ሻምፒዮናው ፋሲል ከነማ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ዛሬ ይቀበላል፤ አሰልጣኙ እና ሁለቱ ተጨዋቾቹ ምን አሉ?

24ኛ ዓመቱን የያዘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ዘንድሮ አዲስ ስያሜን ይዞ እየተካሄደ ሲሆን ሊጉ አራት ግጥሚያዎች ሲቀሩትም በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመራው ፋሲል ከነማ የውድድሩ ሻምፒዮና ሊሆን ችሏል፤ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሚል ስያሜ የተሰጠውን ይህን ዋንጫ በዛሬው ዕለት ፋሲል ከነማ ከሐዋሳ ከተማ ጋር ከተጫወተ በኋላ ከፍ አድርጎ የሚያነሳ ሲሆን ይህ ድል በክለቡ ታሪክም የመጀመሪያው ይሆናል፡፡

ፋሲል ከነማ በደቡብ አፍሪካ ተሰርቶ የመጣውን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ዛሬ ወደ ሜዳ እንዲገቡ በተፈቀደላቸው ቁጥራቸው 2000 በሚደርሱ ደጋፊዎቹ ፊት ማንሳቱን ተከትሎና በክለቡ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎ ጋር በተያያዘ እንደዚሁም ሌሎችንም ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን ለአሰልጣኝ ስዩም ከበደ እና ለሁለቱ የቡድኑ ተጨዋቾች አምሳሉ ጥላሁን /ሳኛ/ እና ሱራፌል ዳኛቸው /ነብሮ/ አንስተንላቸው የሚከተለውን ምላሾች ሊሰጡን ችለዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስቷል፤ ድሉ ይገባዋል?

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፡- መቶ ፐርሰንት ድሉ ይገባዋል፤ ፋሲል የእዚህን ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ያነሳው የሀገራችን ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲ. ኤስ. ቲቪ ጥራቱን ጠብቆ በተላለፈበት ዓመት ላይ ዓለም ጨዋታችንን በተመለከተበትና ያለንንም አቋም ባልዋዠቀ ሁኔታ ቀጥ አድርገን ባስጓዝንበትና የሁሉንም ክለብ አሰልጣኞች፣ ተጨዋቾች እንደዚሁም ደግሞ ደጋፊዎችንም ባሳመንበት ሁኔታም በመሆኑ ያገኘነው ድል ሲያንስብን እንጂ የሚበዛብን አይደለም፡፡

አምሳሉ፡- በጣም ነዋ! ምክንያቱም በእኛ ሀገር የሊግ ደረጃ አንድ ቡድን ተከታዩን ቡድን በ15 በሚደርስ የነጥብ ርቀት ጥሎትና አራት ጨዋታም እየቀረ ባለበት ሰዓት ዋንጫን ማንሳት ያልተለመደ ስለሆነ ከዛ ውጪም የሊጉን ዋንጫ ለበርካታ ዓመታት ሲያነሳ የሚታወቀውን የሀገሪቱን ትልቅ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስንም በ18 በሚደርስ ነጥብ ርቀከው ሄደህ ስኬቱን መቀዳጀት በጣም ከባድና የማይቻልም ነገር ነበርና ይሄን ፋሲል ከነማ እውን ስላደረገው ድሉ ይገባዋል፡፡

ሱራፌል፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ቡድናችን ፋሲል ከነማ ያነሳው ሁሉንም ባሳመነ መልኩ ነው፤ ከእኛ ውጪም የተቃራኒ ቡድኖች ሁሉ ስለድላችን እየመሰከሩም ነውና የዋንጫው ባለቤትነታችን የሚገባን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ለፋሲል ከነማ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫው የሚሰጠው ዛሬ ከሐዋሳ ከተማ ጋር ከተጫወተ በኋላ ነው፤ ዋንጫውን ስትቀበሉ ያኔ ምን አይነት ስሜት ሊኖርህ ይችላል?

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፡– የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን ገና አራት ጨዋታዎች እየቀረን ማግኘታችንን ስናውቅ ተፈጥሮብን የነበረውን የደስታ ስሜት ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ ደስታ ሁሌም ደስታ ነው፤ ትደሰትና ስሜቱ ይወጣልሃል፤ እኛም ዋንጫውን በማግኘታችን ደስታችንን አጣጥመን ጨርሰነዋል፤ ሀዘን ግን ሁሌም ቢሆን ከውስጥህ አይወጣም፤ የዘንድሮ ቡድናችን ግን እኛን እንድንደሰት አደርጎ በዛሬው ቀን ጨዋታ ላይም የእኛ ቡድን ከደቡብ አፍሪካ ተሰርቶ የመጣውን ዋንጫ በክብር ሊቀበል እየተዘጋጀ ይገኛልና የሰዓቱን መድረስ እየተጠባበቅን ነው የምንገኘው፤ ፋሲል ከነማ የዛሬውን ዋንጫ ከፍ አድርጎ የሚያነሳው በጥቂት ደጋፊዎቹም ፊት ነው፤ ከእነሱ ጋር በቅርበት መገናኘትም ነበር የቀረን፤ ከዛ ውጪ የዋንጫ ሴሪሞኒውም ምን ሊመስል እንደሚችል ለመመልከትም እያጓጓኝም ነው፡፡

አምሳሉ፡- የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ዛሬ የምንቀበል ቢሆንም የሚኖረን ደስታ ግን ለእኔም ሆነ ለሌሎቹ የቡድናችን ተጨዋቾች ድሬዳዋ ላይ ሻምፒዮናነታችንን እንዳረጋገጥንበት አይሆንም፤ እኛ ፋሲሎች ትልቁን ደስታ የተደሰትነው ከባድ በነበረው ግጥሚያ ሲዳማ ቡናን ስናሸንፍ የነበረውን ነው፤ ከዛ ውጪ ስለሌሎቹ ግጥሚያዎቻችንም ምን እንደምልም አላውቅም፤ በአጠቃላይ አቅማችንን አሟጠንም ነው ስንጫወት የነበርነውና ከዚህ በኋላ የሚኖሩንን ግጥሚያ መርሀ ግብርን የምናሟላበት ጨዋታ ነው፡፡

ሱራፌል፡- ቤትኪንጉን ማሸነፋችንን አስቀድሞ በማረጋገጣችን የሻምፒዮናነት ስሜቱ አሁንም በውስጣችን ቢኖርም ዋንጫውን ስንቀበል የሚኖረውን ለማወቅ ደግሞ ሰዓቱ ደርሶ ብናየው ይሻላል፤ እስከዛው ድረስ ግን ሁላችንም ዋንጫውን ለማየት በከፍተኛ የጉጉት ስሜት ላይ ነው የምንገኘው፤ የዋንጫው ስነ-ስርዓትም የአማረ ይሆናል ብዬም እያሰብኩ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በቤትኪንጉ ሻምፒዮናነታችሁ አስቀድሞ ቢረጋገጥም ዛሬ በምታደርጉት ጨዋታ ላይ ደግሞ ዋንጫን መቀበል ደስ የሚለው ግጥሚያን አሸንፎም ሲሆን ነው?

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፡- ፋሲል ከነማ ሁሌም ቢሆን ወደሜዳ የሚገባው ግጥሚያዎችን ለማሸነፍ ነው፤ በዛሬው ጨዋታ ላይም ሲኒየር የሆኑና ወጣት የሆኑንም ተጨዋቾች በመጠቀም ከሐዋሳ ከተማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ለማሸነፍና በድል ስሜት ላይም ሆኖ ዋንጫውን ለመቀበል ዝግጁ ሆኗል፡፡

ሱራፌል፡- በእርግጥ በዕለቱ የምታደርገውን ጨዋታ አሸንፈህ ዋንጫን ስታነሳ የሚሰጥህ የራሱ የሆነ የደስታ ስሜት እንዳለ ባምንም ያ ባይሳካም በመሸነፍ ውስጥ ሆነህም ድሉን በጥሩ ሁኔታ የምታጣጥምበት ደስታም ሊኖርህ ይችላል፤ እኛ ጋር በሁለቱም ስሜቶች ውስጥ ሆነን ነው ነገን እየተጠባበቅንም የምንገኘውና ጨዋታውን ለማሸነፍም ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ በቅርቡ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያደረገውንና የተሸነፈበትን ጨዋታ ከአቅም በታች በመጫወት በሚል ወቀሳና ክስ ቀርቦበታል፤ በዚህ ዙሪያ የምትሉት ነገር ካለ?

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፡- ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በነበረን የባለፈው ጨዋታ ላይ ቡድናችን ላይ ከአቅም በታች ተጫውቷል ተብሎ የቀረበውን ክስ እኛ በፍፁም አንቀበለውም፤ ከእነሱ ጋር ግጥሚያን ስናደርግ አራት ከሚቀሩን ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ነጥብን ብቻ ነበር የሚያስፈልገንና ወጣትና ተስፈኛ የሆኑ አንድአንድ ተጨዋቾችን ተጠቀምን፤ አሁንም አምሳ ፐርሰንት ማሸነፍና አምሳ ፐርሰንት መሸነፍም የሚያሰጋን ነገር ስለሌለ ከሐዋሳና ከሰበታ ጋር በሚኖረን ጨዋታ ላይ እነዛንና ሌሎችን ያልተጠቀምንባቸውንም ተጨዋቾች ከሲኒየሮቹ ጋር በመቀላቀል እንጠቀምባቸዋለን፡፡

አምሳሉ፡- ወልቂጤ ከተማ በፋሲል ከነማ ላይ ያቀረበውን ክስ ማንም የማይቀበለው ነው፤ እኛ ፋሲሎች በፍፁም ለድሬዳዋ ከተማ አልለቀቀንም፤ ለምንስ ነው የምንለቀው፤ ደመወዝ የሚከፍለን እኮ ፋሲል እንጂ ወልቂጤ ከተማ አይደለም፤ እኛ ሻምፒዮና ከሆንን በኋላ እያንዳንዱን ጨዋታ የምናደርገው የራሳችንን አቋም በቀጣይ ጊዜም ላሉብን ውድድሮች ምን እንደሚመስልም ለማዘጋጀት ነው፤ በጨዋታው በ7ኛው ደቂቃ ላይ እኔ በጉዳት ከሜዳ ስወጣ ጎል የሚሆን ኳስ አውጥቼም ነው፤ በእግር ኳስ ሁሌ ቶፕ አይኮንም፤ እነሱ እስከዛሬ የት ነበሩ? ኢትዮጵያ ውስጥ በእርግጥ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማውራት የተለመደ ነገር ነው፤ የቡድን አመራሮቹ የእኛን ክለብ ስም በማጥፋት ሊያወሩ አይገባም ነበር፤ ከዛ ይልቅ የራሳቸውን ስራ አስተካክለው መስራት ቢችሉ የት ሊደርሱ በቻሉና ባሉት ነገር አዝኜባቸዋለው፡፡

ሱራፌል፡- ፋሲል ከነማ ዘንድሮ ለሻምፒዮናነቱ ክብር የበቃው በላቡ ነው፤ ለፍቶ፣ ጥሮና ግሮም ስለተጫወተ ለአሸናፊነቱ ሊበቃ ችሏል፤ በእንዲህ ሁኔታ እየተጓዘ ባለበት ሰዓት ላይ በቀደም ሽንፈትን ሲያስተናግድ ለተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ለቆለት ነው በሚል እየተናፈሰና ቡድናችን ላይም ክስ እንዲቀርብበት የተደረገበት ሁኔታ በጣም የሚያሳፍር ነው፤ ፋሲል ከነማ ለድሬዳዋ በፍፁም አልለቀቀም፤ እኛ እኮ ፕሮፌሽናሎች ነን፤ ክብርን እንፈልጋለን፤ ማንም ቡድን ከሊጉ ሲተርፍ በራሱ ጥረት ነው ሊሆን የሚገባው፤ የእኛን ቡድን አይሸነፍም ያለው ማን ነው? አይደለንም እኛ ማንቸስተር ሲቲም እኮ በታችኛው ቡድን ተሸንፏል፤ የተወራብን ነገር በጣም ይደብራል፤ ያሳዝናልም፤ ስሜትንም ይጎዳል፤ ስለመላቀቅ ለሰዎች ሊመስላቸው ቢችልም ጉዳዩን ግን አንተ ብቻ ነው የምታውቀው፤ በእግር ኳስ ዛሬ ያሸነፈ ቡድን ሊሸነፍ ይችላል፤ ይሄ እየታወቀ ዓመቱን ሙሉ ምን እየሰሩ እንደነበሩ ያላወቁት ወልቂጤዎች ስማችንን ለማጥፋት በመሞከራቸው እናዝንባችኋለን፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር 27 ጎሎችን አስቆጥሮ የፕሪምየር ሊጉን የኮከብ ግብ አግቢነት ሪከርድ ሊሰብር ችሏል፤ ይህን ከሰማክና ከተመለከትክ በኋላ በእሱ ዙሪያ ምን አልክ?

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፡- በአቡበከር ብቃት ዙሪያ ብዙ ተብሏል፤ ለእሱ ትልቅ ክብርም ነው ያለኝ፤ ወጣትና እምቅ ችሎታም ያለው ተጨዋች ነው፤ እንደ ቡድን ይጫወታል፤ በግልም ተፅህኖን መፍጠር ይችላል፤ ከኳስ ጋርና ያለ ኳስ ያለው እንቅስቃሴ በጣም አስገራሚም ነው፤ ራሱን ከተከላካዮች ነፃ አድርጎ ሲጫወት ያስደምማል፤ የተቃራኒ ቡድን ተከላካዮችን እንዴት አድርጎ አህምሮአቸውን ሲሰርቅ ስታይም ልዩ ችሎታ እንዳለውም መረዳት ይቻላል፤ በዛ ላይ ፍጥነቱና የአጨራረስ ብቃቱ ስለ እሱ ይህን ታህል ካልኩ ጠንክሮ ከሰራ ደግሞ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ወደውጪ ሀገር በመጫወት ከክለብ አልፎ ለሀገርም በጣም ይጠቅማል፡፡

አምሳሉ፡- አቡኪ ገና የሚያድግና ከዚህ በላይም መስራት የሚችል ነው፤ እኔ ለእሱ በእዚህ ሀገር የሊግ ደረጃ እንዲጫወትም አልመኝለትም፤ በብዙ መልኩ ሊለወጥ ወደሚችልበት ሊግ ውስጥ ሄዶም ነው ችሎታውን ሊያሳድጉለት ወደሚችሉ አካላቶች ጋር በመሄድም ሊጫወት የሚገባው፤ ያኔ እኛም ይሄ ተጨዋች ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሶ ስናየውም አብሮን ተጫውቷል እንድንለውም እንፈልጋለንና ይህ ጥሩ አቅምና ስርዓት ያለው ተጨዋች የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሶ ባየው በጣም ደስ ይለኛል፡፡

ሱራፌል፡- አቡኪ ሪከርዱን መስበሩ የሚገባው ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ በላቡና በብቃቱም ነው በጣምም ስለለፋ ይህንን ክብር ሊቀዳጅም የቻለው፡፡

ሀትሪክ፡- እናንተ ሻምፒዮና ሆናችሁ፤ የትኛው ክለብ ሊጉን በሁለተኝነት ደረጃ ያጠናቅቃል?

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፡- ኢትዮጵያ ቡና፣ ሀድያ ሆሳዕናና ቅዱስ ጊዮርጊስ እድሉ ያላቸው ቢሆኑም፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ማፈግፈግ ይታያል፤ ሀድያም ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ በራሱ ችግር ነጥቦችን አስቀድሞ የጣለበት እና አሁን ላይ ደግሞ ልጆቹን ራሳቸውን ከቡድኑ በማግለል ያጣቸው በመሆኑ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ቡና ካለው ወቅታዊ አቋሙ በመነሳት ሰፊ እድል አለው፡፡

አምሳሉ፡- ኢትዮጵያ ቡና ይህን እድል የሚያገኝ ይመስለኛል፡፡

ሱራፌል፡- ሶስቱም ክለቦች ማለትም ኢትዮጵያ ቡና፣ ሀድያ ሆሳዕናና ቅ/ጊዮርጊስ እድሉ አላቸው፤ ስለዚህም የእዚህን ምላሽ ለማወቅ ውድድሩ ሲያልቅ ብናይ ይሻላል፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፡- ስለ ፋሲል ከነማ ማለት የምፈልገው ነገር አለ፤ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር የሚኖረው ደጋፊው፣ ማኔጅመንቱ፣ ቦርዱ ክለቡን ትልቅ ደረጃ ላይ ለማድረስ ራዕይ አለው፤ በቅርቡም ቴሌቶን አዘጋጅቷል፤ ይህ ክለብ ወደፊት የራሱን ሀብት ሲፈጠር የሚደርስበትም ደረጃ ይታወቃልና በክለቡ ውስጥ እየተሰራ ላለው ነገር አድናቆት አለኝ፤ ከዛ ውጪም ቡድናችን የዘመኑ ሻምፒዮና ስለሆነም እንኳን ደስ አላችሁ ልል እወዳለው፡፡

አምሳሉ፡- ፋሲል ከነማ ለየት ያሉ ሰዎችና ደጋፊዎችም ያሉት ቡድን ነው፤ ሁሌም ቡድኑን ትልቅ ደረጃ ላይ ለማድረስም የሚጥሩም ናቸው፤ ሰሞኑን ቴሌቶን በማዘጋጀትም ክለቡን ለማጠናከር እየተሰራም ይገኛል፤ ይህን ካልኩ በመጨረሻ ለማለት የምፈልገው የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ሶስት ዓመት ብዙዎቻችን ተጨዋቾች ለፍተናልና ደጋፊዎቻችንም ለፍተዋልና በዚህ ሁላችንም ደስተኛ ሆነናል፡፡

ሱራፌል፡- ለፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ዘንድሮ ይህን ድል ስለተቀዳጀን እንኳን ደስ አላችሁ፡፡


 

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport