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም… የእኛ ጥንካሬ ምን ፈጠረ…?… ከፍተኛ ልዩነትንና ብዙ ጎሎችን አስቆጥረን እንድናሸንፍ አደረገን… ሁለተኛውና የማይካዳው ደግሞ የተቃራኒ ቡድን ድክመትም ከፍ ብለን እንድንታይ አድርጎናል….

ሀትሪክ፡-.. የሴካፋ ዞን በወንድም፣ በሴቶችም እግር ኳስ ከአህጉሪቱ ደካማው … ከመሆኑ አንፃር እናንተም በሁለት ጨዋታ 14 ጎል ማስቆጠራችሁ ድክመታችሁን አይሸፍንባችሁም…?… ትክክለኛውን ብቃታችሁን ለማየት ረድቶናል .. ትላለህ…?…

ብርሃኑ፡-… ጥንካሬያችንና ድክመታችንን በማሳየቱ በኩል ብዙ ጎል ካስቆጠርንበት የዛንቢባሩ ጨዋታ ይልቅ የኬንያው ጨዋታ በተሻለ አሳይቶናል ብዬ አምናለሁ…. በማሸነፍ ውስጥም ያሸነፍንበትን ምስጢርም በድሉ ውስጥም ድክመቶችን ታያለህ… በብዙ ጎል ማሸነፋችን ድክመታችን እንዳይሸፍንብን ለመጠንቀቅ እንጥራለን… ከዚህ ውጪ በብዙ ጎል የማሸነፍ ስነ ልቦናችን ከፍ ማለቱን ብዙ ጎል የማስቆጠር አቅምም እንዳለን አጋጣሚው አስመልክቶናል… እውነት ለመናገር ከኬንያው ቬጋ ኩዊንስ ጋር ያደረግነው ጨዋታ በጣም ፈታኝ ጨዋታ ነበር…ጠንካራ ፉክክር ነበር… የጠበቀን … ረዥም ኳስ ሲጠቀሙ፣ ሹት ሲመቱ፣ የአጥቂዎቻቸው ፍጥነት፣ ክፍተት ሲያገኙ የሚያደርጉት ቅብብል የተለየ ነበር… በጨዋታውም በጣም አስቸግረውን ነበር… ይህ ጨዋታ ጥንካሬያችንንም ድክመታችንንም እንደመስተዋት አሳይቶናል…

ሀትሪክ፡- .. ብዙዎች ትኩረታቸው ሎዛ አበራ ላይ ሆኖ አዲስ ክስተት ሆና ብቅ ያላችው ግን መዲና አወል ነበረች.. ይሄ ምን ስሜት ፈጠረብህ….?….

ብርሃኑ፡- … እውነት ለመናገር መዲና አወል ክስተት ሆና ነው ብቅ ያላችው… መዲና አወል ትልቅ አቅም ያላት ተጨዋች ናት… እነ ሽታዬ እና ብርቱካን አቅምና ችሎታን እናታቸው ማህፀን ውስጥ እያሉ ጀምረው ተለማምደው የመጡ ተጨዋቾች ናቸው… እንደ እነዚህ አይነት ተጨዋቾችን የሚተኳቸው እንደ መዲና አይነት ተጨዋቾች ናቸው….መዲና ከሎዛ አበራ ጋር የመጣች ተጨዋች ናት… ግን በአያያዝ ይሁን ቸልተኝነት በመኖሩ በአጨዋወትም ብቻ በተለያየ ነገር ያልተመቻት ነገር ይኖር ይሆናል… በሚፈልገው ደረጃ አልሄደችም… እኔ ግን ያደረኩት ነገር ምንድነው? መጀመሪያ ከእሷ ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር ነበር… ተነጋገርን.. አንቺ ተጨዋች ነሽ ስራሽን መስራት ብቻ ነው የሚጠበቀው አልኳት…. አብረን ሰራን አሁን ግን እንደገና እየፈካች ነው… ፍጥነቷም ጉልብቷም ሁሉም ነገሯም ልዩ ነው… የዚህ ሁሉ ምክንያቱ በሚለውጣት መልኩ መስራታችን ነው… ፕሬስ ኮንፌረንስ ላይ የስኬቷ ምስጢር ትሬይኒንግ ላይ የሠራችው እንደሆነ ተናግራለች… ከትሬይሊንጉ ውጪ ግን በሜዳ ላይ ያለው ስነ ምግባር ላይ መሠራቱ… በውስጧ አምቃ የያዘችውን ተሰጥኦ እንዴት ማውጣት እንዳለባት ተነጋግርን… ሠራን… ይሄ የረዳት ይመስለኛል… ግን እንዳልከው የእውነት ክስተት ናት፡፡

ሀትሪክ፡- በአንድ ጨዋታ ሁለት ሀትሪክ ተሰርቶ ሁለት ተጨዋቾች መዲናና ሎዛ ሁለት ኳስ መውሰዳቸው ምን ስሜት ፈጠረብህ…?

ብርሃኑ፡- … መዲና ሁለት ኳስ ነው… ሀትሪክ ሰርታ በግሏ የወሰደችው… በጥያቄም እንዳነሳኸው በአንድ ጨዋታ ሁለት ሀትሪክ ሰርቶ ሁለት ኳስ መውሰድ ከባድ ነው ብቻ ሳይሆን ያልተለመደ ነው… ልጆቼ ግን ይሄን ከባድ የሚመስል ነገር አድርገውት መመልከት የተለየ ስሜት ይፈጥራል… በጣም የሚገርምህ ይሄ ጥያቄ በፕሬስ ኮንፈረንስ ላይም ያልተለመደ ነገር ነው በሚል ተነስቶ ነበር… ግን የእኛ ልጆች ያልተለመደውን ነገር አድርገውታል… ከስኬቱ በኋላ ተቃቅፈው ደስታቸውን ሲገልፁ ስታይ ትገረማለህ… የውጪዎቹ ሜሲና ስዋሬዝ ወይም ሜሲና ኔይማር የሜዳ ውስጥ ስኬታቸውን ከሜዳው ውጪም በመድገም ቤት እንኳን ሲከራዩ አጠገብ ለአጠገብ መሆንን ነው የሚመርጡት… የእኛም ልጆች ጋር ያለው ስሜት በሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ተመሳሳይ ነው… አሁን በቡድኑ ውስጥ ሌሎች ኮከቦች እየተፈጠሩ እንደሆነ ይሰማኛል… ተጨዋቾች ፍቅር ሲዘሩብህ አሰልጣኝ ሆነህ ፍቅሩንም ችሎታቸውንም ከፍ ማድረግ ይጠበቅብሃል… ለአንድ አሰልጣኝ የተደበቀን መክሊት ከፍ ማድረግ ትልቅ ተሰጥኦ ነው…

ሀትሪክ፡- አሁን ወደ ግማሽ ፍፃሜ ገብታችኋል… ምን እያለምክ ነው….?… ከወዲሁ ግብፅን አሻግረህ መመልከትስ ጀምረሀል…?…

ብርሃኑ፡- …. አዎን ግብፅን አሻግረን መመልከት ጀምረናል… የሚገርምህ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽኝት ሲያደርግልን ክቡር አቶ አቤ ሳኖ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት የበላይ ጠባቂና የባንኩ ፕሬዝዳንት ባሉበት ይህ ጥያቄ ተነስቶ የመለስኩት መልስ “ይሄ ሕልሜ ነው… ሕልም ያለው ሰው ደግሞ ነገሮችን በቀላሉ አያይም… ልጆቼም ቱሪስት አይደሉም… ለጉብኝት አይደለም የሚሄዱት…ተዓምር ለመስራት ነው የሚሄዱት… እኛም ተዓምር ሰርተን እንመለሳለን” ብዬ ነው ቃል የገባሁት… አሁን ላይ ቃላችንን ለመጠበቅ ጥረት እያደረግን ነው… የተሻለ ነገር ለክለባችንም ለሀገራችንም ለማምጣት እንጥራለን… ግን እግር ኳስ ነውና በዚህ ሂደት ውስጥ ሊሳካም ላይሳካም የሚችልበት ድል እንደሚፈጠር አይጠፋንም… ምንም ይሁን ምን ወደ ኋላ የምንመለስበት ነገር አይኖርም…ከላይ እንዳልኩህ ግብፅን አሻግረን እየተመለከትናት ነው… ወደ ግብፅ ፊታችንን አዙረን ለመሄድ 270 ደቂቃ ብቻ ይቀረናል…. ከእግዚአብሔር ጋር ለማሳካት እንጥራለን፡፡

ሀትሪክ፡-.. ብርሃኑ ኮከቦችን ይሰበስባል እንጂ ኮከቦችን አያፈራም ብለው ለሚያሙህ መልስ አለህ…?…

ብርሃኑ፡-… (በጣም ሳቅ)… እንደዚህ አይነት ጥያቄ ሲመጣልኝ በጣም ደስ ይለኛል… እንደዚህ አይነት ጥያቄ በፍቅር ሠርቼ በፍቅር መመለስ ይጠበቅብኛል…ብዬ ስለማምን ሀሜትም ቢሆን ጥያቄው ሲመጣ በደስታ ነው የምቀበለው … ብርሃኑ ኮከቦችን ይሰበስባል እንጂ ኮከብ አያፈራም? ይባላል ላለከው.. ኮከቦችን ይዘህ በኮከብነታቸው እንዲቀጥሉ ወይም መክሊታቸውን አውጥተው ስኬታማ እንዲሆኑ ለማድረግ እኮ በራሱ የሚጠይቀው እውቀት አለ.. በነገራችን ላይ ፍሬሾችን (አዲሶችን) ተጨዋቾችን አምጥተህ ማሠራት ያን ያህል ኮከቦችን እንደማሠራት ከባድ አይሆንም… ለእኔ ከፍ ያሉትን ልጆች ማምጣትና የእነሱን አቋም ተረድተህ በዲሲፒሊን ማሠራት በጣም ከባድና አቅምን ይጠይቃል.. ግን ይሄን ያልተረዱ ብዙ ያወራሉ… በነገራችን ላይ ቁጭ ብለው የሚያወሩ ሰዎች የሆነ ታርጋ ይለጥፉብሃል… ስታሸንፍ ስኬታማ ስትሆን ይረበሻሉ መሠለኝ ከሆነ ነገር ጋር ያያይዙሃል…. በክለባችን ውስጥ አዳዲስና ወጣት ተጨዋቾችን እያፈራን ነው… ኮከቦችን ኮከብነታቸውን አስጠብቆ ማስቀጠልና ለውጤት በማብቃቱ በአሸናፊነት ስሜት ውስጥ በመክተቱ በኩል አልተቸገርኩም… ከእነዚህ ተቃራኒ የሆኑ ሰዎች ያደረጉትን መልካም ነገር ደግሞ ልንገርህ…

ሀትሪክ፡-.. ምን…?…

ብርሃኑ፡-… እንደዚህ አይነት ታርጋ የሚለጥፉ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ደስ ያለኝ አንድ ነገር አይቻለሁ እነ መሠረት ማኔ፣ የሀዋሳው አሰልጣኝ መልካሙ፣ ሠላም ዘርዓይና ሠርክአዲስን የመሳሰሉ አሰልጣኞች ተሰባስበው ትንግርት በሚባል የሴቶች ስፖርት ላይ ለሚሠራ ድረ-ገፅ የሰጡትን አይቻለሁ… እኔም ምላሽ ሰጥቻለሁ… መሆን ያለበትም የሚያዋጣንም እንደዚህ አይነት ነገር ነው እንጂ ሰው ውጤት ሲያመጣ እየተከታተሉ አቃቂር ማውጣት አይመስለኝም… ለምሣሌ መዲና አወል ባለፈው አመት የነበረችበት ይታወቃል… ሀትሪክ መስራት ቀርቶ በአመት ውስጥ ያገባችው ስድስትና ሰባት ጎል አይሆንም… ዛሬ ያበበችበት መንገድ ምንድነው? ብሎ መመርመር ነው የሚጠቅመው.. ልጅቷ አቅም ያላት ልጅ ናት… ምንም ጥያቄ የለም የዛሬ አምስትና ስድስት አመት ሰውን አስጨብጭባለች… ግን ከዚያ በኋላ ራሷን ከጨዋታ ውጪ እያደረገች ወይም የሚረዳት አጥታ ቆይታለች… ልጅቷ እንዲህ ናት የካዛንቺስ ልጅ ናት እያሉ ታርጋ መለጠፍ ጥቅም የለውም… ኮከቦችን ሰብስቦ በኮከብነታቸው ማስቀጠል የራሱን አቅም ይጠይቃል፡፡

ሀትሪክ፡-… በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትልቅ የሚባል ስኬት አለህ.. ራስህን ከንግድ ባንክ ውጪ አስበህው ታውቃለህ…?…

ብርሃኑ፡-… በፍፁም አስቤው አላውቅም…ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጪ ስለማሰልጠን አስቤ አላውቅም…ከክለቡ ጋር ፍቺ የማደርገው ወይም የምለያየው ስልጠና ሳቆም ብቻ ነው የሚል እምነት በውስጤ አለ… ንግድ ባንክ ብዙ ስኬት ያገኘሁበት፣ የተከበርኩበት፣ ቤተሰብ የመሠረትኩበት ቤት ነው…. ይሄን ሁሉ ትርፍ የሰጠኝን ያከበረኝን ቤት ለቆ ስለማስልጠን ለሰከንድም ቢሆን ማሰብ አልችልም… ይሄንን እንዳላስብ የሚያደርገኝ ሌላው ምክንያቴ ደግሞ በንግድ ባንክ ደስ የሚልህ ቦርዱ የቦርዱን፣ ጽ/ቤቱ የጽ/ቤት ሥራቸውን ብቻ የሚሠሩበት ቤት ነው… አንዳንድ የቦርድ አመራሮች እኮ “እኔ ላሰልጥን” እስከማለት የሚደርሱ ደፋሮች ያሉበት እንደሆነ ሰምተን እንታዘባለን… ፍራንክ ስለወረወሩልህ መወሰን ስለቻሉ ብቻ ሊጠመዝዙህ ይሞክራሉ… በንግድ ባንክ ቤት ግን የሆነ የተቀመጠ ድንበር አለ ሁሉም ድንበሩን ጥሶ አይሄድም… አሁን ደግሞ ንግድ ባንክ እድለኛ ነው.. ስፖርትን የሚያውቅ ስፖርትን የሚወድ የበላይ ጠባቂ ነው ያለው.. በዚህ ደረጃ ከተከበበ ክለብ ውጪ ማሰልጠን ለእኔ የማይታሰብ ነው….

ሀትሪክ፡-… በርካታ ድሎችን ዋንጫዎችን አግኝተሃል፤ ከድሎች ወይም ከዋንጫዎቼ ሁሉ ይለይብኛል የምትለው … አለ…?…

ብርሃኑ፡-…በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቆየሁባቸው 10 አመታት 11 ዋንጫዎችን አግኝቻለሁ… የጥሎ ማለፍ፣ የአሸናፊዎች አሸናፊ፣ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን 4 ጊዜ አንስቻለሁ… ለሁሉም ድሎቼና ዋንጫዎቼ እኩል ክብር ቢኖረኝም ለእኔ ግን ከድሎቼ፣ ከዋንጫዎቼም ሁሉ የላቀ ድሌና ዋንጫዬ የምለው ሴት ተጨዋቾች ራሣቸውን ችለው፣ ቤተሰቦቻቸውን በዲፕሲፒሊን ሲመሩ ማየቴ ነው…. በእኔ አሰልጣኝነት ከዚህ በላይ ስኬትም ሆነ ድል የለም.. ሴት ተጨዋቾች 18 እና 13 አመታትን በብቃት ሲቆዩ እግር ኳሱን ሲያገለግሉ ሣይ ምን ያህል ዲሲፒሊን እንደተማማርንና ልፋታችን እንዳልወደቀ እረዳለሁ… ለእኔ ከዋንጫዎች ሁሉ የላቀው ዋንጫና ድል እነሱ ስኬታማ ሆነው ማየቴ ነው… እነዚህ ተጨዋቾች የሴቶች እግር ኳስ አሁን የሚገኝበት ደረጃ እንዲደርስ ብዙ ታግያለሁለ… ጨካኝ ከሆኑ አመራሮች ጋር ሳይቀር በተደጋጋሚ የተጋጨሁበት ጊዜ አለ….

ሀትሪክ፡- በዚሁ በሴቶች እግር ኳስ ….?…

ብርሃኑ፡-…አዎን ለወንዶች ብቻ ከቆሙ ከአንዳንድ ጨቋኝ አመራሮች ጋር በተደጋጋሚ ተጋጭቼያለሁ… ሴት እህታቸውን ይወዳሉ፣ ሴት ልጆቻቸውንና እናታቸውን ይወዳሉ.. የሴቶችን እግር ኳስ ከማይወዱና ከማይደግፉ ጋር ብዙ ጊዜ ተጋጭቺያለሁ ዛሬ ግን ያ ልፋቴ ፍሬ በማፍራቱ ተሳክቶልኛል ብዬ አስባለሁ…

ሀትሪክ፡- በሴቶች እግር ኳስ የአንተን ያህል ስኬታማ የሆነ አሰልጣኝ በባትሪ ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው… ከዚህ አንፃር ብርሃኑ ራሱን እንደተለየ አሰልጣኝ አድርጎ ይቆጥራል…?…

ብርሃኑ፡-… እኔ ራሴን እንደተለየሁ አሰልጣኝ አድርጌ አልቆጥርም… ምናልባት የተለየ አሠልጣኝ የሚያደርገኝ ብዬ የማስበው ዝቅ ብዬ መስራቴን ብቻ ነው… እንኳን ተራው ሰው ተወውና የፈጠረን አምላክም የፈጠራችውን ፍጡራንን ዝቅ ብሎ አገልግሏል… እሱ ምሣሌ ሆኖ ባሳየው መንገድ ዝቅ ብሎ መስራትን ተግባብቼ ለመስራት ነው የምሞክረው… ልጠምዝዝህ ለሚሉ ሰዎች አልመችም.. ከፍቅር፣ ከሠላም፣ ከአንድነት ውጪ ሊያነጋግሩኝ ለሚሞክሩ ወይም ለሚያስቡ በፍፁም አልገዛላቸውም… ከዚህ ውጪ በፍቅር በሠላም ሊሚመጡ አብሬ ለመሥራት አልቸገርም፡፡

ሀትሪክ፡- …ከዚህ በኋላ የወንዶች ቡድን ስለማሰልጠን ታስባለህ…?…

ብርሃኑ፡- …በፍፁም! … የነፍሴ ጥሪ ያለው ሴቶች ጋ ነው… እንኳን የወንዶችን ቡድን ለማሰልጠን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጪ ሌላ ክለብ ለማሰልጠን አልፈልግም… ረዥሙ የስልጠና ህይወቴ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነው… 10 አመታትን አብረን በፍቅር፣ በታላላቅ ስኬቶች አስቆጥረናል… ይሄንን ቆይታችን ለተጨማሪ ሁለት አመታት በማራዘም ወደ 12 አመት አሳድገነዋል.. በአጭሩ የወንዶች ቡድንን ለማሰልጠን ህልምም ፍላጎትም የለኝም… የወንዶች ቡድን ላይ የሚሠሩትን የሙያ ጓደኞቼን ግን አከብራለሁ… የስልጠና ሙያው አንድ አይነት ቢሆንም የእኔ ፍላጎትና የነፍሴ ጥሪ ግን ወደ ሴቶች ነው የሚያደላው….

ሀትሪክ፡- …ከስልጠና ሙያ ውጪ ብትሆን በምን ሙያ ብትሰማራ ትመርጣለህ…?…

ብርሃኑ፡-… እኔ ስልጠናን ባቆም ዘመናዊ ገበሬ መሆን ነው የምፈልገው…እርሻ ወይም ገበሬ ሲባል በእኛ ሀገር የሚሰጠው ግምት ዝቅተኛ ነው… እንደውም ገበሬ ሲባል የሚሳቅበት አጋጣሚ ሁሉ አለ… ግን የሚስቀውም የሚያሳቀውንም የሚቀልበው ይሄው ገበሬ ነው… በሀገራችን ሆነ እንጂ በሌላው ዓለም ግብርና የሚያኮራ ትልቅ ሙያ ነው… ገበሬነትን በጣም ነው የምወደው… ከስልጠና ከራኩ የምታገኘኝ ግብርና ውስጥ ነው… ለወደፊቱ መሆን የምፈልገውም ዘመናዊ ገበሬ ነው…

ሀትሪክ፡- ከአዲስ አበባ ኬንያ ተደዋውለን ይሄንን የመሰለ ቆይታ በማደርጋችን፣ አንተም ለቃለ-ምልልሱ ፍቃደኛ ስለሆንክልኝ በአንባቢያን ስም ከልብ አመሰግኜ ከመለያየታችን በፊት ቀረ የምትለው ካለ…?…

ብርሃኑ፡- … የቀረን ነገር ቢኖር ምስጋና ብቻ ነው… የሴቶች እግር ኳስን፣ ቡድናችንን ለማበረታታ የምታደርጉትን ጥረት አደንቃለሁ…በዚህ አጋጣሚም ምስጋና አቀርባለሁ…. በዋናነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በጣም ነው የማመሰግነው… በንግድ ባንክ ስቀጠር የ2500 ብር ደሞዝተኛ ነበርኩ… ዛሬ ከፊርማ ገንዘብና ከሌሎችም ጥቅማጥቅሞች ውጪ የ50 ሺ ብር ደሞዝተኛ ነኝ… ይሄን የማነሳልህ እንደዚህ አገኛለሁ ብዬ ለመናገር ሳይሆን አንድ ሰው ከትንሽ ነገር ተነስቶ ከለፋና ከደከመ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚችል ምስክር መሆኔን ለማሳየት ነው… ሰዎች ከሠሩ የማይደርሱበት የለም… ንግድ ባንኮች ሁለተኛና ሶስተኛ አመት ላይ ውጤት ጠፋ ብለው ቢያባርሩኝ ኖሮ ከባንክ ጋር ያለኝ ታሪክ ሌላ ይሆን ነበር.. በዚህ አጋጣሚ በአጠቃላይ ቦርዱን፣ ከፍተኛ ማኔጅመንቱን፣ ጽ/ቤቱን ክብር ይገባቸዋልና ላመሰግናቸው እወዳለሁ.. ከዚህ ሌላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንንም እንዲሁ ማመስገን እፈልጋለሁ…በቀድሞ ፕሬዚዳንት በአቶ ሳህሉ ዘመን ስናነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች አሁን በክቡር አቶ ኢሳያስ ዘመን በአግባቡ እየተመለሱልን ነው… አቶ ኢሳያስንና የጽ/ቤት ኃላፊውንም አቶ ባህሩንና አጠቃላይ የፌዴሬሽኑን ሰዎች ማመስገን እፈልጋለሁ… ፌዴሬሽኑን ስተችም ስቃወምም የሃሳብ ሙግት ትግል ነው ብለው ስለሚረዱኝም አከብራችዋለሁ… ከዚህ ውጪ ለሴቶች እግር ኳስ ማደግ የሚደክሙትን ሚዲያዎች እነማን እንደሆኑ ይታወቃሉ ሁሉንም ማመስገን እወዳለሁ፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *