በአራተኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን መርሀ ግብር ወልቂጤ ከተማን ከ ባህርዳር ሲያገናኝ ክትፎዎቹ አሸናፊነታቸውን ያስቀጠሉበትን ውጤት ይዘው ለመውጣት ችለዋል ።
ወልቂጤ ከተማዎች ብልጫ በወሰዱበት የመጀመሪያ አጋማሽ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ የጎል ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል ።ክትፎዎቹ በተለይም ከቆሙ ኳሶች አስደንጋጭ ሙከራን ሲያደርጉ መሪ የሆኑበትን ጎልም ከዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴ ማግኘት ችለዋል ።

ወልቂጤ ከተማዎች በተስፈኛው ታዳጊያቸው ያሬድ ታደሰ የቅጣት ምት ሙከራ አስደንጋጭ ሙከራን ሲያደርጉ ሀሪሰን ሄሱ አልፎም የግቡ ቋሚ ሊመልሱበት ችለዋል ። ክትፎዎቹ መሪ ያደረገችውን ግብ ፍሬው ሰለሞን ከቅጣት ምት ያሻማውን ቶማስ ስምረቱ ከመረብ በማሳረፍ መሪ ሊያደርጋቸው ችሏል ።

የጣና ሞገዶቹ እምብዛም የግብ ዕድል ባለፈጠሩበት እና ተቀዛቅዘው በታዩበት የመጀመሪያው አጋማሽ ከማዕዘን ምት ከተሻገረችው የግብ ዕድል እና የግቡ አግዳሚ ከመለሰው ውጪ አስደንጋጭ ሙከራን ማድረግ ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች መጠነኛ ፉክክርን ለማድረግ ሲሞክሩ በተለይም ባህርዳር ከተማዎች የሚያስቆጩ የግብ ዕድሎች ከሽፈውባቸዋል ። በተቃራኒው ወልቂጤ ከተማ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት በመልሶ ማጥቃት የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ በጨዋታው ሂደት አልሳሪ አልመሀዲን በቀይ ካርድ ለማጣት ተገደዋል ።
ባህር ዳር ከተማዎች በሁለተኛው አጋጓሽ ተጭነው ለመጫወት ሲሞክሩ ግርማ ደሲሳ ያሻማውን ኳስ ፍፁም አለሙ የሞከረው እንዲሁም ባዬ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ጀማል ጣሳው ያወጣባቸው አጋጣሚዎች ለጣና ሞገዶቹ ለግብ የቀረቡ እድሎች ነበሩ ።

በመከላከሉ ላይ ተጠምደው የቆዩት ወልቂጤ ከተማዎች ተሳክቶላቸው ውጤቱን አስጠበቀው ሲወጡ በአራት ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ሽንፈትን ሳያስተናግዱ ቀርተዋል ።
አስተያየት ይስጡ