“ኳሷን ባልወስዳትም በጣፋጩ ድል ሀትሪክ መስራቴ ደስታዬን የተለየ አድርጎታል”ሙጂብ ቃሲም

“ኳሷን ባልወስዳትም በጣፋጩ ድል ሀትሪክ መስራቴ ደስታዬን የተለየ አድርጎታል”

“ወላይታዎች የአቻነቱን ግብ በተከታታይ ሲያስቆጥሩብን ጊዜ በጣም ተደናግጠን ነበር”
ሙጂብ ቃሲም


የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም ቡድናቸው ወላይታ ድቻን ስላሸነፈበት ጨዋታ፣ ሀትሪክ ስለመስራቱ፣ ቡድናቸው ስለሚገኝበት አቋም እና፣ ስለ ዘንድሮ የውድድር ዘመን ግባቸው ይናገራል።

ፋሲል ከነማ ሙጂብ ቃሲም ባስቆጠራቸው 3 ግቦች ወላይታ ድቻን 3-2 አሸንፎ ድል ያደረገ ሲሆን ከጨዋታው በኋላ የቡድኑ ተጨዋች እና የኮከብ ግብ አግቢነቱ ክብር ላይ የተቀመጠው ሙጂብ ቃሲም ለሀትሪክ ስፖርት ድረ ገፅ ይህንን ብሏል።

ተጋጣሚያቸውን ስላሸነፉበት ጨዋታ

“ወላይታን ስናሸንፍ በጎል የቀደምነው እኛ ነበርን ገና 20 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ሁለት ግብ ማስቆጠር ችለናል። ከዛ እነሱም በመነሳሳት 23 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አቻ አድርገውን ጨዋታውን ወደ ጠንካራ ፉክክር ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል”

ስለ ወላይታ ድቻ

“ቡድኑ ከዚህ በፊት ከምናውቀው አንፃር በጣም ተለውጧል፤ በፊት የምናውቀው ዲቻም አይደለም። ጠንካራውን እና በጣም የፈተነንን ቡድንም ነው እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ታግለን በመጫወትም ያሸነፍነው”።

ወላይታ ድቻን 2ለ0 ከመሩ በኋላ በተከታታይ ሁለት ግቦች ሲቆጠርባቸው ስለተፈጠረባቸው ስሜት

“እነሱ አቻ ያደረጋቸውን 2 ግቦች አስቆጥረው ጨዋታው ወደ እነሱ ባጋደለ ሰዓት በጣም ተደናግጠን ነበር። እኛ የጠበቅነው ሌሎች ተጨማሪ ግቦች ስለማስቆጠር እንጂ በዛ ቅፅበት ተከታታይ ግብ ይቆጠርብናል ብለን አላሰብንም ነበር”።

በጨዋታው ሀትሪክ ስለመስራቱ እና እንደ ባህር ማዶ ሀገራት ኳሷን አለመውሰዱ

“እንደ አጋጣሚ ሆኖ አምናም ሀትሪክ ሰርቼ ነበር። ይህን ዘንድሮም ከጅማሬው ፈታኝ ሆኖብን በነበረው ጨዋታ ላይ ምንም እንኳን ሀትሪክ ሰርቼ ኳሷን ባልወስዳትም ግቦቹን በማስቆጠሬ ግን የማላውቀው አይነት ደስታ ሊሰማኝ ችሏል። በሰራሁት ሀትሪክ ኳሷን ከመውሰድ ጋር በተያያዘ እኛ ሀገር እንደ ውጪዎቹ ገና አልተለመደም። ሀትሪክ የሚሰራ ተጨዋች ለወደፊቱ ኳስ ቢወስድ ግን በጣም ጥሩ ነው”።

ሀትሪክ የሰራክበትን የፍፁም ቅጣት ምት በመጀመሪያ ስተህ ነው በድጋሚ እንድትመታ ተደርጎ ያስቆጠርከው። ምቱ ይደገማል ብለህ ጠብቀህ ነበር?

“በፍፁም፤ ኳሷን መትቼ ስስት ይደገማል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር። ያም ሆነ ይህ ግን የግብ ጠባቂውን መስመሩን ለቅቆ መውጣቱን በቅርብ ርቀት በተመለከተው ረዳቱ ዳኛ አማካኝነት ምቱ እንዲደገም ተደርጎ በፈጣሪ እርዳታ ግቧን በማስቆጠሬ ሀትሪክ ልሰራ ችያለሁ”።

ስለ ፋሲል ከተማ ወቅታዊ አቋም እና ስለ ዘንድሮ የውድድር ዘመን ግባቸው

“አሁን ላይ በምርጥ ብቃታችን ላይ አይደለንም የምንገኘው። ገና ይቀረናል። ከሽንፈት መልስም መጥተን ነው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎቻችን ወደ አሸናፊነት የተመለስነውና በማሸነፍ ውስጥ ሆነን ስህተቶቻችንን በማረም ምርጡን ቡድናችንን በቀጣይ ጊዜ እናስመለክታችኋለን። ከዛም ውጪ ፋሲል ከነማ አምናም ከነበረው ጥሩ ብቃት አንፃር ዘንድሮም የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ለማንሳትም ነው የሚጫወተው”።

በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፉ በኋላ ወደ አሸናፊነት ስለመመለሳቸው ሚስጥር

“ሽንፈት በእግር ኳስ ውስጥ ያለና የሚኖር ነው። ትልቅ ግጥሚያ ከነበረው የቡናው ጨዋታም ብዙ ነገር አይተን ተምረንበታል። ለዛም ነው ከስህተቶቻችን ተምረን ስለመጣንም ሁለት ጨዋታዎችን ልናሸንፍ የቻልነው”።

በኮከብ ግብ አግቢነት የመሪነት ስፍራ ላይ ስለመቀመጡ እና ስለ ወቅታዊ አቋሙ

“5 ግቦችን አስቆጥሬ የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት መምራት መጀመሬ በጣም ጥሩ ነው። እንደ አንድ አጥቂም ቡድኔ ለድል የሚበቃበትን ግቦች ከእኔ ይፈልጋልና ያንን ማሳካቴ አስደስቶኛል። ያለኝን ወቅታዊ አቋም በተመለከተ አሁን ላይ ገና ነኝ። አምና ወደ ነበርኩበት ጥሩ አቋም ለመምጣት እየጣርኩ ነው። ያንንም ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ስናመራም አሳካዋለሁም”።
ዲ ኤስ ቲቪ ሊጋችንን ማስተላለፍ ስለመጀመሩ “ጨዋታዎቹ መተላለፋቸው በጣም ደስ ይላል። በዓለም ደረጃ እኛን ብዙውች እየተከታተሉን ነው። የጨዋታ ተነሳሽነትንም እየፈጠረልን ነው”።

በመጨረሻ

“ፋሲል ከነማ ወደ አሸናፊነቱ መጥቷል። ከእዚህ በኋላ አንቆምም። ሰሞኑን ባገኘነው ድልም ደጋፊዎቻችን እንኳን ደስ አላችሁ”።

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor