“የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ የማንሳት ህልሜ ከፋሲል ጋር በመሳካቱ አሁን ኳስ ባቆም ቅር አይለኝም” በዛብህ መለዮ/ፋሲል ከነማ/

ለሆሳዕና ከተማ በመጫወት የእግር ኳስ ህይወቱን ሀሁ ብሎ ጀምሯል… ብዙም ሳይቀይ ለሙገር ቢ ቡድን ፈርሞ ተጫውቷል… ከሙገር ቢ ወደ ሆሳዕና ከተማ በመመለስ በብሔራዊ ሊግ ተጫውቷል.. ከዚያም ምርጡን አቋም ወዳሳየበት ወላይታ ድቻ ተዛውሮ ለ4 አመታት ያህል ተጫውቷል፡፡ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ስኬታማ ጉዞ ያደረገው ቡድን አባልም ነበር እንግዳችን በዛብህ መለዮ ፡፡ ባለፉት 3 አመታት ደግሞ ለፋሲል ከነማ ተሰልፎ እየተጫወተ ነው ከሁለት አመት ልፋት በኋላ ዘንድሮ በ2013 የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አንስቷል ትልቅ ደስታ ላይ ያለው በዛብህ መለዮ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስራ ትዳሩና በፀሎት ስለተወለደችው ልጁ፣ ስለ ፋሲል ከነማ ድል፣ ቡድኑ ስለተጓዘባቸው 3 አመታት፣ በፋሲል ማለያ ስላገኛት ሚስቱ፣ ስለ ኮከብ ግብ አስቆጣሪዎቹ ፍልሚያ፣ ስለ ኮቪድ 19 ዋነኛ ስጋት፣ ከቁመቱ በላይ ስለመዝለሉ፣ ስለ ሻምፒዮንስ ሊግ ጉዞ፣ በሊጉ ስለተገረመበት ጉዳይ፣ ስለ ወላይታ ድቻ ቆይታው፣ ስለ አሰልጣኝ ስዩም፣ ለዋሊያዎቹ ለመጫወት ስላለው ተስፋ።፣ስለአባይ ግድብና ሌሎች ጉዳዮች ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- እንኳን ደስ አለህ…?

በዛብህ፡- አመሰግናለሁ… እውነት ነው በጣም ደስ ብሎኛል
ሀትሪክ፡-ፋሲል ከነማ በዚህ የነጥብ ብልጫ ዋንጫ ይወስዳል ብላችሁ ጠብቃችሁ ነበር..?

በዛብህ፡- ስለ ርቀቱ ባናስብም ዋንጫ መውሰድ አለብን ብለን ከተጨዋቾቹ ጋር በጋራ አውርተን ነው የጀመርነው እምነቱም ነበረን 2 አመት ሙሉ ያለፍንበትን መንገድ ስለምናውቅ ለዋንጫ ተዘጋጅተን ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ዋንጫውን ለመውሰድ የነበረው የቡድኑ ጉጉት ምን ይመስል ነበር…?

በዛብህ፡- በጣም ትልቅ ጉጉትና ፍላጎት ነበረን እስከማውቀው ድረስ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳ ተጨዋች የለምና ሁሉም ለማሸነፍ ጓጉቷል እንደ ታሪክ የምናወራው ዋንጫ ያስፈልገን ነበረና ሁሉም ጋር የነበረው ስሜት ተመሳሳይ ነበር ስለተካልንም ደስ ብሎኛል እንደ እኔ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ የማንሣት ህልሜ በመሳካቱ ኳስ አሁን ባቆም ቅር አይለኝም የለፋሁበትን ዋንጫ አግኝቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከፋሲል ከነማ ውጪ ይሄ ዋንጫ የሚገባው ቡድን አለ ብለህ ታምናለህ…?

በዛብህ፡- በፍፁም የለም… የምጠራውም ክለብ የለም፤ በኛ በኩል ለፍተናል ሰርተናል ባለፉት 2 አመታት ብዙ ለፍተን በ3ኛው አመት ነው ያሳካነው.. ውጤቱ ደግሞ ያንን ያሳያል 1 ጨዋታ ተሸንፈን 4 አቻ 15 ድል መሆኑ የሄድንበት የልፋት ደረጃ ያሳያልና ለዋንጫው ከፋሲል ከነማ ውጪ የማስበው የለም፡፡

ሀትሪክ፡- የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ መታሰቢያነት ለማን ሰጠህ….?

በዛብህ፡- ከፋሲል ከነማ ጋር ያሳካሁት የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ መታሰቢያነት ፋሲል ከነማ ከገባሁ በኋላ ላገኘኋት ውዷ ባለቤቴ ቅድስት አመነ ይሁንልኝ

ሀትሪክ፡- በፋሲል ከነማ ያሳካኸው ዋንጫ ብቻ አይደለም ውድህንም አግኘተሃል…?

በዛብህ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ሚስትም ልጅ ሰጥቶኛል.. ብዙ ነገር ሰጥቶኛል የምወዳት ልጄ በፀሎት ከተወለደች በኋላ ድል በድል ሆኛለሁ ብዙ ነገሮች ተሳክቶልኛል በፀሎት ብዙ ነገር ይዛልን መጥታለች፡፡

ሀትሪክ፡- ልጅህን በፀሎት በዛብህ አልካት…. በፀሎት ውጤት ታምናለህ…?

በዛብህ፡- አዎ ልጄ ብዙ ነገር ይዛልኝ መጥታለች እርሷን ለማምጣት ዋጋ ከፍለናል ወደዚህ ምድር የመጣችው ፈለገን በፀሎት ነው… ብዙ ፈተናዎችን አልፈናል በተለይ ለርሷ ተፀልዮ ነው የመጣችውና ፀሎት ዋጋ እንዳለው ምስክር ነኝ… መፀለይ የግድ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የአመቱ ኮከብን ለማን ሰጠህ…?

በዛብህ፡- ከባድ ይመስለኛል መገመትም ይከብዳል ግን ከፋሲል ከነማ በፍፁም አይወጣም በዚህ ርግጠኛ ነኝ፤

ሀትሪክ፡- ከአቡበከርና ሙጂብ ማን በኮከብ ግብ አግቢነት ይጨርሳል…?

በዛብህ፡- ሙጂብ ቃሲም ይመስለኛል

ሀትሪክ፡- እያዳላህ አይደለም በ3 ግብ አቡበከርኮ ይመራል/ቃለምልልሱ የተሰራው ረቡዕ ዕለት ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ  ከመጫወታቸው በፊት ነው/

በዛብህ፡- አዎ በርግጥ እየመራ ነው አቡበከርም ቢወስደው ደስ ይለኛል ሙጂብ ግን ሁለቱን አመት እንዴት እንዳለፈና እንዴት እንደተበላ ስለምናውቅ ቢሳካለት ደስ ይለኛል አቡበከርም ቢወስድ አልከፋም ሁለቱም የሀገር ልጆች ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡-ፕሪሚየር ሊጉን ላንወስድ እንችላለን የሚል የስጋት ስሜት ተፈጥሮብህ ያውቃል…?

በዛብህ፡- እንደ ክለብ ያሰጋን የለም፡፡ በኮቪድ 19 ምክንያት ሊጉ ሊቋረጥ ይችላል ብለን ሰጋን እንጂ ለዋንጫው ያሰጋን አንድም ክለብ የለም… በግሌ አንድም ጊዜ አስቤው አላውቅም

ሀትሪክ፡- በግንባር ገጭተህ ስታገባ ከረጃጅሞቹ ሁሉ በላይ ዘለህ ነው… እንዴት ነው…?

በዛብህ፡- አዎ በጣም ነው የምዘለው ያደኩበት አካባቢ መርቲጂዱ ይባላል ከሱራፌል ዳኛቸው ጋር አብረን ነው ያደግነው ሱሬ ከጓደኛ በላይ ወንድሜ ነው እዚያ አሸዋ አለና እዚያ ኃይሉ ካሳ ከሚባል አሰልጣኝ ጋር እንሰራ ነበርና ትልቅ እገዛ አድርጎልኛል በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኙን አመሰግናለሁ

ሀትሪክ፡- ለፋሲል ደጋፊዎች የምትለው ነገር አለ…?

በዛብህ፡- የራሳቸውን የልፋት ውጤት አግኝተዋል እንኳን ደስ አላችሁ… ይሄ ቡድን እስከሞት ድረስ ዋጋ ተከፍሎበታል ብዙ ደጋፊዎች አሉ ቡድኑን ብለው ወጥተው የቀሩ አሉ… የዋንጫው መታሰቢያነት ለነርሱም ቢሆነ ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ዋንጫውን እንዳሸነፋችሁ የት ሆነህ ሰማህ… ማንስ ደወለልህ…?

በዛብህ፡- ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ መለያየቱን ተከትሎ ነው ባለ ድል የሆነው… ባለቤቴ ናት ቀድማ ቴክስት ያደረገችውም የደወለችልኝም /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- የ2013 የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማሸነፋችሁን ልዩ የሚያደርገው በምንድነው..?

በዛብህ፡- የመጀመሪያው በዲ.ኤስ.ቲቪ መታየቱ፣ ዋንጫው ከውጪ ተሰርቶ መምጣቱና 1 ሚሊዮን ብር ሽልማት መሆኑ፣ ሊጉ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ መባሉ፣ ሁሉም ውድድር በአንድ ቦታ ተደርጎ እንደሌለው ጊዜ ምን አይነት ተፅዕኖ አለመኖሩ፣ ሆን ተብሎ ውጤት መቀየር አለመቻሉ… የኛን ዋንጫ ልዩ ያደርገዋል በዚያ ላይ ውደድሩ በዲ.ኤስ.ቪ ሲጀመር የመጀመሪያ ግብ ያስቆጠረው የኛው ሙጂብ ቃሲም ነው በዋንጫ ያጠናቀቅንውም እኛ መሆናችን አመቱን የተለየ አድርጎታል፡፡

ሀትሪክ፡- በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮን ሊግ ተሳትፎ ታደርጋለችሁና የት ድረስ የመጓዝ እቅድ ይኖራችኋል…?

በዛብህ፡- በዚህ በፊትም ተሳታፊ ነበርን በኮንፌዴሬሽን ካፕ ጥሩ ልምድ አግኝተናል እንደ ቡድን ከመጀመሪያው አመት ሁለተኛው ከሁለተኛው ሶስተኛው አመት ይሻላልና የተሻለ ጉዞ እናደርጋለን ብዬ አስባለሁ ስህተታችን ምንድነው ጥንካሬያችንስ? የቱ ይጨመር የሚለውን ሰርተን ጠንክረን እንደምንገባ እጠብቃለሁ ተጋጣሚዎቹ ከኛ የሚሻሉበት ምንድነው? ደካማ ጎናችንስ ምንድነው?እኛስ በምን እንበልጣለን ብለን ጠንካራ ስራ ሰርተን የተሻለ ጉዞ ይኖረናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በፕሪሚየር ሊጉ አይተኸው የተገረምከው በምንድነው…?

በዛብህ፡- ተጨዋች በቀይ ወጥቶብን በኢትዮጵያ ቡና ተሸንፈናል ከባህርዳር ከተማ ጋር አቻ ተለያይተናል በእግር ኳስ ያጋጥማል ችግር የለውም አሁን ላይ ሳስበው ግን እንኳን ነጥብ ጣልን እላለሁ ያኔ ነበር እንደገና ተነጋግረን መክረን የፋሲል ከነማ ጥንካሬና አቅም የጨመረው ከዚያ በኋላ ያለውን ጉዟችንን ሳሰብ ይገርመኛል መነካታችንና መሸነፋችን ጠቅሞን ብርቱ አድርጎናል፡፡

ሀትሪክ፡- የወላይታ ድቻ ቆይታህን እንዴት ታየዋለህ…?

በዛብህ፡- የህይወቴ አንደኛው ምርጡ ጊዜዬ እዚያ ነው የጥሎማለፍ ዋንጫ ወስደን በኮንፌዴሬሽ ካፕ ተሳትፈን ጥሩ ጉዞ አድርገናል ምርጥ ቡድን ነበረን ምርጥም ቆይታ ነበረኝ ሙሉ ኢትዮጵያ የደገፈን ጊዜ ነበር ከፋሲል ከነማ ቀጥሎ አሪፍ ቡድንና አሪፍ ቆይታዬ ወላይታ ድቻ ጋር የነበረኝ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- እስቲ ስለ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ አውራኝ?

በዛብህ፡- ምርጥ አሰልጣኝ ነው ፋሲል ከመግባቴ በፊት ፕሬይ ሜከር ነበርኩኝ በአሰልጣኝ ውበቱ ነው እስኪመር ሆኜ መጫወት የጀመርኩት፡፡ ስዩም ከመጣ በኋላ በሁለት እስኪመር ስለሚጫወት ወደፊትም ወደኋላም እያልኩ በነፃነት ነው የምጫወተው ይህም ደስ ብሎኛል በሁለት አይነት ሚና ነው የምጫወተው ይሄ ደግሞ ለኔ ጥሩ ሆኗል የተለያየ ቦታ እንድጫወት ያለኝን እንዳወጣ አድርጎኛል በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ ስዩምን አመሰግናለሁ በነገራችን ላይ በሁለቱ አሰልጣኝ ውበቱ አባተና ስዩም ከበደ ስር መሰልጠኔ በጣም ጠቅሞኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ወቅታዊ አቋምህ ለብሔራዊ ቡድን ይመጥናል ማለት ይቻላል…?

በዛብህ፡- አዎ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ይመንብኝ እንጂ ዝግጁ ነኝ ጥሩ ጊዜ በማሳለፌ እግዚአብሔር ከፈቀደ ዋሊያዎቹን ልቀላቀል በኔ በኩል ዝግጁ ነኝ አሁነ ጥሩ ነኝ ፋሲል ከነማ ስገባና አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱና ብሔራዊ ቡድኑን በያዘ ጊዜ ተመርጬ ነበር በጉዳት ነው ከስብስቡ ውጪ የሆንኩት.. ያኔ ከብሔራዊ ቡድን ጉዳት ነው ቀጥታ ወደ ፋሲል ከነማ የሄድኩት..አሁን ግን ሀገሬን አገላግላለው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የኮቪድ 19 ፍርሃት አንተን አላጠቃህም…?

በዛብህ፡- ኮቪድ 19 ቀድሞ ያገኘውማ እኔን ነው ኳስ ተጨዋች መሆኔና ስፖርተኝነቴ ጠቅሞኛል ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አዲስ አበባ ላይ ከተጫወትን በኋላ 4 ጨዋታዎች አልፈውኛል፤… እንደ ክለብ ግን ጠንካራ መከላከል አድርገናል ትልቁ ስጋት የነበረው ድሬዳዋ ከተማ ላይ ነበር ግን ቡድናችን በሁሉም መልኩ ጥንቃቄ ሲያደርግ ቆይቷል ሞባይል ካርድ እንኳን ለመግዛት የሚወጣ አልነበረም ሁሉም ነገር ካምፑ ውስጥ ነበርና አልወጣንም እቃ የሚገዛና የሚወጣ ተጨዋች አልነበረም የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ ነው ጌሙን ጨርሰን እቃ እንድንገዛ ጠንካራ መመሪያ ተሰጥቶን ወጥተን የገዛነው እንደ ቡድን ጥሩ ዝግጅትና መከላከል ስላደረግን ሁሉ ነገር ተሳክቶልን ጨርሰናል በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በቦታህ ያንተ ምርጥ ተጨዋች ማነው?

በዛብህ፡- በአማካይ ስፍራ ሽመልስ በቀለና ዳዊት እስጢፋኖስን አደንቃቸዋለው በመሀል ቦታ ላይ እነርሱን አደንቃለሁ አቡኪም ዘንድሮ ጥሩ ነበር ለርሱም አድናቆት አለኝ በነገራኝ ላይ በስኪመር ደረጃ ብቻ እንድወስን አልሻም አብዛኛው ጊዜ በዚያ ቦታ ላይ ብቻ አለመጫወቴ ይታወቃልና በመሀል ቦታ የሪያል ማድሪዱ ሉካ ሞድሪች፣ የቀድሞ የባርሴሎና ኮከቦች አንድሬስ ኢኒየሽታና ዣቪ ዥርናንዴዝን አደንቃለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ዋንጫ በልቷል… አባይ ይገደባል…?

በዛብህ፡- /ሳቅ በሳቅ/ የግድ ነው የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ተከናውኗል በቀጣይም በተያዘለት ፕሮግራም ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ ይሄ ሀገር ነው የግብፅና ሱዳን ጩኸት ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም በሀገሬ አይቀለድም ፋሲልም ዋንጫ በልቷል አባይ የግድ ይገደባል በደንብ አድርጎ ይገደባል በአባይ ድርድር የለም፡፡

ሀትሪክ፡- ዋንጫውን ከወሰዳችሁ በኋላ ቀጣይ ተጋጣሚዎቹ ወልቂጤዎች እያጨበጨቡ ተቀበሏችሁ ምን ተሰማህ?
በዛብህ፡- ደስ የሚል ስሜት ውስጤን ውርር አድርጎኛል ይህን ጊዜ እናፍቅ ስለነበር የተለየ ስሜት ተሰምቶኛል ዋው የደስታ ስሜቱ የገዘፈ ነው እኔም በዚህ መልክ ዋንጫ ተቀብዬ አላውቅም ይሄ ታሪክ እኔ ላይ ደርሶ በማየቴ ኮርቻለሁ ለልጄ ለቤተሰቤ የምናገረው ታሪክ አለኝ ዋንጫውን በተመለከተ አመቱ ሲያልቅ በክብርና በደስታ እየጨፈርን ከደጋፊዎቻችን ጋር እናከብረዋለን ዋንጫውን የምንወስደው ጨዋታው ሲያልቅ ቢሆን ደስ ይለን ነበርና በመሳካቱ ተደስተናል፡፡

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ቃል ….?

በዛብህ፡- በመጀመሪያ ለዚህ ክብር ያበቃኝ አምላኬ እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ነው የማመስግነው…. የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችን፣ አመራሮችን፣ ኮቺንግ ስታፉን አመሰግናለሁ ሙሉ ቤተሰቤ በተለይ እናትና አባቴ ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል ለዚህ እንድደርስ አድረገውኛል ሁለቱንም አመሰግናለሁ ውዷ ባለቤቴንም በጣም ነው የምወዳት የማፈቅራት ብዙ አግዛችለችና እርሷንም አመሰግናለሁ በአጠቃላይ በሁሉም የእኔ ጉዞ ላይ ድጋፋቸውን ላደረጉ በሙሉ አመሰግናለሁ እግዜር ይሰጥልኝ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport