በ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት መርሀ ግብር ሁለቱን ቡድኖች ሲያገናኝ በአፄዎቹ አሸናፊነት ለመጠናቀቅ ችሏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እና እልህ አስጨራሽ የጨዋታ እንቅስቃሴን በሁለቱም ቡድኖች መካከል ስንመለከት በርከት ያሉ ጎሎች አራት ከመረብ ላይ ተቆጥረዋል ።
ፋሲል ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ አስራ ሁለት ደቂቃዎች ተጭነው ሲጫወቱ የቀኝ መስመር ተጫዋቹ እንየው ካሳሁን ከመስመር ያሻማውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግምባር በመግጨት መሪ ያደረገቻቸውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል ። ከግቡ መቆጠር በኋላ በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ የሄዱት አፄዎቹ ሽመክት ጉግሳ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ከሊጉ ኮከብ ግብ አግቢዎች ተርታ የሚያስቀምጠውን ግብ ከመረብ ሊያሳርፍ ችሏል ።

በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ብልጫ የተወሰደባቸው ወላይታ ድቻዎች ወደ ጨዋታው ቀስ በቀስ ሲመለሱ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተሻማውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ሲጨርፈው ስንታየሁ መንግስቱ ለጦና ንቦቹ የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል ።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ወደ ማጥቃቱ ዳግም ለመመለስ የሞከሩት አፄዎቹ የዲቻ የተከላካይ ስህተትን ተከትሎ ሙጂብ ቃሲም ወደ ሳጥን በመግባት ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል ። በመጀመሪያው አጋማሽ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የቆየው የወላይታ ዲቻው ቸርነት ጉግሳ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ፀጋዬ ብርሀኑ በማስቆጠር አቻ ለመሆን ችለዋል ። ከግቡ መቆጠር በኋላ ዳግም ወደ ግብ ያቀኑት ዲቻዎች ጥሩ የሚባል ኳስን መሞከር ቢችሉም በአፄዎቹ ተከላካይ ከመስመር ሊወጣባቸው ችሏል ።

ከአቻነት ግቡ በኋላ የተቀዛቀዙት አፄዎቹ ወደ ሙከራዎችን ማድረግ ሳይችሉ ሲቀሩ በተቃራኒው የጦና ንቦቹ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ ለአጥቂዎች በሚጣሉ ኳስ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይተዋል ። ዲቻዎች አልፎ አልፎም ወደ ግብ ሲደርሱ በተለይም መሳይ አገኘሁ የግብ ጣበቂውን መዘናጋት አይቶ ከርቀት የሞከረው እና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ለግብ የቀረበች ሙከራ ስትሆን የመጀመሪያው አጋማሽ በዚህ መልኩ ሊጠናቀቅ ችሏል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተቀዛቅዘው ሲገቡ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ብዙ የግብ እድሎችን ለመመልከት ሳንችል ቀርቷል ።
አፄዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ ከሚላኩ ኳሶች የግብ ዕድልን ለመፍጠር ሲሞክሩ ሙጂብ ቃሲም ከ ግራ መስመር የተሻማለትን ኳስ እንዲሁም ሱራፌል ዳኛቸው ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ አምሳሉ ጥላሁን የሟከራቸው ሙከራዎች ለግብ ከቀረቡ ሙከራዎች የሚጠቀሱት ነበሩ ።

በረጅሙ በሚላኩ ኳሶች ማጥቃታቸውን የቀጠሉት አፄዎች ከመሀል ሜዳ በተሻገረች እና የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ደጉ ደበበ በናትናኤል ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ሙጂብ ቃሲም በድጋሚ አፄዎቹን መሪ ሲያደርግ ሀትሪክ መስራት ችሏል ።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቀረዘው የቀረቡት ወላይታ ዲቻዎች ስንታየሁ መንግስቱ ካደረጋት ሙከራ ውጪ በሁለተኛው አጋማሽ የሚያስቆጭ እድል ለመፍጠር ተቸግረው ተስተውለዋል ።
ሁለተኛው አጋማሽ ከ መጀመሪያ አጋማሽ ተቃራኒ በሆነ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሲጠናቀቅ ፋሲል ከተማዎች ተከታታይ ድል ያስመዘገቡበትን ውጤት ይዘው ለመውጣት ችለዋል ።
አስተያየት ይስጡ