“የኢትዮጵያ ቡና መዘናጋት ለድል አብቅቶናል፤ ሐዋሳ ትልቅ ቡድን ነው፤ አይወርድም” ብሩክ በየነ /ሐዋሳ ከተማ/

ሐዋሳ ከተማ በወጣቱ አጥቂ ብሩክ በየነ የ60ኛው ደቂቃ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፤ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ሐዋሳ ከተማ ቀደም ሲል አድርጓቸው የነበሩትን ሁለት ጨዋታዎች መሸነፉን ተከትሎ እና በመጨረሻው ረድፍ ላይ መገኘቱን በመገንዘብ ብዙዎች ክለቡን ዘንድሮ ወራጅነት ያሰገዋል በሚል አስተያየታቸውን ቢሰጡም በዛሬው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ካደረጉት እና ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ ክለባቸው ስላገኘው የድል ውጤት እና ሰሞኑን ከወራጅ ጋር በተያያዘ ስለቡድናቸው ስለሚሰጠው አስተያየትም አጥቂው ብሩክ በየነ “በዛሬው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና መዘናጋት እኛን ለድል አብቅቶናል፤ ሐዋሳ ከተማ የሊጉ ትልቅ ቡድን ነው፤ ወራጅነትም ይገጥመዋል ብዬ አላስብም” በማለት ምላሽን ሰጥቷል፡፡
የሐዋሳ ከተማውን አጥቂ ብሩክ በየነን ቡናን ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ አጠር ባለ መልኩ አናግረነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቡና ላይ ድልን ስለተቀዳጁበት የዛሬው ጨዋታ?

“ጨዋታው የአየሩን ተፅህኖ ጨምሮ ትንሽ ይከብድ ነበር፤ ቡድናችን ከሽንፈቶችም ነበር የመጣው፤ የዛሬው ውጤት ስለሚያስፈልገን ለማሸነፍ ተጫወትን በመጨረሻም ባለድሉ እኛ ሆንን”፡፡


ኢትዮጵያ ቡናን ለማሸነፍ ስለቻሉበት መንገድ?

“ኢትዮጵያ ቡና ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው፤ ያንን እናውቃለን፤ ስለ ሰሞኑ ጨዋታቸውም በቪዲዬ የተመለከትነው ነገር ነበር፤ እነሱ በሚሰሩት ስህተትና መዘናጋት ማሸነፍ እንዳለብን ስለተነገረንና የምናገኘውን የግብ እድልም ወደ ጎልነት መቀየር ስለሚያስፈልገን ያንን ተግባራዊ አድርገን ነው የጨዋታው ባለድል ልንሆን የቻልነው”፡፡

ስለ ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና?

“ኢትዮጵያ ቡና ኳስ የሚጫወትና አሪፍ ቡድን ነው፤ ዛሬ እኛንም ፈትኖናል፤ ያም ሆነ ይህ ግን ውጤቱ የግድ ያስፈልገን ስለነበር ባለድሉ እኛ ሆነናል”፡፡

የሐዋሳ ከተማ የድል ግብን ስለማስቆጠሩ እና በቀጣይ ጊዜም ሌሎች ግቦች ይኖሩት እንደሆነ?

“የዛሬዋ የድል ግቤ በትልቁ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ላይ እና በተለይም ደግሞ የዓመቱ የቅዱስ ገብርኤል በዓል በተከበረበት ቀን ላይ ያስቆጠርኳት ስለሆነች በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ይሄ ጎል ማስቆጠሬ በቀጣይነትም አብሮኝ ነው የሚኖረው”፡፡

የሐዋሳ ከተማ ክፍተቱ ምን እንደነበር?

“ባለፉት ሁለት ጨዋታዎቻችን በመከላከሉ ላይ ድክመት ነበረብን አሁን ግን ከቡና ጋር በነበረን ጨዋታ ይሄ ችግራችን ተቀርፎልን ወደመስተካከሉ መጥተናል”።

ሐዋሳ ከተማን ዘንድሮ ወራጅነት ሊያሰጋው ይችላል ስለመባሉ?

“ካለፉት ሁለት ጨዋታዎቻችን ሽንፈት በመነሳት ሰዎች ስለ እኛ ብዙ ነገርን ሊሉ ይችላል፤ ሐዋሳ ከተማ ትልቅ ቡድን ነው፤ ቀደም ሲል በነበሩት ጨዋታዎችም ውጤትን አጥቶ የነበረው የአዲስ አበባው አየር ትንሽ አስቸግሮት ስለነበርና ዘግይተንም ስለመጣን ነበር፤ ይሄ የሀገሪቱ ትልቅ ቡድን ከእዚህ በኋላም አሸናፊነቱን እያስቀጠለ ስለሚሄድ ወራጅነቱ ፈፅሞ አያሰጋውም”፡፡

በመጨረሻ…

“ሐዋሳ ከተማ ያገኘው የዛሬ ድል ከፍተኛ ደስታን በሁላችንም ውስጥ ፈጥሮብናል፤ ለዛም ነው በመልበሻ ክፍል ውስጥ ሁሉ የቡድኑን መዝሙር በመዘመር ጭምር ስንጨፍር የነበረው፤ አሁን ቡድናችን መነቃቃት ጀምሯል፤ ከእዚህ በኋላም እያንዳንዱ ጨዋታ ለእኛ ወሳኝ ስለሆነም አሸናፊነታችን በእርግጠኝነት ይቀጥላል”፡፡

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor