የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐግብሮች በዛሬው ዕለት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ተደርገዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ከረፋዱ 3:30 ጀምሮ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ስሁል ሽረ ተገናኝተው ሻምፒዮኑ ንግድ ባንክ 1 ለ 0 አሸንፏል።
ለ81 ደቂቃዎች ግብ ሳያስተናግድ በተጓዘው ጨዋታ ዘላለም አበበ ኪቲካ ጀማ እና ሳይመን ፒተር ለመቀነስ ሞክረው በሽረ ተከላካዮች የተመለሰውን ኳስ አግኝቶ በማስቆጠር ቡድኑን አሸናፊ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ከሽንፈት ርቆ በመጓዝ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአራቱ አሸንፎ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል።
- ማሰታውቂያ -

ቡድኑ ባሸነፈባቸው አራቱ ጨዋታዎች ላይም ምንም ግብ ያላስተናገደ ሲሆን ነጥቡን 28 በማድረስ ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል።
የውድድር ዘመኑ አስረኛ ሽንፈት ያስተናገደው ስሁል ሽረ በበኩሉ የወራጅ ቀጠና ቆይታውን ለማራዘም ተገዷል።
በ22ኛ ሳምንት መርሐግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ሲገናኝ ስሁል ሽረ በበኩሉ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማል።
ከ9:00 ጀምሮ በተደረገው የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማ መቀሌ 70 እንደርታ ላይ አምስት ግቦችን በማስቆጠር 5 ለ 2 አሸንፏል።
የአምናው የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አሊ ሱሌማን በ15ኛ ፤ 70ኛ እና 90+4ኛ ደቂቃዎች ላይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ከወንድወሰን በለጠ ቀጥሎ ዘንድሮ ሀትሪክ የሰራ ሁለተኛው ተጫዋቾች ለመሆን ችሏል።
አሊ የመጀመሪያውን ግብ ከእስራኤል እሸቱ በረጅም የደረሰውን ኳስ ተቆጣጥሮ ሁለት የመቀሌ 70 እንደርታ ተጫዋቾችን በግሩም ሁኔታ በማታለል ከመረብ አዋህዷል።
በ70ኛው ደቂቃ ላይም በተመሳሳይ ከብሩክ ታደለ የደረሰውን ረጅም ኳስ ተጠቅሞ ግብ ሲያስቆጥር በ90+4 ደቂቃ ላይ ደግሞ ቸርነት አውሽ ከተከላካዮች ጀርባ የጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ሀትሪክ ሰርቷል።
አሊ ዛሬ ያስቆጠረችውን ግቦች ተከትሎም በውድድር ዘመኑ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች 8 አድርሷል።
በተጨማሪም በ55ኛው ደቂቃ ላይ አምበሉ ቢንያም በላይ ከእስራኤል እሸቱ የደረሰውን ኳስ እና ከሳጥን ውጪ ደጋግሞ ግቦችን እያስቆጠረ ያለው አቤኔዘር ዮሐንስ ደግሞ ዛሬም ከርቀት በአስደናቂ ሁኔታ ያስቆጠሯቸው ግቦች ሀዋሳውያን አስደሳች ቀን እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል።
ለመቀሌ 70 እንደርታ 10ኛው ደቂቃ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት ያመከነው ያሬድ ብርሀኑ በ84ኛ ደቂቃ ላይ ብሩክ ኤልያስ በሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጥር ቦና አሊ ደግሞ ከአሸናፊ ሀፍቱ የተቀበለውን ኳስ 90+5ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።
ውጤቱንም ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 19 በማድረስ ወደ 15ኛ ደረጃ ከፍ ሲል መቀሌ 70 እንደርታ በበኩሉ በ22 ነጥቦች 13ኛ ላይ ተቀምጧል።
በ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና መቀሌ 70 እንደርታ ደግሞ ከ አርባምንጭ ከተማ ይጫወታሉ።
በዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር ደግሞ አርባምንጭ ከተማዎች በአህመድ ሁሴን ሶስት ግቦች አዳማ ከተማን በማሸነፍ ጣፋጭ ምሽትን አሳልፈዋል።
በጨዋታው በነቢል ኑሪ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ስንታየሁ መንግስቱ በሶስተኛው ደቂቃ ላይ በማስቆጠር አዳማ ከተማን መሪ አድርጓል።
የአዳማ ከተማ መሪነት እስከ 50ኛው ደቂቃ ድረስ ቀጥሎ ነበር። በ50ኛው ደቂቃ ላይ ቡታቃ ሸመና ከአህባዋ ብሪያን የደረሰውን ኳስ በቮሊ ለአህመድ አቀብሎት አህመድ ሁሴን በማራኪ ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎታል።
ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ አህመድ ሁሴን በሬድዋን ሸረፉ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር ለቡድኑም ለራሱም ሁለተኛ የጨዋታውን ግብ አስመዝግቧል።
በሁለቱ ግቦች ያላበቃው አህመድ ሁሴን በ84ኛው ደቂቃ ላይ ከቻርልስ ሪባኑ በረጅም የደረሰውን በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ በአዳማ ከተማ መረብ ላይ አሳርፏል።
አህመድ የዛሬ ግቦቹን ተከትሎ በውድድር ዘመኑ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች 10 በማድረስ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን መምራት ጀምሯል።
የጨዋታውን ውጤት ተከትሎም አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 30 አድርሶ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አዳማ ከተማ በ19 ነጥቦች 17ኛ ላይ ተቀምጧል።
በቀጣይ ሳምንት መርሐግብር አርባምንጭ ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ እንዲሁም አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና ይገናኛሉ።


